Samstag, 5. Juli 2014

ባህላችን ሲደቁስን፡፡



ባህላችን ሲደቁስን፡፡

እንቅልፌ የሰላም እንቅልፍ ነው፡፡ ምንም እንኩዋን ብዙ ውጣ ውረድ በሕይወቴ ቢኖርም እና፤ የተበላሸው አለም ብዙ ጥቁር ነጥብ ጥሎብኝ ቢገኝም፤ ያንን መርሳት ባይቻልም የሆነውን እንዳለፈ ተቀብዬ የምኖር ሴት ሆኛለሁ፡፡ መቆዘምም አልወድም፡፡ ሁሉን በሳቅ ማሳለፍ እፈልጋለሁ፡፡ እንዳውም ቢገርማችሁ በሚደርስብኝ ችግር ሁሉ ወደኮሚዲ እቀይረዋለሁ፡፡ እና እስቅበታለሁ፡፡ አስቅበታለሁ፡፡  ምንላድርግ፤ ኮስተር ብልበት እኮ በጋለ ብረት ምጣድ የሚያምሰኝ ሳያሳርር አይለቀኝም እና፡፡ ተወት ማድረግ ነው፤ ይህቺ አታላይ እና ውሸታም አልም፤ አይዞን ሁሉም አላፊ ነው፡፡  ዛሬ ለሊት ግን ጸጥ ብዬ ከተኛሁበት ቀስ እያለ የተነሳ አውሎ ንፋስ አገሩን ሲያምሰው እና መወጣጫ ሊፍቶችን ሁሉ ሲገነዳድሰው አለምኩ፡፡ „ሕልም እረኛ“ ነው፡፡ ይላል ያገሬ ሰው፡፡ ብንን ስል ግን ደስ አለኝ፡፡ ምክናያቱም ያየሁት አውሎ ንፋስ የሚገነዳድስ በመሆኑ አስጨናቂ ነበር እና፤ የማይጨበጠው ህልም በመሆኑ፡፡ ለማንኛውም ጠቀመም አልጠቀመም፤ ጸጥ ስል መጻፍ እወዳለሁ፡፡ ያሰብኩትንም በቶሎ ወረቀጥ ላይ ማስፈር እወዳለሁ፡፡ እና እነሖኝ፡፡
ስትፈራ የምትፈራውን አካል ገጽታውን ትገልጻለህ፡፡ ስትደፍር ደግሞ ብዙ ሚሊየን ታስነሳለህ፡፡ ደፋርም ሆነ ፈሪ ሁለቱም ግን የጠሉት ነገር አለ፡፡ ስለዚህ መረዳት ያለብን ነገር ቢኖር፤ ስለፈራ ሰው ተስማመቶአል ማለት አይደለም፡፡ ግን የተፈራው አካል ካሰበበት፤ በመፈራቱ መኩራራት ሳይሆን፤ እግዚአብሄር የሰጠውን ግዜ አስተውሎ እንዲፈራ ሳይሆን እንዲከበር የሚያደርግ ለውጥ ማሳየት ነበር፡፡ በኢትዮጲያ የምመለከተው ገጽታ፤ ሰው በመፈራቱ የሚያሳዝነው ሳይሆን የሚያስደስተው እና የሚያጀግነው ባህል በፖለቲካው እንዳልጠፋ እያየሁት ነው፡፡ ለእኔ ጀግና ማለት የማይፈራ ግን የሚከበር ነው፡፡ ተፈጥሮአዊ እውቀት እየጠፋብን ጡንቻችንን እያሳደግን ስንሄድ የአይምሮአችን ህዋሳት መንቀሳቀስ ያቆማሉ መሰል፤ ሰው ከተፈራ በቃ ማንነቱ ወደመርሳት ይሄድና በጣም መኮፈስ ያበዛል እንደአምላክ ይሆናል፡፡ ተፈርቶ መኖር እና ተከብሮ መኖር የተምታታበት አንዳንዱ ባህል ከድሮው ሀግ ያልተደረገ፤ የአውሬ ምስል እያያዘ ሄዶአል፡፡ ይህ የአላማ ጉዳይ ሳይሆን ከጥንት የወረስነው ባህሪ ስለሆነ በማስፈራራት እያስገደዱ መብላት፤ የመንደር አውደልዳይ ጎረምሳ የመሰለ ባህሪ እንዳለን እያንዳንዳችን እራሳችንን እንመርምር፡፡ ለእኔ ጀግና ማለት ስለእሱ ያለኝን አስተሳሰብ የሚለውጠኝ እንጂ እንድደብቅ እና በውስጤ እንዲይዘው የሚያደርገኝ አይደለም፡፡ ብዙ ነገሮች በባህሪ ዕድገታችን ውስጥ ከፍ እያሉ ሄደው በመንግስታቶችም ውስጥ ዘው ብለው እየገቡ የጅብ ቸኩል ቀንድ ይነክሳል እያደረጉት ይገኛሉ፡፡ ገብቶትም ሆነ ሳይገባው፤ በልቡ ተቃውሞ የያዘን ህዝብ ሰውን በማሰር እና በማባረር ደጋፊ ወይም ተመስጋኝ ማድረግ አይቻልም፡፡ መሆን የነበረበት ህዝብን የሚያሳምን ስራ መስራት እንጂ እንዲፈራ ማድረግ ከእኔ ከፊቴ ተደበቅ ወግድ ማለት ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ እስከመጨረሻው ያስኬዳል ወይ ብሎ መጠየቅ ያሻል፡፡ ኢትዮጲያ ኤርትራዊም፣ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ትግሬ…..ወደንም ሆነ ተገደን  ከብዙ ዓመታት ጀምሮ በአንድ አገር ተሰይመን በአንድ የአስተሳሰብ ባህል ኖረናል፡፡ እሱም ፊትለፊት መናገር መፍራት፤ መድፈርን መፍራት፣ ልጆቻችንን አይቀጡ ቅጣት ቀጠን ፈሪ የሚያደርግ አስተዳደግ ማሳደጋችን በተዘዋዋሪው ማደጋችን የምንክደው ሀቅ አይደለም፡፡ ዳር እስከዳር እንጀራእና ወጥ ብቻ በልተን፣ የአገር ልብስ ለብሰን፣ እስላም እና ክርስቲያን ተባብለን በፍቅር መኖራችን ብቻ ሳይሆን፤ የአስተሳሰብ እድገታችንም አብሮ የተጉዋዘ አንዱ ከሌላው የማይሻል የማይበልጥ መሆናችንን ሁላችንም ልባችን ያውቀዋል፡፡ ዛሬ አንዱ ከአንዱ የተሻለ እንደሆነ ወይም እንደተበደለ እንደተገፋ ሊያሳየን ይሞክራል፡፡ አይደለም፤ ለአገራችን ትልቁ ወሳኙ የአስተሳሰብ ባህላችን እንጂ በስጋ የምናየው የምንበላው እንጀራ አይደለም፡፡ ስለዚህ ውስጣችን እየቆሰለ የኖርን ሰዎች፤ ነጻ አስተሳሰብን ያለመድን ሰዎች መሆናችንን መዘንጋት አይገባንም፡፡ አስተዳደጋችንም ጨዋ ተብለን ቤተሰብ የሚለንን እየፈጸምን ያደግን፤ ቤተሰብ ደግሞ አምባገነን መንግስቶችን የዘሩልንን ዘር ፤እየራበን፣ እየጠማን ወይም ልዩነትን እያየን እንዳንናገራቸው፤ እንዳንቃወማቸው እየተጎሰምን በባህል እስር አድርገው ደህና አድርገው ፈሪ አድርገውናል፡፡ „ፈርታ ታስፈራለች ምን ያለችው ሴት ነች“ የተባለው አባባልም የሚናቅ አይደለም፡፡ በመንደር አንድ ጎረምሳ በጥባጭ ካለ ያንንም ያንንም እየጎሰመ በስሩ ደግሞ የሱን ድርጊት አይተው የፈሩትን እያሰለፈ ቡድን መመስረቱን ማስተዋል አለብን፡፡ እንግዲህ ይህ ሰው፤ እየተፈራ በሰፈር ስለሚሄድ የተከበረ እየመሰለው ማንነቱን እና ጥፋቱን ሳያውቅ ይኖራል፡፡ እንዳውም „ጀግና ነው፤ እሱ እኮ ያላሸናው ሰው የለም፡፡ ሴት አይል ወንድ አይል“ ተብሎ ስመ ገናና ይሆናል፡፡ እንግዲሕ ይህ መሰል እድገታችን ጀግና ተብየውም ሆነ ደግሞም አጃቢውእና አጫፋሪው፤ በዚህ ተፈጥሮአዊ እውቀቱን በሳተ ባህሪ  አድገው ትምህርትም ቤት ተገብቶ ተምሮ ጨረሰ ተብሎ ይመረቃል፡፡ እንግዲህ የተረገመ ተመረቀ፡፡ ግን የሚገርመው እና ልብ ያላልነው ነገር ቢኖር ይህን ግሩፕም እየፈራው ያደገው፤ ፈሪ ሆኖ ትምህርት ቤትም ገብቶ ተምሮ እኩል እንደዛኛው ይመረቃል፡፡ ታዲያ ሁሉም በስራ አለም ይገባል ይሰራል ደመወዝ ተከፋይም ይሆናል፡፡ ይወልዳል ይከብዳል፡፡ አስፈራሪውም ፈሪውም ማለቴ ነው፡፡ አለም ፍርደገምድል፤ አሰሱን ገሰሱን ተሸክማ አንዱን እያስለቀሰች አንዱን ሌላውን እያስደሰተች ትኖራለች፡፡ እኩልነት መብት ይከበር ተብሎ ይጮሕ እንጂ፤ አለም ግን ድርጊትን ብቻ ፈጽማ የምታልፍ እንጂ ጆሮ ያላት ሰሚ አለመሆንዋን እያየነው ነው፡፡ እንግዲህ ያለው ገዢም ፓርቲ የመጣው ከዚህ ደፋር ሆኖ ከሚያንበረብረው ደግሞም እሱን ከሚፈራው ፈሪ ባህሪ ከተላበሰ ውስጥ ነው፡፡  እንደእኔ እና እንደእናንተ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ በባህሪ ሁኔታችን አንዱ ከአንዱ ይለያል የሚል እምነት የለኝም፡፡ የምናየው፤ አንዱ ተፈሪ ሌላው ፈሪ ነውእና፡፡ አዲስ ነገር የለም፡፡ ለማንኛውም መፍራትም አንድ የተቃውሞ መንገድ መሆኑን አንዘንጋ፡፡ በቸር
ባዩሽ    

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen