Montag, 31. März 2014

ከፈለክ አንብበው፤ ድምጽ ካልታሰበም ይወጣል እና



ከፈለክ አንብበው፤ ድምጽ ካልታሰበም ይወጣል እና

ኢትዮጲያ ውስጥ ትልቁ ችግራችን በብዛት እንጂ በጥራት አናምንም፡፡ ይህም ሁኔታ በቤተክርስቲያን አመርቂ ስራ ሊሰራ አልቻለም፡፡ ከቶም ለእግዚአብሄር የሚቀርቡ ሰዎች የተገለሉበት ወቅት ላይ ደርሰናል፡፡ እግዚአብሄር ኢትዮጲያን ብዙ ጊዜ በመጽሀፍ ቅዱስ ላይም ቢጠራትም መከራችን ግን እንዲሕ በቀላሉ የሚቁዋጭ አልሆነም፡፡ እግዚአብሄር የመንፈስ ጉዳይ ሆኖ ሳለ ግን ቤተክርስቲያን እያተኮረች ያለችው በስጋ የምንከብርበት ነገር ላይ እየሆነ መጥቶአል፡፡ እኩል በልቶ ባማይታደርበት አገር ስለ ስጋ ጸጋ ማውራት ቢከብድም ይሁን ብለን የተቀበልነው ነበርን፡፡ ግን የሀብቱ ሁኔታ ሊመጣጠን አልቻለም፡፡ በሀብታም እና በደሃ መካከል ያለው ሁኔታ እንደኢሮፕ አይደለም፡፡ ኢትዮጲያ የተራበው ደመውዝ ማገኘቱ ይቅርእና፤ ደመወዝ ስለመኖሩም የማያውቅ ብዙ ነው፤ ደመወዝ የተያያዘው ከስራ ጋር ነውእና፡፡ ብዙው በእግዚአብሄር ጥበብ ብቻ የሚኖር መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሀብታም ለምን ሀብታም ሆነ አልልም፡፡ ግን የሚራበው እንዴት ይሁን ነው ጥያቄው? የተራበውን እጠገበው አጠገብ አስቀምጠሕ የእግዚአብሄርን ቀን ጠብቅ የሚል ክርስቲያን ምንአይነት ክርስቲያን እንደሆነ እራሱን ይመርምር፡፡ በውነቱ ሰው ሀብታም  የሚሆነው እግዚአብሄር መርጦት ነው የሚለውን፤ የሱን ጽድቁን ቢነገረኝ ደስ ይለኛል፡፡ ሰይጣንም የመረጠው ሰው፤ መቼ በአለም ደሃ ሆነእና፡፡ ጭራሽ ባይበልጥ? የተራበው ደግሞ ሀጢያቱ አለማመኑ ነው የሚለኝ እርሱ አምኖ ያመጣውን ሳይ ነው፡፡  ታዲያ የእግዚአብሄር ፍቅር በአለም ሀብት የሚወሰን ከሆነ እና የስጦታ ነገር ከሆነ ሰይጣንስ ይሰጥ የለምእን? ከእንግዲሕ ወንጌልን ማስረዳት የሚቻለው በኑሮሕ እና በባህሪ መለወጥ አሳይተህ  እንጂ፤ መጽሃፉ ላይ የሚነገረውን ደጋግመህ ካለባህሪ መለወጥ በመናገር አይደለም፡፡ እንግዲህ ኢሕአዴግ ከገባ 20 አመት ሆኖታል፡፡ 20 አመት ሙሉ ወንጌል በነጻነት ሲሰራጭ ቆይቶአል፡፡ ኢሕአዴግ ጠረፍ እስከጠረፍ ወንጌልን ለሚሰብኩ ሁሉ ነጻ አድርጎታል፡፡ ግን የተማርነው ያደረገን እራሱ ኢሕአዴግ የተባለውን እንድነፈራ እና እንድንሽቆጠቆጥለት እንጂ እግዚአብሄርን አይደለም፡፡ ብዙ ሰው ስለወንጌል ሰምቶአል፡፡ ግን አሁን ብዛቱ ሳይሆን ጥራቱ ላይ ችግር እንዳለ ለእግዚአብሄር ብቻ ሳይሆን ለአለም እንኩዋን ስውር ሊሆን አልቻለም፡፡  ኢትዮጲያ ጥሩ ግዜ እንደሚመጣላት ትንቢት ተነግሮላታል ቢባልም፤ መነገሩ ቀኑን ያሳጥረዋል ማለት አይደለም፡፡ እና ግን ዛሬ ኢትዮጲያ ተለውጣ ብናይ ደስ ይለን ነበር፡፡ ይህ ተስፋ ግን ከቀን ወደቀን እየጨለመ ሄድዋል፡፡ ከመቼውም በላይም በንዋይ ውዴታ ባህር ውስጥ ገብተን መዋኘት እና መውጣትም የተሳነን ክርስቲያኖች እየሆንን ነው፡፡ አንዳንዱም ጸሎቱ ከጥቅሙ ጋር በተያያዘ እንጂ ከምድራችን መለወጥ ጋር የተያያዘ አይደለም፡፡ የመንግስትን እድሜ መርዘም የሚመኘው ከራሱ በመነሳት እንጂ ከእግዚአብሄር ድምጽ አይደለም፡፡ ለሚያምኑ ሁሉ መክበር በመንፈስ እንጂ በስጋ እንዳልሆነ ለማንም ለገባው ግልጽ ነበር፡፡ ዛሬ ግን ስለ ንዋይ ጸጋ የማያወራ የከሰረ ክርስቲያን ተብሎአል፡፡ ይህ ከክርስቶስ መልእክት ጋር በጣም ይጋጫል፡፡ ማውራት ያለብን ስለምድራችን መባረክ ነበር፡፡ መስራትም ያለብን ስለአገራችን ህዝብ ነበር፡፡ ዛሬ ግን ከፋፍለነዋል፡፡ ግልጥ ለማድረግ፤ ሕዝብ በሚለማመደው ልምምድ በዘር ጉዳይ፤ በኑሮው ውድነት ጉዳይ እና በተለያየው ነገር ላይ ኢሕአዴግን ጥፋተኛ አድርጎ ሕዝብ አፍጥጦበታል፡፡ እኛስ ወንጌልን አውቀን ስናጠፋ እግዚአብሄር ሳይሆን ሰውስ ምን ይለኝ ይሆን ብለን ተየቅን? እውን የተራበ ፔንጤ የለምእን? እውን ባለው ልዩነት እምነቱ ፈተና ላይ የወደቀበት ክርስቲያን የለም እን?
 እንግዲሕ እግዚአብሄር ይርዳኝ እና ሀሳቤን ግልጽ ላድርገው፡፡ ከኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ሀይማኖት እጅግ ብዙ ሰው ወደ ጴንጤ በወንጌል መማረክ የተነሳ ሄዶአል፡፡ ተስፋውን የሚፈልግ ሰው በወንጌል እንደሚረካ አንድእና ሁለት የለውም፡፡ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የመጀመሪያዋ ሆና ሳለች ግን በወንጌል ትምህርት አሰጣጥ በኩል ዘመኑን መከተል እና ወጣቱንም በሚገባው መንገድ ለመሳብ የምታደርገው ጥረት በሁሉም አካባቢ ያልተስተካከለ በመሆኑ ብዙ ሰው ወደ ፔንጤ መዞሩ የታወቀ ነው፡፡ እንዳውም ከሌላ ሀይማኖት ወይም ከማያምን ወገን ወደፔንጤ ከሚመጣው ይልቅ ከኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እየፈለሰ የሚመጣው በእጅግ ይበልጣል፡፡ ወንጌልን መስበክ የቀለለው ድሮም ክርስቲያን ለነበሩት እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ከኦርቶዶክስ የሚፈልሰው የምትሀት ጉዳይ ሳይሆን፤ የነፍስ ጥሜት ጉዳይ ነው፡፡ ነፍሳችን ወንጌል ነው ምግቡዋ፡፡ አፈጣጠሩዋም ከዛው ነበር፡፡ ሌላው ከኦርቶዶክስ የምእመናን ወደ ፔንጤ መሸሽ  ወይም በቤት ውስጥ ተደብቆ መቆየት ያመጣው ደግሞ፤ የኦርቶዶክስ ለሁለት መሰንጠቅ ያመጣው እሰጥ አገባ ነው፡፡ ይህ በምእመናን መካከል አለመተማመንም ፈጥሮአል፡፡ ይህን ከልምድ ልናገር የምንችል ሰዎች አለን፡፡ በሁሉም ያለው ችግር እግዚአብሄርን ከመከተል ስርአትን የሙጥኝ በማለታችን ጉዳት በቤተክርስቲያን ውስጥ መጥቶአል፡፡ የተቃዋሚ ነህ የደጋፊ የሚለው ንግግር ሁላችንንም ያስደነግጣል፡፡ እምነት ባወከው ብቻ የምትኖረው አይደለም፡፡ ሁልግዜ አዲስ መመገብ አለብህ፡፡ ልብ ካልን እምነት ግንኙነቱ ከመንፈስ ጋር እንጂ ከስጋ ጋር ባለመሆኑ፤ እምነታችን ለስጋ በሚያስፈልገው ምግብ የሚኖር አይደለም፡፡ እኛ ሁልግዜ ስለዚህ አለም ባሰብን ቁጥር መንፈሳችን እጅግ ያዝናል፡፡ ለእሱ የሚሆን ምግብ ስለማናቀርብለት ይሳሳል ይከሳል፡፡ ይሞታልም፡፡ መንፈስህን ገለህ ግን በውስጥህ ተሸክመሕ ትሄዳለሕ፡፡ አሁን ስለመንፈስ አስፈላጊነት ከገባህ ዛሬውኑ ከሞተበት ለማስነሳት ትችላለህ፡፡ ይህ እግዚአብሄር ለሁሉ የሰጠው ስጦታ ነው፡፡ ንስሀ ትገባለሕ፤ አዎ የሞተው መንፈስህ አራስ ሆኖ ይወለዳል፡፡ በቃ ዳግም ይወለዳል ማለት ነው፡፡ ይሁንና ይህ በቂ አይደለም፡፡ መልሶ እንዳይሞት የሚገባውን መንፈሳዊ ምግብ መስጠት አለብህ፡፡ እንግዲሕ ይህ ነው ሰው ነፍሱ ወደእግዚአብሄር ያላት ጥሜት እንጂ ከአንዱ ወደአንዱ የሚሮጠው ሌላውን ስለካደ አይደለም፡፡ የሚካደው ሰይጣን ነው እንጂ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አይደለችም የምትካደው፡፡ ግን ስለመንፈስ ከተረዳን የነፍሳችን ጥሜት ወንጌል ፍለጋ እንድንሄድ የሚያስገድዱን ነገሮች አሉ፡፡ ይህ የምትኖረው እንደተሰጠህ ነው፡፡ እኔ ወደ ፔንጤ ስሄድ የወንጌል ጥሜቴ እንጂ ገንዘብ ተከፍሎኝ ወይም ሰው ሰብኮኛ አይደለም፡፡ አንዳኑዱ ብዙ መጨናነቅ ይደርስበት እና ወንጌልን ሲሰማ በውነት ይድናል፡፡ ወንጌል መድሀኒት ነው፡፡ ሰካራም የነበረው ተደባዳቢ የነበረው ሁሉ ወንጌልን ሲሰማ የተለዬ ሰው ይሆናል፡፡ ክርስቶስ መዳኒት የሚሻ ብሎአል፡፡ አዎ መድሀኒት ፍለጋ ይኬዳል፡፡ ነፍሳችንን ለማዳን ወደወንጌል ሄደናል፡፡
አሁን እኔ ወንጌልን ልሰብክ አይደለም፡፡ እኔ ለዚህ ነገር የሚገባው ጸጋው የለኝም፡፡ የምመሰክረው ግን ለእኔ ህይወት ወንጌል ወሳኝ እንደሆነ እና እውነትን መረዳት መቻሌ ነው፡፡ በክርስቶስ ፍቅር እንዳለ አውቃለሁ፡፡ ዘወትር ስለክርስቶስ ስሰማ ልቤ የተለየ እርካታ እና ደስታ ያገኛል፡፡ ሀብት አገኘሽ ወይ አትበሉኝ፡፡ እንዳውም የዚህ አለም ሀብቴ እየቀነሰ የሄደው ክርስቶስን ካወኩ በሁዋላ ነው፡፡ ግን ያገኘሁት ሀበት ከዚህ አለም ሀብት ለየት ያለ ነው፡፡ በቃ ነውር የሆኑ ነገሮችን ሁሉ እንድጠየፍ እንዳልስገበገብ በልቤ ወስጥ ያስቀመጠው ነገር ያለ ይመስለኛል፡፡ ወገኔ ያሳዝነኛል፡፡ ያስለቅሰኛል፡፡ ይህቺን የመሰለች ምድር ኢትዮጲያ ልጆቹዋ ሲንከራተቱ ልቤ ይሰበራል፡፡ ምሁሮቻችን ተምረው እንዳልተማሩ ሲሆኑ አልያም ለእኛ ሳይሆኑ ለሌላ አገር በረከት ሲሆኑሣይ፤ ጌታ ሆይ እላለሁ፡፡ ፖለቲከኞቻችን ሁሉ መስማማት ሲያቅታቸው አስታራቂ ለመሆን ይቃጣኛል፡፡ ከፍቅሬ የተነሳ አወናባጅ ፖለቲከኛ መስዬ ወዲህ ወዲያ እላለሁ፡፡  ለእኔ መንፈሴ ከስጋዬ በልጦአል እና ከክርስቶስ በተሰጠኝ ነገር እርካታን አገኝቻለሁ፡፡ ሀብቴ ሰማያዊ አለም እንጂ ይህ አለም ከቶም አይሆንም፡፡ የመጨረሻው የሚያዋርድህ ወርቅ አለመልበስህ መኪና አለመንዳትህ ሳይሆን ሆድህ ሲርበው ነው፡፡  ለምነህ የማታገኝበት፤ ሰርተህ የማትጠቀምበት አገር እራብ ያዋርዳል፡፡ ለስጋዬ የእለት እንጀራ ይበቃኛል፡፡ ሆድ ግዜ የሚሰጥ ነገር አይደለም፡፡ ኢንቬስት አድርገህ ሰርተህ የማትጨርሰው ሆድ ተሸክመሃል፡፡ እሱ አዋራጅ ነው፡፡ እየሱስም የእለት እንጀራችሁን ለምኑ ያለው፤ ከዚህ ሌላው ሁሉ ቢቀርም የማይጎዳ ነው፡፡ በውነት አይጎዳም፡፡ መኪና ባይኖርህ ምንትሆናለሕ? እሚወልድ ገንዘብ ባይኖርህ ምን ትሆናለሕ? በቃኝ ካልክ በሆድህ ይብቃህ ወዳጀ፡፡ ካልሆነ አለም እና መሬት በልተው የማይጠግቡ ናቸው፡፡  ሌላው ደግሞ „ጥረህ ግረሕ ብላ“ ያለውን ፍርድ እና እርግማን ስላለ፤ ካለፋሁ እንደማላገኝ አድርጌ እራሴን ስላሳመንኩት የላቤን እንዲበቃኝ እጸልያለሁ፡፡ ግን ወደተነሳሁበት ልመለስ እና ከየትም መጣ ከየትም የፔንጤ ምእመናን በእጅጉ በዝቶአል፡፡ እኔም እዛ ውስጥ ነኝ፡፡ ግን ምድራችን ደግሞ ከመቸውም በበለጠ፤ ሞራል ለለው ነገር ብዙው ተጋልጦአል፡፡ ሙስናው የሚያስመርር እና በምድሪቱ ላይ መርገምን የሚጠራ ሆኖአል፡፡ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ሴት አዳሪው በዝቶአል፣ ህጻናት ጎዳና ላይ ወጥቶአል፡፡ የተስፋውም ሆነ የትንቢቱ ነገር ጭላንጭል ማሳየት አቅቶታል፡፡  ታዲያ ቤተክርስቲያን ብዙ ሚሊዬን ክርስቲያን ከያዘች፤ ምነው ምድሪቱን የሚታደግ አንድ ሙሴ ወይ አንድ ዳዊት አልያም ዮሴፍ እንዴት ይጠፋል? እኛ ሁሉ ለወንጌል ከቆምን ያለው መንግስት መልካም ሰርቶ እንዲያልፍ ባህሪው እንዲስተካከል ምነው ጸሎት አልረዳውም ? ውድ የቤተክርስቲያን ሰዎች መጥፎውንም ስንቃወም የታየነው እንደፖለቲካ ሰው ሆኖ ስንሰደድ ቤተክርስቲያን ለምንስ ዝም ትላለች፡፡ በስነምግባር ብልሹዎች ሰንረበሽ ቤተክርስቲያን ምነው ከመንግስታቶች ጋር ቀርበው ወንጌልም ስራ አለው ብለው ያልተፋጠጡት፡፡ ለመሆኑስ መንፈስ ሊታገድ እንደማይችል ለማስረዳት ምንነው የቤተክርስቲያን አፍ ተዘጋ፡፡ ሰው ዲሞክራሲ አለ ተብሎ ተከርቸም ሲወርድ ምነው አንድ የቤተክርስቲያን ሰው ጠፋ ሀግ የሚለው፡፡ አልገባኝም፡፡ ግን ዛሬ ፍርሀት አለኝ፡፡ እሱም የሚቀጣው አውቆ ያጠፋ ነውእና፡፡ የሚቀጣው አስመሳዩ ነውእና፡፡ ወዳጄ ሆይ ንጉሱ ሳዖልን ከረሳህ፤ በእግዚአብሄር የተመረጠውን ዳዊትን እንዴትስ አውቃለሁ ትላለህ፡፡ ዳዊትንስ ካላወቅ ወንጌል ሲናገሩት ቀላል ሲፈጽሙት ከባድ ይሆንብሀል፡፡ በዘር ክፍፍል ባልነበረ ሁኔታ ምነው ዛሬ ወንጌል በይፋ ሲሰበክ መጣ፡፡ እውን እግዚአብሄር አይፈርድምእን? ወገኔ ሆይ ኢትዮጲያን አሳልፈህ ለክፉ እንዳትሰጣት ወደእግዚአብሄር ንስሀ ግባ፡፡ አንተም የከፋህ ወንጌል በእጁ የያዘ ሲያጠፋ ባየህ ቁጥር ከወንጌል ጋር ለምን ትታገላለህ፤ እግዚአብሄርስ ለሰው ስገዱ ብሎ ወንጌል ላይ አስፍሮላቼዋልእን? የኢትዮጲያ ህዝብ የማረፊያ ቀንህ አይዞሕ ይመጣል፡፡ ግን ቀኑ እንዲፋጠን የሰው ጀግና ከምትመኝ እጅህን ወደ ፈጣሪህ አንሳ፡፡  ከቶ ለእግዚአብሄር ምን የሚሳን ነገር አለ፡፡ ለቃሉስ የሚቀርቡ ደግሞም ወደንጉሶች የተላኩ ነበሩ፡፡ ግን የሚደፍረው መንፈስ እንጂ ስጋ አይደለም እና፤ ባስቀየምኩ በጌታዬ በእየሱስ ክርስቶስ ስም ይቅር በሉኝ፡፡ በሉ በቸር፡፡
ባዩሽ









Samstag, 29. März 2014

ጀርመን --------እንተዋወቅ



                                        ጀርመን --------እንተዋወቅ

በጀርመን አገር ሁሉም ሀብታም አይደለም፡፡ ግን የሚራብ የለም፡፡ እስራኤሎች በጀርመን ናዚ ዘመን በጀርመኖች በጣም አሰቃቂ ድርጊት ተፈጽሞባቸዋል፡፡ ዛሬ ግን ምህረት አድርገው አብረው በፍቅር እና በምክክር ይኖራሉ፡፡ በጀርመን አገር ሚሌኒየር አነስተኛ ገቢ ያለው ማህበረሰብ መካከል ይኖራል፡፡ የጀርመን ቤቶች አደገኛ አጥር የላቸውም፣ ዘበኛም የላቸውም፡፡ በጀርመን አገር ግብር የማይከፍል ሰው እንደከባድ ወንጀለኛ ሆኖ እስር ቤት ይወረወራል፡፡ በጀርመን አገር ሁሉም ሀይማኖቶች በነጻነት ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ቄሶቹም አንዱ አንዱን ምሳሌ የሚያደርግ ትምህርት  አይሰጣጡም፡፡ በጀርመን አገር ትልቅ መስጊድ አለ ትልቅም ቤተክርስቲያን አለ፡፡ በጀርመን አገር ሀብታም በሚከፍለው ግብር ደሀ ጠግቦ በልቶ ያድራል፡፡ ደሀ ማለት በጀርመን አገር እንደልቡ አይሮፕላን ከፍሎ ከጀርመን ውጪ ለእረፍት የማይሄድ እነደማለት ነው፡፡በጀርመን አገር ከተለያየው የአለም ክፍል ሁሉ የመጣ  ዜጋ እኩል የሚኖርበት ሆኖአል፡፡ ዛሬ በጀርመን አገር ጥቁሮችም ፓለቲካ ውስጥ እየገቡ እየሰሩ ነው፡፡ እዚህ አገር የሚኖር ማንኛውም ዜጋ የሕክምን ኢንሹራንስ አለው፡፡ ጀርመን አገር ማንም እንደፈለገ ፖሊከኞችን መተቸት ይችላል መንቀፍ ይችላል፡፡ ጀርመን አገር የሞት ፍርድ የለም፡፡

ሌላው ጀርመን ትምህርት ቤት የወንጌል ትምህርት በቤተሰብ ፍቃድ እንደሳብጀክት ይሰጥ ስለነበር ብዙው ህዝብ ስለክርስቶስ ያውቃል፡፡ እንደእውነቱ ከሆነ ለሰብአዊ ነገር በጣም የተዘጋጀ የጀርመን ህዝብ ነው፡፡ ሀይማኖታቸው ፔንጤ እና ካቶሊክ ነው፡፡ ጀርመን አገር ምንም አይነት በሽታ ይዞት ቤተሰብ ቢያገለው መንግስት እና የሀይማኖት ድርጅቶች እንደካሪታስ ወይም ዲያኮኒ የሚባሉ ተረክበው ያስታሙሙታል ይረዱታል፡፡  እንዳውም እዚህ አገር በረከታቸው የተትረፈረፈው የተገለለውን የተጣለውን በማንሳታቸው ይሆናል ብዬ እገምታለሁ፡፡ በየቤቱ ምግቡ በጣም በረከት አለው፡፡ ትንሽ ብለን የሰራነው በጣም ይበዛል፡፡ ማለቂያ የለውም፡፡ ይበረክታል፡፡ ሁሉም እዚህ አገር የቴሌቪዥን ተጠቃሚ ነው ከፈለገ ማለት ነው፡፡


የጀርመን ህዝብ ስራ ይወዳል፡፡ በዚህ የተነሳም ባለሆቢ ነው፡፡ እያንዳንዱ ካለሆቢ አይንቀሳቀስም፡፡ መጠጥ የሚጠጣው በፕሮግራም ነው፡፡ ብዙውም የሚጠጣው ቢራ ነው፡፡ የውስኪ ባህል ብዙም የላቸውም፡፡ ጀርመን ካለቢራ ማለት ኢትዮጲያን ካለጠላእና ጠጅ እንደማለት ነው፡፡ ሰክሮ ብዙ የሚረብሽ የለም፡፡ አንድ ሰው ካልበረደው እራቁቱን ቢሄድ ዞሮ የሚያየው የለም፡፡
በጴንጤዎች ቤት አልኮሆል አይጠጣም፡፡ ፔንጤ ማለት ነጻ የሆነ ኢቫንጀሊስ ማለት ነው፡፡  ከፍተኛ ትምህርት ያለውም የለለውም አብሮ ይውላል፡፡ አንዱ አንዱን የመናቅ ሁኔታ በጭራሽ አይታይም፡፡ የጀርመን ህዝብ አብዛኛውን ግዜውን በስራ ስለሚያሳልፍ ሚስት እና ባል በሚለው ነገር ላይ ብዙም የቀናው አይደለም፡፡ቢሆንም ግን በጀርመን አገር ከስራ ቢዚ ከመሆን የተነሳ በጋዜጣ ወይም በቴሌቪዥን ወይም ለትዳር ማገናኛ በሆኑ ቢሮዎች ለትዳር የሚፈልጉትን መተዋወቅ ብልግና ሳይሆን እንደባህል እየሆነ እንዲመጣ የጊዜ እጥረት እያስገደዳቸው መጥቶአል፡፡ የሆሞሴክሹዋል ባህልን ሁሉ የተቀበለው እና የወደደው አይደለም፡፡ ግን እኔ ካልሆንኩ ስለሌላው ምንአገባኝ አይነት ነገር ይታያል፡፡

ይህም ሆኖ የኑሮው ውድነትን ሁሉም እየተናገረ ነው፡፡ ሰሞኑንም ሰራተኛው ሁሉ ለሰላማዊ ሰልፍ የደመወዝ ጭማሬ እየተነሳሳ ነው፡፡ ባለፈው የከተማው የትራንስፖርት ሰጪው አገልግሎት ክፍሉ የስራ ማቆም አድማ አድርጎ የደመወዝ ጭማሬ ጠይቆአል፡፡ ይህም በአገሩ ውስጥ የሰራ ቀውስ አምጥቶአል፡፡ ብዙው ሰው የከተማ ትራንስፖርት ተጠቃሚ በመሆኑ ስራ ሊሄድ ባለመቻሉ ብዙ ቀውስ ተፈጥሮ ውሎአል፡፡ መልስም ካላገኙ ይቀጥላል፡፡ በሚቀጥለውም የሉፍታንሳ ሰራተኛ እንዲሁ የስራ ማቆም አድማ ለደመወዝ ጭማሬ እንደሚያደርጉ ነው፡፡ የሚሰራ ሰው ስራ ማቆም አድማ ሲያደርግ ውጤት እንደሚያመጣ አይካድም፡፡  
ሰሞኑን በጀርመን አገር የሰራተኛው የደመወዝ ክፍያ መነሻ እስኬል እንዲጨምር ፖለቲከኞች ተሰባስበው ወስነዋል፡፡ ይህ ሲሆን ግን ሌላ ስጋትም አለ፡፡  ስጋቱም አሰሪው ክፍል የምግብ ዋጋ  ጭማሬ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ነው፡፡ እንግዲሕ ጀርመን ይህን ይመስላል፡፡  

ይህም ሆኖ ግን እዚሕ አገር በልተው ጠጥተው በዲሞክራቲው ተጠቅመው የኖሩ የሶስተኛው አለም ስደተኞች ምን ህል ተለውጠው ይሆን? በዘር ክፍፍል ይሆኑ? ለተቃዋሚ ለገዢው ፓርቲ እያሉ ተከፋፍለው ይሆን? ተሰብስቦ ከማውራት የሆቢ ልምምድ ጀምረው ይሆን? ልብስ ከመቀያየር ሕሊናቸውን የሚያለብሰውን ስብእና ተምረው ይሆን? ክሪቲክ ጥቅሙን ተላምደውት ይሆን? ምንአልባት አገሩ ውስጥ የሚኖሩት ሳያውቁት ይሆን?  እንግዲህ ለእናንተው ልተወው፡፡ በቸር ልበላችሁ
ባዩሽ

Freitag, 28. März 2014

ድባቅ የሚከት ድምጽ ካልተጠበቀ አፍ ሲወጣ ንቃ፡፡




         ድባቅ የሚከት ድምጽ ካልተጠበቀ አፍ              
                              ሲወጣ ንቃ፡፡
 


„እናንተ የእፍኝት ልጆች ከሚመጣው ቁጣ እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ፡፡ እንግዲሕ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ፡፡ በልባችሁም አብርሃም አባት አለኝ እንደምትሉት አይምሰላችሁ“  ይህ የመጥመቁ ይሁዋንስ ንግግር  አይናችንን ሊከፍተው ይገባል፡፡ ገና ያልመጣው ግን ለመምጣት ዳር ዳር እያለ ያለውን ዘመን አስከፊነት፣ መራራነት፣ አሰቃቂነት የሚናገር እንጂ እስከዛሬ የሆነውን አይደለም፡፡  የሁሉም ሀይማኖት አንድ ቀን አለም እንደምታልፍ ይናገራል፡፡ ያንንም በጉጉት በናፍቆት የሚጠብቅ ሲኖር፤ አንዳንዱ ደግሞ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ እንኩዋን አለም እሱም እንደማያልፍ መስሎት በመርሳት ይኖራል፡፡ መርሳት የሚያመጣብን ሁኔታ ደግሞ የሕመም ምልክት እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ ሰው እንግዲሕ እግዚአብሄርን ካልፈራ ማንን ይፈራል፡፡ ነገ ሁሉንም ነገር ትተን እንደምንሄድ የረሳነው እኛ አለም አንድ ቀን ትጠፋለች ብሎ ለማሰብ ከባድ ነው፡፡ ጭራሽ ለነገር ፍለጋ ነገር ከየቦታው እየቆፈርን እየመዘዝን ሰው በመልካም አምልኮ የአምላኩን መምጣት እንዳይጠባበቅ አካባቢያችንን በነገር ቆሻሻ ሞልተን ትውልዱን እናጨናንቃለን፡፡ በእምነት ከሄድን የየአንዳንዳችን ፍርድ ከፈጣሪ የሚመጣ እንጂ ከአንድ ሰው ወይም ከአንድ ግሩፕ የሚመጣ አይደለም፡፡ ምንአልባት አይናችንን ብንከፍት አጠገባችን ስንት ሰው እግዚአብሄር ልኮልን በሀጢያት የተሸፈነው አይናችን ሳይመለከት አሳልፈናቸው ይሆናል፡፡ ወይም ደግሞ በሀይማኖት የታወረው ልባችን ብርሀን አጥቶ እየወነጀልን አባረናቸው ይሆናል፡፡ እግዚአብሄር አንድም ቀን የሰውን ልጅ ብቻውን ጥሎት እንደማያውቅ መረዳት አለብን፡፡
           ምንም እንኩዋን የመጀመሪያው የክርስትና ሀይማኖት  ኦርቶዶክስ መሆኑ አለም የመሰከረለትም ቢሆን፤ ግን እግዚአብሄር አሁንም ቢሆን ስራ አላቆመም፡፡ እግዚአብሄር አብርሀምን ሲመርጠው አብራሀምን ብቻውን ለማዳን ሳይሆን የፈጠረውን ሕዝብ ለማዳን ያደረገው አንዱ የመገናኛ መንገድ ነው፡፡ እግዚአብሄር ዘወትር ለማያውቁት ሁሉ እንዲያውቁት ጥረት የሚያደርግ እሩህሩህ አምላክ ነው፡፡ አብራሀምን ብቻ ለማዳን ቢሆን ኖሮ እሱን እስከቤተሰቡ እንደእነ ኤልያስ መንጠቅ ባላቃተው ነበር፡፡ ባለችሎታ አምላክ መሆኑን ሁላችንም እናውቃለን፡፡ ባይሆን በአንድ ክፉ የሆነ የፖለቲካ መሪ ዘላለም አለም ታልፈን በተሰጠን ነበር፡፡ አስቸጋሪ መሪዎች ምን ልግባ ብለው ሲሽመደመዱ ሰምተናል አይተናል፡፡ ክፉ መሪዎች ደዝባቸው የሚጠፋው የእግዚአብሄር ጣት ጣልቃ ሲገባ ብቻ ነው፡፡ መጥፎ መሪዎችም ልባቸው እንደፈርኦን የደነደነ ይሆናል፡፡ እርግጠኛ ሆኘ በእምነቴ የምነግራችሁ በመሪዎች ላይ  ተግሳጽ፣ ምክር እና ወንበሩንም እንዲያስተካክሉ አልያም እንዲለቁ ዘወትር መልእክት ይመጣል፡፡ይህንንም ካልሰሙ በሕልም ብሎም በራእይ የእግዚአብሄር ተግሳጽ ለመሪዎች ለእራሳቸው እንደሚያስከትል ነው፡፡ ሁሉ መልእክት የሚደርሳቸው ወይም የሚመጣባቸው  እነሱ ስላመኑ ሳይሆን ሕዝብን የፈጠረው እራሱ ስለሆነ ሕዝብን ሲታደግ ብቻ ነው፡፡ እንደእውነቱ የእግዚአብሄር ስራ ተሰርቶ ያበቃ ሳይሆን ያንኑ ያንኑ የሚደጋግም ነው፡፡ ይህንም የምለው፤ ያንኑ ትምህርት ዘወትር በተለያዩ ሰዎች እና በአዲስ መንገድ ያስተምራል ያሳያል፡፡ የእግዚአብሄር ህግ ሲነሳም አንድ ነው መደምደሚያውም ያው ነው፡፡ ዛሬ አስተማሪ ቢበዛ አይድነቅህ፡፡ እግዚአብሄር አንድም ሰው እንዲጠፋበት የማይፈልግ በመሆኑ ሁሉን ለማዳረስ የሚፈልግበት ግዜ ላይ ደርሰናል፡፡ የምስራቹን ሁሉ መስማት አለበት፡፡ ስለዚህ ወገኔ ሆይ የምስራቹን አብሳሪ ወንጌላዊ ቢበዛ አይድነቅህ፤ አያስደንግጥህ፡፡ ማመን ግን የየግልህ ጉዳይ ነው፡፡  አንድ ሰው ሌላውን የሚያንገላታው፤ እግዚአብሄር ስለፈረደበት ሳይሆን የአንተ ሀጢያት ልብህን ስላሳወረው ብቻ ነው፡፡ ሁሉንም ተግሳጽ መሪ ካልሰማ  እንደአክቲቪስት አይነት ድምጽ ከየቦታው ያስነሳበታል፡፡ ከመካከልህም የወደድከውን ያመንከውን ማንነትህን እንዲዋጋ ሙሴን የሚያስነሳብህ አምላክ ለፈጠረው ህዝብ እንደሚጥር እመን፡፡ ድባቅ የሚከት ንግግርም ካልጠበቀው አፍ እንደሚወጣ ማየት እና መጠበቅ ነው፡፡ እግዚአብሄር እንኩን ሰውን ከአህያዋ መልእክት ያወጣል እና፡፡ ባላባት እና ቄስ  የመረጠው ሳይሆን ዳዊት እግዚአብሄር የቀባው ነበር፡፡ አንተ የናከው፣ አንተ ያንቁዋሸሽከው፣ አንተ እብድ ያልከው፣ አንተ ተቀዋሚ ያልከው  በየቤቱ እና በየአደባባዩ በየእስርቤቱ ስንት  የተቀባ እንዳለ ወገኔ ሆይ እምነህ አይንህን ክፈት፡፡  መሪን የደፈረ እብድ ነው እንጂ ለአንተስ መቼ እግዚአብሄርን ለማየት የተሰጠህ ነገር አለእና፡፡ መንፈስን ሁሉ የመመርመር ችሎታስ እንዲኖረው ማን ይሰጣል እና፡፡ እግዚአብሄር የሚሰራው፤ እሱ በመረጠው እንጂ መቺ አንተ ወይስ ቡድን የመረጠው ሆነና፡፡ ሁሉም ሆኖ ግን   ተግሳጽን ያልሰማ እምቢተኛ የተናገረውን በመግደል በማሰር በማሳደድ እጁን በሀጢያት የበለጠ እየነከረ ይሄዳል እንጂ ለማያቀው አምላክ መች ይታዘዛል፡፡
           እግዚአብሄር ስለእኛ ሕዝብ ጥረት ያደርጋል፡፡ ለእኛ ለምናምን እግዚአብሄር የፈጠረን እንድንጠፋ ሳይሆን እየተደሰትን እንድንኖር መሆኑ ይታወቃል፡፡ ግን ሕግን ለመጠበቅ ከመጀመሪያውም የተቸገርን በመሆናችን በአዳም እና በሒይዋን ምክናያት ከገነት ውጭ እንድንጣል ሆነናል፡፡ እንግዲህ ከገነት ውጭ ከተጣልን ምን ያህል አሰቃቂ እና አሳዛኝ የሚያሰቃይ ቦታ ላይ ዛሬ እንዳለን እንረዳለን፡፡ እኛ ወደእዛ ለመግባት ለመታገል አቅም እንዲኖረን ዘወትር እግዚአብሄር በተለያየ መንገድ የሰውን ልጅ ሲገናኝ ሰምተናል አይተናል፤ አለም እስከአለፈችም እግዚአብሄር እኛን መገናኘቱ ይቀጥላል፡፡  ጥረቱም ከወጣንበት እንድንመለስ ለመታደግ እና ወደእሱ የሰው ልጅ እንዲመለስ ብዙ አዳዲስ መንገዶችን ለመፍጠር የሚሳነው አምላክ እንዳልሆነ መዘንጋት የለብንም፡፡ አይናችንን ከከፈትን እግዚአብሄር የታምራት አምላክ ነው፡፡ ለምናምን የዘር ልዩነት ቴማችን ሊሆን የሚገባው አይደለም፡፡ አንዱ የባብልን ታሪክ ሰው እግዚአብሄርን የተወዳደረበት ወቅት ቁዋንቁዋን መደበላለቁን እናስታውስ፡፡ ሌላው ደግሞ እኛ የእግዚአብሄር ጥበብ ማሳያ እንጂ ሰው በተፈላሰፈ ቁጥር ለሚያወጣው ህግ ቀለማችንም ሆነ ቁዋንቁዋችን መግለጫ እና መለያያ እንዲሆን አታድርጉ፡፡  አንድ ነገር ልንገርህ ወዳጀ፤ ሀብትን የሚመኝ የሚያሰርቀውን መንገድም ይመርጣል፡፡ እኛ ግን የእለት እንጀራችንን ስንመኝ እግዚአብሄርን እናያለን፡፡ ዛሬ አንተ ሀብታም ብትሆን የነገውን የልጅህን እጣ ፋንታ ግን በአንተ ሀብት እጅ መሆኑ ምንም ዋስትና የለሕም፡፡ ደሀም ብትሆን ለምን ተስፋ ትቆርጣለህ የነገውስ በእግዚአብሄር እጅ አይደለም እን? በራእይ ከእግዚአብሄር መላእክ ጋር ተገናኘሁ ብሎ ሰው ቢነግርህ አትደንግጥ፡፡ የአንተም ነፍስህ እግዚአብሄርን ታውቀዋለች እና፡፡  ነጭ ይሁን ጥቁር፤ አማራ ይሁን ትግሬ ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሄር አምሳል እንጂ መች በሰው ነው እና፡፤ ጥበብ ከሁሉም በኩል ተሰጥቶአል እና፤ በሀሉም ዘር ደግሞም ጽድቅ እና ኩነኔ አለች እና የአገሬ ሰው ሆይ አይንህን እራቅ አድርጎ እንዲያይ አድርገው፡፡ አሕያ ብቻ ናት ከአምስት መቶ ሜትር በላይ የማታየው፡፡ አንተ ግን በእግዚአብሄር አምሳል የተፈጠርክ ሰው ነህእና ትግሬው አሻግሮ ይይ፤ ኦሮሞውም ማዶውን ይይ፤ አማራውም እንዲያው፡፡
ንብ ከየት አምጥታ ማር እንደምትተፋ ሳታውቅ ንብ ነኝ አትበል፡፡ ንብ አበባ መርጣ ትቀስማለችእን? ደግሞስ ከአፍዋ መራራ ትትፋለችእን? ነኝ እንዳለክው ወገኔ ሆይ ሁን፡፡ ቃልን የሚጠብቅ የአምላክህ ክንድ በአንተ ላይ አለች እና፡፡ ካጠፋሁ እና ከደፈርኩ በጌታዬ በእየሱስ ክርስቶስ ስም ወገኔ ሆይ ይቅር እንድትሉኝ እማጸናለሁ፡፡ ሰይጣንን የካድኩ ስለሆነ ከሰይጣንስ አልናገርም እና፡፡ በቸር እላለሁ፡፡

ባዩሽ

Dienstag, 25. März 2014

እራስን የመኖር ወሳኝ ሚና



                   እራስን የመኖር ወሳኝ ሚና

ስለዘር ማውራት ጥቅሙ ብዙም አይታየኝም፡፡ ግን ስለሰው ብናወራ ደስ ባለኝ ነበር፡፡ ይህንም የምልበት ምክናያት፤ ሰው እንጂ ባለባህሪ ዘር መቺ ሆነእና፡፡ ለነገሩ እኔ ከአማራነቴ ለመሸሽ እንዳልሆነ እወቁልኝ፡፡ አማራ ነኝ አንተ ኦሮሞ አንተም ትግሬ እንደሆንከው፡፡ እኔ ግን ከማንኛችሁም ጋር ለመኖር ችግር የለኝም፡፡ ግን ምንአልባት ልብ አለን እና ከልብ እንድንሆን፤ ይህቺን ጡሁፌን ላቅርብ፡፡ መጀመሪያ እናንተ ሁላችሁንም የሚመቻችሁን ጽሁፍ ባልጻፍኩ ቁጥር፤ አንደዬ ወያኔ አንደዬ ተቃዋሚ ብሎም አንደዬ ትግሬ አንደዬ አማራ ናት እያለ የሚሞግተኝን ዝም ብዬ አየዋለሁ፡፡ እኔ ለሁሉ መመቸት የለብኝም፡፡ አይግረማችሁ እና ሁሉንም እመቻለሁ ብዬ እራሴን ሳልኖር እንዳልሞት ስለምፈራ ነው፡፡ ለማንኛውም የሽሽት ወይም የማፈር እንዳይመስላችሁ፤ እኔ ግን ጥርት ያልኩ አማራ ነኝ፡፡ ወያኔም ሆኜ አልጨፍርምም አልቆዘምም ፤ ተቃዋሚም ሆኜ የተቃዋሚን ፓርቲም ደግፌ ሆ የምል ወይም የምደበር አይደለሁም፡፡ ሳይጠሩት አቤት ሳይልኩት ወዴት የማልል አንዲት የኢትዮጲያ አገር ሴት ነኝ፡፡ አንዲት ሴት፤ ወሎ ደሴ ላይ ተወልዳ ያደገች ፡፡ አዎ ከነሸህ ኑሩ መንደር እነ ንጉስ ሚካኤል ቤተመንግስት አጠገብ፡፡ አድራሻ ያለኝ አማራ ነኝ፡፡  አንድ ግን ነገር አለኝ ከሁሉ ጋር የመኖር ችግር የለለኝ ነኝ፡፡ ሰውን የማየው ዘሩን ሳይሆን ባህሪውን ነው፡፡ የተሰጠኝ የልብ ኩራቴ ጣቴን አለመቀሰር በትናንትናው አለመቆዘም፤ የዛሬውን መኖር፤ ነገን በተስፋ መጠበቅ ነው፡፡ ነገን እኖራለሁ ብሎ ዋስትና የተሸከመ ሞኛ ሞኝ ቢጤም አይደለሁም፡፡ አማራ ብለህ አትስደበኝ፡፡ ብትሰድበኝም እታዘብሃለሁ እንጂ አልሰድብህም፡፡ እውቀትህን እመዝንብሃለሁ እንጂ ደንቆሮ አልልህም፡፡ ከወጣህበት ደረጃ ላይ እንዳትወድቅ ቀስ በል እልሃለሁ እንጂ አልደግፍህም፡፡ አረማመድህን እይ እልሃለሁ እንጂ፤ እንቅፋቱን አላነሳልህም፡፡ ወዳጄ ወገኔ አይንህን ክፈት እልሃለሁ እንጂ፤ እንድታዬኝ አላስገድድህም፡፡ ይህን ካልኩኝ ዘንዳ፤ እስኪ ትንሽ ልበላችሁ፡፡
አፍንጫን ሲመቱት አይን ያለቅሳል እንዳይሆንብኝ፤ አሉኝ የምለውን ዶሴ ከፍቼ ዘርን ወደዘር ለመክሰስ አልሮጥም፡፡ ከዘር አጥፊው መች ሁሉ ሆነእና፡፡ አንድ ቀን የገጠመኝን ልንገራችሁ፡፡ ምክናያቱን በማላውቀው ነገር አንዲት ሴት ጥምድ አድርጋ በድንገት ያዘችኝ፡፡ ጥረቱዋ ሁሉ በምኖርበት ሰፈር ታማኒነትን እንዳላገኝ ነበር፡፡ ስራዋን ምንነቱን ባላውቀውም ግን ቀበሌ ጋር እጅግ የጠበቀ ግንኙነት አላት፡፡ በውነት ለማጣራትም አልሞከርኩም፡፡ እኔ የእራሴን ኑሮ ለማሳካት ደፋ ቀና የምል ሴት ነኝ እንጂ ስለሰውም ስለፓርቲም  የማስብበት ግዜው አልነበረኝም፡፡ በዚች በሴትዮም የተነሳ ማህበራዊ ኑሮዬ የደመቀ ሊሆን አልቻለም፡፡ የአገሬ ሰው ለመፍረድ የሚቸኩል በሰማው የሚጉዋዝ እንዳይሆን የፈራሁበት ወቅት እና የፈራሁትን ደርሶ ማየቴ ይገርመኛል፡፡ ሰው የሚያውቅህ በሰው ነው፡፡ የሰነፍ ልብ ጉዞ፡፡ ስለዚህ ትቸዋለሁ፡፡ ከስደት የተመለስኩት ሕግን ተማምኚ ነበርእና፤ ይህቺ ሴት ለምታደርስብኝ ችግር የዘመድ አዝማድ ስብስብ ለማግኘት አልጣርኩም፡፡ ዘመድ አብረህ የኖርከው እንጂ፤ የተወለደህ አይደለም፡፤ ከተወለደህ ጋር ለብዙ አመታት ከተለይ የመረሳት ነገር አለ፡፡ ዝመድናው ከስም ያላለፈ ይሆናል፡፡ የኢትዮጲያ ኑሮ በህግ የተከበረ ሳይሆን በማህበራዊ ኑሮ ትሰስር በቲፎዞ አይነት ነገር ሆኖ አየሁት፡፡ በልጅነቴ የተለየሁት  አገር አድካሜ እንደሆነብኝ ተረዳሁ፡፡ ያ የማህበራዊ ህይወት በመቻቻል የሚኖር ህዝብ መካከል ስኖር ለእኔ ህግን ለተመረኮዝኩት ሴት ባይተዋርነት በልቤ ውስጥ እየሰፋ ሄደ፡፡ ያቺ ሴት ስትጨመር ጭራሽ አስቸጋሪ ሆነብኝ፡፡ ቀስ ብላ እየመጣች ነፍጠኛ ብላ ሰድባኝ ትሄዳለች፡፡ በውነት ምንም ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ብዙም ስለፖለቲካው የማውቀው ጉዳይ የለኝም፡፡ የተመለስኩት ከተዘጋው ጀርመን ነው፡፡ ዝግ ያልኩት ዲሞክራሲ ነው፤ በህግ የበላይነት እሚጠላህ ሰው መካከል በሰላም መኖር ነው፡፡ ግራ ግን ተጋባሁ፡፡ ኢትዮጲያ ይህ የለም፡፡ ለመታየትም ጭላንጭል የለውም፡፡ ፍርድ ቤቱ ምን እንደሚሰራ አላውቅም፡፡ የሕግ ጥሰት እንደመብዛቱ፤ ፍርድ ቤቱ ሀያአራት ሰአት በሰራእና ሰውን ወደህግ በጋበዘ ነበር፡፡ ግን ፍርድቤቱ የሚጋብዝ አይደለም፤ የሚያስደነግጥ እንጂ፡፡ አንዳንዱ ግለሰብ እንደተፈቀደለት ሁሉን ሲያደርግ ሲፈጽም ታየዋለህ፡፡ የወረዳው ቢሮ፣ ፖሊስ ጣቢያው እና የፓርቲው ጸ/ቤት እንደእራሱ ጉዋዳ ነው የሚያየው፡፡ ስለዚህ በሴትዮዋ ጋጥ ወጥነት ብዙም አልደነገጥኩም፡፡ ሕግን እንድታፈርስ እንጂ እንድታከብረው የሚያደርጋት አስተማሪ አላገኘችም፡፡ ጭራሽ እንድታበላሸው እንጂ፡፡
ለምን ዘመቻው እንደመጣ አላውቅም፡፡ ሕይወቴ ከቀን ወደቀን የሰቆቃ ሆኖአል፡፡ ሴትዮዋ ስለእኔ ዘር ከእኔ በላይ አጥንታለች፡፡ አልፎ አልፎ ሸርሞጣ ብላ ትሰድበኛለች፡፡ እኔ ግን መልስም አልሰጥ፡፡ ደፍሮ እሕዝብ መካከል የሚሰድበኝ ዱላ አንስቶ ለመማታት ወደሁዋላ ስለማይል ሰባራ አጥንት አልፈልግም እና ዝም ካለማለት በቀር አማራጭ የለኝም፡፡ እኔ የእሱዋን ባል ቀርቶ የእራሴ የሆነም ለመፈለግ የምነሳሳ የወንድ ሱስ ያለኝ ሴት አይደለሁም፡፡ ሴት ወንድ የሚፈልገው በአይምሮው ነው፡፡ ሴት ባለጡንቻ አይደለም፡፡ አይምሮዬ የተጠመደው በኑሮዬ ላይ ነው፡፡ በስራ ይደክመኛል፡፡ ስለዚህ ሸርሙጣ ብሎ የሚያሰድበኝ እንዝላልነት የለኝም፡፡ ደግሞም በኢኮኖሚ እራሴን የቻልኩ ስለነበርኩ፤ እንደቸገራቸው ሴት እህቶቼ ወደዚህ ስራ ለመሄድ የሚያስገድደኝም ነገር አልገጠመኝም፡፡ አልኮሆልም በተፈጥሮዬ ስለማልወድ ስለማልጠጣ ስክሬም የሳተ ስራ ስሰራ አላየችኝም፡፡ የሰው ባልም አልነካም፤ አልመለከትምም፡፡ ይህ ባህሪየን የሚገልጥ ስላልሆነ በስተጀርባው ያለውን የዘር ጥላቻ እንዳለው የተረዳሁት እናንተ ሸርሙጦች ብላ ደግሞ መጨመሩዋ ነበር፡፡ ገብቶኛል የትውልድ አካባቢዬን እያሰደብኩም እንዳለሁ፡፡ እጅግ በጣም በሁኔታዋ ባዝንም፤ ምንም ምላሽ መስጠት አልቻልኩም፡፡ ምን እንዳደረኩዋትም ባለማወቄ ልጠይቃትም ብዙም ሞክሬአለሁ፡፡ ማንም ደግሞ የሚናገራት የሚቆጣትም  የለም፡፡ ማንነቱዋን የሚያውቁ ይመስለኛል፡፡ አንድ ቀን ግን አስቸጋሪ ነገር ተፈጠረ፡፡ ብዙ ሰው በተገኘበት አካባቢ አንቺ ቡዳ፤ ቡዶች ብላ ተሳደበች፡፡ ዘርንም ጠቅሳ ስለነበር፤ ሁሉም በድንጋጤ ተሞላ፡፡ መጀመሪያ አንድ ትግሬ ሰውዬ አንቲብሎ ተለይቶ እራቅ ብሎ ቆመ፡፡ ብዙ ካሬጅ የሚያደርጋትእና የሚረዳት ሰው መሆኑን አውቃለሁ፡፡ በፋይናንስ ማለቴ ነው፡፡ ሁሉም ግን በነገሩ ደስተኛ አልነበረም፡፡ ይህቺ እንደልቡዋ የምትናገር ሴት የትግራይ ተወላጅ ከአማራ የተጋባች ሴት ነበረች፡፡ የጠቀሰችው ዘር ሰው ሁሉ በሙሉ ተናደደ፡፡ ግን ምላሽ የሰጠም አልነበረም፡፡ቸኩሎ ስድብን በስድብ አለመመለስ ትልቅ ስጦታ ሆኖ አየሁት፡፡ እኔ ግን ወደዛ ትግራይ ሰው ሄድኩእና ልክሰሳት አልኩት፤ እሱ ግን እኔ አልሰማሁም አልመሰክርም ብትተይውስአለኝ፡፡ ሰውየው በተናገረችው ቢደነግጥም እና ቢገሥጻትም ግን ለሕግ አሳልፎ ሊሰጣት አልፈለገም፡፡ ማህበራዊ ኑሮ ብሎ ወይስ ዘርን አሳልፎ ላለመስጠት፡፡ ሁለቱም ነገሮች የህግን ጥሰት የሚያስከትሉ ናቸው፡፡ እኔም ሴትየዋ እንደኮኮብ የሚያያት የምትደነቅበት ቀበሌ/ወረዳ ሄጀ ተናገርኩ፡፡ ፍርድ አገኛለሁ ብዬ አልነበረም፤ ግን ደግፈው የያዙዋቸው በሕብረተሰብ መካከል ያሉ ሰዎች ምን ያህል ብልሹ ሞራል እንዳላቸው ለማስረዳት ነበር፡፡ ግን ያገኘሁት መልስ እሱዋ ጥሩ የልማት አበረታች መሆኑዋን ነበር እንጂ የማዘን እንኩዋን ነገር ያሳዩት ምንም አይነት ነገር አልነበረም፡፡ ይሁንና ግን ዘር ጠቅሳ የሰደበችው ዘር ከሴትዮዋ ጋር አንድ እርምጃ ወደሁዋላ እንደሄደ ተመለከትኩ፡፡ ግን ከዛ በላይ ለመሄድ የህግ እምነት ስለሌላቸው ማንም የሞከረ የለም፡፡ ወሎ ሸርሙጣ ጎጃም ቡዳ የሚለው ብልሹ አስተሳሰብን የቀረጸ ግንዛቤ የጎደለው ሁዋላ ቀር ሰዎች እየተከተልኩ ባብድ እኔም ሁዋላ ቀር ነው የምሆነው፡፡ በዚች በአንድ ሴት ብዬ በጅምላ ትገሬን ብሳደብ የተረዳሁትን ማፍሰስ እና የደረስኩበትን የአስተሳሰብ ስልጣኔ መናድ ማለት ነው፡፡ ሌላውን ወደእኔ እንዲመጣ ማድረግ እንጂ ወደሁዋላ መመለስ አልፈልግም፡፡ ሰው እንጂ በባህሪ ብልሹ የሆነው ዘር አይደለም፡፡ የወሎ ቁንጅናን መቀበል ያቃታቸው እና የሚቀኑ ሴቶች የተነሳ ሸርሙጣ የሚል ስም አሰጥቶታል እንጂ ሌላ ጉዳይ የለውም፡፡  ሌላው ደግሞ ጎጃምንም የሚያሰድበው፤ በአካባቢው ያለው የወባ በሽታ ድሮ ስለማይታወቅ፤ ጭንቅላት ላይ እየወጣ እያሳበደ የሚገለው ሰው ሰውን እንደሚበላው ሆኖ እየተለመደ እየተዛመደ ሄደ፡፡ በማሃይሙ ዘመን በይምሰል የሚነገሩ ልምዶች፤ ሰው ሲጨንቀው የሚሰጠው ምክናያት ዘይቤ ሆኖ ይቀራል፡፡  አዎ ወባ ሰውነትን ትበላለች ትቆረጥማለች፡፡ ሌላው ሰነፍ ሰዎች ጥበበኛን ሰው፤ ብረት የሚያቀልጠውን፤ ወርቅ የሚያቀልጠውን ደግሞም ሸክላ የሚሰራውን ሁሉ ቡዳ ነው በማለት ያወጁት አዋጅ ነው፡፡ ቢገባቸው ግን ቡዳ ሰነፉ መሆን ነበር የነበረበት፡፡ ጎጃምም ይሰራል ወሎም ግን ቆንጆ ነው፡፡ ይህም የሸርሙጣም የቡዳነት ምልከት አይደለም፡፡ ሰውን ሰው ቢበላው ኖሮ ትግሬውም ኦሮሞውም የጎጃምን ጤፍ ባልበላ ነበር፡፡ ከጡዋት አንስቶ እስከማታ የሚለፋውን የሚሰራውን የሚጎለጉለውን ህዝብ ቡዳ የሚል ስያሜ መስጠት እጅግ በጣም የደንቆሮ አነጋገር ነው፡፡ የበሉበትን ወጭት ሰባሪ መሆን ነው፡፡ የጎጃምስ ህዝብ የሚያመርተውን ምን ያህል የኢትዮጲያን ህዝብ እንደያዘው የሚያውቅ ቢኖርስ ጎጃም ተበይ እንጂ የሚባላ አለመሆኑን ባወቅን ነበር፡፡
በስሜት የምትወልደው ልጅ ዲቃላ ሲባል፤ በፍቅር የምትወልደው ልጅ የተፈቀደ ይሆናል፡፡ ሁሉም ግን የሚወለዱት ከአንድ ማሕጸን ነው፡፡ ይህቺ የትግራይ ሴት አንዲት ናት እሱዋም ከአማራ ተጋብታ የወለደች፡፡ „የሚናገሩትን አያውቁም እና ይቅር በላቸው“፡፡ ተብሎ ተጽፎአል እና ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡ ሁለቱም ስድብም ቅም አይለኝም፡፡ ቡዳም ያስባለኝ፤ ሸርሙጣም ያስባለኝን ሁለቱንም እወደዋለሁ እና፡፡ ሰውስ የመብላት ስጦታ ቢኖረኝ፤ ይህቺ ሴት የምትበላ ሳትሆን የምትተፋ መሆኑዋን በነገርኩዋት ነበር፡፡ ሰውን እናስደስታለን ስንል እግዚአብሄርን እናሰድባለን፡፡ እኔ ግን የትግራይ ህዝብን ለመስደብ እደፍራለሁን? አልደፍርም፡፡ የለም ያለውን ገዢ ፓርቲ በመፍራት አይደለም፡፡ ከልጅነቴ ጀምሬ በማከብረው አምላክ ስር ስለኖርኩ ነው፡፡ የሚመቱኝን የሚሰድቡኝን መታደግ አለመቻሌ እኔን ፈሪ እነሱን ጀግና ብሎ የሚያሞግስ ኢትዮጲያዊ ህብረተሰብ መካከል ኖሬ አይቸዋለሁ፡፡ አዎ ኢትዮጲያ የጀግኖች መኖሪያ ጀርመን የፈሪዎች መኖሪያ በመሆኑ ይሆናል ወደዚህ የመጣሁት፡፡ እኔም  የዚህ አይነቱን ጀግንነትን አልፈልገውም እና፡፡ ድንግል ማርያም እንኩዋን ሀያሉን ይዛ የትውልድ አገሩዋን ዘሩዋን ትታ ወደማታውቀው ኢጅብት እንድትሸሽ ተገዳ ነበር፡፡ እየሱስ እና ማርያም የመቻል እና የመሰደድ ምሳሌ ሆነውኛል፡፡ መታደግ ያልቻለ ይሸሻል እንጂ፡፡ ሰው ክፉ ሰርቶ ሳይሆን በመልካምነትም ስፍራን ይለቃል፡፡ በመጨረሻ የምለው የሰደበችኝ አንዲት ናትእና፡፡ የምትችለው ይህን ነው፡፡ ሌላስ ቢኖራት ሌላ በሰራች ነበር፡፡ ነገ የሚመጣው በአንተ እጅ አይደለም ወዳጀ፡፡ ለሁሉም ግዜእና ወቅት አለው፡፡ ዛሬ ዘርተህ ዛሬ አታጭድም፡፡ እግዚአብሄርም እንዲሕ ነው፡፡ „ ሰው የዘራውን ያጭዳል“ እና ዘርን የሚሳደብ ሰው የደረሰበት የእውቀት ደረጃውን የሚያስረዳ እንጂ፤ አንተ እንደሚለው ሆነህ እንዳልሆነ እወቅና ተገንዝበህ ስድብን በስድብ አትመለስ፡፡ ሰው የሚሰድብህ አዳማጭ ሲያጨበጭብለት ነው፡፡ ይህንንም ማንኛውም በመቻቻል ያለ ማሕበራዊ ኑሮ ሁሉ ታዝቦ ዝም ከሚል ቢችል ይገሥጽ ባይችል አብሮ አያዳንቅ አያፊዝ፡፡ ማኝናውም እምነት ፌዝን አይደግፍም እና፡፡ ሶስተኛ አዳማጭ በሌለበት ሰው አይሳደብም፡፡ በቸር ልበላችሁ፡፡
ባዩሽ