ወንጌል እና ፖለቲካ
መጽሀፍ ቅዱስን ያነበብኩትእና ውስጡ ጠልቄ የገባሁት በመካነእየሱስ ቤተክርስቲያን እና በሙሉ ወንጌል ቤተክርስቲያን ውስጥ ነው፡፡ እራሴን እንዳይ፣ አካባቢዬን እንዳውቅ እና ውድቀቴንም እንድረዳ ያደረገኝን ወንጌል የተማርኩበት በእነዚህ ቤተክርስቲያኖች ነው፡፡ እንደክርስቲያንነት ወንጌልን ማወቅ ግዴታ እና ሌላ አማራጭ የሌለህ መንገድ ነው፡፡ ክርስቲያን ሆኖ ካለወንጌል መኖር ማለት ሆድህን ካለምግብ እንደማለት ነው፡፡ ወደዚሕ ቤተክርስቲያን እንድሄድ ያደረገኝ ሰው አይደለም፡፡ አንድም ቀን በተለምዶ ፔንጤ ተብሎ ስለሚጠራው ሰምቼ የማውቅ ሰው አልነበርኩም፡፡
የእኔ እምነት ኦርቶዶክስ ነኝ ካለማለት አልፎ የሚያውቅ አልነበረም፡፡ ወንጀል እንዳልሰራ አስርቱቃላትን ልማር እንጂ ከዚህ ያለፈ ግን አላውቅም፡፡ ወንጀል ባልሰራም፤ ወንጀል የሚሰራብኝን ሰው ተቀብዬ እንድኖር የሚያስችል የሚያቻችል ጉዞ፡፡ እግዚአብሄር ውነት ይህንን ይፈልገው ይሆን? የሆነውን እንዳልሆነ ሆኖ ማየት ችለነው ይሆን? ወይስ ግፍን በመካፈል እና በማየት ስነልቦናችን ሊቁዋቁዋመው የማይችለውን ነገር በውስጣችን ደብቀነው ይሆን? እራስን ማታለል ይቻል ይሆን? ጭራሽ መጽሀፍ ቅዱስ በእጄም ገብቶ አያውቅም ነበር፡፡ በተለምዶ ግን በውስጤ ስለእግዚአብሄር ደስታ እና የማላውቀው ናፍቆት ስለነበረኝ፤ በልጅነቴ በቤተክርስቲያን አካባቢ አንዣብብ ነበር፡፡ ምናአልባት እግዚአብሄር እምነቴ ሳይሆን ሆቢዬ እና ባሕሌ አድርጌው ይሆን ወይ ብዬ ባለፈው ጉዞዬ እገረማለሁ፡፡ ቤተክርስቲያን አዲስ ባሕታዊ መጣ ሲባል ማየት እና መስማት እወድ ነበር፡፡ ምንነቱን የማላውቀው የእግዚአብሄር ናፍቆት በውስጤ ቢኖርም ግን ናፍቆቴን የሚያረካ ነገር ላገኝ እንዳልቻልኩ ውስጤ ያውቀው ነበር፡፡ የሕይወት መመሪያ የነበረውን መጽሀፍ ቅዱስ ሳላውቅ እና ሳላነበው ቤተሰብ ባስተላለፈው የሀይማኖት መስመር ተጉዞ መሄድ ደስ የሚል የዋሆች መንገድ ቢሆንም ግን በወቅቱ የተረዳሁት ነገር ቢኖር ሰውን እንደራስህ አድርገህ ውደድ የሚል ሳይሆን፤ ለእኔ ሰውን ከእራስህ በላይ ውደድ የሚል የተማርኩበት ይመስለኛል፡፡ የማይቻለውን ውስጥህ እያረረ አንተ ሳትኖር ሌላውን ማኖር ነበር በልጅነቴ የተረዳሁት፡፡ ብቻ ምንም አይነት መንፈሳዊ ትምህርት ጨብጨ አላውቅም፡፡
በውነቱ ኦርቶዶክስ ነኝ ብቻ ብዬ በተጉዋዝኩበት ያ ዘመን መጽሀፍ ቅዱስን አንብቤእና ተምሬ በነበር ሕይወቴ በውጣ ውረድ ባልተሞላ ነበር፡፡ ከመጽሀፍ ቅዱስ እንጂ ማንም ሰው ከቤተሰቡ ሕይወቱን ለመምራት እና ማንነቱን ለመለማመድ አይችልም፡፡ መጽሀፍ ቅዱስ ከእኔ ውስጥ ሊኖር የሚገባው የህይወት ማንዋል መሆኑን የነገረኝም አልነበረም፡፡ ካለምሪትም በአንድ ሀይማኖት ውስጥ መኖር አስተማሪነቱ ምንም አመርቂ ሊሆን እንደማይችል ተረድቻለሁ፡፡ እግዚአብሄር ሕይወተን ለመቀየር ያለውን አቅም አልተማርኩም፡፡ የተማርኩት ነገር ቢኖር ድህነትንም ተመስገን እያሉ ተቀብሎ መኖርን ብቻ ነው፡፡ ድህነትን እንደእድል መቀበል? ድህነት በእድል የሚመጣ ነገር ሳይሆን፣ የአስተሳሰባችን አለመለወጥ መሆኑን ደፍሮ ሊነግረን የሚችል አስተማሪ ወይም የተማረ አስተማሪ አልነበረንም፡፡ እድል እንደሰጠን ለዘመናት ኢትዮጲያን እንደደሀ አገር አድርገን ቆሎ እየበላን ተመስገን ይሕቺን አታሳጣን ማለት እንደዘወትር ጸሎት ሆኖ አልፎአል፡፡ እንደእውነቱ ከሆነ የእለት እንጀራችንን ስጠን ከሚለው ከእየሱስ ጸሎት ፍጹም የተለየ ነው፡፡ ይህን ስል ግን ቤተሰብ መጥፎ አስተማሪ ነው ብዬ ሳይሆን፤ በወቅቱ የነበረው የቤተሰብ ሁኔታ በባሕል እና በታሪክ ብቻ የተሞላ እና ያም በእጅጉ የሀይማኖት ሽፋን ስለነበረው ትውልዱ ሊማር የሚችለው ያለፈውን ብቻ ማስተላለፍ እንጂ አዲስ ነገርን መፍጠር አልነበረም፡፡ እግዚአብሄር ከቆሎ በላይ ሙክትም የሚሰጥ ሆኖ ሳለ ወደሰፊ ስጦታው ለመመልከት የዘጋ ዝሪት ብዬ ዛሬ አይቸዋለሁ፡፡ በዚህም የተነሳ ወጣቱ ለመፍጠር የተቸገረ እና የታፈነ ነበር ብል ስህተት አልነበረም፡፡
በሀይማኖት ውስጥ የነበረው ሁኔታ አፋኝ፣ዝምታን የሚያበዛ፣ መቻቻልን የሚያጎላ በመሆኑ እጅግ ብዙ ሰው እየተበደለ በደሉን እንኩዋን መናገር የሚደፍርበት ሁኔታ ያልነበረው እምነት ምን ያህል መጉዋዝ እንደሚችል ባለማወቃችን ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄር ግን ከዛ በላይ የሆነ አምላክ መሆኑን ለማገናዘብ በዘመኑ ለነበረው ወጣት የሚተላለፍ ነገር አልነበረም፡፡ ወንጌል ይፋ የወጣ ሳይሆን የተደበቀ
ነገር ነበር፡፡ በግእዝ የሚሰበከውም ሰበካ እንኩዋን ለመከታተል ግእዝ እኔ አልችልም ነበር፡፡ አይምሮ የሚያድግ በመሆኑ፤ በየእለቱ ግን እድገቱን የሚቆጣጠርለት ምንም አይነት መንፈሳዊ እርዳታ የለለበት በመሆኑ፤ የምንኖረው ኑሮ የጥንት እድገትን የማያሳይ፤ከቀን ወደቀን የሚያሽቆለቁል ነበር፡፡
በሴት ላይ የሚደረጉ ቅጣቶች አሳዛኝ እና ስውር ሆነው በዘመኑ እንዳለፉ የማይካድ ሀቅ ነው፡፡ አንዲት ሴት አስገድዶ መደፈር ቢደርስባት እንደእራሱዋ ጥፋት ታይቶ እንደምትንገላታእና እንደምትገለል በሽማግሌዎች ተደፋፍኖ ከመቅረቱም በላይ፤ ሬፕ አድራጊዋን እንድታገባ የምትደረግበት ሁኔታ ይህ ሁሉ ለሀይማኖት መሪዎች የተደበቀ አልነበረም፡፡ ሴቶች ካለአቻ ጋብቻ በሚደረግበት በፊስቱላ በሽታ የሚሰቃዩትን ባሕል እረጅም ግዜ ይዘን የተጉዋዝነው ይህም ለቤተክርስቲያን መሪዎች የተደበቀ አልነበረም፡፡ ስልጣኔያችን ከብዙ አገሮች ቀድሞ ቢጀምርም እድገታችን ግን ከሁሉም አገር እጅግ በጣም ወደሁዋላ የቀረ ያደረገውን
ነገር ለማየት አልደፈርንም፡፡
ሀይለስላሴ ቢወርዱ ልክ በኢትዮጲያ ላይ መቅሰፍት እንደሚወርድ አድርጎ እንድናይ ያስደረገን ነገር ቢኖር መሪዎችን ከፈጣሪ ባልተናነሰ መልኩ እናመልክባቸው እንደነበር የሚያሳይ ነው፡፡ ያንን የመሰለ ለም መሬት ያልተበከለ አየር ይዘን ግን ስንኖር የነበረው ሕይወት በችግር የተሞላ እንደነበር የማይካድ ሀቅ ነው፡፡ ዛፍን ቆርጦ እንኩዋን መልሶ አለመትከል የሚያሳየን ወፍ ዘራሽ የሆነውን ብቻ በመጠቀም መኖርን ነበር፡፡ የሀይለስላሴ መውረድ እንኩዋን እንደመቅሰፍት ሊሆን ቀርቶ፤ ወጣቱ በእልልታእና በሆታ ተቀብሎታል፡፡ ግን የተቀበለው የሚተካውን አገዛዝ የተሻለ ይሆናል ብሎ በመገመቱ አልነበረም፡፡ ለውጥ የሚፈልገው እግዚአብሄር የፈጠረው አይምሮ የደረሰበትን ለማሳየት የራሱን ዘመን እግዚአብሄር ይሰጣል እና እንጂ፡፡ ደርግ ግን ጭራሽ ወንጌልን አፋኝ ሆኖ ተነሳ፡፡ ደርግ የእግዚአብሄር ነገር አላስፈላጊ ነው ብሎ የተነሳበት ምክናያትም ያለፉት መሪዎች እግዚአብሄርን እያመለኩ እያስቀደሱ የሚሰሩት ስራ ትክክል ባለመሆኑ ነበር፡፡ የሀይማኖት መሪዎቹም ሆነ ወይም ክርስቲያን ነበሩ የተባሉት መሪዎች ስለእግዚአብሄር ሊመሰክሩለት የሚችሉበት የእግዚአብሄርን ስራ ሊያሳዩበት የሚችሉት እድገት ላይ ኢትዮጲያን አላመጡዋትም ነበር፡፡ ታዲያ ደርግ ምን አይቶ እግዚአብሄርን መኖሩን ይመን፡፡ የእግዚአብሄር ነገር በምስክርነት የተሞላ ነው፡፡ ግን በኢትዮጲያ ከደርግ ጊዜ በፊት የነበሩ ምን ብለው ስለእግዚአብሄር ስራ ይመስክሩ፡፡ ደርግስ ምን አይቶ እግዚአብሄርን ይፍራ ያክብር፡፡
እጃቸው ላይ ደም ያለባቸው መሪዎች አገሪቱዋን እየመሩዋት ቀሳውስት እየሰገደላቸው፤ እንዴት ተብሎ ነው ትውልዱስ ያንን የሚረከብ? ደርግ እኮ ማለት ሀይለስላሴ የወለደው ትውልድ ማለት ነው፡፡ ኢሕአፓ ማለት እኮ ወይ ሚኤሶን አልያም ወያኔ ሁሉም ሀይለስላሴ ያፈራው የወለደው ትውልድ ነው፡፡ አንድኛቸውም ከሰማይ ዱብ አላሉም፡፡ ሁሉም ለውጥ ፈላጊ በማይለወጥ ነገር የተሰላቸ ነበር፡፡ ይህ የሚያሳየው
ሁሉም ሀይለስላሴን ለመጣል አስተዋጽኦ ማድረጉን ነው፡፡ ወዳውም ደርግ ጋር ሁሉ ውጊያ ጀመረ፡፡ አዎ ሁሉም የተለያዬ መንገድ ያዙ፡፡ መከፋፈል የተፈጠረበት ሁኔታ የተፈጠረው በባህል በሀይማኖት ስር ታፍኖ የነበረው እውነት ድንገት ገሃድ በመሆኑ ብቻ ነው፡፡ እንዴት እንግዲሕ ለዘመናት ሀይማኖት ያለበት አገር ሪቮሊሽን አስፈላጊ ሆነ? ሀይማኖት እኮ የሰውን ልጅ ባህሪ የንጉሶቹን ባህሪ መለወጥ ስላልቻለ ነው፡፡ መጥፎ አገዛዝ የባሕሪ ምንጭ ነው፡፡ ኢትዮጲያ ከቀን ወደቀን ድህነትዋ እየበዛ የሚሄድ አገር እና ድርቅ እየመታት የሚሄድ አገር ሆና ነበር አኮ፡፡ ታዲያ ደርግ የሚመስለው ኢትዮጲያን ወደሁዋላ ያስቀራት ወንጌል መስሎ በገሀዱ ታይቶት ነበር፡፡ የእግዚአብሄር ስራ ምስክርነት የማይታይበት አካባቢ ዝምብሎ ሀይማኖት ብቻ ቢጋነን እግዚአብሄር ጠላት መስሎ ይታያል፡፡ አዎ እግዚአብሄርን የሚያሰድብ እግዚአብሄርን አውቃለሁ የሚል ነው፡፡ ዛሬ እኔ በመካነእየሱስእና በሙሉወንጌል እርዳታ ወንጌልን ተምሬአለሁ፡፡ ነውርን በእጅጉ እንድጠየፍ ሆኛለሁ፡፡ በቃ ማዳላትን፣ በሀሰት መመስከርን፣ ሰውን ማሳደድን፣ ውሸትን፣ ክደትን፣
አድሎን፣ ስግብግብነትን፣ አላግባብ መበልጸግን፣ ጥላቻን እና ዘረኝነትን መጥፎ መሆኑን እና ሀጢያት መሆኑን በደንብ ተምሬአለሁ፡፡ እግዚአብሄር የሞላው ሰው ደግሞ ይህንን የሚያደርጉ ሰዎችን መቃወም መብቱ ነው፡፡ በእርግጥም ያስፈራል በመንግስት የተቀመጡ ሰዎችን ሲያጠፉ መናገር፡፡ ግን እንድትደፍር የሚያደርግህ እግዚአብሄር በመንፈስቅዱስ ሲሞላሕ ብቻ ነው፡፡ እውነት ክርስቶስ ነው፡፡ ክርስቶስ ውስጥህ ሲገባ ብቻ ነው ነውርን የሚጠየፍ ነገር የሚኖርህ፡፡ ነውር የሚፈጽም ክርስቲያን፤ እየሱስ ውስጡ አልገባም ማለት ነው፡፡ አምናለሁ ወንጌል ኢትዮጲያን ይቀይራል፡፡ ግን ይህ የሚሆነው ሰው ሲማር እና የተማረውን ተረድቶ ሲፈጽመው ነው፡፡ መረዳትህ እውስጥህ የተደበቀውን ሕግ ማውጣት ስትችል ብቻ ነው፡፡ እውስጥህ ያለው እየሱስ የሞራል እና የባህሪህ ሕግ ነው፡፡
በቸር
ባዩሽ
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen