በኢትዮጲያ አስፈሪው ገጽታ ምእራፍ 3
ኮኮቤ ኮኮቤ፤ የአይምሮ ትብታቦች
በውስጣችን ያለውን እግዚአብሄርን መጠቀም ሲያቅተን
የሀጢያት መንገድ እንሄዳለን፡፡ በውስጣችን የሚኖረው እግዚአብሄር ካልረዳን በስተቀር ሁላችንም ወንጀለኛ ነን፡፡ ተው አታድርገው
የሚለው ከውስጣችን ይወጣል፡፡ ደግሞ እምቢ ብለን ካደረግነው ሕሊና ይወቅሳል፡፡ በቃ እረፍት አይሰጥህም፡፡ አንተኑ ወቃሽ እሱ እንጂ
ሰው ባላየው ነገር ሊወቅስሕ አይችልም፡፡ለዚህም ነው የበደልከው ሰው ጋር አብረሕ እየኖርክ ያለው፡፡ ሰውማ ቢያውቅብህ ህሊናህም
ባልወቀሰሕ ነበር፡፡ በውስጣችን እንግዲሕ ስህተት እንዳንፈጽም የሚመክረን ሲኖር፤ካደረግንም እራሱ ወቃሽ እና ገሳጭ ሆኖ ይቀርባል፡፡
አንዳንደዬ ስገምተው ከምክሩ በላይ ተግሳጹ የበለጠ አስደንጋጭ እና እረፍት ነሽ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የሐጢያት ትንሽ የለውም፡፡
ይህ በእኛ ውስጥ ያለ መንፈስ ግን ስራውን የሚሰራው አንተ ውስጥ የእግዚአብሄር መንፈስ እንዳለ ስትረዳ ብቻ ነው፡፡ ሰዎች ፍጹም
ከእግዚአብሄር የሚለዩበት ምክናያት እግዚአብሄርን ኑዋሪነቱን ከእነሱ ውጭ እራቅ ብሎ የሚኖር ስለሚመስላቸው ይመስለኛል፡፡ እግዚአብሄር
ግን በውስጣችን እንዲኖር ለክርስቲያኖች በእየሱስ ክርስቶስ በኩል እንድናይ እንድንማር ሆነናል፡፡ እየሱስ ለዘላለም ከእኛ ጋር መኖሩን
ሲነግረን በመንፈስ እንጂ በስጋ እንዳልሆነ የምናየው እሱን በስጋ ስለማናየው ነው፡፡ ደግሞ ለዘላለም በአካባቢያችሁ እኖራለሁ ስላለ
የት እንዳለ እየተዘዋወርን የምንፈልገው እንዳልሆነ መመልከት ግድ ሊለን ይገባል፡፡ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ ሲል ታዲያ በእያንዳንዳችን
ውስጥ ማለት ሆኖ ይሰማናል፡፡ በውስጣችን አዛኝ ሊያደርገን የሚችለውን መንፈስ እኛው እራሳችን ደብቀን ከያዝነው ዋጋ የለውም፡፡
ግን መረዳት ያለብን በውስጣችን መንፈስ እንዳለን ነው፡፡ ይህ መንፈሳችን ነው ከእግዚአብሄር መንፈስ ጋር ሊገናኝ የሚችል እንጂ
ስጋችን አይደለም፡፡ እግዚአብሄር በስጋ የምናየው አይደለም፡፡ በአምሳያ ፈጠርኩዋችሁ ሲለን የእሱን አምሳያ በአይኑ ያየው የለም፡፡
ግን አምሳያ ማለት የመንፈስ ጉዳይ ነው፡፡ እግዚአብሄር የሰውን መንፈስ ያውቃል፡፡ ሰውም ደግሞ በመንፈሱ ስለሌላው የመንፈስ ሁኔታ ሊረዳበት የሚችል ሁኔታ ይኖራል ማለት ነው፡፡ ይህ
ግን የሚሆነው ጌታ በሰጠው በረከት እንጂ ሰው በፈጠረው አለመሆኑን እናውቃለን፡፡ በውስጣችን ስለሌላው በደል መታወክ መቃተት ያለን
ሰዎች እናስተውል፡፡ ይህ አዛኝ የሆነ ከውስጥ የሚመነጭ ምንጭ ለአንድ ግለሰብ የተቸረው ሳይሆን በሰው ልጅ ሁሉ ውስጥ እኩል የተሰጠ
መንፈስ ነው፡፡ ለዚህም ነው ብዙ ስለዳግም መወለድ የሚነገረው፡፡ ዳግም መወለድ የሚረዳሕ በውስጥህ ያለውን እግዚአብሄር የሰጠህን
ትልቅ ስጦታ እንድትጠቀም ያደርግሀል፡፡ እንድታስብ እንድታውቅ ይጠቅመሃል፡፡
ደግሞም የትናንት ሀጢያትህን እንዳትደግመው አድርጎ ወደመጸጸት ያመጥሀል፡፡ ነውርን ቁልጭ አድርጎ የሚገልጽልህ ከውስጥህ ይወጣል፡፡
ነውርን የማያውቅ መሪ ቢሆን ሕዝብን ይጎዳል፡፡ ይህ እንዳይሆን ሁሉም ሰው በመንፈሱ ከእግዚአብሄር መንፈስ ጋር የሚገናኝበትን መቃተት
መፍጠር አለበት፡፡ በመንፈስህ መጸለይ፣መዘመር፣ሀሴት ማድርግ፣ በውስጥህ ያለውን የተዳፈነ እሳት ያቀጣጥለዋል፡፡ ይህ በውስጥህ ያለው
መንፈሳዊ እሳት ስለአካባቢያችን ሁኔታ እንኩዋን እንድንረዳ የማድረግ ሀይል አለው፡፡ እራስን ወዳድ ፣ ቀናተኛ፣ ስግብግብ እንዳንሆን ይረዳናል፡፡
ለሌላው እንድናዝን የሚያደርገን ሀይል የሚመነጨው ከውስጣችን እንጂ ከፖለቲከኞች ወይም ከፓርቲያቸው የሚመጣ አይደለም፡፡
የእኛ ወደእግዚአብሄር ሞራል ማሰብ እርግጥ ነው ጥሩ ፖለቲከኞች እንድናፈራ ሊያደርገን እንደሚችል ጥርጥር የለውም፡፡ ክርስቲያኖች
ስል የክርስቲያን ፖለቲከኞች ብቻ ይቁዋቁዋሙ ለማለት ፈልጌ እንዳልሆነ ሙስሊም ወይም ሌላ እምነት ያላችሁን ሰዎች ተረዱልኝ፡፡ ሌላውን
ለመጫን ፈልጌ እንዳልሆነ እንድትረዱልኝ ከመፈለጌም በላይ መንፈሳዊ
ሕይወቴም ሌላውን እንዳገል አያበረታታኝም፡፡ ይህቺ አለም የሁሉ መኖሪያ እንድትሆን ያደረገው የፈጠረን እንጂ ሀይማኖታችን አይደለም፡፡
በዚህም የተነሳ የሀይማኖትም ግጭት ፍሬ የማያፈራ ይሆናል፡፡ በእምነት በኩል ሰው ሰውን ሊፈርድበት አልተጠራም፡፡ ማንም ሆነ ማንም
እውስጡ ያለውን ነገር መርምሮ ይድረስበት፡፡ በጎ የሚወጣው ከሚራራው ፈጣሪያችን ብቻ ነው፡፡ ክፉ ከሰይጣን ነው፡፡ ፈጣሪያችን መራራቱን
የምናውቀው በሰጠን የዚሕ አለም እኩልነት ነው፡፡ እራቁታችንን ተወልደን ሁላችንም እራቁታችንን ከዚህ አለም መሄዳችን ደስ ሊላችሁ
ይገባል፡፡ በወርቅም ሳጥን ተቀበር በሰሌን ተቀበር የአንተ የስጋ ሰውነት አገልግሎቱ እዚህ ላይ ያቆማል፡፡ እነፈርኦን ወርቅ ይዘው
መቀበራቸው አንሶአቸው ድስትና ጀበናም አስከትለው ነበር፡፡ ይህ ብቻ
ሳይሆን አገልጋዮቻቸውንም ደግሞም ሚስትም ይዘው ተቀብረዋል፡፡ የመሰላቸው የወዳኛው አለም በዚህ አለም እንደነበሩ ሆነው የሚፈላሰሱ
መስሎአቸው ነበር፡፡ ግን ዛሬ መቃብራቸው ሲከፈት ከእነሱ ሰውነት ይለቅ ወርቃቸው እና ሸክላዎቻቸው በደህና መውጣቱእና ለሙዘየም
ታሪክ መሆኑ ነው፡፡ እነሱ „አፈር ነሕእና ወደአፈር ትመለሳለህ“ ባለው መሰረት አፈር ጋር ተቀላቅለዋል፡፡ አጥንታቸውም መመራመሪያ
ሆኖአል፡፡ ተገፍተው ግን ያለፉት ማንም ስላልነበሩእና ወርቅም ይዘው ስላልተቀበሩ የተቀበሩበትን ጉድጉዋድ ለመማስ የሞከረም የለም፡፡
የዚህ አለም ነገር የሚያገለግልህ ለዚህ አለም ብቻ ነው፡፡ ወርቅ ይዘህ ብትቀበር ከሞት በሁዋላ ተፈላጊው ወርቁ እንጂ አንተ አለመሆንህን
ተረዳ፡፡
እኔ የተማርኩትን እና ያወኩትን ነገር ለመኖር
ወደሀይማኖት እሄድ እንደሆን እንጂ፤ ሀይማኖት በእራሱ ወደእግዚአብሄር መንፈስ ያመጣኛል ብዬ አልገምትም፡፡ ሀይማኖት የበለጠውን
ነገሩን ወደባሕል አዝማሚያ ወስዶት የእግዚአብሄርን ነገር እንዳያዘናጋኝ እፈራለሁ፡፡ ይህ ባይሆን ሁሉም እንደአብራሀም በሰንበሌጥ
ቤት በኖረ መሬትንም ባላበላሻት ነበር፡፡ ሌላውን በስውርም መበደል ሞራል የሌለው ነገር መሆኑን ብናውቅም የምንፈጽመው በውስጣችን
የሚኖረውን የእግዚአብሄር መረዳት በመናቅ ወይም በመዘንጋት ነው፡፡ ወቃሹ እግዚአብሄር በውስጣችን እንዳለ መቀበል ግድ የሚለን ምእራፍ
ላይ መድረስ አለብን፡፡ እየተወቀሰ የሚኖር ሰላሙን የነሳ ይሆናል፡፡ አንድ ታሪክ ላጫውታችሁ፡፡ አንድበካቶሊክ እምነት ያደገ ሰው፤
ትልቅ ሆኖ ከአንድ የጀርመን ባንክ ገንዘብ ይዘርፋል፡፡ ከዛም በጣልያን አገር ተሰውሮ ለአስራአምስት አመት ስጋዊ ሰላም ከኖረ በሁዋላ፤
ከአስራ አምስት አመት በሁዋለ እጁን ለፖሊስ ይሰጣል፡፡ እሱም እያለቀሰ
የአስራአምስት አመት ስቃዩን ይናገር ነበር፡፡ ይህን እረጅም አመት የኖረው እንቅልፍ በማጣት ፣በውስጣዊ መረበሽ እና አለመረጋጋት በመሆን ማሳለፉን ያስረዳል፡፡ ፖሊሶች ይህን ሰው አውቀው አልተከታተሉትም፡፡
ፋይሉ የተዘጋ ማንነቱ ያልታወቀ ሌባ ሆኖ አልፎአል፡፡ ግን ውስጠ ኅሊናውን በወቀሳ በመሙላት፤ ያ በልጅነቱ የተማረው ፈሪሀ እግዚአብሄር
ወደሰላሙ እንዲመጣ አድርጎታል ፡፡ „ ስተኛ የማልመው ሕልም ህይወቴን ፍሬን እንደለለው መኪና ሆኖ በአየር ላይ ሲበር ነበር፡፡
እጅግ በጣም በስቃይ ኖሬአለሁ“ በማለት እያለቀሰ በፈቃደኝነት ወደእስር ቤት ገብቶአል፡፡ ይህን ተንፍሶ ግን ከታሰረ በሁዋላ የተሰማው
ደስታ ካለፈው ዘመኑ ሁሉ የተሻለ ነው ብሎአል፡፡ እንግዲሕ ከውጩ ይልቅ በእስር ቤት ያለው ደስታ የበለጠበት ሰው፤ መንፈሳዊነቱ
ከስጋዊ ህይወቱ መብለጡን የምናይበት ነው፡፡ ግን ከገንዘብ በላይ
በመካድ፣ በሀሰት በመመስክር፣ በፍርደገምድልነት፣ ሆን ብሎ ከሕብረተሰብ አንድን ሰው እንዲገለል የማደረግ አሉባልታ ፈልስፎ
በማግለል የብዙ ሰዎ አይምሮ ያበላሹ ዛሬ ካለምንም ንስሀ አብረውን
ይገኛሉ፡፡ ይህ የሚሆነው ህሊናቸውን የሚወቅሳቸው መንፈሳዊ ትምህርት ባለመማራቸው ነው፡፡ እነሱም በዚሁ ሁኔታ መካከላችን ተገኝተው
ተግባራቸውን ይቀጥሉበታል፡፡ ሕሊናቸው የሚወቅሳቸውን ዳግም መወለድ ይጠሉታልእና፡፡ አገራችን በዚሕ የታደለች ትመስላለች፡፡ በእያንዳንዳችን
የደረሰብንን በደል ስንመለከተው ሰዎች አሰቃቂ የሆነ ነገር ልንሸከመው የማንችለውን ነገር ይፈጽሙብናል፡፡ ከቶም ከራሳቸውም አልፈው
ግሩፕ በመፍጠር አንድን ሰው ብቸኛ አድርገው በውስጡ የብቸንተን በረዶ ይከቱበታል፡፡ ይህን ቅዝቃዜ ያልቻለ ያብዳል፡፡ የቻለው ደግሞ
ጥግ ይዞ የደም እንባ ያለቅሳል አልያም እራሱን ይገላል፡፡ እነሱም ሰውን በማግለል እና ስቃዩን በማብዛት ከፊታቸው ሲያጡት በደስታ
ይሞላሉ፡፡ ሰውን በማሰቃየት በደስታ የሚሞላ ግሩፕ ወደሳዲስትነት እንዳለፈ ለማገናዘብ መንፈሳዊ እውቀት የላቸውም፡፡ እንዳውም እንደድል
አድራጊ የሚቀጥለውን ተጠቂ በመቀጠል ይፈልጋሉ፡፡ በዚህም የተነሳ
ነው ኢትዮጲያ ውስጥ ግሩፕ አበልጅ አይት ምራት እያለ የቤተሰብ ሴክት ደግሞም የሰፈር እና የጉዋደኛ ግሩፕ ፈጥሮ ጠንካራ ተከላካይ
መስሎ የሚታየው፡፡ እውነቱ ግን እኔ እነደተለማመድኩት ግሩፕ የሚፈጠረው ሌላውን ሰባብሮ ለመጣል እንጂ ብዙ ግዜ በጎነቱን ልለማመድ
አልቻልኩም፡፡ ካለምንም ምክናያት አንዱ የጠላውን ሌላውም አብሮ ይጠለዋል፡፡ ይህን ግሩፕ ሁሉ የአይምሮ ትብታቦች ብያቸዋለሁ፡፡
ይህ አይነት በፍቅር ሳይሆን ከቅናት የተነሳ ደግሞ እራስን ከመከላከል ብሎም አላግባብ ለማካበት የተነሳ የሚፈጠር ቡድን አደገኛ
እና የስልጣኔ እንቅፋት ከመሆን አልፎ እግዚአብሄር የፈጠረውን አገልጋይ አይምሮ የሚያበላሽ ነው፡፡ ይህ አይነት ባህል ከአገራችን
ካልጠፋ የፖለቲካ ለውጥ ይመጣል ብሎ መገመት አይቻለም፡፡ ግሩፕ ሁልግዜ ሀሰተኛ ምስክርን የሚያዘጋጅ ወጥመድ ነው፡፡ ውድ ወገኖች
በብቸኝነት የተነሳ ተዘዋውሬ እራሴን ለመርዳት ያደረኩት ጥረትም በቤተክርስቲያን ውስጥ ጥላ እንድፈልግ አድርጎኝ ነበር፡፡ እዛም
ግን ከአካባቢ የወረስነው የግሩፕ ባህል አብሮን ገብቶ ኖሮ የተከፋፈለ ግሩፕ እና መናቆር እና አዲስን ሰው የማግለል አባዜ የሞላው
ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ በአድሎ የተሞላ ነበር፡፡ እንግዲሕ ቤተክርስቲያን ውስጥ መገኘት ማለት ዳግም መወለድ እንዳልሆነ ተረድቻለሁ፡፡
ዳግም መወለድ ለእኔ ውስጣዊ ውድቀትህንም የሚያሳይ መንፈሳዊነት ነው፡፡ ግሩፕ ወደአላስፈላጊ ፍርድም ያስገባናል፡፡ ግሩፕ ሌላውን
ለምድራችን ያለውን እውቀት እንዳይጠቀም ያደርጋል፡፡ ግሩፕ የምድራችንን በረከት ያዘጋል፡፡ የአንተ በክርስትና አለም ውስጥ እረጅም
አመት ማሳለፍህ ሳይሆን መንፈሳዊነትን የሚናገረው፤ በውስጥህ ያለውን እግዚአብሄር መጠቀም ስትችል ብቻ ነው፡፡ መንፈሳዊ የሚያደርግህ
መንፈሳዊ መረዳት ብቻ ነው፡፡ መንፈሳዊ ማንነትን በስጋ ለመተግበር
ወሳኙ መንፈሳዊ እውቀትህ ነው፡፡ ይህን እስከምትረዳ ድረስ ሌላውን በሚሰቃይበት በማየት ደስታ ተውጠህ ትኖራለህ፡፡ ታዲያ ሙስና
እራሱ ምንም ስለማይመስልህ ግሩፕህን ይዘህ ትጠቀማለህ፡፡ በሌላው እሬሳ ላይ እየተራመድክ ፖለቲከኞች ህይወታቸውን የሰጡበትን ለውጥ
ታበላሻለህ፡፡ ቄሶችን ታሳስታለህ ባለስልጣን ታባልጋለህ፡፡ ሴትንና ህጻናትን ሜዳላይ ትበትናለህ፡፡
እንግዲህ እኔም ወደሰማይ ያንጋጠጥኩትና የምትሄደውን
ኮኮቤን ማየት የቀጠልኩት በውስጤ ያለውን በረዶ የሚያቀልጠው ሙቀት ፍለጋ ነው፡፡ ግን የሚገርማችሁ እኔ ወደሰማይ በተመለከትኩ ቁጥር
በውስጤ የተለየ ሙቀት ይሰማኝ ነበር፡፡ በረዶውን ላስበው እንጂ ለካስ እየቀለጠ ኖሮአል፡፡ የሚያስፈራን ነገር ሁሉ እነሆ አልፎአል፤ያልፋልም፡፡
ነገሩ ከአይምሮ ውስጥ ነው፡፡ እይኔ ወደሳመይ ይሁን እንጂ ጨለማውን
የሚያበራው መብራት ከእኔ ውስጥ አለ፡፡ ግን የሚያቀጣጥለውን ዘይት ተስፋዬ በውስጤ ያፈሰዋል፡፡ ኮኮቤ ኮኮቤ አንቺን ለማየት ወደሰማይ
በአንጋጠጥኩ ቁጥር የእግዚአብሄርን ታምር ከአይምሮበላይ መሆኑን ተረዳሁ፡፡ የማየው ነገር ሰፊ እና በምንም መመራመር የማይደረስበት
ስለሆነ ኮኮቤንም ሳተላይት ናት ብላችሁ ትመልሱልኝ ይሆናል፡፡ አዎ ለመንፈሳዊ ሕይወት ለማይቀበል ሰው መልሱ አጭር እና አንድ ነው፡፡ ታአምር ሰሪውን የማያውቅ ታአምርን ማየት ይሳነዋልእና፡፡ እኔ ግን
ያለምኩትን የማይ ባለራእይ ስለሆንኩ አገሬም ማየት የሚገባትን እውነትን እንደምታይ ተስፋዬ ሙሉ ነው፡፡ በቸር ልበላችሁ፡፡
ባዩሽ
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen