Donnerstag, 24. Juli 2014

ከአፉ የሚሮጠውን አንተ እየተጣልክም አስተምረው፡፡



ከአፉ የሚሮጠውን አንተ እየተጣልክም  አስተምረው፡፡

ደንቆሮ ነህ እንግሊዘኛ አትችልም ብሎ የሚሰድብህ ያገርህ ሰው፤ በእንግሊዘኛ የጻፍከው ጽሁፍ ጭንቅላቱን መቶታል ማለት ነው፡፡ ምክናያቱም ቁዋንቁዋ አለመቻል አያሰድብም እና፤ ሁልግዜ እየተንተባተብክም በሁሉም ቁዋንቁዋ ጻፍ፡፡ አያችሁ፤ መሰረቱ  ዘሩ እንግሊዝ የሆነ ፈረንጅ፤ ሰበር ያለ እንግሊዘኛ ብትናገር፤ እንግሊዘኛህ ጥሩ ነው የት ተማርከው ብሎ እንድትደፍር ያበረታታሃል፡፡ ያገርህ ሰው ግን ኦሪጅናል ቁዋንቁዋው እንግሊዘኛ ያልሆነ ፌስ ቡክ ላይ ይመጣና እንግሊዘኛህ ጥሩ አይደለም ብሎ ሊሰባበርህ ብዙ ተቀጥያ ቃል ያወጣል፡፡ ይህ እንግዲህ አይምሮውን ሚዛን ላይ ያስቀመጠ ሁዋላ ቀር ነው፡፡ ቁም ነገሩ ቁዋንቁዋ አለማወቅህ ሳይሆን የሚያሰድበው አላማህ ነው፡፡ እናውቀዋለን ሰም እና ወርቁን፡፡ ብቻ እንደምንም ብለው ሞራል አድቀው ሊያባርሩህ የሚፈልጉ አንዳንድ ሰዎችን እንድትነቃባቸው ብዬ ነው ወዳጄ ይህን ጽሁፍ የማቀርብልህ፡፡ በቃ የማይጭሩት ጉድጉዋድ የለም፡፡
ዋናው ነገር ማንም ሰው ቁዋንቁዋ አወቀ አላወቀ የሰው ልጅ ፈጽሞ ማለፍ ለሚገባው ነገር ሁሉ፤ እንደአስተሳሰብ መስጠት መንቀፍ እና ተካፍሎ መኖር መብቱ ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ነገር ፈጥመህ ለማለፍ የግድ ቄስ መሆን ይጠበቃል እንዴ?  እንግሊዘኛ አወክ አላወክ ደግሞ ድምጽህን ለመስጠት ማነው ከልካዩ፡፡ የአለም ትምህርት ተማርክ አልተማርክ ማነው ከልካዩ፡፡ የመጀመሪያው አስተማሪ እኮ ያስተማረው እግዚአብሄር እንጂ ሰው አይደለም፡፡ መብቴ ነው ብለህ መጋፈጥ ነው እንጂ የምን መሸሽ ነው፡፡ በጀርመን አገር ብዙ የጀርመን ምሁሮች  አሉ፤  ወ;ሮ አንጀላ መርክል አይምሮ ያላት እውቀቱዋ የላቀ አገሩን በደንብ የምታስተዳድር ሆና እያለች፤ እንግሊዘኛዋ ግን በቂ አይደለም ተብላ እውቀቱዋን እውን እንዳታደርግ አልተከለከለችም፡፡ የእሱዋ ቁዋንቁዋ ጀርመነኛ ነውአሃ፡፡ እንግሊዘኛ የማይችሉ፤ እና ከማወቅ የከለከላቸው ነገር ምንድን ነው? ቁዋንቁዋ መቻል የመጨረሻው የእውቀት ደረጃ ነው ላችው ማን ይሆን እነዚህ የሞራል ላጲሶች?  አንዳንድ የቁዋንቁዋ ባሪያ ወይም ዝም ብሎ ተገዢ የሆነ ሰው ብቅ ይልና ትንሹዋን ችሎታውን ለማሳየት እንግሊዘኛህ ብሎ ሊተች ይነሳል፡፡ የቁዋንቁዋ ችሎታ የአንተን አይምሮ መመዘኛ ሊሆን አይችልም፡፡ በቃ ቁዋንቁዋ የአካባቢው ሰው መገናኛ መገላላጫ ብቻ ነው፡፡ በቁዋንቁዋ አነስተኛነት እራስህን መግለጥ ሊያቅት ይችላል እንጂ፤ ለአንተ መሰደቢያ እና መዘለፊያ መሆን የለበትም፡፡ ቁዋንቁዋ የአይምሮ መመዘኛ ቢሆን ኖሮ ቁዋንቁዋ ባለማወቅ ተሳዳቢው ባልተቸህ ነበር፡፡እሱ ችሎታውን ቁዋንቁዋ በደንብ በመቻሉ ደምድሞታል፡፡ እድገቱ በዚህ ተወስኖአል፡፡  ከዛ ማለፍ አይችልም፡፡  ስለዚህ ቁም ነገሩ አካባቢን እና አገርን ወገንን በሚለውጥ ነገር ላይ መነጋገሩ ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡ እኔ ለእራሱ የሚገርመኝ የተለያየው የአካባቢያችን ቁዋንቁዋ የዘር መለያ እና መጫኛ ሆኖ ሲቀርብ እንኩዋን ያስቀኛል፡፡በቃ ቁዋንቁዋ የአካባቢ መለያ ሳይሆን መግባቢያ ነው፡፡ ሌላውን ቁዋንቁዋ ተሰባብሮም ይሁን ተጣሞ ማወቅ እንዴት ጠቃሚ ይመስላችሁዋል፡፡ ምንው ሰባብሬም ቢሆን ሁሉንም የአለም ቁዋንቁዋ በቻልኩ፡፡ እኔ ከአለም ሰው ሁሉ ጋር ተግባብቸ ለመኖር አይምሮዬ እያስገደደኝ ነው፡፡
ሌላው ውጭ አገር የምትኖሩ ሳሃን አጣቢ እያለ የሚሳደብ አለ፡፡ ፈረንጅ አገር  ኮቢሊስቶን ተነጥፎ  ካለቀ ብዙ አስርተ አመታቶች አልፈዋል፡፡ ስለዚህ እዚህ ኮቢሊስቶን ማንጠፍ የለም፡፡  ታዲያ ምን እንስራ፡፡ ለነገሩ እውጭ የሚኖር ሰው በፖለቲካው አለም የሚነቅፍ ነገር ሲፈጽም፤ አልያም ደግሞ የሚጻፉ ጽሁፎች አንዳንዱን ጭንቅላቱን ሲመታው እና ማንነቱን ለእራሱ ሲገልጽለት፤  አንጀቱን የሚያቃጥለው ይመስለኛል፡፡ ይህንን ሰሃን አጣቢ የሚል ተቀጥያ የሚናገረው ማለቴ ነው፡፡   ኮብሊስቶንም ማንጠፍ ስራ ነው፤ ሳሃንም ማጠብ ስራ ነው፡፡ ዛሬ እኮ ሳሃን ለማጠብ ባገኝ ብሎ ነው አብዛኛው የውጭ እድል የናፈቀው ባገኘበት አገር እየለቀቀ የሚወጣው፡፡ ሳሃን እንዳያትብ እዛ ሰላም ስጡታ፡፡ ስራ ስጡታ፡፡ የት ሊደርስ መሰለህ ታዲያ፡፡ በሰላም አጥቦ ለመኖር ነው፡፡ ዶክተር ሆነህ ሰላም እና እኩልነት በለለበት ስፍራ ከመኖር ፤ሳሃን አጥቦ ስብእናህን ሲከበር ማየት ደስ ይላል፡፡ ያስደስታል፡፡ ፊት ያፈካል፡፡ እዚህ እኮ ሳሃን አጣቢ እና የታወቀ ሳይንቲስት እኩል የሚኖርበት አገር ነው፡፡ ቁጭ ብሎ አስተያየት የሚሰጣጥበት ደግሞ አስተሳሰብ የሚደማመጥበት አገር ነው፡፡ ግን ሳሃንም አጥበሕ ቂጡ ያበጠ ደላር ይከፈልሃል፡፡ አገሬ ሀኪሙ ከሚያገኘው በላይ እዚህ ሳሀን አጣቢው ያገኘዋል፡፡ ስለዚህ ሳሃን አጣቢ ስድብ እንደማይሆን ልንገራችሁ እና ግንዛቤያችሁን አሳድጉ፡፡ ሳሃን አጣቢ የአገሩ ሁኔታ አይመለከተውም የሚል ማነው ለመሆኑ?  ለምንድን ነው ሰው የዋሕ የሚሆነው?  ስራ ክቡር ነው፡፡ እንኩዋን እኛ ፈረንጁ ለእራሱ ተወልዶ ባደገበት አገር ሳሃን ያጣባል፡፡ እቤቱ የበላበትን ለማጠብ እናቱን አይደለም የሚያሳጥበው፡፡ ደግሞም ሰራተኛ ቀጥሮ አይደለም የሚያሳጥበው፡፡ እንደአገራችን ወይ በዘመድ ስም ከገጠር አንዲቱን አስመጥቶ አልያም እርካሽ ጉልበት ቀጥሮ አይደለም፡፡ እዚሕ ጉልበት እንደአገራችን እርካሽ አይደለም፡፡ የሰው ጉልባት ዋጋ ያለው አገር ሆኖአል፡፡ ስለዚህ እንደአገርህ እየመሰለሕ ሳሃን አጣቢ አትበል፡፡ ይህን ቃል ከአፉ የሚያወጣ መቸም፤ ያደገው በደሃ ገጠር ቤትሰብ የሆነች አስጠግቶ፤ በእናቱ እና በእህቱ፤ በርካሽ ሰራተኛ ጉልበት የኖረ አውደልዳይ ነው፡፡ እሱ እኮ ይህን ቢያገኝ የእናቱን ቤት አሲዞ ተበድሮ ለደላላ ከፍሎ ልውጣ የሚል ነው እንዲሕ የሚለው፡፡ ምንድን ነው ሳሃን ማጠብ የሚያሰድበው፡፡ ቢሆንስ፤ ሰርቶ መብላት ያሰድባል?  ወይስ ሳሃን ማጠብ ፤በአገርህ ጉዳይ አስተሳሰብ መስጠት ይገደባል?  እንዴ የተማረ ብቻ ነው እንዴ አስተያየቱን መስጠት የሚችለው?  ማነው ይህን ያስተማረህ?  ደሞም እንዲሕ ስልህ ሁሉም ሳሃን እሚጥብ አይምሰልህ፡፡ ናዛ ብትገባ ሀበሻ አለልህ፤ ሳይንቲስት ብትፈለግ ሀበሻ አለልህ፤ ሜዲካል ዶክተር ብትፈልግ ሀበሻ አለልህ፡፡ፊልም  አክተር ብትፈልግ ሀበሻ አለልህ፡፡ ፖለቲከኛ ብትፈልግ ሀበሻ አለልህ፡፡ ፓይለት ብትፈልግ ሀበሻ አለልህ፤ ወታደር ብትፈልግ ሀበሻ አለልህ፡፡ ሌባም ብትፈልግ አለልህ፡፡ ቦዘኔም ብትፈልግ አለልህ፡፡ ተማሪ አለልህ፤ ሴት አዳሪም አይጠፋም፡፡ በቃ አቃጥሮም የሚበላ አይጠፋም፡፡ በቃ የሰው ባህሪ ሁሉ በማንኛውም ስፍራ በማንኛውም ዘር አለልሕ፡፡ ወይኔ የምታሰኘውስ የምትጣጠብ ሳህን የጠፋች ለታ ነው፡፡ በጠቅላላው፤ ለአለም ፖለቲካ ሁሉ አማካሪ የሚሆኑም ኢትዮጲያውያኖች ከወደአሜሪካ፤ ካናዳ“ እና እንግሊዝ አገርም እኮ ሞልተዋል፡፡ ምነው በታደልክ እና ወደአንተም በመጡልህ እና በረከትን በበላሕ፡፡ ለመሆኑ የተማረው መናሀሪያ የት ሆነእና ሳሃን አጣቢ ትላለህ፡፡ ግን እኔ አልተማርኩም፡፡ አይዞአችሁ፤ ላስተዳድር አልመጣም፡፡ ግን ግን አስተሳሰቤን ለመስጠት የሚገድበኝ ድንቁርእና ግን እኔ ጋር ከጠፋች ዘመናት አስቆጥሮአል፡፡ እራስህን ለውጥ እና ስብእናን ተማር፤ ለእኩልነት እና ለዲሞክራሲ ተናገር እንጂ አፍን ለማሰር አትሩጥ፡፡ አስተሳሰብ አንድ ከእግዚአብሄር አንድ ከሰይጣን ነውእና ማንነቱን ለይ፡፡ ሰላም ይብዛላችሁ የምላችሁ እማማ ባዩሽ ነኝ፡፡

Donnerstag, 17. Juli 2014

ቁዋንቁዋ ስለሚገባህ ሳይሆን መረዳትን ይዘህ አንብብ



ቁዋንቁዋ ስለሚገባህ ሳይሆን መረዳትን ይዘህ አንብብ
 
እኔ እምጽፈውን እያነበበ የሚናደድ ሰው፤ አቁሚ እያለ ይሰድበኛል፡፡ ቢያገኙኝ ምን እንደሚያደርጉኝ ክርስቶስ ያውቃል፡፡  የሚያስቀኝ ስድብ ግን  አሮጊት የሚለው ነው፡፡ ተሳድቦ ሞቶ ነው በእሱ ቤት፡፡ እኔ ግን በአሮጊትነቴ የምኮራ እና፤ ምንም አይነት የማጎብጉብም ሆነ የአድርባይነት ባህሪ የለለኝ አሮጊት ነኝ፡፡ በዚህ ባህሪዬ እኮራለሁ፡፡ አብሮ አረጀብኝ፡፡ አጎብጉቤ አልበላም፡፡ መንግስትንም የለለሁትን አለሁልህ እያልኩ አልሸነግለውም፡፡ አልበላውም አልጠቀምበትም፡፡ የኢሕአዴግ ገንዘብ የሕዝብ ነውእና፡፡ የእኔ ነውእና፡፡ የእናንተ ነውእና፡፡ እንደሚሳደቡት ማለቴ ነው፡፡ እውነቱን እውነት እያልኩ እዚህ ደርሻለሁ፡፡ ለማንኛውም ይህ እናቱን እየተሳደበ ያደገ አንዳንድ ሰው ምንም አይገባውም፡፡ የባህሪ ለውጥ ካላመጣ በስተቀር፡፡ ፖለቲከኛም ደግሞ ያደርጋቸዋል፡፡ ከአንጀቴ ብስቅበት ደስ ባለኝ ነበር፡፡ ግን አገርን ወገንን አለምን ይዞ የሚሞት ድንቁርናን ስለተሸከሙ በእነዚህ ሰዎች መሳቅ ሳይሆን መጸለይ ነው፤ ኮስተር ብሎ መንገር እና ማስተማር ነው፡፡ እንዳውም መንግስትን የጠቀሙ መስሎዋቸው ገደል የሚከቱት እነዚህ እንደ ክረምት ጻሀይ ብልጭ ድርግም ዕያሉ አንድ ቃላት ወርወር አድርገው የሚሄዱ ናቸው፡፡ እዛም አለንልህ ይሉታል፡፡ አድርባይ የትም ቦታ ግን ተገኝቶ የማያውቅ የማይጨበጠው ንፋስ ነው፡፡ አድርባይን እጠላለሁ፡፡ እናንተም ጥሉ፡፡ ለምድራችን አሳች ነው፡፡ ለማንም አይጠቅምም፡፡
ግን ዲሞክራሲ ማለት ፤ከዚህ ጀምሮ እኔንም ነጻነቴን አለመንፈግ መሆኑን እንኩዋን የማያውቅ አለ፡፡ ይገርማል፡፡ አቁሚ አትጻፊም የሚለኝ ወንድ መሳይ ሴትም ሊሆን ይችላል፤ ያው የፌስ ቡክ ነገር አይታወቅም፡፡ ያም ሆነ ይህ አንዳንዱ ጽሁፍ ማንነትን የሚነካ፣ የሚያስታውስ በመሆኑ ውስጡ ሲነካ የሚናደድ ይኖራል፡፡ እዚህ ላይ ጹሁፌ ታርጌቴን መታ እላለሁ፡፡ በሚሰድቡኝ እስቃለሁ፡፡ እኔ ምንም ማድረግ አልችልም፡፡አንድ ሰውን አነጻጽሬ አልጽፍም፡፡   በናታችሁ እዛው እንደለመደ እናቱን እና ሚስቱን ያፍን እንጂ፤ እኔ ጋር ምን አለው?  እሱ መንግስት ነውን? አንዳንዱ እኮ የፖለቲካ ፓርቲን የሚረዳው፤ ሌላውን በመሳደብ ነው፡፡ አያስቅም? ወይ ግንዛቤ? 23 ዓመት እድሉ እያለ ዲሞክራሲን ለማስተማር ሳይጠቀሙበት፤ ሹል ምላስ አሲይዘው አፍ ጠባቂ ማስኮልኮል እና ሞራልን ለመግደል ማሰማራት ምን ትርፍ አመጣ፡፡ በአጠቃላይ ስድብ ከፖለቲካ ጋር፤ ከአገር ፍቅር ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የለውም፡፡ የሰውን የእራሱን የወደቀእና ያዘቀጠ ባህሪ የሚያስረዳ ነው፡፡ ገዢውን ፓርቲም ሆነ ተቀዋሚን ደጋፊ ነን ወይም አጃቢ ነን የምትሉ እርስ በእርሳችሁም አትሰዳደቡ፡፡ ልብ በሉ ስድብ ይዞ የሚሰለፈውን መልስ አትስጡት፡፡ ቁም ነገር የምትለዋወጡበትን ግዜ ሊያቃጥል የገባ ቦዘኔ ነው፡፡ ዝም ብሎ ያለችውን ያልታደለች የኢንተርኔት ገንዘብ ገደል እየከተተ ያለ፡፡ ወይም ያገኘውን የነጻ የኢንተርኔት መጠቀሚያ እድል በከንቱ የሚያቃጥል፡፡ ስድብ ክርቲክ አይደለም፡፡ ስድብ የእራስህን ማይንድ የእድገት ደረጃ የሚያሳይ ነው፡፡  ጥቂት ሰዎች ዲሞክራሲ እንዴት እንደሚሄድ ተማሩ፡፡ ሰውን ለማፈን አትሞክሩ፡፡በምታነቡት  አትናደዱ፡፡ በተለይ ስለእራሴ የምናገረው በእኔ ጹሁፍ የሚናደድ አያንብብ፡፡ እኔ አስተያየቴን ከመጻፍ ስለማልቆጠብ ጨርሳችሁ እንዳትቀውሱ ብዬ ነው፡፡ ጠንከር  ለክርቲክ፤ አስተያየቴን መቃወም መብት ነው፡፡ እኔም መማር እፈልጋለሁ፡፡ ጎበዝ ወይም ጀግና አልያም ሰነፍ እና ፈሪ ስለሆንኩ አይደለም የምጽፈው፤ መብቴ ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ ማመዛዘን የሚችል መሆን አለበት የተጻፈን ማንበብ የሚችል፡፡ እንዳው ቁዋንቁው ስለሚገባህ ብቻ አይደለም የሚነበበው፡፡ መረዳትህንም ይዘህ ነው፡፡ ክሪቲክ እና ስድብ ለዩ፡፡ ለነገሩ ተመስገን ነው ለዛሬ እድሜ ያደረሰኝ፡፡ ስንቱን አየሁት፡፡ አሮጊት ሹመት መስሎ እስከሚታየኝ ደስ ይለኛል፡፡ አያሳፍርም፡፡ ዛሬ ስንቱ በለጋ እድሜ እየተቀጨ አይደል? ለሊቱን በጫት፤ በዲስኮ እና በልቅነት የሚያሳልፈው አላማ የለሹ አሮጊት እናቱን የሚሳደበው፤ አገሩን የረሳው እረ ስንቱ፡፡ ለዛሬ እድሜ በቅተህ ታዝበህ የምትተች የምትነቅፍ ደግሞም ዘመንን የምትመሰክር ሽሜ እና አሮጊቴ ደስ ይበልህ፡፡  ሽበት ማየትህ፤ እፊትህ ላይ የተጣጠፈው ጨምድድ ያለው ቆዳሕ ደስታ ነው፡፡  በውስጡ ብዙ ልምድ እና ተመክሮ አለእና፡፡ ስለዚህ አሮጊት መባሌን ወድጀዋለሁ፡፡ አይግረማችሁ እና፤ ሽበቴን ቀለም  ደግሞም ጨምዳዳውን ቆዳየን ልጅ ለመምሰል ሜክአፕ  አልቀባውም፡፡ እግዚአብሄር የሠጠኝን ነገር ሁሉ ተቀብዬ ተመስገን ብዬ እደሰትበታለሁ፡፡ ወዳጄ ሆይ፤ ገና አገራችን በዛ ደረጃ ስለማትገኝ፤ የመልክህ ማንነት ላይ ብዙም ኢንቭስት አታድርግ፡፡ የውስጥህ ማንነት ነው ለአገርህ ወሳኙ፡፡ ለለውጥ ወሳኙ፡፡ ለዲሞክራሲ ወሳኙ፡፡ ለመብትህ ወሳኙ፡፡ ለእኩልነት ወሳኙ፡፡ ለሰላም ወሳኙ፡፡ ለእርህራሄ ወሳኙ፡፡ ሌላውን ዘር ለመቀበል ወሳኙ፡፡ ለቆዳህ ሳይሆን ለህሊናህ ኑር፡፡ ቆዳን መልሰህ ብትለጥጠውም ነገ ማንነቱን አይክድም፡፡ ያው ታረጃለሕ ትሞታለሕ፡፡ በቸር የምላችሁ This is me Bayush Abebe.

Mittwoch, 16. Juli 2014

እውን ኢሕአዴግ ከእግዚአብሄር ይበልጣል እን?



እውን ኢሕአዴግ ከእግዚአብሄር ይበልጣል እን?

ወንድና ሴት ሊነጣጠሉ የማይታዩ በአንድነት ለአለም አስፈላጊ የሆኑ እና ለእግዚአብሄርም ስራ ሰውን በነሱ በኩል እንዲፈጥር የሚረዱ መሳሪያዎች ናቸው፡፡ መጣመር እለዋለሁ እኔ፡፡ እንደ አፈር እና ውሃ፡፡ እግዚአብሄር አፈርእና ውሃ ፈጠረ እና እጽዋቶች እንዲበቅሉ አድርጎአል፡፡ ማዳበሪያ የመጣው ሰው ለበደለው ላበላሸው እንደማገገሚያ ለማድረግ ይመስለኛል፡፡ አለምን ባናበላሸው ኖሮ እና መሬቱን እንኩዋን ሰላሙን ብንሰጠው ኖሮ ማዳበሪያ ባላስፈለገን ነበር፡፡ በሌላ መልኩ ግን ፤ እንደጊዜው ወንድ ወንድን ሴት ሴትን አግብቶ  ለእግዚአብሄር ስራ ማሳያ፤ ዘርን እንዲፈጥሩ የሚያደርግ ሁኔታ የለም፡፡ ቢጣመሩም ማለቴ ነው፡፡ ያም ሆነ ይህ ሁሉም የሰው ልጅ አስፈላጊ እንደሆነ እራሱ መገንዘብ እና እኔ ለዚህ አለም አስፈላጊ ሆኜ ተፈጥሬአለሁ ብሎ እራሱን መቀበል አለበት፡፡ እዚህ አለም ላይ የሚንቀሳቀሱ ነገሮች ሁሉ የአንተንም ፍቃድ ወይም ተቃውሞ ማለትም አይስማማኝም ብለሕ አስተያየትህን ለመስጠት ወደሁዋላ የሚያስብልህ ነገር በጭራሽ አይኖርም፡፡ በዚህ መልኩ በዚህ አለም ላይ አንተም ለመኖር ውዴታህ ብቻ ሳይሆን ግዴታህ ነው፡፡ ምክናያቱም ማንም በምርጫ አልተፈጠረም፣ አልተረገዘም ደግሞም አልተወለደም፡፡ በግዴታ እያለቀስክ ወደዚህ አለም ተልከሃል፡፡ ድርሻም አለሕ፡፡ መኖርም መካፈልም አለብህ መብትህ ነው፡፡ በእግዚአብሄር ካየነው፡፡ ግን እስኪ ይችን ነገር ተካፈሉኝ፡፡
ስለአምባገነን አሰላሰልኩ እና፤ አምባገነን ማለት እኔ ብቻ ልኑር ልዘዝ ልብላ ልጠጣ የሚል፤ እግዚአብሄር ከፈጠረው ህዝብ መካካል እሱ ጥቂቶችን መርጦ መሳሪያ አድርጎአቸው የሚኖር ሀጢያተኛ ማለት ነው፡፡ አምባገነን እራሱን የሾመ  የምድር አምላክ ማለት ነው፡፡ ቢችልም እግዚአብሄርን ቦታውን ለመሻማት የተነሳ ጨካኝ፣ ስግብግብ፣ የነገን ሁኔታ የማያስብ፣ አስተሳሰብን መካፈል የማይችል እና እራሱ ጠይቆ እራሱ የሚመልስ ደግሞም የሚወስን  ነው፡፡ አምባገነንን ሁሉም አለም አንድ ግዜ አስተናግዶአል፡፡ በአፍሪካ ግን ድግግሞሽ ይታይበታል፡፡ የሚገርመኝ ግን አምባገነንነት ከወንዶች የተፈጠረ መሆኑእና ደግሞም የሚስተናገድ መሆኑ ነው፡፡ ከወንዶች አለም ብቻ ሳይሆን ከጎኑ የተፈጠረችውም ሴት እንድትንቀጠቀጥለት ይፈልጋል፡፡ ብዙ ግዜ ወንዶች፤ በጉልበታቸው እና በሀይላቸው ተጠቅሞ የመኖር ተፈጥሮአዊ ስጦታ ያላቸው ሳይሆን አይቀሩም ብዬ አስባለሁ፡፡ ሁሉም በስልጣን አለም የአምባገነንነት ድርሻ ባይደርሳቸውም፤ ግን አባወራ፤ የጎበዝ አለቃ፣ ምስለኔ፣ ጭቃሹም እያለ የሚቀጥለው ነገር ሁሉ በብዛት የተስተናገደው በወንዶች ነው፡፡ ሴትም ወንድም የመልካም መሪነት ተሰጥትኦ ቢኖራቸውም፤  አምባገነን ግን የሚፈጠረው ከወንዶች ውስጥ ነው፡፡ ወንዶች ደፋሮች ናቸው፡፡ ይህ ድፍረት ከተፈጥሮዊ ነገራቸው ጋር የተጣመረ እንደሆነ ያጠናው ካላ ቢያሳውቀን መልካም ነው፡፡ ለማንኛውም ስለአምባገነን ሳወራ ወንዶች ላይ ጣት መቀሰሬ አልቀረም፡፡ ብዙ ሚሊዬን ህዝብ የሚያልቀው በአንድ አምባገነን ትእዛዝ ነው፡፡ ተኩዋሹም ተከታዩም ሁሉንም ጾታ ቢነካም፡፡ ልብ በሉልኝ ሴቶች አይገሉም አይተባበሩም አይደለም የምለው፡፡ ግን አምባገነን ሆኖ የሚያዘው አንድ ነው፤ እሱም ወንድ ነው፡፡ ማስገደድ ይችላል ማስፈጸም ይችላል፡፡ የሚገርመው የአምባገነን ሁኔታ፤ መጥፎም መሆኑን እያወቀ ተግባሩን የሚፈጽምለት ሰው አያጣም፡፡  ጀብዱኛነት ብዙውን ባህሪ የተላበሰው በወንዶች ላይ ነው፡፡ ይህ ባህሪያቸው ብዙውን ግዜ ችኩል ያደርግእና ያሰቡትን ያለሙትን በቶሎ ይፈጽሙታል፡፡ መግደል ማሰር የደመነፍስ ስራ ጀብደኛነትን ያሳል፡፡ የገዛ ባህሪያቸውም  ብዙ ጊዜ ሲጥላቸው ሲያዋርዳቸው  እናያለን፡፡ ሁሉም አንድአይነት ባይሆንም ውንብድና ግን ታላቁን ቁጥር ዬዘው በወንዶች ነው፡፡ የሴት ውንብድና ካለወንድ አይዞሽ ባይነት አይፈጸምም፡፡
ወንዶች ጦርነትን መፍጠርእና መምራትም ተሰጥትኦ አላቸው፡፡  ወንዶች ሰውን በአሰቃቂ ሁኔታ ይመረምራሉ ያሰቃያሉ፡፡ በአምባገነንነት ደግሞ ሰቆቃ ማድረግ የሚወዱእና መንገዱንም እንደግዴታ አድርገው የሚያዩ ናቸው፡፡ አስገድዶ መደፈርም በወንዶች ይካሄዳል፡፡ ወንዶች እርስበእርሳቸውም እንደአውሬ ሲደባደቡ እናያላን፡፡ የወንዶች ተፈጥሮአዊ ስጦጣ አልምን በጦርነት ያምሳል ደግሞም ይጋብዛል፡፡ በቃ የተነቀፈ የመሰለው ወንድ እማ ሽንፈቱ አይድርስ  ነው፡፡
ግን ዛሬ በኢይሮፕ ብዙ የወንዶች ባህሪ ተቀይሮአል ሰላማዊ አስተሳሰብን ይዞአል፡፡ አንባገነንም ደዝባው እየጠፋ የሄደበት ማንአለብኝ አመራራ የቀረበት ህዝቡ በዲሞክራሲእና በሰላም ለመኖር የወሰነበት በታሪካቸው ውስጥ  እንደዛሬው ዘመን ተፈጥሮ አያውቅም፡፡ ሕዝብ ነጻ ሆኖ እየተደሰተዘ ለአጭሩዋን ዘመኑን ለመኖር ወስኖአል፡፡ ሰው ከፈለገ፤ ፖለቲከኞችን ይቆጣል፣ ይተቻል፣ ይገስጻል፣ ይመርጣል፣ ይሾማል ባጠቃላይም የመሻር ችሎታ እና መብት ተላብሶአል፡፡ ጀግና ህዝብ ካልክ ይህን መብት ታግሎ የደረሰ ነው፡፡ ፈረንጅ ህዝብ ለዚህ ደረጃ በቅቶአል፡፡ ጀግና ነው፡፡ ቀልድ የለም እሱን ማታለል ማንም አይችልም፡፡ በየቀኑ ፖለቲካውን ያል ይመረምራል፡፡ እንደኛ አይከለከልም፤ ሊከለክለው የሚችል የለም፡፡ ምክናቱም መሪውም እንደህዝቡ የተቀየረ ነው፡፡ የሰለጠነ ነው፡፡ ከእራስ ወዳድነት ወጥቶአል፡፡ አገሩን እንጂ ኪሱን አያይም፡፤ አምባገነን የሰላም ጦስ መሆኑን አውቆአል፡፡ የዘር የባልይነት የሚባል ነገር ብታነሳ መሳቂ ነህ ማሃይም ነህ፡፡ ሞኝ ነው እንዴ ብቻዬን ይመቸኝ የሚል ይልሃል፡፡ ዘረኝነት፤ የበላይነትን የሚመኝ ክፍል ያዘጋጀው እና በጥላቻ እና በእልቂት የተሞላ መሆኑን ሁሉም ልምዱን አካብቶበታል፡፡ ዘረኝነት የድንቁርና  ምንጭ መሆኑ ታውቆአል፡፡ አይምሮ ነው ወሳኙ ላካ፡፡ ጉልበትን መጠቀም አዲዮ ያለበት ዘመን ላይ ኢይሮፕ ገብታለች፡፡ በህዝብ ትግል ሁሉም ተቀይሮአል፡፡ እኔ< እበልጣለሁ የሚያመጣው ትርፍ ትእቢት፣ ሀይልእና ጉልበት ነው፡፡ እራስህን መቆጣጠር እና እራስን መግዛት ሚዛናዊ ያደርግሃል፡፡ ከዛ ነው ዲሞክራቲክ ልትሆን የምትችለው፡፡ ከልብህ ትእቢት ጥርግ ብሎ ሲወጣ፡፡ አስተዳደጋችንም ለአገራችን ወሳኝነት አለው፡፡ ጀብዱኛ መሆን እውስጥህ ነቀርሳ መትከል ነው፡፡ የመሪዎቻችን ችግር ይህ ነው፡፡ መሸነፍን አለመቀበል ከጀብዱኝነት የተያያዘ ነው፡፡ አንድሰው አምባገነን የሚሆነው ህዝብ ሲፈቅድለት ነው፡፡ መከላካያው ሲፈቅድለት ነው፡፡ ዳኛው ሲፈቅድለት ነው፡፡ ሁሉም መዋቅር ከአምባገነን ነጻ ካልወጣ የተጻፈ ህግ ከወረቀቱ ተነስቶ አይራመድም፡፡ ዳኛ፣ መከላከያ ከህዝብ ጎን መቆም ግድ ሊለው ይገባል፡፡ በደሃ ላይ ፤ባልመረጠው ህዝብ ላይ፣ በደካማ ላይ እና በተቃዋሚው ላይ ክንዱን የሚነሳ ወንድ አስተዳደጉን ይጠይቅ፡፡ ጀብዱኛ አድርገው ገለው አሳድገውት ይሆናል፡፡ አንዱ ሌላውን እንዲጫን የሚል ሳይንሳዊም ሆነ መንፈሳዊ ሕግ የለም፡፡ ፈሪ ስለሆንክ ነው የተወሰነብህ፡፡ አንዱ አንዱን ቀምቶ የሚበላበት የሚከብርበት እራስን ወዳድነት ከምድሪቱ መጥፋት አለበት፡፡ ይህ ምንም አይነት ሙግት አያስፈልገውም፡፡ ደሃእና ሀብታሙ ልዩነቱ ሆድእና ጀርባ ነው፡፡ አንድ ፓርቲ አይምሮ ብቻ ወይ አስተሳሰብ ብቻ ለኢትዮጲያ በቂ አይደለም፡፡ አንድ ፓርቲ ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ ሊኖር ይችላል፡፡ ግን መከላካውንም ፍርድቤቱንም ካዝናውንም ለመግዛት ምንአይነት ፍጡር ቢሆን ነው፡፡ ይህ እጅ እጅ የሚል ነገር ህዘብ ሊገባው ይገባል፡፡ ተመችቶሃል ወይ የአድሎእና የጥቂት ሰዎች መናሀሪያ የሆነችው ኢትዮጲያ፤ ካልተመቸህ ወኪል የሚሆንህን ሰው መጠበቅ መከላከል መብትህ ነው፡፡ ነገ ወኪል እንዳታጣ ለዲሞክራሲእና ለሰላም ድምጽህን ማሰማት መድፈር አለብህ፡፡ ፍርሀታችን ለማንም አይጠቅምም፡፡ አድርባይ የበዛበት ኢትዮጲያ ባህሪውን ይቀይር፡፡ በፍርሀት እና ደግሞም በግል ጥቅም ወገንህን አገትጎዳ፤ ነገ የዛሬው ያልፋል፡፡ እምነትም ያለሕ ለእግዚአብሄር ተንቀጥቀጥ እንጂ ለሰው ከንቱ ምግባር እራስህን አትሽጥ፡፡ እኔ ባዩሽ አበበ በእግዚአብሄር አምናለሁ፡፡ „ሽ ጦር ቢሰለፍ አምላክ ከእኔ ጋር ነውእና ማን ይቃወመኛል“፡፡ ሰው በውሸትም ለማደር ሲል ያቃጥራል፡፡ ግን አንድ ነገር አለ፤ እግዚአብሄር ግን የሚመሰክርልኝ ዘመን ይመጣል፡፡ ሰው እምነቱን ይተግብር እንጂ አይደብቀው፡፡ ኢይሮፕን ኢይሮፕ ያደረገው የህዝብ ፍላጎት እንጂ የፖለቲከኞች አይደለም፡፡ አንተ ፈልግ የኢትዮጲያ ህዝብ፡፡ እንኩዋን ሰው፤ እግዚአብሄርም ክፉና በጎውን አሳይቶ፤ ወደመረጥከው ሂድ ብሎአል፡፡ እውን ኢሕአዴግ ከእግዚአብሄር ይበልጣል እን?  ሰላማችን ተቃዋሚም በሰላም ሲሳተፍ ብቻ ነው፡፡ በአንድ ፓርቲ የትም አለም ሰላም ሆኖ አያውቅም፡፡ በቸር ባዩሽ

Sonntag, 13. Juli 2014

ህዝብ የሚከፍለው ግብር የአንድ ፓርቲ ሳይሆን የተቃዋሚውም ክፍል ነው፡፡



ህዝብ የሚከፍለው ግብር የአንድ ፓርቲ ሳይሆን የተቃዋሚውም ክፍል ነው፡፡
እኔ የማንኛውም ፖለቲካ አባልም ደጋፊም ሆኘ አላውቅም፡፡ ግን ዲሞክራሲን ምንነቱን እና ምቾቱን ስለማውቅ፤ ዲሞክራሲ እውን እንዲሆን እና፤ እረጅም ግዜ በምእራቡ አለም በመኖሬ የዲሞክራሲን ባህሪ ለማሳየት ብዙ ሞክሬአለሁ፡፡ በወሎ አካባቢ ያሉ በተለይ ደሴ ላይ ያሉ የኢሕአዴግ ባለስልጣናት እና የበለጠውም የአካባቢው ተወላጅ ጥረቴን እና ደግሞም በበጎ ያደረኩት እና የተናገርኩት ሁሉ እንደተቃዋሚ ታይቼ መንገላታቴን እና  በእጅ አዙር እንዳልሰራ መደረጌን ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ በእጅ አዙር ሲያንገላቱኝ የነበሩትን ሀሰተኞችም፤ እግዚአብሄር እንደሚበቀላቸው ጥርጥር የለውም፡፡ ስለዚህ ኢሕአዴግ ይህንን ስርአት አያውቅም ልል አልችልም፡፡ ግን ስርአቱ የተሳሳተ የሚጥለው አካሄያድ ነበር፤ ነውም፡፡ ይህ የረጅም ግዜ የዋህ ትግሌ ግን ኢሕአዴግን አይኑን እንዲከፍት ሊያደርገው አልቻለም፡፡ ምክናያቱም እነሱ ትኩረታቸው እራሳቸው ብቻ ይጠቅመናል ያላችሁት ሰው ላይ እንጂ፤ ቁምነገሩ ላይ ባለመሆኑ አፋችን እንድንሸብብ ያደረጋችሁን ሰዎች እንደነበርን የአደባባይ ሚስጥር አይደለም፡፡ ይቃወማል ብላችሁ የምትጠረጥሩትን ሰው፤ አይምሮውን የሚፈታተን፣ ስብእናውን የሚገድል፣ ስነልቦናውን የሚሙዋጥጥ፣ ማንነቱን እንዲያጣ፣ ታማኒነት እንዳያገኝ ማድረግ እና የገቢ ምንጩን በመምታት ለዲሞክራሲ እንዳይቆም በማድረግ ከጨዋታ ውጭ እንዲሆን ማድረጋችሁን አዙሮ ማየት መልካም ነው፡፡ ዲሞክራሲን እንፈልገዋለን ማለት ተቀናቃኝን በመምታት አልነበረም፡፡ ምንአልባት ተቃዋሚ ሆኘ ብገኝ እንኩዋን፡፡ ግን እንደእውነቱ ተቃዋሚያችሁ አልነበርኩም፡፡ ያቃታችሁ ግን እኔን ደጋፊ ማድረግ ብቻ ነበር፡፡ ይህንንም ያልቻላችሁበት ምክናያት የዲሞክራሲ ብቃታችሁ እና ፍላጎታችሁ ፈተና ላይ የወደቀ፤ የምትፈልጉትን የማታውቁ በመሆናችሁ ነው፡፡ እኔ ኢሕአዴግ ልሆን አልችልም፡፡ ምክናያቱም ከህዝብ ማሃል ህዝብ መርጦ የሚኖር ድርጅት በመሆኑ ነው፡፡ አውቃለሁ፤ ኢሕአዴግ ቢያጠፋም   አይቀጣም፤ ከእለት ወደእለትም ኢኮኖሚው ያድጋል፡፡ ችግር ቢደርስበት የእኛ ነው ተብሎ ጸጥታው በቶሎ ይረዳዋል፡፡ ስለዚህ በኢንቬስትሜንትም ውስጥ ሰው ልግባ ካለ፤ ኢሕአዴግ አባል ወይም አይን ያወጣ ደጋፊ መሆን አለበት፡፡ እንግዲህ ፋክቱን እንጋፈጥ ካላችሁ፡፡ ግን ደግሞ ተቃዋሚ ይሆናል እና ንግግሩ ህዝብን ያነቃቃብናል የምትሉትን ሰው፤  የወንጀል ድርጊት ሲፈጸምበት ጸጥታ አስከባሪ ሊያገኝ ቀርቶ፤ ጭራሽ ጸጥታውም አብሮ ተባባሪ ሆኖ ያሸዋል፡፡ እንግዲህ በጠራራ ጸሀይ ወንጀል ሲፈጸምበት እጅ በእጅ እየታዬ እርዳታ ቢጠየቅም የቁራ መጮሕ ይሆናል፡፡ ይህ አይምሮን የምታዛቡበት መንገድ ምን ያህል እንደሚጎዳችሁ እንኩዋን መገንዘብ አልቻላችሁም፡፡ እኝም እንዲህ አላደረግንም ብትሉም፤ የሚከወንበትን ፍጡር ግን የውሻችሁን ያህል አልቆጠራችሁትም፡፡

 በእውነት አይምሮ የእግዚአብሄር እንጂ የሰው ስላልሆነ፤ ሀሳብስ ከየት ይፈልቃል፤ ብላችሁ እንኩዋን እግዚአብሄርን ማስታወስ አልቻላችሁም፡፡ ሳኦል፤ አምባገነንነቱ አይሎ እግዚአብሄር የሰጠውን እረዳት ዳዊትን እንኩዋን ያሳድደው ነበር፡፡  ኢሕአዴግ አስተዳደሩን የሚቃወመውን ህዝብ፤ ወኪል እንዲያጣ ለማድረግ የሚያደርገው ጥረት እጅግ አሳፋሪ እና፤ በልማትም ልንረዳችው ያልነውን ሁሉ ያሸማቀቀ መሆኑን እንድትመለከቱት ያሻል፡፡ ጀመርነው ወይም እኛ ነን አስተማሪው የምትሉለትን ዲሞክራሲን የዝናብ ጸሀይ አድርጋችሁ፤ ብልጭ ድርግም ስታደርጉት መቆየታችሁ አልክደውም፡፡ ዲሞክራሲ አለ ብዬ እዛው ኢትዮጲያ ነበርኩእና አካሄዱን ሁሉ አይቸዋለሁ፡፡  ዛሬ ደግሞ፤ ወሰን ተሻግራችሁ እሰው አገር ሰው ጋር አብራችሁ አድማችሁ በትውልድ ኢትዮጲያዊ፤ በዜግነት እንግሊዛዊ የሆነውን ሰው አፍናችሁ እስር ቤት ከታችሁታል፡፡ የት እንዳለእና ደግሞም ያም የወሰናችሁበት ግድያ ይፈጸም እንደሆነም ሰብአዊነት ያለው ኢትዮጲያዊም የሆነ ወይም የሰብአዊ መብት ተሙዋጋች እና ስብእና ያተላበሰው ደጋፊዎቻቸው፤ አፍጥጠው በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡  አንድ ነገር ልበል፡፡

ምንም እንኩዋን አገርቤትም መመላለሱ፤ ልማት ሳይሆን፤ ልማት የሚደግፈው መንግስት እራሱ ኢሕአዴግ በጥርጣሬ እያዬ ህይወትን ከንቱ ያደረገብን ሰዎች ብንኖርም፤ ሌላውም የኢሕአዴግ ተቃዋሚ ወይም ነገሩን እያየውም ግራ የገባው፤ አምባገነን መንግስትን ደግፋችሁ እየተባልን ብንሰደብም የልማቱ ተጋሪ ለመሆን ወደሁዋላ ያላልን እንደነበር ልታውቁት ይገባል፡፡  ዛሬ የደረስኩበት ደረጃ ግን ባለፈው ዲሞክራሲ አለ እያልኩ የተመላላስኩበት የኢህአዴግ መንግስት እንድሸማቀቅ እና እንዳፍር ከነአካቴው አድርጎኛል፡፡ ምክናያቱም፤ ህዝብ በትክክል ግብር እንዲያስገባ እና የቫት ስርአትንም ጥቅም ለኢትዮጲያ እድገት አስፈላጊ መሆኑንም እና እንዲተገብረው ተናግሬአለሁ እና፡፡ ዛሬ ግን ግብር የሚገባው ለአንድ ፓርቲ መፈንጫ እየሆነብኝ መጥቶአል፡፡ ለነገሩ ጠቀስ ባደርገው፤ ዲሞክራሲ አለ ካለ፤ ለተቃዋሚም መንቀሳቀሻ እኮ የግድም አስፈላጊ ነው፡፡እንግዲህ ኢሕአዴጎች ከነእንግሊዝ ጋር እራሱን አወዳድሮአል እና፡፡ ኢህአዴግ ግን፤ ለየትኛው ተቃዋሚ ክፍል ነው ከከፈልነው ግብር የምትሰጣቸው  ብዬ ብጠይቅ ደስ ባለኝ ነበር፡፡ የለም አሁን አሁን ሳስበው፤ ግብር የምንከፍለው ለአንድ ፓርቲ ብቻ መገልገያ ከሆነ፤ እውን የኢትዮጲያ ህዝብ አገር ገብተን የምንቀሳቀሰውን፤ ኢንቬስት የምናደርገውን፤ ዲሞክራሲ አለ ብለን እየተመላለስን እየመሰከርን ያለነውን፤ ቢጠላን ትክክል ነው ለማለት የምደርስበት ደረጃ ላይ ደርሻለሁ፡፡ ተቃዋሚ ሳልሆን፤  ዲሞክራሲን በመናገሬ  ሰብአዊ መብቴንም  የተነፈኩበት አጋጣሚ በኢትዮጲያ ውስጥ ተለማምጃለሁ፡፡ አዎ ዲሞክራሲ የለም፡፡ ተጀመረ ያልነው በዳዴ እንኩዋን ሲሄድ የነበረው፤ ከነአካቴው ተመቶ መሬት ላይ ተዘርሮ ሞቶአል፡፡  የፈለገ ነብይ ይመስክርለት፤ የፈለገ የውጭ አገር ለኢሕአዴግ ይመስክርለት፤ ግን አንድ የኢትዮጲያ ህዝብ የሚያውቀው ሀቅ ዛሬ ተፈጥሮአል፡፡ ኢትዮጲያውያኖች ከውጭም አገር እየታፈኑ እየተወሰዱ ነው፡፡ የሚታፈኑትም ለ23 አመት ያለማቁዋረጥ ኢትዮጲን የሚገዛው፤ በመሳሪያ ሀይል ደርግን ጥሎ ዙፋን የጨበጠውን ወያኔ ኢሕአዴግ የሚባለውን የፖለቲካ ፓርቲ የሚቃወሙት ናቸው፡፡ ስንት ናቸው ቢባል፤ ሁሉም ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው፡፡ እኛን ኢሕአዴግ አልነካንም የሚል ካለ አቤት ማለት ይችላል፡፡ እነዚህ ሰዎች   አለም እንዳወጀው አይነት ሽብርተኞች አይደሉም፡፡ ከሁሉም የኢትዮጲያ ዘር እየታፈኑ እንደሚመለሱ በገተቃዋሚዎች ሲነገር አላምንም ነበር፡፡ ኢህአዴግን እንዲጠላ የሚያደርግ የተቃዋሚ ወሬ መስለኝ ነበር፡፡ ዛሬ ግን ከተቃዋሚዎች የምሰማው፤ በምእራቡ አለምም መታወጅ የጀመረው፤ አንድ የበላይነትን የተቀናጀ ፖለቲካ ፓርቲ ተቃዋሚውን ለማፈን ሽብርተኛ የሚለውን ቃል ይጠቀማል የሚል ነው፡፡ ከአገሩ የተባረረውንም ስደተኛ በአለም እንዳይኖር ለማድረግ ይጥራል ተባለ፡፡  እንዳውም፤ የሞት ፍርድንም ሀሰት እና አዳፍኔ አድሎ በሚደረግበት ኢትዮጲያ እውን ላመድረግ የሚሩዋሩዋጥ ስልጣን የጠማው ማለት ጀመሩ፡፡ አቶ አንዳርጋቸው በሚባለው የነጻነት ታጋይ እያንዳንዳችንን ምን እያደረግን እንዳለን፤ ለውነትስ እየተሙዋገትን እንደሆነ አይናችንን ከፍተን እንድናይ ሀ ብሎ ምእራፍ ከፋች ሆኖአል፡፡ እስከዛሬ ተቃዋሚ ሲጮህ፤ ዲሞክራሲ አለ ብሎ፤ ከደርግ በሁዋላ ምንም ስለኢትዮጲያ ለመስማት ጆሮውን የዘጋው አለም ዛሬ ይኮረኩረው ጀመር፡፡ 
 እንግሊዝስ ይህንን የመን የሰራችውን ስራ ትደግፋለች? አትደግፍም፡፡ የመን እና ምእራቡ አለም እኮ የከረረ ቂም አላቸው፡፡ ያ ብቻ አይደለም ምንአልባት ለታይታ ሊመስል ይችላል፡፡ ዛሬ ብትወድ ነገ የሚነሳባት አቁዋም የለሽዋ የመን፤ ውሎ አድሮ ተጠያቂነቱዋ አይቀርም፡፡ ምእራቡ አለም ቸኩሉ የሚሰራ አይደለም፡፡ ለአንዳልካቸውም ብቻ ሳይሆን ለሚጠይቁዋቸው ዜጎቻቸው፤ ለሰብአዊ መብት ሲሉ፡፡ ሰብአዊ መብት እኮ ብዙ ሚሊዮን ደጋፊ ህዝብ ያለው ድርጅት ነው፡፡ትክክል እንዲሰራ ደጋፊው ግፊት ያደርጋል፡፡ ደግሞ ሰብአዊ መብት ፖለቲከኞችንም ምርጫ ላይ ፈተና እንዲመጣባቸው ያደርጋል፡፡ ለምን ቢባል እሱ የሚጽፈው ሪፖርት በመራጩ ሕዝብ ይነበባል እና፡፡ ስለዚህ የእንግሊዝ መንግስት የሰበአዊ መብትን ጥሰት ይቃወማል፡፡ ምንአልባት ቸኩሎ እርምጃ ባይወስድም፤ ለኢሕአዴግ ግን አንድ ቀን ለፍርድ እሱን ለማቅረብ አንዱእና ትልቁ ነጥብ ይሆንበታል፡፡ ደግሞም የእንግሊዝ አገር በኢትዮጲያ ለምታደርገው የማንኛውም ልማት እንቅስቃሴ የሰብአዊ እርዳታ ከህዝብ ለማግኘት ፈታኝ ይሆንባታል፡፡ ምክናያቱም የምእራቡ አለም የሚያደርገው በአፍሪካ እርዳታ በህዝቡ ድሮም ጥያቄ አለው፡፡ ትክክል ሰው ያገኘዋል? እርዳታስ የሚሰጠው አገር ሕዝብ አስተዳደሩ በአምባገነን የተያዘ ነው? ብር ወደውጭ አውጥተው የሚያስቀምጡ መሪዎችን አትተባበሩም ሌላው ድብቅ ወቀሳ ነው፡፡ የዛሬው ሃይጃክ ግን ለሁሉም ጥያቄ አውንታዊ ነገር ሊፈጥር የችላል፡፡  እኔ ምንም እንኩዋን የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ባልሆንም፤ ግን ተቃዋሚ መገኘት መንቀሳቀስ ያለበት አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ስለወደደ ሳይሆን ግድ ስለሆነ ነው፡፡  ግልጽ ላድርገው፤  ያለውን መንግስት የአስተዳደር ብሉሽነት የሚቃወመው የሕዝብ ክፍል ተቃዋሚን ይፈልጋል፡፡ ተቃዋሚው በብልሹ አስተዳደደር ለተንገላታው፤ ለሚሰደደው፤ በሙስና፣ በበላይነት፣ በማንአለብኝነት፤ በሀሰተኛ ፍርድ፤ በኑሮው ውድነት የተንገላታ ህዝብም የሚፈልገውም አካል ነው፡፡ የደላውም ምንአልባት የሞቀው ጎጆው ሰብአዊነትን ካዘናጋው እና ለግፍ ጆሮውን ከደፈነ፡፡ በቃ ይህ ስለሆነ ተቃዋሚ ፓርቲ መታሰር መሰደድ መገደልም የለባቸውም፡፡ ዲሞክራሲእና መብትን አካሄዱን እንወቅ እንረዳ ካልን እነሆኝ ኢሕአዴግ ብያለሁ፡፡ በቸር ኑ የምላችሁ፤ አንዲት በሰብአዊነት ላይ ያገባኛል የምል  ባዩሽ አበበ ነኝ፡፡

Freitag, 11. Juli 2014

የትጥቅ ትግልን የወለደው የኢሕአዴግ አምባገነንነት ነው፡፡



የትጥቅ ትግልን የወለደው የኢሕአዴግ አምባገነንነት ነው፡፡
  
ይቅርታ ይደረግልኝ እና፤ ግንቦት 7 የሚባለውን ድርጅት በኤርትራ በኩል ትጥቅ ትግል ስለጀመረ፤ አቶ ኢሳያስ አፈወርቄ ፈቅደውለታል እና ከሽብርተኛ ከአቶ ኢሳያስ አፈወርቄ ጋር ተግባብተዋል እና ሽብርተኛ ነው የሚለውን እኔ አልስማማም ምክናያቱም፤ ድሮም የኢትዮጲያ መንግስት የነበረው ደርግ ከኢሳያስ አፈወርቄ ጋር ሲዋጋ የነበረ ጊዜ ኢሕአዴግም ደርግን የጣለው እና ስልጣን ያገኘው ሻቢያ ጋር ለዛውም አቶ ኢሳያስ አፈወርቄ  ጋር ተስማምተው ነው፡፡ ዛሬ እንደቻይና እቃ ተጠቅሞ መጣል ቢሆንም፤  ስለዚህ ይህ ያለ ነው፤ ኢትዮጲያ ውስጥ አልለቅም ስልጣንም አላጋራም ላለ   በዛ በኩል ሁልግዜ በር እና ቦታ ማገኘቱ የተለመደ ስለሆነ፡፡ ለምሳሌ ዛሬም ቢሆን ኢሕአዴግ የመንን ተጠቅሞ ተቃዋሚያቸውን አቶ አንዳርጋቸውን አፍኖ ወስዶአል፡፡ አቶ አንዳርጋቸው የታወቁ ባይሆኑ ኖሮ ይህም ባልታወቅ ነበር፡፡ ስለዚህ ግንቦት 7ን የጀመረውን የትጥቅ ትግል በእጅጉ ያሳሰበኝ የነበረ ቢሆንም እና ደግፌው ባላውቅም፤ እሳት ካየው ምን ለየው እንደሚባለው፤ ኢሕአዴግ መረብ ተሻግሮ፤ ምንም ትጥቅ ወይም አጃቢ ያልያዘውን ሰው ማርኮአል፡፡ በዚህም የተነሳ እኔ ግንቦት 7ን ሽብርተኛ ነው አልልም፡፡ ከሆነ ሁሉም ከሻቢያ ጋር የሰራ ሁሉ ሽብርተኛ ነው፡፡ አልያም ሌላ አጥጋቢ ምክናት ካለ ብሰማ በሽብርተኛ አባባል ለመፍረድ ይመቸኛል፡፡  ምንአልባት ለእኛ ለሕዝብ የተሰወረ ሌላ ችግር ካለ ማለገቴ ነው፡፡ በሌላ መልኩ የኢሕአዴግ ከተቃዋሚ ጋር ለመካፈል ወይም አብሮ ለመስራት ፍቃድኛ ባለመሆኑ ይህ ተመሳሳይ ነገር ማለትም የትጥቅም ትግል እንዲፈጠር ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ የትጥቅ ትግልን የወለደው   የኢሕአዴግ አምባገነንነት ነው፡፡ በአገሩ ውስጥ ወይም በፓርላማ ውስጥ ተቃዋሚ ቢኖር ኖሮ እውነት የእነሱም ግንቦት 7ን ወንጀለኛ ወይም ሽብርተኛ መሆን አብረው በፈረሙእና በነገሩን ነበር፡፡ ግን አንድ ሰው ብቻ ተቃዋሚ ሆኖ በተቀመጠበት ቦታ ይህን አይነት ውሳኔ ሰውን ከማስፈራሪያነት እና ከማባረር፤ ሰው ፖለቲካን እንዲሸሽ  እና ተቀናቃኝ እንዳይኖር፤ ብቸኛ ገዢ ለመሆን ከመርዳት ውጪ ሌላ የሚያመጣው ፋይዳ የለም፡፡ ኢህአዴግ በአገሩ ተቃዋሚ አለ ካለ፤ ከእነሱ ጋር ሆኖ ተስማምቶ ማን ሽብርተኛ ማን ደህና እንደሆነ ቢያስረዳን ምልካም ነው፡፡ ካልሆነ አንድ ፓርቲ ብቻ በአገሩ ውስጥ የሚናገረው ንግግር የሚየሳልፈው ውሳኔ ኢትዮጲያን የሚወክል ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡ ችግሩ እዚያ ላይ ነው፡፡ ስለዚህ አገር ውስጥ አለን የሚሉ ተቃዋሚዎች ደግሞ ሁልግዜ ስሞታ እያወሩ የህዝቡን ሁኔታ በአጉል ተስፋ ጉጉት ውስጥ ከሚጥሉን፤ አንድ ቁርጥ ያለ ነገር ቢነግሩን መልካም ነው፡፡ ኢህአዴግ ዲሞክራቲክ  ነው  ፈቅዶልናል ካሉ ለምን እንደሚያማርሩ አይገባኝም፡፡ ማማረራቸውም የማይፈታ እንዲህ አውንደሚሉን የሚንገላታ  ከሆነ፤ ለምን  ፓርቲ ጸ/ቤታችውን ከነአካቴው ዲሞክራቲ የለም ብለው እንደማይዘጉ አይገባኝም፡፡   ምክናያቱም በኢህአዴግ ላይ የምንሰማው እረፍት የሚነሳ በመሆኑ፡፡ የምንሰማው ሁል ነገር እጅ እጅ የሚል ሆኖአል፡፡ ወጣቱም በእስር እና በስደት በፍርሃት እና በድፍረት አይሰቃይ፡፡ ተቃዋሚም ፓርቲ ከለለ አርፎ ይቀመጣል፡፡ እኔ ወያኔ ኢሕአዴግን ኢትዮጲያዊ አይደለም አልልም፡፡ ግን የምለው ዲሞክራሲን መተግበር ያቃተው ወይም የማያውቅ ነው፡፡  እና በስልጣን ከተወሰነ በላይ መቆየቱም እና ተቃዋሚን ያለመቀበሉ ጉዳይ ህዝቡን ወደትጥቅ ትግል እየመራው የሚገኝ ማንአለብኝ ያለ ሆኖአል፡፡ ስለዚህ የትጥቅ ትግል ማንኛውንም መንግስት ነኝ የሚለውን የደፈረ ይሆናል፤ መሰቃየቱም እንደማይቀር፤ በእራሳቸው የትግል ዘመን አይተውታል፡፡ ሁሉም እጅ እጅ የሚል የሚመር እና የሚያሳፍር በመሆኑ፤ ሁሉንም  ተቃዋሚ የተባለውን ሁሉ እየወነጀሉ ከመስመር እንዲወጣ መገፋፋት ለእኛ ለህዝብ እይታ የሚመች ወይም የተረጋጋ አለመሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ አለም ሁሉ ኢሕአዴግን ዲሞክራቲክ ነው ብሎ አቅፎ ደግፎ ይዞታል፡፡ ስለዚህ ግንቦት 7 በመሳሪ ትግል ሲጀምር ግን ደግሞ ሰላማዊ የሚባሉት ፓርቲዎች የፖለቲካ አክቲቪስት እንጂ እንደፓርቲ ሆነው መታየት እስከሚያቅታቸው እያየን ነው፡፡ ስለዚህ ትግላቸውን ጥርት እያደረጉ ቢሄዱ መልካም ነው፡፡ እስካሁን ይታሰራል ይፈታል፡፡ ወይም ኢሕአዴግን ፍቀዱለት እና ብቻውን እንደፈለገ ያድርገው፡፡ እጣ የወጣለት ይብላ ያልወጣለት ያልቅስ፡፡ ለነገሩ የትጥቅ ትግል የተጀመረው በወራት እድሜ መሰለኝ፤ ግንቦት 7ን ማለቴ ነው፡፡ ስለዚህ እነሱ አዲስ አበባ እስከሚመጡ ድረስ ሌላ ሃያ አመት ኢሕአዴግ ለመቆየት እድሉ አለው፡፡  የታሰሩትን ይፈታል ስንል ሌላ ይጨምራል፡፡ ስለዚህ ኢሕአዴግ ጋር ጨዋታውን መቀየር ያዋጣ ይሆናል እንጂ በተያዘው መንገድ ሁሉ ወይ ፍንክች፡፡ ለነገሩ ሽብርተኛ መቼም እንግሊዝ አገር ወይም አሜሪካ አገር አይቀመጥም፡፡ ስለ አቶ አንዳርጋቸው ማሻሻያ ክስ ይቅረብ፡፡ ይቅርታ በነጻነት ሀሳቤን እንድሰጥ  እንድናገር ከተፈቀደልኝ፡፡  አቶ መለስም „እኛ በመሳሪያ ትግል ነው እዚህ የደረስነው፣ የፈለገ ይታገል “ ብለው በር የከፈቱ እራሳቸው ናቸው፡፡ ካልተፈቀደም ይቅርታ፤ መቼም ከተናገርኩትም በሁዋላ ቢሆን፡፡ እኔንም ሽብርተኛ እንዳትሉኝ አስመራ ገና አልሄድኩም፡፡  በቸር ባዩሽ