Dienstag, 25. März 2014

እራስን የመኖር ወሳኝ ሚና



                   እራስን የመኖር ወሳኝ ሚና

ስለዘር ማውራት ጥቅሙ ብዙም አይታየኝም፡፡ ግን ስለሰው ብናወራ ደስ ባለኝ ነበር፡፡ ይህንም የምልበት ምክናያት፤ ሰው እንጂ ባለባህሪ ዘር መቺ ሆነእና፡፡ ለነገሩ እኔ ከአማራነቴ ለመሸሽ እንዳልሆነ እወቁልኝ፡፡ አማራ ነኝ አንተ ኦሮሞ አንተም ትግሬ እንደሆንከው፡፡ እኔ ግን ከማንኛችሁም ጋር ለመኖር ችግር የለኝም፡፡ ግን ምንአልባት ልብ አለን እና ከልብ እንድንሆን፤ ይህቺን ጡሁፌን ላቅርብ፡፡ መጀመሪያ እናንተ ሁላችሁንም የሚመቻችሁን ጽሁፍ ባልጻፍኩ ቁጥር፤ አንደዬ ወያኔ አንደዬ ተቃዋሚ ብሎም አንደዬ ትግሬ አንደዬ አማራ ናት እያለ የሚሞግተኝን ዝም ብዬ አየዋለሁ፡፡ እኔ ለሁሉ መመቸት የለብኝም፡፡ አይግረማችሁ እና ሁሉንም እመቻለሁ ብዬ እራሴን ሳልኖር እንዳልሞት ስለምፈራ ነው፡፡ ለማንኛውም የሽሽት ወይም የማፈር እንዳይመስላችሁ፤ እኔ ግን ጥርት ያልኩ አማራ ነኝ፡፡ ወያኔም ሆኜ አልጨፍርምም አልቆዘምም ፤ ተቃዋሚም ሆኜ የተቃዋሚን ፓርቲም ደግፌ ሆ የምል ወይም የምደበር አይደለሁም፡፡ ሳይጠሩት አቤት ሳይልኩት ወዴት የማልል አንዲት የኢትዮጲያ አገር ሴት ነኝ፡፡ አንዲት ሴት፤ ወሎ ደሴ ላይ ተወልዳ ያደገች ፡፡ አዎ ከነሸህ ኑሩ መንደር እነ ንጉስ ሚካኤል ቤተመንግስት አጠገብ፡፡ አድራሻ ያለኝ አማራ ነኝ፡፡  አንድ ግን ነገር አለኝ ከሁሉ ጋር የመኖር ችግር የለለኝ ነኝ፡፡ ሰውን የማየው ዘሩን ሳይሆን ባህሪውን ነው፡፡ የተሰጠኝ የልብ ኩራቴ ጣቴን አለመቀሰር በትናንትናው አለመቆዘም፤ የዛሬውን መኖር፤ ነገን በተስፋ መጠበቅ ነው፡፡ ነገን እኖራለሁ ብሎ ዋስትና የተሸከመ ሞኛ ሞኝ ቢጤም አይደለሁም፡፡ አማራ ብለህ አትስደበኝ፡፡ ብትሰድበኝም እታዘብሃለሁ እንጂ አልሰድብህም፡፡ እውቀትህን እመዝንብሃለሁ እንጂ ደንቆሮ አልልህም፡፡ ከወጣህበት ደረጃ ላይ እንዳትወድቅ ቀስ በል እልሃለሁ እንጂ አልደግፍህም፡፡ አረማመድህን እይ እልሃለሁ እንጂ፤ እንቅፋቱን አላነሳልህም፡፡ ወዳጄ ወገኔ አይንህን ክፈት እልሃለሁ እንጂ፤ እንድታዬኝ አላስገድድህም፡፡ ይህን ካልኩኝ ዘንዳ፤ እስኪ ትንሽ ልበላችሁ፡፡
አፍንጫን ሲመቱት አይን ያለቅሳል እንዳይሆንብኝ፤ አሉኝ የምለውን ዶሴ ከፍቼ ዘርን ወደዘር ለመክሰስ አልሮጥም፡፡ ከዘር አጥፊው መች ሁሉ ሆነእና፡፡ አንድ ቀን የገጠመኝን ልንገራችሁ፡፡ ምክናያቱን በማላውቀው ነገር አንዲት ሴት ጥምድ አድርጋ በድንገት ያዘችኝ፡፡ ጥረቱዋ ሁሉ በምኖርበት ሰፈር ታማኒነትን እንዳላገኝ ነበር፡፡ ስራዋን ምንነቱን ባላውቀውም ግን ቀበሌ ጋር እጅግ የጠበቀ ግንኙነት አላት፡፡ በውነት ለማጣራትም አልሞከርኩም፡፡ እኔ የእራሴን ኑሮ ለማሳካት ደፋ ቀና የምል ሴት ነኝ እንጂ ስለሰውም ስለፓርቲም  የማስብበት ግዜው አልነበረኝም፡፡ በዚች በሴትዮም የተነሳ ማህበራዊ ኑሮዬ የደመቀ ሊሆን አልቻለም፡፡ የአገሬ ሰው ለመፍረድ የሚቸኩል በሰማው የሚጉዋዝ እንዳይሆን የፈራሁበት ወቅት እና የፈራሁትን ደርሶ ማየቴ ይገርመኛል፡፡ ሰው የሚያውቅህ በሰው ነው፡፡ የሰነፍ ልብ ጉዞ፡፡ ስለዚህ ትቸዋለሁ፡፡ ከስደት የተመለስኩት ሕግን ተማምኚ ነበርእና፤ ይህቺ ሴት ለምታደርስብኝ ችግር የዘመድ አዝማድ ስብስብ ለማግኘት አልጣርኩም፡፡ ዘመድ አብረህ የኖርከው እንጂ፤ የተወለደህ አይደለም፡፤ ከተወለደህ ጋር ለብዙ አመታት ከተለይ የመረሳት ነገር አለ፡፡ ዝመድናው ከስም ያላለፈ ይሆናል፡፡ የኢትዮጲያ ኑሮ በህግ የተከበረ ሳይሆን በማህበራዊ ኑሮ ትሰስር በቲፎዞ አይነት ነገር ሆኖ አየሁት፡፡ በልጅነቴ የተለየሁት  አገር አድካሜ እንደሆነብኝ ተረዳሁ፡፡ ያ የማህበራዊ ህይወት በመቻቻል የሚኖር ህዝብ መካከል ስኖር ለእኔ ህግን ለተመረኮዝኩት ሴት ባይተዋርነት በልቤ ውስጥ እየሰፋ ሄደ፡፡ ያቺ ሴት ስትጨመር ጭራሽ አስቸጋሪ ሆነብኝ፡፡ ቀስ ብላ እየመጣች ነፍጠኛ ብላ ሰድባኝ ትሄዳለች፡፡ በውነት ምንም ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ብዙም ስለፖለቲካው የማውቀው ጉዳይ የለኝም፡፡ የተመለስኩት ከተዘጋው ጀርመን ነው፡፡ ዝግ ያልኩት ዲሞክራሲ ነው፤ በህግ የበላይነት እሚጠላህ ሰው መካከል በሰላም መኖር ነው፡፡ ግራ ግን ተጋባሁ፡፡ ኢትዮጲያ ይህ የለም፡፡ ለመታየትም ጭላንጭል የለውም፡፡ ፍርድ ቤቱ ምን እንደሚሰራ አላውቅም፡፡ የሕግ ጥሰት እንደመብዛቱ፤ ፍርድ ቤቱ ሀያአራት ሰአት በሰራእና ሰውን ወደህግ በጋበዘ ነበር፡፡ ግን ፍርድቤቱ የሚጋብዝ አይደለም፤ የሚያስደነግጥ እንጂ፡፡ አንዳንዱ ግለሰብ እንደተፈቀደለት ሁሉን ሲያደርግ ሲፈጽም ታየዋለህ፡፡ የወረዳው ቢሮ፣ ፖሊስ ጣቢያው እና የፓርቲው ጸ/ቤት እንደእራሱ ጉዋዳ ነው የሚያየው፡፡ ስለዚህ በሴትዮዋ ጋጥ ወጥነት ብዙም አልደነገጥኩም፡፡ ሕግን እንድታፈርስ እንጂ እንድታከብረው የሚያደርጋት አስተማሪ አላገኘችም፡፡ ጭራሽ እንድታበላሸው እንጂ፡፡
ለምን ዘመቻው እንደመጣ አላውቅም፡፡ ሕይወቴ ከቀን ወደቀን የሰቆቃ ሆኖአል፡፡ ሴትዮዋ ስለእኔ ዘር ከእኔ በላይ አጥንታለች፡፡ አልፎ አልፎ ሸርሞጣ ብላ ትሰድበኛለች፡፡ እኔ ግን መልስም አልሰጥ፡፡ ደፍሮ እሕዝብ መካከል የሚሰድበኝ ዱላ አንስቶ ለመማታት ወደሁዋላ ስለማይል ሰባራ አጥንት አልፈልግም እና ዝም ካለማለት በቀር አማራጭ የለኝም፡፡ እኔ የእሱዋን ባል ቀርቶ የእራሴ የሆነም ለመፈለግ የምነሳሳ የወንድ ሱስ ያለኝ ሴት አይደለሁም፡፡ ሴት ወንድ የሚፈልገው በአይምሮው ነው፡፡ ሴት ባለጡንቻ አይደለም፡፡ አይምሮዬ የተጠመደው በኑሮዬ ላይ ነው፡፡ በስራ ይደክመኛል፡፡ ስለዚህ ሸርሙጣ ብሎ የሚያሰድበኝ እንዝላልነት የለኝም፡፡ ደግሞም በኢኮኖሚ እራሴን የቻልኩ ስለነበርኩ፤ እንደቸገራቸው ሴት እህቶቼ ወደዚህ ስራ ለመሄድ የሚያስገድደኝም ነገር አልገጠመኝም፡፡ አልኮሆልም በተፈጥሮዬ ስለማልወድ ስለማልጠጣ ስክሬም የሳተ ስራ ስሰራ አላየችኝም፡፡ የሰው ባልም አልነካም፤ አልመለከትምም፡፡ ይህ ባህሪየን የሚገልጥ ስላልሆነ በስተጀርባው ያለውን የዘር ጥላቻ እንዳለው የተረዳሁት እናንተ ሸርሙጦች ብላ ደግሞ መጨመሩዋ ነበር፡፡ ገብቶኛል የትውልድ አካባቢዬን እያሰደብኩም እንዳለሁ፡፡ እጅግ በጣም በሁኔታዋ ባዝንም፤ ምንም ምላሽ መስጠት አልቻልኩም፡፡ ምን እንዳደረኩዋትም ባለማወቄ ልጠይቃትም ብዙም ሞክሬአለሁ፡፡ ማንም ደግሞ የሚናገራት የሚቆጣትም  የለም፡፡ ማንነቱዋን የሚያውቁ ይመስለኛል፡፡ አንድ ቀን ግን አስቸጋሪ ነገር ተፈጠረ፡፡ ብዙ ሰው በተገኘበት አካባቢ አንቺ ቡዳ፤ ቡዶች ብላ ተሳደበች፡፡ ዘርንም ጠቅሳ ስለነበር፤ ሁሉም በድንጋጤ ተሞላ፡፡ መጀመሪያ አንድ ትግሬ ሰውዬ አንቲብሎ ተለይቶ እራቅ ብሎ ቆመ፡፡ ብዙ ካሬጅ የሚያደርጋትእና የሚረዳት ሰው መሆኑን አውቃለሁ፡፡ በፋይናንስ ማለቴ ነው፡፡ ሁሉም ግን በነገሩ ደስተኛ አልነበረም፡፡ ይህቺ እንደልቡዋ የምትናገር ሴት የትግራይ ተወላጅ ከአማራ የተጋባች ሴት ነበረች፡፡ የጠቀሰችው ዘር ሰው ሁሉ በሙሉ ተናደደ፡፡ ግን ምላሽ የሰጠም አልነበረም፡፡ቸኩሎ ስድብን በስድብ አለመመለስ ትልቅ ስጦታ ሆኖ አየሁት፡፡ እኔ ግን ወደዛ ትግራይ ሰው ሄድኩእና ልክሰሳት አልኩት፤ እሱ ግን እኔ አልሰማሁም አልመሰክርም ብትተይውስአለኝ፡፡ ሰውየው በተናገረችው ቢደነግጥም እና ቢገሥጻትም ግን ለሕግ አሳልፎ ሊሰጣት አልፈለገም፡፡ ማህበራዊ ኑሮ ብሎ ወይስ ዘርን አሳልፎ ላለመስጠት፡፡ ሁለቱም ነገሮች የህግን ጥሰት የሚያስከትሉ ናቸው፡፡ እኔም ሴትየዋ እንደኮኮብ የሚያያት የምትደነቅበት ቀበሌ/ወረዳ ሄጀ ተናገርኩ፡፡ ፍርድ አገኛለሁ ብዬ አልነበረም፤ ግን ደግፈው የያዙዋቸው በሕብረተሰብ መካከል ያሉ ሰዎች ምን ያህል ብልሹ ሞራል እንዳላቸው ለማስረዳት ነበር፡፡ ግን ያገኘሁት መልስ እሱዋ ጥሩ የልማት አበረታች መሆኑዋን ነበር እንጂ የማዘን እንኩዋን ነገር ያሳዩት ምንም አይነት ነገር አልነበረም፡፡ ይሁንና ግን ዘር ጠቅሳ የሰደበችው ዘር ከሴትዮዋ ጋር አንድ እርምጃ ወደሁዋላ እንደሄደ ተመለከትኩ፡፡ ግን ከዛ በላይ ለመሄድ የህግ እምነት ስለሌላቸው ማንም የሞከረ የለም፡፡ ወሎ ሸርሙጣ ጎጃም ቡዳ የሚለው ብልሹ አስተሳሰብን የቀረጸ ግንዛቤ የጎደለው ሁዋላ ቀር ሰዎች እየተከተልኩ ባብድ እኔም ሁዋላ ቀር ነው የምሆነው፡፡ በዚች በአንድ ሴት ብዬ በጅምላ ትገሬን ብሳደብ የተረዳሁትን ማፍሰስ እና የደረስኩበትን የአስተሳሰብ ስልጣኔ መናድ ማለት ነው፡፡ ሌላውን ወደእኔ እንዲመጣ ማድረግ እንጂ ወደሁዋላ መመለስ አልፈልግም፡፡ ሰው እንጂ በባህሪ ብልሹ የሆነው ዘር አይደለም፡፡ የወሎ ቁንጅናን መቀበል ያቃታቸው እና የሚቀኑ ሴቶች የተነሳ ሸርሙጣ የሚል ስም አሰጥቶታል እንጂ ሌላ ጉዳይ የለውም፡፡  ሌላው ደግሞ ጎጃምንም የሚያሰድበው፤ በአካባቢው ያለው የወባ በሽታ ድሮ ስለማይታወቅ፤ ጭንቅላት ላይ እየወጣ እያሳበደ የሚገለው ሰው ሰውን እንደሚበላው ሆኖ እየተለመደ እየተዛመደ ሄደ፡፡ በማሃይሙ ዘመን በይምሰል የሚነገሩ ልምዶች፤ ሰው ሲጨንቀው የሚሰጠው ምክናያት ዘይቤ ሆኖ ይቀራል፡፡  አዎ ወባ ሰውነትን ትበላለች ትቆረጥማለች፡፡ ሌላው ሰነፍ ሰዎች ጥበበኛን ሰው፤ ብረት የሚያቀልጠውን፤ ወርቅ የሚያቀልጠውን ደግሞም ሸክላ የሚሰራውን ሁሉ ቡዳ ነው በማለት ያወጁት አዋጅ ነው፡፡ ቢገባቸው ግን ቡዳ ሰነፉ መሆን ነበር የነበረበት፡፡ ጎጃምም ይሰራል ወሎም ግን ቆንጆ ነው፡፡ ይህም የሸርሙጣም የቡዳነት ምልከት አይደለም፡፡ ሰውን ሰው ቢበላው ኖሮ ትግሬውም ኦሮሞውም የጎጃምን ጤፍ ባልበላ ነበር፡፡ ከጡዋት አንስቶ እስከማታ የሚለፋውን የሚሰራውን የሚጎለጉለውን ህዝብ ቡዳ የሚል ስያሜ መስጠት እጅግ በጣም የደንቆሮ አነጋገር ነው፡፡ የበሉበትን ወጭት ሰባሪ መሆን ነው፡፡ የጎጃምስ ህዝብ የሚያመርተውን ምን ያህል የኢትዮጲያን ህዝብ እንደያዘው የሚያውቅ ቢኖርስ ጎጃም ተበይ እንጂ የሚባላ አለመሆኑን ባወቅን ነበር፡፡
በስሜት የምትወልደው ልጅ ዲቃላ ሲባል፤ በፍቅር የምትወልደው ልጅ የተፈቀደ ይሆናል፡፡ ሁሉም ግን የሚወለዱት ከአንድ ማሕጸን ነው፡፡ ይህቺ የትግራይ ሴት አንዲት ናት እሱዋም ከአማራ ተጋብታ የወለደች፡፡ „የሚናገሩትን አያውቁም እና ይቅር በላቸው“፡፡ ተብሎ ተጽፎአል እና ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡ ሁለቱም ስድብም ቅም አይለኝም፡፡ ቡዳም ያስባለኝ፤ ሸርሙጣም ያስባለኝን ሁለቱንም እወደዋለሁ እና፡፡ ሰውስ የመብላት ስጦታ ቢኖረኝ፤ ይህቺ ሴት የምትበላ ሳትሆን የምትተፋ መሆኑዋን በነገርኩዋት ነበር፡፡ ሰውን እናስደስታለን ስንል እግዚአብሄርን እናሰድባለን፡፡ እኔ ግን የትግራይ ህዝብን ለመስደብ እደፍራለሁን? አልደፍርም፡፡ የለም ያለውን ገዢ ፓርቲ በመፍራት አይደለም፡፡ ከልጅነቴ ጀምሬ በማከብረው አምላክ ስር ስለኖርኩ ነው፡፡ የሚመቱኝን የሚሰድቡኝን መታደግ አለመቻሌ እኔን ፈሪ እነሱን ጀግና ብሎ የሚያሞግስ ኢትዮጲያዊ ህብረተሰብ መካከል ኖሬ አይቸዋለሁ፡፡ አዎ ኢትዮጲያ የጀግኖች መኖሪያ ጀርመን የፈሪዎች መኖሪያ በመሆኑ ይሆናል ወደዚህ የመጣሁት፡፡ እኔም  የዚህ አይነቱን ጀግንነትን አልፈልገውም እና፡፡ ድንግል ማርያም እንኩዋን ሀያሉን ይዛ የትውልድ አገሩዋን ዘሩዋን ትታ ወደማታውቀው ኢጅብት እንድትሸሽ ተገዳ ነበር፡፡ እየሱስ እና ማርያም የመቻል እና የመሰደድ ምሳሌ ሆነውኛል፡፡ መታደግ ያልቻለ ይሸሻል እንጂ፡፡ ሰው ክፉ ሰርቶ ሳይሆን በመልካምነትም ስፍራን ይለቃል፡፡ በመጨረሻ የምለው የሰደበችኝ አንዲት ናትእና፡፡ የምትችለው ይህን ነው፡፡ ሌላስ ቢኖራት ሌላ በሰራች ነበር፡፡ ነገ የሚመጣው በአንተ እጅ አይደለም ወዳጀ፡፡ ለሁሉም ግዜእና ወቅት አለው፡፡ ዛሬ ዘርተህ ዛሬ አታጭድም፡፡ እግዚአብሄርም እንዲሕ ነው፡፡ „ ሰው የዘራውን ያጭዳል“ እና ዘርን የሚሳደብ ሰው የደረሰበት የእውቀት ደረጃውን የሚያስረዳ እንጂ፤ አንተ እንደሚለው ሆነህ እንዳልሆነ እወቅና ተገንዝበህ ስድብን በስድብ አትመለስ፡፡ ሰው የሚሰድብህ አዳማጭ ሲያጨበጭብለት ነው፡፡ ይህንንም ማንኛውም በመቻቻል ያለ ማሕበራዊ ኑሮ ሁሉ ታዝቦ ዝም ከሚል ቢችል ይገሥጽ ባይችል አብሮ አያዳንቅ አያፊዝ፡፡ ማኝናውም እምነት ፌዝን አይደግፍም እና፡፡ ሶስተኛ አዳማጭ በሌለበት ሰው አይሳደብም፡፡ በቸር ልበላችሁ፡፡
ባዩሽ

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen