በኢትዮጲያ አስከፊው ገጽታ ክፍል 1
እኔእና ኮኮቤ ክፍል
በጡዋት ስነሳ ጸሀይዋን ማየት እፈልጋለሁ፡፡ድቅድቁ
ጨለማ ኑዋሪነቱ መሬት ላይ ነው፡፡ ፈገግታን ከሰማይ እጠብቃለሁ፡፡ አዎ ጨለማ ኑዋሪነቱ መሬት ላይ ነው፡፡ ጨለማ
በመሬት ላይ ባይወሰን ኖሮ ማንም ጨረቃን ወይም ከዋክብትን ባላዬ ነበር፡፡ ሀይል ከሰማይ መሆኑን የተመለከትኩት ጨለማን የሚያጠፋ
ብርሀን ከዚያ ሲፈልቅ በማየቴ ነው፡፡ የጡዋቱ ሲገርማችሁ ለሊትም ከዋክብትን እያየሁ ብቆጥራቸው ደስ ይለኛል፡፡ የከዋክብትን ቲያትራቸውን
ለማየት ስል አንዳንድ ግዜ የጨረቃን መውጣት እጠላለሁ፡፡ በድቅድቁ
ጨለማ ውስጥ ወደሰማይ ማንጋጠጥ እንዴት ደስ ይላል መሰላችሁ፡፡ በጨለማም ውስጥ ልመልከት ያለ ሰው የሚመለከተው አለ ማለቴ ነው፡፡
ልዩነቱ ግን እጨለማ ውስጥ ሆነህ እሱን ልመልከተው ካልክ ክብብ እፍን አድርጎ ይዞ ያስጨንቅሀል፡፡ በውስጡም ልመልከት ብትል የምታስበው
የጨለማው ጀግኖችን አይጥ፣ሌባ፣ሽፍታ፣ጅብ መከራና ጭነቅ ብቻ ነው፡፡ አንተ ግን ብልጥ ከሆንክ ጨለማውን ማየት ትተውና ወደሰማይ
ታንጋጥጣለህ፡፡ አዎ አንጋጥ፡፡ የጨለማውን ፍርሀት እና ድንዛዜ የምትወጣው እንደልባቸው የሚዘሉትን ከዋክብት ስትመለከት ብቻ ነው፡፡
ከአንዱ ወደአንዱ እንደጥሩ ፖስተኛ ይወረወራሉ፡፡ ይሽከረከራሉ፡፡ ማን ያውቃል መልክተኞችስ እንደሆኑ፡፡ ተመራማሪዎች እንኩዋን ተመራምረው
ያልደረሱበት አለም ላይ እንኖራለን እና፡፡ ይገርማል የማታየው ነገር የለም ትእግስት ኖሮሕ ወደሰማይ ካንጋጠጥክ፡፡ አይሰልችህ አንተ
የተፈጠርከው ሁሉንም ነገር አታካች በሆነ መልኩ እንድታገኝ ነው፡፡ ጨለማ የወሰደብህን ለማግኘት ከመታገል፤ ብርሀን የሚሰጥህን ደስታ
መፈለግ ይሻላል፡፡ ሁልግዜ አዲስ ነገር ታገኛለህእና፡፡
የለመደብኝ ይህ ነው፡፡ የከበቡኝን የጨለማ ሰዎች
ተወት አደረኩእና ወደሰማይ ተመለከትኩ፡፡ ፍርሀቴም እየቀነሰ የመጣው ወደብርሀን መመልከት ስጀምር ነው፡፡ አይኔን ከምድር ጨለማ
ሳነሳ፡፡ ታዲያ ትንሽ ልምዶቼን ላጫውታችሁ፡፡ ለነገሩ ኢትዮጲያ የእኔ እንግዳ ሆናችሁ ብጋብዛችሁ እውጭ ቁጭ ብለን ከዋክብትን እንድናይ
ነበር፡፡ ይህ ተረት ተረት አይደለም የማወራችሁ፡፡ እውነትን መሰረት አድርጌ ነው፡፡ ስለዚህ እኔን ሊጎበኘኝ የመጣ ወዳጅም ጠላትም
ከዋክብትን ሳላስቃኝ አለቀውም ነበር፡፡ የነበርኩበትም አስጨናቂው ሰፈሬ ከዋክብትን ለማየት ይመች ነበርእና፡፡ ታዲያ በተነሳሁበት
ሰአት ብነሳ ሁልግዜ አንዲት ለእኔ እይታ የምትሄድ ኮኮብ አያለሁ፡፡
በማንኛውም ሰአት ብነሳ ይህችን ነገር አያለሁ፡፡ እና ልቤ በደስታ ይሞላል፡፡ በተለያዩ ሰዎች የፍርሀቴ ደረጃ አይሎ ስለነበር፤
እግዚአብሄር ከእኔ ጋር ለመሆኑ ምልከት የላከልኝ መስሎ እስከሚታየኝ በዚች ሰማይ ላይ በምትሄድ ነገር/ኮኮብ/ ልቤ ይመሰጣል፡፡
እምነት ሞኝ ያደርግህና እንደልጅ ትሆናለሕ፡፡ „አጽናኜ ከሰማይ መጣ“ ተብሎአልእና አይኔን ከምድር ላይ ያስወገድኩበት ወቅት ነበር፡፡
አስፈሪዎቼን እቤት ውስጥ መጡ አልመጡ እያልኩ እራሴን ከማጨናንቅ፤
እውጭ እደጅ ሆኜ ልጠብቃቸው በማለት ነበር ውጩን የተላመድኩት፡፡ ጀግንነቴ ጨለማውን እንድሸሽ አደረገኝ እንጂ ሰዎቹን ግን ለመጋፈጥ
ደፍሬ አልነበረም፡፡ በውነት ፈርቻቸዋለሁ፡፡ ማነው የጨላማውን ጅብ የሚደፍር፡፡ እየሱስ ታልፎ የተሰጠበት ለሊት ትዝ ትለኛለች፡፡
የሚወዱት ሁሉ ዙሪያውን ተኝተው፤ እሱ ብቻውን ነበርእና፡፡ ይህ የክርስቶስ ለሊት በጭንቅ ውስጥ ብቻችንን እንደምንሆን አንድ መሰረት
የጣለ ትምህርት ለእኔ ሆኖአል፡፡ ጨለማን ማን ይወዳል? ምንአልባት በእጁ መሳሪያ የያዘ? ወይም አይምሮውን የሳተ? እርግጥ ነው ብዙ አይምሮዬን ሊያስቱኝ የሚችሉ መስፈራራቶች እና ክህደቶች
ደርሰውብኛል፡፡ ግን እየታገልኩ የነበረው ለመኖር ሳይሆን ላለማበድ
ነበር፡፡ ፖሊስ፤ እንኩዋን በስልክ ሄደህም ሊረዱህ የማይችሉበት አካባቢ
ኖሬአለሁ፡፡ እያሉ እንደለሉ ሆነው የሚኖሩ ማለቴ ነው፡፡ አያድርስ ነው፡፡ መንግስት አለሕ ግን ብቻህን ነህ፡፡ እንደምንም ብዬ
ዘመኑን መግፋት እንዳለብኝ የወሰነው የተሰጠኝ እድሜ እንጂ እኔ አይደለሁም፡፡ በጭራሽ እንኩዋን እራሴን ሌላውንም ለመጉዳት ፍላጎቱ
የለኝም፡፡ ጭካኔው የለኝም፡፡ የኢትዮጲን አስከፊ ገጽታ ተጋፍጨዋለሁ፡፡
መንግስት ቢቀየርም ይለወጣል የማልለው የጨለማው አለም ተገልጋዮች እየበዙ ሄደዋል፡፡ አዎ ብቸኛ የሆኑ ሴቶችን፣ ሕጻናትን እና በእድሜ
የገፉትን የሚጫን ብዙ ነገር ተፈጥሮአል፡፡ ልማት ሰብአዊነትን እየረገጠው እያፈነው የሚሄድበትን የአለምን አስተሳሰብ ፈጥሮአል፡፡
የማተርያል ጉጉት፤ የማንአለብኝነት ሁኔታ እየተስፋፋ የሄደባት ኢትዮጲያ፤
የሕግ የበላይነት አዲዎ ያለች መስላለች፡፡ ውነት በኢትዮጲያ የህግ የበላይነት ሊታወቅበት የሚችልበት ጊዜ ቅርብ ይሆን? ወይስ ነገሮች
ሁሉ ከፍተው ወደአልታሰበ አቅጣጫ ይጉዋዙ ይሆን? ሰው ሰውን ሲያስጨንቅ ምንአልባት ይህንን ሥጽፈው ቀሎኝ እንዳይመስላችሁ፡፡ ግን
እግዚአብሄር ከፈቀደ አንባብያን እራሳችሁን ትመረምሩበት ይሆናል ብዬ ስለምገምት ነው፡፡ ለውጥን ከመሰረቱ ምን ይመስላል እንድትሉ
ነው፡፡ አንዳንዶች ገመናን አታውጡ በማለት እራሳቸውን ደብቀው ለከፍተኛ የስነልቦና ቀውስ ይጋለጣሉ፡፡ እኔ ይህን አላምንበትም፡፡
በነገራችን ላይ እራሱን ትልቅ ያደረገ ሰው፤ ሁሉ ሚስጥሩ ነው፡፡ ለእኔ ግን ለእግዚአብሄር የሚታይ ነገር ሁሉ ሚስጥርነት የለውም፡፡
ነፍስ ገለህ እንኩዋን ብትደበቅ ለሰው ሚስጥር አድርገው እንጂ ለእራስህ ስቃይ ነው፡፡ አዎ እግዚአብሄር እንዳየብህ ውስጥህ ስለሚያይ
ትሰቃያለሕ፡፡ በመካከላችን መቼም ዩኒቲ እና አንድነት ለመፍጠር የተቸገርን ነን ብዬ እገምታለሁ፡፡ ይህ እከሌን እከሌን ማለት ያዳግተኛል፡፡
አዎ ግሩፕ መፍጠር እና የተወሰኑ ሰዎችን ብቻ ተጠቃሚ ማድረግ እንችላለን እንጂ ሰፋ ያለ የፍቅር እና የእኩልነት አንድነት ለመፍጠር አልታደልንም፡፡ በቤተክርስቲያን
እንኩዋን ግሩፕ አለ፡፡ የቄሱ የሆነ የወንጌላዊው የሆነ……..እያለ ይቀጥላል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በሰፈርም ያው ነው፡፡ በቤተሰብ
እንኩዋን ቢታይ እንዲሁ የተከፋፈለ እና በአድሎ የተሞላ ነው፡፡ ገዢው ፓርቲም ውስጡ በግሩፕ የተከፋፈለ መሆኑን እንሰማለን፡፡ ለምን
ይገርመናል ተቃዋሚም ፓርቲ በግሩፕ የተሸነሸነ ነው፡፡ አዎ በሁሉም የእነ እከሌ ግሩፕ አለ፡፡ ይህ የሚያሳየን የታመሰ ፍቅርን ነው፡፡
ገባችሁ አባባሌ፡፡ እንዋደዳለን እንላለን፤ ግን መዋደዳችን ጠላት ለሚባለው እይታ እንጂ እኛ ግን በያዝነው ነገር ላይ ውስጣችን
ያልተገናኘ ነን፡፡ አንተ ለሌላው ጀርባህን ሰጥተህ ታሳክካለህ፤ አንተ
ደግሞ የሌላውን ማከክ ነው፡፡ ሀሎ እከክልኝ ልከክልሾች፡፡ ካላችሁ በዬ ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ ጨለማውን ማሸነፍ ሳይሆን በውስጡ
ብቻህን ለእራስህ ትኖራለህ፡፡እራስህን ያሸነፍክ የሚመስልህ ሌላውን በሚጎዳ መንገድ ሄደህ መሆኑን አትዘንጋ፡፡ እንደኢትዮጲያ ባለው
አገር ማለቴ ነው፡፡ እኩልነት በለለበት ልልህ ፈልጌ ነው፡፡ ዩኒትን
መፍጠር የማይችል ባሕል ጎጆ የሰራብን ህዝቦች ነን፡፡ በነገራችን ላይ በጭንቀት የተነሳ ጎዳና ላይ የወጡትን ምክናየታቸውን በጭለፍታ ታሪክ ስንሰማ በቤተሰብ አካል፣ በሰፈር አሉባልታ
መገለል፣ እና በፍርደገምድል ዳኛ ውሳኔ እና በጉቦኛ ስራ አስፈጻሚ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ስለዚህ እኔ የማጫውታችሁን ገበና ማጋለጥ
ብሎ ወደንቀት የሚጉዋዘው አንባቢ እራሱን ትልቅ ወንበር ላይ ያስቀመጠ ጉረኛ ነው ብዬ ላርዳችሁ፡፡ከአንተ ብታሳንሰኝም እኔ ግን
እኔ እንጂ አንተን መኖር አልፈልግም፡፡ ለእኔ እግዚአብሄር ያየውን ነገር ሁሉ ሚስጥር እንዳልሆነ አውቃለሁ፡፡ ለማንኛውም በእኔና
በምትሄደው ኮኮቤ መካከል ያለውን ጉዋደኝነት እና ከሰማይ የመጣ ብርሀን ወደ ሰላም ምሪት ፍቅር፣ እና የእግዚአብሄር እመነት እና
መጽናናት ማወቅ ከፈለጋችሁ ሰሞኑን ክፍል ሁለትን ተከታተሉ፡፡ ደግሞም በኢትዮጲያ ውስጥ ያለውን የገጠሙኝን ችግሮች ቁልጭ ላደርግላችሁ
ተዘጋጅቻለሁ፡፡ አንዱ በአንዱ ላይ የሚሰራው ደባ ምንድን ነው? ገዢው ፓርቲ አመርቂ ስራ ሊሰራ ያልቻለበት እና የተቃዋሚ ፓርቲስ
ህልም የማይፈታበት ምክናያቶች ምን ይመስላሉ፡፡ ዘረኝነት በህብረተሰብ የፈጠረው መለያየት ምን ይመስላል፡፡ የትኛውን ክፍል ይጎዳል፡፡
ሕዝብስ እያወቀ እንዳላዋቂ የሆነበት ምክናያት ምንድን ነው? ፖለቲከኞች ኢትዮጲያን እንጂ ሕዝቡን አላወቁትም የምልበት ምክናያቶችን
እና እራስን ወዳድነትን ወደማይፈታ ጠብ ሊዳርገን እንደሚችል አብረን ይህንን ተከታታይ ጹሁፍ እንካፈል፡፡ ይህንን ጹሑፌን የግል
ህይወቴን ልምድ ያካተተ በመሆኑ፤ ላቀርብ የምችለው የአንባቢውን ቁጥር ስለሚወስን ጽሁፉን ሸር በማድረግ እንድትተባበሩ እጠይቃለሁ፡፡
ይህን የምልበትም ምክናያት የአንዳንዶቻችን ልምድ በመካከላችን ያለውን አስቀያሚ ስራዎች እንድናይ እና፤ ኢትዮጲያን መሰረታዊ ችግሮቹዋን
አይተን እንድንቀርፋቸው ይረዳናል ብዬ ስለምገምት ነው፡፡ አንድ እማምነው ነገር የእኛ መነጋገር እና ማወቅ፤ በፖለቲካው አለም የማየው ድግግሞሽ ጥፋት ኢትዮጲያን ወደስርአት አልበኝነት
እንዳይመራት ሊረዳን ይችላል፡፡ በሉ ከስደት አገር በኢትዮጲያ ያየሁዋትን የምትላወሰውን የተስፋዋን ኮኮቤን ትዝታ ይዠ እቀርባለሁ
እና በክፍል ሁለት እንገኛኝ፡፡በቸር ልበላችሁ፡፡
ባዩሽ
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen