Mittwoch, 25. Februar 2015

ከከሳሽነት ወጥተን ወደእርምጃ እንሸጋገር



               ለዚህ ጽሁፌ መነሻ ያደረኩት „በአሰሪዎቾ የታገተችው ኢትዮጵያዊት የሰቆቃ ደምጽ“ !    የሚለውን የተለቀቀ አርቲክል ካነበብኩ በሁዋላ ነው፡፡ ይህንንም በፌስ ቡክ ድረገጼ አካፍያችሁዋለሁ፡፡ ማንበብ ትችላላችሁ፡፡ ሳነበው ነገሩ ውስጤን የመናደድም ሆነ የቁጭት ነገር ሲቀሰቅሰው ይሰማኛል፡፤ የዚህ አይነት ስሜት ውስጤን ሲረብሸው መጻፍ እመርጣለሁ፡፡ ልተኩስስ ብል የትኛው አካል ላይ በምንስ መሳሪያ፡፡ ብእርን የመረጥኩትም ለዚህ ነው፡፡ ብእርም ጥይት መስሎ ሌላ የሚደግንብህ እንደሚከፍት አውቃለሁ፡፡ ቢሆንም፤ ትእግስተኛው ነጭ ልሙጥ ወረቀት የማይቀበለው ነገር የለም እና የስሜቴ እና የቁጭቴ ተካፋይ ጉዋደኛ አድርጌዋለሁ፡፡ በአረብ አገር ታገተች የተባለችው ልጅ ብዙ ነገር እንዳይ አድርጎኛል፡፡ ሊረዳት የፈለገው አካልም ስሞታ በማሰማት ይመስላል፡፡ ግን ሰሚ በለለበት አለም ዋይታ ለምኑ ፡፡

                ይህንን ዜና ያስተላለፉት ልጆች ያለችበትን ካወቁ፤ ለምን ወደ ሰብአዊ ድርጅቶች አይሄዱም እና አይጠይቁላትም፡፡ የዚች ልጅ ዜና እንዲህ በይፋ ከታወቀ፤ ሴቶችንም ሊረዳ የሚችል የሆነ የግልም ድርጅት ቢሆን  በአረብ አገር አካባቢ ላይጠፋ ይችላል ብዬ እገምታለሁ፡፡ በዚህ ህገውጥ የሆነ የሰው ባርነት በየአለማቱ የቆሙ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ በአረብ አገርም ሁሉም ሰው አንድ አይነት የሆነ አረመኔአዊ ተግባር የሚያካሂድ አይደለም፡፡ በእርግጥ የቤት ሰራተኛ ጉልበት ብዝበዛ በአገራችንም ቢሆን ሲታይ ኖሮአል፡፡ ዛሬም ይታያል፡፡ የሰው ልጅ ሲባል ጉልበት እማይጠቅመው ነው፡፡ ስለዚህ እኔ በበኩሌ፤ አሁን ይህን አይነት ችግር ሊረዳ የሚችል ማነው የትስ ይገኛል ብለው እዛው አካባቢ ያሉት ኢትዮጲያውያኖች የሳውዲ አረቢያን ውስጡን መበርበር እና ማግኘት አለባቸው፡፡ እራሳቸውን ለመርዳት እና ለመታደግ ዘዴ መቀየስ ይገባቸዋል፡፡ ሌላው ቢቀር ህጋዊ የሆኑት ከፖለቲካ ውጭ የሆነ ማህበር በማቁዋቁዋም ከእራሳቸውም አልፈው ሌላውን መታደግ ይችላሉ፡፡ ከፖለቲካ ውጭ ያልኩበት ምክናያት፤ ገዢውም ተቃዋሚውም ይህንን የሰውልጅ ሰቆቃ የፖለቲካ ፍጆታ አድርገው፤ በፉክክር ማህበሩ እንዳይፈርስ ለማድረግ ነው፡፡ ሁሉንም ማህበር የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ካለው፤ ከእንግዲህ በሁዋላ ኢትዮጲያዊ በየትም አገር ቢሄድ ከመበደል የጸዳ አይሆንም፡፡ ስለዚህ ህብረተሰቡ ወይም ማህበረሰቡ የመጀመሪያውን ደረጃ ሰብአዊነትን ለማግኘት የምገምተው፤ ከማንኛውም ፖለቲካ የጸዳ የመረዳጃ ማህበር ማቁዋቁዋም ብቻ ነው፡፡ ዛሬ ብዙውን ግዜ የተላመድነው በደልን ማውራት እንጂ ከበደል እንዴት እንደምንወጣ ዘዴ መፈለግ ተስኖናል፡፡ ኢምባሲው አይረዳም ከተባለ ደግሞ ፤በቃ አለመርዳቱን ተቀብሎ ሌላ ዘዴ መቀየስ ነው፡፡  ሽ ግዜ ይህ ቢሰማ ዋጋ ቢስ ነው፡፡ እንዳውም ሲደጋገም የፖለቲካ ፍጆታ ሆኖ ይሰለቻል፡፡ ሰለኢህአዴግ ብዙ ሰምተናል፡፡ እስኪ ደግሞ እራሳችንን ማዳመጥ እንጀመር ባይ ነኝ፡፡ የኢህአዴግ አላደረገም የምንለው ነገር የተደጋገመ ሆነ፡፡

                  ዞሮ ዞሮ የመጀመሪያው አላማ መሆን ያለበት ስብእና ነው፡፡ መቀደም ያለበት፤ እነዚህ ሴት ልጆቻችን ወይም እህቶቻችሁ ከሚደርስባቸው የቁም እስር፤ የአይምሮ ቅጣት እንዲወጡ ማድረግ ነው የሰው ልጅ ተግባር መሆን ያለበት፡፡ ከአገር ያስወጣቸው የኦኮኖሚ ችግር ነው፡፡ ኢትዮጲያ ከአለም አንደኛ በመሆን ዘወትር የምትወሳ ደሃ አገር ነች፡፡ ይህ እንግዲህ ወደፊትም ለረጅም ግዜ ይቆያል፡፡ እራሳችንን መሸንገል የለብንም፡፡ ትልቁ ስህተት እራስን መዋሸት ነው፡፡ ለማንኛውም ነገር ሕግ አስፈላጊ ነው፡፡ አሁን የማየው ነገር ፤  ፖለቲከኞቻችን   እልክ እና ፍልሚያ ደግሞም ስም መጠፋፋት እንጂ ምንም አይነት የፖለቲካ ስራ በሁሉም አይታይም፡፡ ኢህአዴግም ባለው በእራሱ መንገድ ቀጥሎአል፡፡ ተስማማችሁ ወይሰ አልተስማማችሁ በማለት ህዝብንም አያማክርም፡፡ ይህም ሁኔታው ህዝብን ተስፋ እንዲቆርጥ እና እንደአለፈው ዘመን ተቃዋሚን ተስፋ በማድረግ  አልያም በቃ እንዲህ ከሆነ የእራሴን መንገድ ልጠቀም ያለ ይመስላል፡፡ ግማሹ በሙስና ለመክበር ሲጥር፤ ያልቻለው አገር ጥሎ እግር አውጪኝ ያለ ይመስላል፡፡ ይህ ፖለቲካ የፈጠረው መደነጋገር በየአቅጣጫውም የእሮሮ ድምጽ ይሰማል፡፡ ውጭ አገር እንደሎቶሪ የሚታይበት ባህል ያካበተችው ኢትዮጲያ፤ የቸገረውም ያልቸገረውም ፍርጣጭ ሆኖአል፡፡ አንዳንዱ ለዳቦ አንዳንዱ ውጭ አገርን ለጉራ ይጠቀምበት ይራወጣል፡፡ ያም ሆነ ይህ የፖለቲከኞቻችንን የጎሪጥ መተያየት እና የብሄር የሚለው አንዱ ገንቢ ሌላው ናጂ የሆነው የፖለቲካ አካሄያድ የኢትዮጲያን አቅጣጫውን ሊያስተው     ደርሶአል፡፡ ፖለቲከኞች ወደህዝብ ሳይሆን ወደእራሳቸው የግል አላማዬ የሚሉት ገብተው ይዳክሩ ይዘዋል፡፡ ይሳካላቸው አይሳካላቸው የሚለውን እኛም መመልከት ትተነዋል፡፡ እንደለሉ አድርጎ መኖርን መርጠናል፡፡ እራሳቸውን ማስተካከል ያቃታቸው እኛን ያስተካክሉናል ብሎ ተስፋ ማድረግን ከነአካቴው ገደል አፋፍ ላይ አቁመነዋል፡፡ የዚህ አይነት መደነጋገር ደግሞ፤  በእጅጉ ሰለባ ያደረገው ሴቶችን እና በአጠቃላይ ወጣት ስደተኞችን ነው፡፡ በቃ የኢትዮጲያ ወጣት አገር እንደለለው እየተደረገ በነቂስ እግር አውጭኝ ብሎ በሕገወጥ ደላሎች የተነሳ ስቃይ እየደረሰበት ነው፡፡

                 እንደእውነቱ ከሆነ በአረብ አገር እየተሰቃዩ ነው የሚባሉት ወጣቶች ጠላታቸው የቀጠራቸው አረቡ ሳይሆን የገዛ ወገናቸው በእራስ ወዳድነቱ፤ ኪስ ለማዳለብ ወይም ደግሞ መተዳደሪያው በማድረግ በጭፍን አሳልፎ የሰጣቸው ነው፡፡ ለበረሃ እራት ለአውሬ መጨዋቻ ያደረጋቸው፡፡  የአረብ አገር ሰራተኛ ሁሉም ባይሆኑ፤ ግን በእራሳቸው እጅ የከፈሉት ጠላት፡፡ እሱን ነበር ቀድሞ መምታት፡፡ ግደሉት ማለቴ አይደለም፡፡ ደግሞ ግድያ አወጀች እንዳትሉኝ፡፡ በቃ ወደፍርድ ቤት የሚቀርብበትን መንገድ ፤የከፈላችሁት ገንዘብ እንዲመለስ ማድረግ፤ ማሳሰር ማስፈርድ ነበር፡፡ ይህ ለጅብ እንዲሰጣችሁ በገዛ እጅ የከፈላችሁት ጋር ነው ቀድሞ መታገል፡፡ ሁልግዜ ትልቁ ችግራችን አጠገባችን ያለውን ጠላት ሳንቁዋቁዋም የውጩ ላይ የምናደርገው ትችት ነው፡፡ ለምሳሌ ብንወስድ፤ መነሻችን ወያኔ ተቃዋሚን ባንዳ ይላል፡፡ ተቃዋሚ ወያኔን ባንዳ ይላል፡፡ ሁልግዜ ውድቀትን ወደላሌ ማሸጋገር የለመድነው ይመሰላል፡፡ የውጭ የምንለውን ሸክም በማሸከም ከእራሳችን ውድቀት የምንሸሽ ብዬ እገምታለሁ፡፡ በቃ የቤታችንን አመል ወደሌላ ማላከክ፡፡ ይህ ሁሉ ነገር ወንጀለኛን እንዳናይ ያደርገናል፡፡  በሰራው ወንጀል እንዲጠየቅ ለማድረግ የምናደርገው እርብርብ የለም፡፡ ይህን ለምደነዋል፡፡ በቃ ኢሌጋልነት፤ እራስን ወዳድነት ፤ እና ሙስና አስተዳደሩ ብቻውን ሊያጠፋው የሚችል ነገር ከእንግዲህ ሊሆን አይችልም፡፡

                       ይህ በጨካኝ ሰዎች የሚደረግ እርምጃ ሊያቆመው የሚችለው ሕብረተሰቡ እራሱን በሰብአዊነት፣ በማህበር በመደራጀት፣ በግልጽነት  እና እራስን በእራስ የመርዳት ባህሪ ሲገነባ ነው፡፡ ዘወትር ከሌላ ይረዳናል ብለን የምንጠብቀው መጠበቅ ሰነፍ እና አልቃሻ ምስኪን ነው የሚያደርገን፡፡ ሰው አይምሮ አለው፡፡ ስለዚህ ዘወትር ከመንግስት ወይም ከዚህ ከዚያ እያልን መጠበቃችንን ማቆም እና እኛው እራሳችን ወደእርምጃ ለመግባት መማር መላመድ አለብን፡፡ ስለዚህ አረብ አገር ያሉ ወጣቶችን ሊረዳቸው የሚችል እራሳቸውን በእራሳቸው ማደራጀት እና ችግራቸውን ወደኢምባሲው ከማሸከም በእጃቸው ማድረግ እንጂ ሌላ አማራጭ የለም፡፡ ከሌላ መጠበቅ ቆማጣ የሚያደርግ የሕይወት ልምድ ያከናንባል፡፡ ለምሳሌ ገዢው ፓርቲ ላይ ሁሉንም አገር ውስጥ ያለውን ጥፋት ማሸከም፤ ባህሪያችንን እና የአስተሳሰብ ውድቀታችንን እንዳናይ ሲያደርግ፤ ተቃዋሚንም ብቻውን ወደስልጣን ይመጣል ብሎ ማሰብ፤ ሁሉም አልሸሹም ዘወር አሉ ይሆናል፡፡
ባዩሽ

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen