Samstag, 15. März 2014

ድክመቴን ያየሁበት ጉዞ






                    ድክመቴን ያየሁበት ጉዞ

አስተያየት መስጠት የአንዱ ከአንዱ አይበላለጥም፡፡ አስተያየት እራስን የሚገልጽ ነው፡፡ ለዚህም ነው እግዚአብሄር ለእያንዳንዱ ጭንቅላት ሰርቶ አይምሮን የሰጠው፡፡ ሁሉም ማሰብ ይችላል፡፡  ችግራችን በአገራችን ሁልግዜ፤ መስማት የምንፈልገው የምናውቀውን ወይም የምንፈልገውን ብቻ ነው፡፡ ተቃዋሚ መስማት የሚፈልገው ስለገዢው ፓርቲ ጥፋት ነው፡፡ ገዢው ፓርቲ ደግሞ ሁሉንም አስተያየት ሰጪ በተቃዋሚ የሚወነጅለው፤ የሕዝብን የማወቅ ችሎታ ለመመዘን ግዜ ስላላገኘ ነው፡፡ ልማት እና ደግሞ ተቃዋሚን መጠበቅ የህዝብን ግንዛቤውን አቅጣጫ ለማወቅ ግዜ ያሳጣል፡፡ ሕዝብ ዝም ስላለ አያውቅም አልተረዳም ማለት አይደለም፡፡ ብቻ ሁሉም ህዝብን እንደአላዋቂ ስለሚያይ የፈለገውን ይናገራል ይሰራል፡፡  ባወቅነው ነገር ላይ ብቻ እሱኑ ደጋግሞ በመስማት መኖር ማለቴ ነው፡፡ ሕግ እኮ አለ ግን የአፈጻጸም ችግር ነው ያለው፡፡ እውነቱ ሰው የሚፈራው ሕጉን ሳይሆን አሥፈጻሚውን ነው፡፡ ለምን ቢባል እሱም በሕግ መገዛት ምንነቱን ያላወቀ እና ያልተደራጀ ዜጋ ስለሆነ ሕጉን ማጣመም ቻለ፡፡ ጉቦ መክፈል ለምሳሌ የህዝብ ችግር ነው፡፡ ለመታገል ጉልበት ድሮም አላስተማረውም፤ ያስተማረው ፍርሀት ነው፡፡ የጥይትን ውለታ የሚያውቅ ተኩዋሹ ብቻ ነው፡፡ ኢላማውን ሲመታ፡፡   ስለዚህ  ጉልበቱ በቃ ቶሎ ገንዘብ ከፍሎ ማስፈጸም ነው፡፡ የሚገርመው ጉዳይህም ጥሩ ቢሆን ለዛ ለጥሩነት ለማስፈጸም ወደጉቦ ነው የምትሄደው፡፡ ሰውየው ስለለመደ ሁልግዜ ይጠብቃል፡፡ ስለዚህ የተወሰነውን ለመፈረም  ነገ ዛሬ ይልሀል፡፡  በጣም የሚገርም ነው፡፡ ይህ ለምዶእና  አድጎ ነው ጠቀም ያለ ጉቦ ደግሞ መክፈል የቻለ ህጉ ተጣሞለት አስወስኖ ይወጣል፡፡ „የሚልህ እሱ እነዴ ህይወቴን ሽጬ ነው እጀን የሰጠሁልህ“ ነው፡፡ለውጥ መጀመር ያለበት መጀመሪያ ከአስተሳሰብህ ነው፡፡ እውነት ነው፡፡ መለወጥ ከየአንዳንዳችን ማይንድ ውስጥ ነው ያለው፡፡ ለመታገል ጉልበት አለን ወይ? ከመሳሪያ በፊት እያንዳንዱ ለእራሱ ጉዳይ መቆም ችሎአል ወይ? አልቻልንም፡፡  የተማርኩት ሽሽት እና ዝም ማለት፤ ነው፡፡ ግን አንድ ነገር አለ፤ መለማመጥ እና ጉቦ መክፈል አልፈልግም ነበር ፡፡ ካልከፈልኩ መኖር እንደማልችል ግን አላወኩትም ነበር፡፡ ግን ደግሞ አንደዬ ጉቦ የከፈለ ሁልግዜ የሚኖረው በመክፈል መሆኑን አውቃለሁ፡፡  አንድ ሰው ከበደለን አቅሙ ስለለለን ቶሎ ብለን ተቃዋሚ ሊሰማ ወደሚፈልገው ነገር እንገባለን፡፡ አዎ አንድ ሰው በበደለን ኢሕአዴግ ወይም ወያኔ እንልእና እንቆዘማለን፡፡ እንጀራ አባት እንፈልጋለን፡፡ ይህ እኮ የእኔም ችግር ነው፡፡ ዛሬ ውድቀቴን ያየሁበት ነው፡፡ አቅም የለኝም ጉዳየን ለማስፈጸም ስለዚህ ሌላ አቅም ፍለጋ እወጣለሁ፡፡ እውነቱ ግን እዛም መብትን አላገኝም፡፡ መብት ከእኔ ውስጥ ኑዋሪ ናትና፡፡ ድክመት የሚገነባው ሌላ ደፋር ስለማይታይ ነው፡፡ሁሉም ተበድሎ ያነቁጣል፡፡ ማስፈጸም አንችልም፡፡ እራሳችን ባህሪውን ያበላሸነው ሰው ይጫወትብናል፡፡  እንዳውም የተበደለ ሰው አስፈራሪ ሆኖ የተመደበ ይመስልሀል፡፡ አለምን ድፍት የሚያደርግብህ፡፡ አንዳንዱማ ገና ጉዳይ ይኖረኛል ብሎ በምኑም በምኑም ለመዛመድ ጥረት ያደርጋል፡፡ አስቀድሞ መለማመጥ፡፡ ትክክል ነው ከጠመደው አይለቀውም እና፡፡ እኛ ፖለቲከኞችን የመርዳት አቅም የለንም፡፡ ገዢው ፓርቲን ያረዳ ተቃዋሚን ሊረዳም ልምምድ የለውም፡፡ ይህ እኮ የህብረተሰብ የልምድ ጉዳይ ነው፡፡ የባሕል ጉዳይ ነው፡፡ መረዳት እንጂ መርዳት በፖለቲካው አለም አናውቅም፤ ስራ ከማጣት መታገል ስራ አያስገኝም፡፡ ቢገኝም አንዱን አስወጥቶ ሌላውን መተካት ነው፡፡ ፖለቲካ እንግዲሕ በዚህ መሰል ከእንግዲሕ ቢጉዋዝ አደጋ ነው፡፡ እዛው ተፋጠን  ክፉውን መቃወም አንችልም፡፡ ለመደገፍም ለመጣልም ልምድ የለንም፡፡ በቃ በውስጡ የመደበቅ ልምድ ነው ያለን፡፡ ድሮም አንድ ባላባት በዘርህ ካለ በቂ ነው አትደፈርም፡፡ የእነእከሌ ዘር ትባላለህ፡፡ የሚገርመው ዛሬም ድረስ በዛው ዘር የሚኮራ ሞልቶአል፡፡  በደርግም አንድ ኢሰፓ ካለ አትደፈርም፤ ዛሬም አንድ ኢሕአዴግ ካለ አትደፈርም፤ በቃ ነገስ ለውጥ ቢመጣ ምን ዋስትና አለሕ? አንተ መስገድ ካላቆምክ ነገም ለሰው ትሰግዳለሕ፡፡ አዎ ዋስትናህ እራስህ ነሕ እንጂ ሀይለማርያም ወይም ብርሀኑ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ እነሱን አታገኛቸውም በቃ፡፡ ደረጃህም አይፈቅድም፡፡ ደረጃህ አጠገብህ ያለው ነው፡፡ በናታችሁ ብዙው እኮ ይህ መንግስት ደጋፊ መስሎ የተቀመጠ አለ፡፡ ግን ለመደገፉ ምንም አስተዋጽኦ የማያደርግ፡፡ ፓርቲን እራሱን መደበቂያ ነው ያደረገው የማስፈራሪያ፡፡ ምንም የፖለቲካ ስራ አይሰሩም፡፡ እራሳቸው እንዲፈሩ ብቻ ነው የሚሰሩት፡፡ ታዲያ እኒሕ ደጋፊ ይባላሉ እንዴ? ሌላውም ያው ነው ተቃዋሚውንም ዘራፍ ይላል ግን በቦታው አይገኝም፡፡ ግን በቃ ባህላችን ፍርሀት እና ማስፈራራት ብቻ ነው፡፡ በዚህ ታዲያ ስንት ፖለቲከኞች እናስረግማለን እናስጠላለን፡፡  በአጠቃላይ ሁሉንም ፖለቲከኞች እየጎዳን ከጨዋታ እያስወጣን ያለን የምንጠብቀውን ገደብ ያላበጀንለት ሰው ስለሆን ነው፡፡ በቃ እንደነብይ ነው መሰል የምናያቸው፡፡  ተቃዋሚ የዚሕ አይነት ስብስብ ይፈልጋል እነዴ ጉዳዩን ማስጨረስ ያቃተው ሁሉ? ወይም የግል ጠብ ያለው ሁሉ? ይቅርታ ሁላችንም ፖለቲከኞችን እንጎዳለን፡፡ የገዢው ፓርቲ ደጋፊውም ኪሱን እና ምቾቱን ብቻ አይቶ ከደገፈ፤ ሲወነጀል ወይም ሲከስር ተቃዋሚ ሆኖ እንደሚነሳ ጥርጥር የለውም፡፡ ስለዚህ ደጋፊም የሆነ አደጋገፉን ግንዛቤ በጨበጠ ምልኩ ያድርግ፤ የተቃዋሚም ደጋፊ እንዲሁ በግንዛቤ ያድርገው፡፡ ተቃዋሚ ወንጀል ያለበት እና የከፋው መሸሻ፤ ደግሞም ገዢው ፓርቲ የጉቦ በላተኛ እና የደላው መደበቂያ መሆን የለበትም፡፡ ይህን ከተለማመድን ፖለቲካ በእራሱ ነጻ ይወጣ ይሆናል፡፡ በአገራችን ፖለቲካ እራሱ ነጻ ሳይሆን ዲሞክራሲ ሊመጣ አይችልም፡፡ ዛሬ እኔ የምጽፈው የዲሞክራሲ እይታየን ለማሳደግ ፖለቲካ መጀመሪያ ከእኔ ከእራሴ እስር ነጻ እንዲወጣ ነው፡፡ በቸር እላለሁ
ባዩሽ
 


Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen