Sonntag, 8. Februar 2015

ስደት እና አደጋው በዲሞከውራሲው አለም



ስደት እና አደጋው በዲሞከውራሲው አለም

       ደርግ 60  ሚኒስተሮችን ከረሸነ በሁዋላ ነው ከኢትዮጲያ የወጣሁት፡፡ ቀይ ሽብር የሚባለው ሽብር አልተጀመረም ነበር፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሬ የተሰደድኩ ቢሆንም፤ አገሬ ግን ገብቼ ለመኖር ዘወትር ሞክሬአለሁ፤ ግን አለቻልኩም፡፡ ይሁን እና ግን ከመጀመሪያው ስደቴ ጀምሮ እና አሁንም የተደጋገመው ስደቴ ድረስ፤ እኔ ሀይም የሚባል የስደተኛ ቤት ውስጥ ኑሬ አላውቅም፡፡ በውነትም እዛ የሚኖርም የማቀው ስለለለኝ ሀይም የሚባለውን አይቸው አላውቅም፡፡ እኔ በስደት ዘመኔ ሁሉ፤ በስደት አገር የኢኮኖሚ ችግርን አላውቅም፡፡ ይህን ስላችሁ ግን ደግሞ ሚሌኒየር እንዳታደርጉኝ፡፡ በዚህም የተነሳ ሁልግዜ ጠንካራ የፖለቲካ ሲስተም ያላቸውን እንደጀርምን አይነት አገሮች አገሬን ሳስብ መቼ እንዲህ ትሆን ይሆን ብዬ ውስጤ በቅናት እቃጠላለሁ፡፡ ጥሩ ሲስተም የማያስርብ የማያስጠማ፤ ማያስቀና ምን ያስቀናል፡፡ የራበውን በረንዳ ጻሀይ እና ዝናብ የሚፈራረቅበትን በአገሬ አይቻለሁ እና፡፡ ልንናገረው ያልደፈርነው ግን በውስጣችን የደበቅነው ሀቅ፡፡ ሌላው ከመጠን ያለፈ ሲበላ ብዙሀኑ ደረቅ ዳቦ ያረረበት አገር፡፡ በውነቱ ማንም ሰው በዘመኔ ለእርሃብ እና ለመታረዝ ለመጠለያ እጦት ተዳርጎ በኢይሮፕ አይቼ አላውቅም፡፡ ማንም የውጭ አገር ዜጋም ቢሆን ፤ሰው ጀርመን እግሩ እስከተረገጠ ድረስ ምግብ የመመገብ፤ የመጠለያ እጦት፤ መታረዝ የለም፡፡
 
         ለዚህ የፖለቲካ ስርአት ወይም ሲስተም የፖለቲከኞች ብርታት ሳይሆን የሕዝቡ ያለሰለሰ ትግል እና ንቃት ነው፡፡ ጀርመን ውስጥ ሕዝብ ሁልግዜ ሰላማዊ ሰልፍ በመውጣት ነገሮች እንዲታረሙ፤ እንዲወሰኑ እና ፖለቲከኞች ማድረግ ያለባቸውን ነገር መመሪያ የሚሆን አቤቱታ ከማሰማት እና ከማስታወስ ቦዝነው አያውቁም፡፡ ይህ የህዝብ ሰላማዊ ሰልፍ ደግሞ ጠቅላላ በፖለቲከኞች አጥብቆ የሚደገፍ፤ እንዳውም በአንዳንድ ሕግ ድንጋጌ ላይ ህዝቡ አስተያየቱን ደግፎም ሆነ ተቃውሞ እንዲያሰማ ፖለቲከኞች ያለሰለሰ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ እዚሕ አገር ተቃዋሚውም ሆነ ደጋፊውም አውቃለሁ ብሎ ፉክክር የገባ ሳይሆን እንወቅ ብሎ የሚሰራ አይምሮ የያዘ ህብረተሰብ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ የማንኛውም የፖለቲከኛ አስተያየት የሚገለል አይደለም፡፡ ዞሮ ዞሮ ህዝቡ ነው መጨረሻው እና መደምደሚያው ያለው፡፡ ነገሮች የሚወሰኑት በድምጽ ምርጫ ነውእና፡፡ እንደእኛ አገር ሰውን ማጥቃት ሲፈለግ ሌሊቱን በተዘጋ ቤት ህግ ደንግጎ የሚያድር የፖለቲካ አመለካከት ያለው የለም፡፡ ቢኖር ሕዝብ ብሎ እንደሚወጣ የታወቀ ነው፡፡ አዎ ነጮች 3ግሩ ቢኖር ለአመጽ ወደሁዋላ አይሉም፡፡ በዚህም ነው ሕዝብ ይከበራል ይፈራል፡፡ ደግሞም የሚደርሱበት ታላቅ የፖለቲካ ደረጃ ላይ እኩል የሚያበላ የሚያጠጣ እድርገውታል፡፡ ይህ የማንክደው የማንደብቀው ሀቅ ነው፡፡ ሆዴም ሞላ ብሎ ከሰኞ እስከሰኞ የሚዝናና አይደለም፡፡

      ይህንን ካልኩኝ ዘንዳ፤ ሰሞኑን በጀርመን ስደተኛው በዝቶአል የሚለው ክፍል ከቀን ወደቀን እየጨመረ እየሄደ ነው፡፡ ይሁን እና ግን፤ ይህንን በሰላማዊ ሰልፍ መንግስታቸውን መጠየቅ ጤነኛ ቢሆንም፤ ይህንን ጤነኛ መልኩን ሊስጥ ይችላል ተብሎ የተፈራበት ነገር አለ፡፡ ምክናያቱም አዲስ ናዚ የሚባሉት የሒትለር ተከታዮች የውጭ አገር ዜጋውን ለማባረር አልያም ለአደጋ የሚያጋልጥ ጤነኛ ጥያቄ የሚያቀርቡት ጋር በመቀላቀል ቁጥሩን በማብዛት ወደሁከት ወይም ወደተናዳጅነት እንዳይሄድ ስጋት የፈጠረ ሆኖአል፡፡ ይህ ለሁለት የከፈለው የስደተኞች ብዛት ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ሊደርስ የቻለው ሕዝቡ ፖለቲከኞችን ምንድን ነው እያደረጋችሁት ያላችሁት የሚለው ጥያቄ ምላሽ ቶሎ ምላሽ ባለማግኘቱ ነው፡፡ ህዝብ ሰላማዊ ሰልፍ ካደረገ አዎ ምላሽ ይፈልጋል፡፡ ይሁን እና ስደተኛውንም የማይቃወም አካል ስላለ ፖለቲከኞች በማስተዋል ሊሰሩ ግዴታቸው ነው፡፡

            ከቀን ወደቀን በአለም ላይ የሚደረገውም በምእራቡ አለም ላይ ያተኮረው የሽብር ጥቃት የሚባለው ስጋት ያሳደረበት ክፍል ቢፈጠርም፤ ግና አንዳንድ በዘረኝነት ሰልፍ የሚኖሩትን ለሰበካቸው የተመቸ ጊዜ እና አጋጣሚ ሆኖላቸው የቁዋመጡ ይመስላሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ቅልጥ ያለ ጥላቻ በአይሁድ ዘሮች ላይ ያተኮሩ የነበረ ቢሆንም በዛሬው ሁኔታ ደግሞ አረብ አልያም ሙስሊም የሚባል በሽብር ስም ፈርጀው፤ ከአገር እንዲወጡላቸው ያለሰለሰ አቤቱታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ስደተኛውን የሚጠላ  ክፍል እየተፈጠረ በመምጣቱ አገራችንን ለሙስሊም አሳልፋችሁ ልትሰጡ ነውእን በማለት ስደተኛው ከአገራቸው እንዲወጣላቸው በመማጸን ላይ ይገኛሉ፡፡ በውነቱ ሙስሊም እያለ አንዳንዱ ለማስመሰል ይፈልጋል እንጂ ጥላቻው ሁሉም ማንንም የሚለይ ሊሆን እንደማይችል ውስጥ ያውቀዋል፡፡ ብዙውን ግዜ የውጭ አገር ዜጋ ያው ነው፡፡ ነገሩ ብዛቱ አስግቶአቸዋል፤ አረቡ እና አፍሪካው ግልብጥ ብሎ ወደኢሮፕ እየፈለሰ ነውእና፡፡ ምንም እንኩዋን ስደተኛውን የማይቃወምም ክፍል ቀላል ባይሆንም፤ ስደተኛውን የሚቃወመው ብዙውን ግዜ ተናዳጅ ስለሚሆን፤ ምንግዜም የተናደደው ክፍል አስፈሪ እየሆነ እንደሚሄድ አይካድም፡፡ ስደተኛውን የማይቃወመው ክፍል የተረጋጋ  ለዘብ ያለ እና በማስተዋል የሚጉዋዝ አልያም በእምነቱ ጠበቅ ያደረገ በመሆኑ በሚቃወመው አካል ላይ ተናዳጅ በመሆን አደጋ የሚያደርስ አይደለም፡፡ ይህን ያሰጋው የጀርመን ፖለቲከኞች ህዝብን በማረጋጋት እና የፖለቲካውንም ሁኔታ በመመልከት በመስራት ላይ መሆናቸው የሰሙኑ ሰላማዊ ሰልፎች እንደሚነግሩን ግድ ነው፡፡ በጀርመን ማንኛውም ሰላማዊ ሰልፍ አዳማጭ እና መልስ ሰጪም አካል አለውእና፡፡

      ዛሬ ዛሬ ከሕዝቡ መካከል የሚወጣው የፖለቲካ ወሬ፤ እርግጥስ ስደተኛው የውነት የፖለቲካ ስደተኛ ነውእን? በማለት ማሰብ እና የስድተኛውን የፖለቲካ እይታእና ግንዛቤ እንደገና መመዘን ጀምረዋል፡፡ ለምሳሌ የፖለቲካ ስደተኛ ጥረት ማድረግ የሚገባው አገሩ ለመመለስ መታገል ሆኖ ሳለ፤ ስደተኛው ግን የፖለቲካው ተሳትፎም ምንም የማይታይ በመሆኑ እና ዝምብሎ ማተርያልን እና ምቾትን የሚፈልግ በመሆኑ ልባዊ ቅናትንም ይፈጥራል እና፡፡ ብዙውን ግዜ ስደተኛው እዚህ ከመጣ በሁዋላ፤ በተለይ ከአፍሪካ የሚመጣው ውድ የሆነ ልብስ/ ብዙውን ግዜ በዛሬው ሰአት እንኩዋን ጀርመኖች እራሳቸው መልበስ ያልቻሉትን/ ገዝቶ በመልበስ፤ በውድ የሚሸጠውን የሰው ጸጉር በመግዛት ጸጉራቸውን በመቀጠል እና ልክ የኢይሮፕን ስታይል በመከተል የሚያያቸው፤ በኢኮኖሚ ቀውስ የሚታመሰውን ወይም የሰጋውን ህዝብ ያስደስተዋል ማለት ዘበት ነው፡፡  የዛሬው ስደተኛ አካሉ ላይ እንጂ አይምሮው ላይ ኢንቬስት ሲያደርግ ባለመታየቱ አገርም መመለስ እንዳለ ዘንግተዋል እና ጠባቡዋ ኢይሮፕ ስንት ሰው መሸከም ትችላለች የሚለው በስደተኛው ላይ ጥላቻን ሊያባብስ ይችላል፡፡ ወሰኑን ከፍቶ የለቀቀው የዛሬው የአለም ፖለቲካ ለብዙ ሰው የሚዋጥ አልሆነም፡፡ በዚሕ ላይ ትናንት ፈረንሳይ ውስጥ በመጽሄት አዘጋጆች ላይ የተደረገው 12 ሰዎች የገደለው ጥቃት ለስደተኛውም ቀላል አመለካከት እንደማይኖር እና በስደተኛው ላይ የሚደረገው ጥላቻ ይጨምራል ተብሎ በፖለቲከኞች እና ስደተኛውን የሚያዝንለት ክፍል ስጋት የፈጠረ የማይናቅ ጉዳይ ሆኖአል፡፡ ስደተኛው አገሩ ሆኖ ይታገል የሚለው ቁጥር እያመዘነ መሄዱም የቤት ለቤት ወሬ ሆኖአል፡፡ በሌላ መልኩ ስንት የደከሙበትን ለአገራቸው የተመቸውን ዲሞክራሲያቸውን ሁሉም ኢይሮፒያዊ ቢሆን እንዲበላሽበት አይፈልገውም፡፡ የዲሞክራሲው ስጋት ላይ መውደቅ ደግሞ ለመታደግ አሁንም ዳር አስከዳር አንድነታቸውን እንደሚያጠነክሩ ጥርጥር የለውም እና፤ ለስድተኛው ቀላል ጊዜ አይሆንም፡፡ ለሰውነት የሚቀርበው ከሸሚዝ ካኒተራ ነውእና፡፡ ባዩሽ ነኝ

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen