Freitag, 11. April 2014

የአይምሮ ችሎታ ከትምህር የማይገናኝበት



         የአይምሮ ችሎታ ከትምህር የማይገናኝበት

የፊውዳል ሰርአትን ለማምጣት አይደለም እኮ ሰው መታገል ያለበት፡፡ ጥቂት የተወሰኑ ሰዎችን ባለአባት አድርጎ እና ብዙሀኑን ባሪያ አድርጎ ያለፈውን ስርአት ለመገልሰስ ወጣቱም ሆነ ፖለቲከኞች ብዙ ተጋድሎ ማድረጋቸው የቅርብ እሩቅ ትዝታ ነው፡፡ እርግጥ ነው ጥለውታል፡፡ ግን ጥለውታል ማለት ሞቶአል ማለት አይደለም፡፡ ወድቆአል እና ሞቶአል ልዩነቱን ለእናንተ ልገልጽላችሁ አልችልም፡፡ አዎ ወድቆአል፡፡ ግን በማንኛውም ስርአት ውስጥ እየገባ ስራውን እየሰራ የሚገኝ  ነው፡፡ አሁንም ቢሆን በኢሕአዴግ የፖለቲካ ክስረት ያመጣው ይሕ የፊውዳሊዝም ሁኔታ በሕብረተሰባችን ውስጥ ከአይምሮ ስላልጠፋ ብቻ ነው፡፡  ለምሳሌ ጥቂት በኢሕአዴግ ጊዜ በተሳሳተ መንገድ የከበሩ ከበርቴዎችን ሰዎች እንደትክከለኛ አድርገው ወይም እንደሚበልጡዋቸው አድርገው በማየት የሚያደርጉት የእጅ መንሳት ሁኔታ እና ተመሳስሎ መኖርን የባላባትነት ስርአት ከሰው ልጅ አይምሮ ያለመጥፋቱ ጉዳይ ነው፡፡ አንዱን የበላይ አድርጎ ማየት እራስን ለባርነት አጋልጦ መስጠት ነው፡፡ እርግጥ ነው፡፡ የነበሩት ጥቂት ባላባቶች በዋናነት ተፈርዶባቸው በደርግ ግዜ ተገድለዋል፤ ንብረታቸው ተወርሶአል፤ ደግሞም አይሆኑ ሆነው እንዲወድቁ ተደርጎአል፡፡ እዚሕ ላይ ደርግ ያደረገው ስህተት ብንመለከት ትግሉ የነበረው እና ያነጣጠረው ከስርአቱ ጋር ሳይሆን ከሚሊዬን ሕዝብ ውስጥ በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች ብቻ ላይ ነበር፡፡ሚሊየኑ ህዝብ ላይ በአይምሮ ጥሎ የሄደውን ውስብስብ ነገር ሊያገናዝብ አልቻለም፡፡ እንግዲሕ ደርግ ቤት ቀምቶ ቤት ሰጥቶአል፡፡ ግን ደሃውም ሰርቶ ያገኘውም አብሮ ስለተቀማ የስርአቱን መውደቅ ሳይሆን የሚያመለክተው ባለሀብትን የሚያጠፋ፤ ሰርቶ ማገኘትን የሚቃወም ስርአትን አምጥቶ ተጨማሪ ቡቱቶ የሆነ ነገር ለጥፎአል፡፡ ወዳጆቼ እንግዲህ አልጠፋው ስርአት ላይ ሌላ ስርአት አምጥቶ ለጠፈ እንጂ ሌላ የሰራው ነገር የለም፡፡ ስርአት አይምሮን ተብትቦ የሚይዝ በቀላሉ ሊወጣ የማይችል ካንሰር ነው፡፡ ከተፈለገ ግን ይህ ካንሰር ወደትውልዱ እንዳይዛመት ማድረግ ይቻል ነበር፡፡ ግን በኢትዮጲያ መድሀኒት እንዲገኝለት ሀኪም አላገኘም፡፡  የደረግ ስርአት ለእኔ ሰው ሊያጠፋ የመጣ እንጂ ፊውዳሊዝምን ሊያጠፋ የመጣ አልነበረም፡፡ ይቅርታ ለአባባሌ፤  ለውጡ መሆን የሚገባው ቢሆንም፤ ቀዳሚው ትግል የፊውዳል ስርአት ከሕብረተሰብ አይምሮ ውስጥ እንዲወጣ ነበር እንጂ ሰው ወደመግደሉ መሆን ባልተገባው ነበር፡፡ ያልገባውን ሰው መግደል ምን ጥቅም አለው? አገሪቱን የትም ሊያደርሳት የማይችል በሰዎች አስተሳሰብ ውስጥ የባርነት እና   የነጻነትን  ስሜት  እያንጸባረቀ የሚኖር እና የመጥፎ ባህል ተገዢ አድርጎን የሚቀርውን ነበር መታገል የነበረብን፡፡ ከአይምሮው የባላባት ስርአት ያልጠፋበት ሕዝብ መካከል መሆን የሚገባውን የፖለቲካ ስራ መስራቱ ቀርቶ ደርግ ደሃን መብቱን የተሰጠው ሀብታምን መብቱን የነፈገው አስመስሎ የቀረበ አታላይ ስርአት ብየው ባልፍ አይገደኝም፡፡ ይህ በእጅ አዙር የሆነው ደርግ የደሀው ጌታ ሆኖ መቅረብን እና በሌላ መልኩ ሌላ ባላባትን ማዘጋጀት ነው፡፡  ይህ ግራ የሚያጋባ ነገርን መፍጠሩ አይካድም፡፡ ግን ባላባቶች አይሆኑ ሆኖ አወዳደቅ ቢወድቅም፤ ለዘመናት የኖረው ፊውዳሊዝም ግን ከሰው ልጅ አይምሮ እንዲለቅ የተደረገ ምንም አይነት ጥረት ባለመደረጉ ስርአቱ አሁንም ቢሆን ከልጅ ወደልጅ እየተላለፈ እንዱን ባለባት ሌላውን ባሪያ እያደረገው እያየን ነው፡፡ ከዘር ወደዘር የሚተላለፈውን የባላባትነት ሁኔታ ደርግ የተፈታተነውእና እንዲጠፋ ያደረገው መንገድ የማይካድ ቢሆንም፤ ግን ከሰው ልጅ አይምሮ ፍርሀት እስካልጠፋ ድረስ አዲስ ባላባት መመስረቱ እንደማይቀር ሀቅነቱን መጋፈጥ ነበረብን፡፡ የአይምሮ መለወጥ የሚያመጣው የባህሪን መለወጥ መሆን አለበት ብለን አንዳንዶች የምንለፈልፈው ወደን እንዳልሆነ መገንዘቡ መልካም ነው፡፡ በደርግ ግዜ የጎመጀውን ሁሉ ባላባት የሆነውን ሰው ጥሎ የተጠቀመም አልጠፋም፡፡ ለምሳሌ በገንዘብ መጉዋጉዋት ሳይሆን አባትየውን አስሮ ልጅቱን ማግባት አልያም አስገድዶ እንድታገባው ማድረግ እና ይህን መሰል ተልካሻ ነገር ይታይ ነበር፡፡ እንደእውነቱ ከሆነ የመሬት እንጂ የብር ከበርቴ ብዙም ስላልነበረእና የደርግም ሶሻሊዝም ወይም ኮሚኒዚም በሉት፤ በነበረው እንደዘመኑ የአለም መሰል አገሮች አስተሳሰብ የማተርያል ከበርቴ በደርግ ጊዜ ሊፈጥር የሚችል ሁኔታ አልነበረም፡፡ ስለዚህ ሲታይ የነበረው ብዙሃኑን መከላከያ ጦር ግንባር ላይ አጋፍጦ በሴት እና ለአይን በማይታየው የስጋዊ ደስታ በየከተማው መምቦጫረቅ ነበር፡፡ አስተያየቴን እዚህ የምሰጠው ከሌላ የተሻልኩ አስተሳሰብ አለኝ ብዬ ሳይሆን፤ የተሳሳተ ጎዳና ላይ ገብተን አገራችንን ወደሁዋላ እየጎተትናት እንዳንሄድ ስለሰጋሁ ነው፡፡ ስለዚህ ማንም ሰው ያገባኛል ብሎ ለሀገሩ ሲል አይምሮአችንን ተብትቦ ከያዘን መጥፎ ባህሪ ወይም ልምድ እንድንላቀቅ ጥረት ማድረግ አለብን ባይ ነኝ፡፡ የተሻለው ፖለቲካ ፓርቲ ይህ ነው  ብዬ አፌን ሞልቼ ለመናገር እንደእራሴ ይከብደኛል፡፡ ምክናያቱም ከአይምሮአችን ውስጥ የሚያቃጭል ግን ልናወጣው የማንችልበት ያለመለወጥ ሁኔታ ስላለ ነው፡፡ እንናገር ብንል ብዙዎች መናገር እንችል ይሆናል፡፡ ግን በውስጣችን ያለው የባላባትነት ስርአት ከውስጣችን አልወጣም፡፡ እንድናይ ተደርገን ያለፍነው ሁሉ የውጭን ጠላት እንደፈረንጅ ኮሎኒ አይነቱ ላይ እንድናተኩር እንጂ በእራሳችን መካከል ያለውን ጠላታችንን የሆነውን ያለመለወጥ ጉዳይ እንድናይ አይደለም፡፡  ዛሬም ለብዙ መቶ አመታት ያለፉብን አንድአይነት ስርአት ለጥቂት ሰዎች ማጎብደድ ሰዎቹም ቢቀየሩ የወረስነው ባህሪ ሊለቀን ባለመቻሉ በላይታችን ላይ አዲስ ባላባቶች ምንግዜም እየመሰረትን እንሄዳለን፡፡ ለምሳሌ ዛሬም የእነ እከሌ ዘር ነኝ ብሎ መኩራት፣ ወይም የከበርቴ ሰዎችን ጥግ መፈለግ፣ እንደምንም ተጋድሎ አድርጎ አላቸው የተባሉ ሰዎች ጋር መጋባት፣ ደግሞም ለቀበሌ ሹማምንቶች ጉቦ አቀባይ መሆን፣ ስላለው ብቻ ወሬ አዳናቂ መሆን እና በትልቁ ደግሞ ምንም ሳያደርጉን እነዚህን ሰዎች የመፍራት የመንቀጥቀጥ እና ከሚገባው በላይ የማክበር ጉዳይ የመጣው ጥሎ የሄደብን የበላይነት እና የበታችነት ስሜት ነው፡፡ ይህ ከአይምሮአችን ሊወጣ የማይችል ነው፡፡ በፖለቲካውም ውስጥ ያለው ችግር ይህ ነው፡፡ የመቃወሱን መሰረት አያውቁትም፤ የመረዳት አቅምም ሁሉም ያጡ ይመስላሉ አልያም እነሱም ያው ስለሆኑ ትልቅ የመሆን የበላይነት አስተሳሰብ አለቀቃቸውም፡፡ የሰው ልጅ ምን ያሕል ባህሪው አገሩን እንደሚሰባብረውእና ምን ያህል የአይምሮ አለመለወጥ የሚያመጣውን ቀውስ በተቻለ እንድንነጋገርበት እና አይናችንን እንድንከፍት ያሻናል፡፡ ዛሬም የተለወጠ ቢለወጥ አንዱ ባላባትነት ስሜት ገንብቶአል ሌላው ደግሞ የባርነት ስሜት ገንብቶአል፡፡ ይህ የአይምሮ አለመለወጥ ባርነትም ባላባትነትም በአይምሮአችን የምንገነባው እንጂ የለለ ነገር ነው አልፈልገውም አልቀበለውም ብሎ ወደዘመናዊነት መምጣት አልተቻለም፡፡ ለምሳሌ ሰው  ካለግሩፕ እና ካለሰብሳቢ የሚኖርበት ሁኔታ አይታይም፡፡ አሁን አሁን እያየሁ የመጣሁት፤ ሰው ባሪያእና ተገዢ ወደሚያደርገው አስተሳሰብ እራሱን እየጋበዘ መሆኑን ነው፡፡ ሰዎች በፈረንጅ አገር እንኩዋን እየኖሩ በየግሩፓቸው አንድ ባላባት አላቸው፡፡ አሳቀኝ በጣም፡፡ አንዱ እንደ በግ ሌላውን የሚነዳው ሁኔታ ነው ያለው፤ ለግለሰቡም አፍ እና ተሙዋጋች አድርገዋቸዋል፡፡ ይህን የምለው ግን ከፖለቲካ ውጭ ነው፡፡ ይሁንና ግን ባሪያም ነጻ ነህ ብትለው ለመቀበል ያዳግተዋል እና፤ ከአንዱ ጌታ ብታላቅቀው ሌላ ጌታ ሁልግዜ ይፈልጋል፡፡ ፖለቲከኞችም ሁሉ ይህን የአይምሮ ለውጥ እንዲኖር አጋዥ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ ጭራሽ ወደ መካከለኛው ዘመን ኢትዮጲያን እንዳትመለስ ያሰጋል፡፡ አይዞን በአለባበስ ስልጣኔ ግን ፈረንጅንም አልፈን እንደምንሄድ አትጠራጠሩ፡፡ ለዚህ አይምሮአችን በጣም የተዘጋጀ ነው፡፡ በቸር ልበላችሁ? ወይስ ምን
ባዩሽ

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen