Dienstag, 29. April 2014

ፖለቲካ ማሸነፍ እና መሸነፍ ሳይሆን ስራ ነው፡፡



ፖለቲካ ማሸነፍ እና መሸነፍ ሳይሆን ስራ ነው፡፡

ጥያቄው ለእኔ ፤ ያለው ገዢ መጥፎ ነው ጥሩ ነው የሚለው አይደለም፡፡ ያሳሳበኝ ነገር ሁልግዜ ከዘመን ዘመን እየተሸጋገረ እና እያደገ የመጣው የሰባአዊነት ነገር እየጠፋ የሰዎች ፍላጎት በእራስ ወዳድነት እየተመሰረተ መሄዱ ነው፡፡ በኢትዮጲያ ውስጥ የተደረጉ ማንኛውም ለውጦች አስፈላጊነታቸው ትክክል የነበረእና አንገብጋቢም የሕዝብ ጥያቄ የነበረ ቢሆንም ግን የተመለከትነው ሁልግዜ በቤተመንግስት ውስጥ የተወሰነ የሀይልእና የስልጣን ብሎም እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ የሆነ እንጂ ሕዝቡን ወደአስፈላጊ ዲሞክራሲ እና የመብት ጉዳይ ሊያመጣው አልቻለም፡፡ ይህም አሳሳቢ የሆነው ነገር ድህነት እየተስፋፋ እህል ባለበት አገር ሰው ጾሙን እያደረ የሚሄድበትን ጉዳይ ትክክል እንዳልሆነ እና አላግባብ የሚያካብቱም ሰዎች ትክክል እንዳልሆኑ የሚያገናዝብ የአብሮነት የስበአዊነት ስራ ግንዛቤ ካልተሰራ ህዝብ ወደሚፈልገው ለውጥ ሊመጣ አይችልም፡፡ ግን ሁልግዜ የተወሰኑ ሰዎች ያመኑበትን የቤተመንግስት ለውጥ ሊያመጡለት ይችላሉ፡፡ይህ የለመድነው ነው፡፡ ካፒታሊዝም የሚደግፈው ቢኖርም፤ ካፒታሊስት የሆኑ አገሮች እንደኢትዮጲያ ጾሙን የሚያድር ሰው የለበትም፡፡ ስለዚህ ካፒታሊዝም በኢትዮጲያ  የህልም እሩጫ ነው፡፡ በካፒታሊስት የሆኑ አገሮች የሚኖረው ህዝብ፤ ሰውን ጾም አሳድረው ግለሰቦች የነሱን ከፍታ የሚገነቡበት ጭካኔውም የላቸውም፡፡ ለዚህ ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ ንቃተ ሕሊና ገንብተዋል፡፡ እኛ ጋር ግን የሚቀድመው ከፖለቲካው ስራ በፊት የበላይነት፣ ስልጣን፣ ከሕዝብ መሃል አባል ሰብስቦ ያንን ክፍል ማክበር ማሰዳግ እና እንደልቡ እንዲሆን ማድረግ የራሱን ገነት መገንባት ነው፡፡ ይህ የሞኝ ጉዞ ነው፡፡ ዘላቂነት የለውም፡፡ ሕዝብ ዝም አለ ማለት አላወቀም ማለት አይደለም፡፡  ጦምአዳሪው፣ ስራ አጡ  እየበዛ በሚሄድበት አገር ኢትዮጲያ፣ በልቶ የሚያድረው ክፍል ያኛውን ክፍል ልክ እንደዳቢሎስ በማየት ወይም እንዳልተሳካለት በመቁጠር“ ጆሮ ዳባ ልበስ“ ብሎ ይባስም ብሎ የተቸገረ እንደለለ በማስመሰል ሁኔታውን መርሳት እጅግ የሚያሳስብ ሁኔታ ነው፡፡ ሴቶች ከመቸውም በላይ በድካም በሚገኙበት ወቅት የጥቂት ሴት ሚኒስተሮች ቦታ መያዝ ወይም በስልጣን መቀመጥ ሴቶች እተሸለ ደረጃ ላይ ደርሰዋል ማለት ያሳዝናል፡፡ እንዳውም ከመቸውም በላይ ማጣት ያሰማራቸው የስራ ዘርፍ ወይም መንገድ ሁሉ ለከፍተኛ ትቃት ዳርጎአቸዋል፡፡  በላጩ ሕዝብ እየተቸገረ በድህነት እየተቆራመደ ጦሙን እያደረ የሚሄድበት አገር ላይ የሚደረጉ መረን የለቀቁ የማተርያል ውድድሮች ፤ካፒታሊዝም የሚለውን ሲስተም ወይም አመለካካት እየጠላ እንዲሄድ እና ህዝብንም ወደኮሚኒስት ሪቮሊሽን እንዲሄድ እንደሚያደርገው ምእራቡ አለም መጠርጠርም ያስፈልጋቸዋል፡፡ ኮሚኒዚም እያቆጠቆጠ በመሄድ ላይ ይገኛል እና፡፡ ሰው ወደእዛ የሚሄደው ይጠቅመኛል ብሎ ሳይሆን ያለበት ሁኔታ መክፋት ይሆናል፡፡
ይህን የኢትዮጲያን በድግግሞሽ የምናልፍባቸው የማንአለብኝነት ሁኔታ ሰባአዊነትን በእጅጉ እያጠፋው እየሄደ ነው፡፡ ኢንቬስትሜንት የሚያስፈልግበትን ትምህርት የሚሰጥ አካል ከመፈጠሩ በፊት ወይም ተገቢውን መተካካያ ሳይስተካከል ስፍራ ማስለቀቅ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ እሱም ፖለቲከኞችን እንዳይታመኑ እና ደግሞም ኢንቬስተሮችን እንዲጠሉ የሚያደርግ ሀይል አለው፡፡ ይህ በእጅጉ ቀውስ ፈጣሪ ነው፡፡ የአካባቢን ደግሞ ሁኔታ አንድ ኢንቬስተር ሳያጠና አይገባም፡፡ ከበሳል አገሮች የሚገቡ ኢንቬስተሮች የሚመለከቱት የሚጠብቃቸውን ጥበቃ ብዛት ሳይሆን ከማን እንደሚጠበቅ የሚያደርገውን ምንጭ ነው፡፡ ወደአፍሪካ የሚገቡ ኢንቬስተሮች ተቃዋሚ  በሕዝብ መካከል የሚጫወተውን ሀይለኛ ሚና ስለሚያቁት በቀላሉ ሰፍ ብለው ነዋያቸውን ሊያፈሱ አይገቡም፡፡ ሕዝብ ካልተመቸው ጉሬላም በለው ሰላማዊ ወደትግል መግባቱ አይቀርምእና፡፡ ስለዚህ በኢትዮጲያ ያየሁት ችግር ለሕዝብ የሚገባውን መረጋጋት የሚሰጥ የፖለቲካ አመራሮች ሊፈጠሩ አለመቻላቸው ነው፡፤ አልያም ባላወቅነው ምክናያት ቤተመንግስቱን ከጨበጡ በሁዋላ ጥበቃቸውም ስጦታቸውም ስራቸውም ቤተመንግስት አካባቢ ለሚገኙት ለመረጡዋቸው ሰዎች ብቻ ነው፡፡ ቤተመንግስት ስል በሁሉም ክልል የምናየው የፖለቲከኞቻችን ቤተመንግስት አላቸው፡፡ በፓርቲ ስም የታቀፈው ክፍል እንደልቡ ሆኖ ሰዎችን በማሰላቸት አገሪቱን ልክ እነሱ ብቻ እንዲዝናኑበት፣ እንዲናገሩበት እንዲመሩበት የተሰጣቸው እስከሚመስል ድረስ ሌላው ተሸማቆ የሚኖርበት ሲስተም የተገነባበት ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ተበዳዩ ሕዝብ ለመኖር ሲል የሀሰት መስካሪ ከሳሽ እና ተበዳይም እርስ በእርሱ በማድረግ የበላይነትን እንዱ ተቀናጅቶ አስታራቂ በመምሰል ሰነልቦናን በመግደል ይገኛል፡፡ ተቃዋሚም በአንድነት ሊሰሩበት ያልቻሉት የንቃተ ህሊና አለመዳበር ጉዳይ ነው እላለሁ፡፡
ይህ ትልቅ ቀውስ ያመጣብን ነገር ብዬ የምገምተው፤ ፖለቲከኞች ቤተመንግስቱን ሲጨብጡ ልክ የእግዚአብሄርን ወንበር እንደተረከቡ ሆኖ ስለሚሰማቸው የሚሞላቸው ትምክህት ወይም የአሸናፊነት ስሜት ፖለቲካ ስራ እንዳለው ይዘነጉታል፡፡ ፖለቲካን እንደስራ ሳይሆን እንደድል መቀናጀት ስለሚያዩት አንደዬ የጨበጡትን ስልጣን የሚያጡት አይመስላቸውም፡፡ ይህ ሁሉንም ፖለቲከኞች ባያካትትም፤ የበለጠው ግን በግልስግብግብነት እና በመሰረታዊ ድህነት የተነሳ ስሕተት ይፈ›ጸማል፡፡ ግን ድንገት ያንን ማጣቱ ሲሰማቸው ትኩረታቸውም አሁንም ለመስራት ሳይሆን በመከላከል ስልጣንን መቀጠል ነው፡፡ የግል ጥቅም የአገሪቱን ጉዳይ ያዘናጋል እና፡፡ ኢሕአዴግ ዛሬ ላርመው ቢልም በብዙው መረን ለቆት የነበረውን ነገር ዛሬ ሊያስተካክለው አይችልም፡፡ ችግርም የተፈጠረው እዚህ ላይ ነው፡፡ ባህሪ ይለመዳል እና፤ ያስለመደው ባሕሪ በእራሱ አባል እንዲናቅ እንዳይከበር የማድረግ ጫና ፈጥሮአል፡፡ ህዝብን የሚያንገላቱ ሰዎች መፈጠር የበላዮቹን እንዲናቁ ያደርጋል እና፡፡ ይህ ልቅነት የፈጠረው ጉዳይ አገሪቱን ወደሙስና እንድትገባ አድርጎአታል፡፡ ይህም ብዙው ያመጣው ችግር  ፖለቲካ ከስልጣን በላይ የሆነ ስራ እንዳለው በመዘንጋቱ ነው፡፡ ዛሬ የኢትዮጲያ ሕዝብ ከኢሕአዴግ ላይ እሰከአካቴው አይኑን ያነሳበት እና በዝምታ እንዲያየው የሆነበት ሁኔታ የተፈጠረበት ደረጃ ላይ ደርሶአል፡፡ ኢሕአዴግም ሆነ ደርግ ወይም ሀይለስላሴ የተሰጣቸውን የአደራ እረጅም ጊዜ እና አመኔታ ሳይጠቀሙበት አልፈውታል፡፡ እጅግ የሚሳዝነው ሁሉም በገዛ አገሩ ለመናገር አቤቱታ ለማቅረብ ለመክሰስ መፍራቱ ነው፡፡ ስትፈራ መናቅ እንደሚከተል መገንዘብ ነበረብን፡፡ ፖለቲካ ስራው ቀሎ የሚታይበት አገር እንደኢትዮጲያ ያለ የለም፡፡  ስልጣን ለማያዝ ብዙ መስዋእትነት ከፍለው፤ በወራት እድሜ ውስጥ ግን ስራ መስራት ሳይሆን የሚያሳዩን ማንአለብኝነት ነው፡፡ ሁሉም ሊገለሰስ የማይችለውን መገልሰስ እንደትልቅ ዝና ይቆጥሩታል እና፡፡ አሁንም የምፈራው ይህ የኢሕአዴግ መንግሰት በቀላሉ የሚነሳ ባለመሆኑ እሱን የሚገለስሰው ደግሞ ፖለቲካ መጣል ብቻ ሳይሆን ሕዝብንስ የማንሳት ስራ እንዳለው ያውቁ ይሆን? በቸር ልበላችሁ
ባዩሽ

Samstag, 26. April 2014

እድገት የማያሳይ ፖለቲካ



እድገት የማያሳይ ፖለቲካ


ፈሪሃ እግዚብሄር በኢትዮጲያ ላይ እንዲኖር የፈለኩት ሀይማኖትን ለመስበክ ሳይሆን፣ ሰው እንደሰደድ እሳት በእራስወዳድነት የተጠመደበትን እና እኔ ብቻ ልኑር ልዳን የሚለውን አመለካከት እንዲመለከት በማስታወስ ነው፡፤ ይህም ለዚህ ያበቃኝ በቂ ሰዎች የደረሰብኝን ችግር እና ብዙዎች ደግሞ በመመልከት ከቶም በማሾፍ እና በመሳቅ እየተመለከቱ ማለፋችው እጅግ በጣም ገርሞኝ ነው፡፡ እንደኢትዮጲዊነት ደግሞ ይህ አሳፋሪ ምግባር ነው፡፡  እኔ በኢኮኖሚ እራሴን የቻልኩ ሰው ስለሆንኩ፤ እንደሰው ለመስራት እና ለማደግ የኢትዮጲያ ሁኔታ አልፈቀደልኝም እንጂ፤ እራብ ላይ ልወድቅ የማልችልበት እምነት እና ደግሞም ኢኮኖሚ ላይ ለመድረስ  ችያለሁ፡፡ ይህን ስናገር እርቦኝ ጥግ ይዠ ቆሜ የማለቅስ ሴት አልሆንኩም፡፡ ግን ሁኔታዎችን የግድ ለመጥቀስ እራሴን በኢትዮጲያ ያስቸገረኝን የብዙ  የሴት ችግር ስለሆነ በጋራ እንዲታወቅ  ልገልጸው እገደዳለሁ፡፡ እንጂ እንደሌባ ተኮፍሼ ትእቢተኛ መሆን አልፈልግም፡፡ በነገራችን ላይ ትክክለኛ ግብር ከፋይ ሆኜ አይኑ ለታወረው ኢሕአዴግ ጠቅሜዋለሁ፡፡ በወሬ ልጠቅመው ግን አልችልም፡፡ ተግባሬ መስራት እና እራሴን መቻል ነው፡፡ ይህንም አድርጌአለሁ፡፡ ከእሱ ግን ያገኘሁት አምስት ሳንቲም የለም፡፡ ሳንቲምን የምገልጸው በሚደረግልኝ ድጋፍ  ነው እንጂ እኔ ከኢሕአዴግ ቀርቶ ከሌላም በፖለቲካ ስም ፍጆታ አልፈልግም፡፡ ፍጆታዬ ህግ የበላይነት አለበት አገር ለመኖር መጣር ነው፡፡ ለሴት ይህ በጣም ጠቃሚ ነውእና፡፡ ገንዘቡ የሕዝብ ስለሆነ አልመኝም፡፡ በቃ ኢሕአዴግ ለእኔ ለሴቱዋ ያደረገው መከላከል  ዜሮ ነው፡፡ ምንም የረዳኝ ነገር የለም፡ያለው መንግስት ጣፋቱን እራሱ ማወቅ አለበት፡፡ እኔ ግን ችግሬ የፖለቲካ ፍጆታ ብቻ ሆኖ እኔ ሳልኖር እንዳልሞት ስለማልፈልግ እራሴ ችግሮችን ይፋ ለማድረግ ተገድጃለሁ፡፡ ሕግን ሳይሆን ሕግ አስከባሪውን እየፈራን የምንኖርባት አገር፡፡  ኢትዮጲያን ስመለከታት የአንድ ጉረኛ ሰው ቤት ትመስለኛለች፡፡ እሱም ሳሎኑን አሳምሮ ጉዋዳው የቆሸሸን፤ አልያም የአንዲት ሴት ወይዘሮ ሙያ፤ ጉዳጉዱ በተጥለቀለቀ ቅቤ የተሸፈነ፡፡
  „ብቻ የቄሰራን ለቄሳር“ ሀቄን የተወጣሁ ሴት ነኝ እና በእዚህ እኮራለሁ፡፡ ኢሕአዴግ ደግፎ ካሳደጋቸው ሰዎች እጅግ በጣም የተለየ ያልተስገበገበ  ማንነት ያለኝ ንቃተህሊና ያለኝ ሴት ነኝ፡፡ ስለዚህ በኢህአዴግ መንግስት እሱ ለእኔ ያልተወጣውን ግዴታ እንድወጣ እግዚአብሄር ቆራጥነቱን ሰጥቶኛል፡፡ ግን ለአንድም ችግር ደርሶልኝ የሚያውቅ ድርጅት አይደለም፡፡ አገራችንን የጣላት የአስተሳሰባችንን እድገት ቆልፎ ያያዘው የውስጣችንን ባዶነት በአፍ ለመሙላት የምናደርገው ጥረት ነው፡፡  በእርግጥ እኔ በሰው ላይ የማላደርገው ጨካኝ ተግባሮች በኢትዮጲያ ውስጥ ሲፈጸሙ አይቻለሁ፡፡ ይህም ከቀን ወደቀን እያደገ የሚሄድ እንጂ የሚቀንስ አይደለም፡፡ እንግዲሕ በኢትዮጲያ የፖለቲካ ማንአለበኝነት የሰፈነበት ቦታ ሕብረተሰቡን ፈር  የሚያሲዝ ሕግ መተግበር ካልቻለ፤ ያለን አማራጭ ህብረተሰቡ እግዚአብሄር የሚለውን ትክክለኛ መንገድ እርስበእርሳችን ተማምረን አገሪቱን መራራ እንባ በበደል የተነሳ እንዳይፈስባት ለመታደግ ያለን አማራጭ ወደእግዚአብሄር መመለስ ብቻ ነው፡፡ እንደእውነቱ ዛሬ ከጥጋብ በላይ የሳቀ ነገ ያለቅሳል፤ ዛሬ ያለቀሰ ነገ ይስቃል፡፡ ይሕ የማይቀር ሀቅ ነው፡፡ ይህም የምላችሁ፤ ሁሉም በፖለቲካ እያሳበበ መረን የለቀቀ ማንአለብኝነትን የሚያሳዩ ግለሰቦች ብዙወን ሰው መራራ ሕይወት እያስኖሩት እና የደም እንባ እያስለቀሱት ይገኛሉ፡፡ ባይመችም አንድ ነገር ለማለት እሞክራለሁ፡፡ ባይመችም የትግሌ ዋንኛው መሰረት ከጨቆነኝ እና ካሳደደኝ ማንአለብኝ የሆነ በትእቢት የተሞሉ ሰዎችን ባሕሪያቸውን መቃወም ነው፡፡ ምክናያቱም እኔም የመኖር መብት አለኝ እና ነው፡፡ ተዝናንተህ ሳሆን ተሸማቀህ የምታሳልፍባት ኢትዮጲያ ባንዲራ ብቻ እጃችን ላይ ጠምትመን ወይም እጆሮአችን ላይ አንጠልጥለን በመሄድ ለውጥ ልናመጣላት አንችልም፡፡
 እርግጥ ነው፤ ጡንቻቸው የፈረጠመ እና ብልሹ አመራሮችን መከታ ያደረገ  ወይም ያደረገች ግለሰብ ሊሆኑ ይችላሉ የሚያሳድዱ፤ ግን ይህ ብልሹ አመራር እስከሚጠፋ፤ እንዳው እንኩዋን እስከሚቀንስ መታገል ግድ ይለናል፡፤ በተለይ ሴቶች፡፡ ሴቶች ትዳርን ለፍቅር እንጂ ለኢኮኖሚ ደግሞም ባልን ለአብሮነት ለቤተሰብ እንጂ  ለመከላከል /ቦዲ ጋርድ/ ለማድረግ ለማይፈልጉ ለውጥን መመኘት አለባቸው፡፡ ካልሆነ ለመኖር እራሱ ሴት በኢኮኖሚ እራሱዋን ቻለችም አልቻለችም የብልሹ አመራሮች ተጠቂ ሆና ህይወቱዋ ውስብስብ ያለ እና ትዳሩዋም የፍቅር ሳይሆን እራሱዋን ለማዳን የቦዲ ጋርድ ቅጥረኛ ለመቅጠር እንዳይሆንባት ያሰጋል፡፡ ሁሉም ገቢውን ለማግኘት የመጣር እና እራሱንም የማስተዳደር ግዴታ ቢኖርበትም፤ ሌላው ደግሞ የሌላውን ሕይወት በመበጥበት ንብረቱን በመዝረፍ መሸጋገሪያ ድልድይ መሆን የለበትም፡፡ ኢትዮጲያ ግን የደቡብ አፍሪካ አይነት ሁኔታ በህብረተሰቡ መካከል እየታየበት የሚሄድ ሆኖአል፡፡ ለጊዜው ገዢው ፓርቲን ጥፋተኛ እያስደረገ የሄደው ስድነት የእያንዳንዳችንን በተለይ በኢኮኖሚ እራሳችንን ለመቻል ጥረት የምናደርግ ሴቶችን እያንገላታ እያሳደደ ወይም ደግሞ እዛው ለአላስፈላጊ ወጪ እንደጉቦ እና ደግሞ ላልፈለግነው ትዳር ወይም ተደራቢ ውሽማ ቢጤ እንድንይዝ የሚያስገድደን ስውር ሲስትም ውስጥ እንድንገባ እየተገደድን ነው፡፡ ይህን ለገዢው ፓርቲ ለማሳወቅ የጣርን አንዳንድ ሴቶች እንደፖለቲካ ተቃዋሚ እየታየን ተገለን ንብረታችንን እንኩዋን እንዳንሰበስብ ተደርገናል፡፡ ደግሞም ዲያስፖራ  ብለው በስም የተከፈለው ኢትዮጲያዊ በተለይ ሴቱ ለዘረፋ በእጅጉ የተጋለጠ ሆኖአል፡፡ ኑ ተራግፋችሁ ሄዱ ኤነት ነገር፡፡ ይህ ገዢው ፓርቲ ሊያፍርበት የሚገባው ነገር ቢኖር፤ በኢኮኖሚ እራሱዋን እንድትችል የምትጥርን ሴት ሊያበረታታ ቀርቶ እንደለለችም በመቁጥር ቀንዱዋን እያሉ የሚያስባርሩዋትን  ስውር ሌቦች ወይም ስውር የገባያ ተወዳዳሪዎች አሳልፎ ሰጥቶዋት ይገኛል፡፡ ነውርእና አሳፋሪ የሆነው ይህ ነገር ግን መቆሚያ ሊኖረው ቀርቶ እየባሰ እየሄደ ነው፡፡ ብዙዎቹ ገዢው ፓርቲ ቂጣቸውን ወደላይ እየገፋ  ያወጣቸው ግለሰቦች በዚህ መልኩ በደካማው ገንዘብ እና በሴቶች ገንዘብ ያደጉ ናቸው፡፡ ብቻ እኔን ብቻ አይቃወመኝ እንጂ እሱ ወይም እሱዋ በፈለገው መንገድ ይደጉ ማለት፤ ግብር ከፋዩን ህብረተሰብ በጣም ያስመረረው እና የሴቶችንም የኢኮኖሚ ትግል በእጅግ እየቀጨው እንዳለ እያየነው ነው፡፡ ይህ መቼ እንደሚሻሻል ባናውቀውም ግን ተጠቂዎች የምናነባው እንባ ለምድሪቱ በረከት የሚዘጋ እና የሰውንም የአይምሮ እድገት ተቆጣጥሮ የሚዘጋ ነው፡፡ ይህ ጋጥወጥነት እየሰፋ ከሄደእና ምንም አይነት ቆጥጥር የማይደረግበት ሁኔታ ፤ማንም ሰው ሊረዳው የሚችለው ቀምተው አስፈራርተው እና ደግሞም አሳደው የሚበሉ እራሳቸውንም ወደላይ የሚሳያሳድጉ ወንበዴዎች ቁጥር በሰፊው እያደገ የሚሄድ መሆኑን ከወዲሁ ማንም መረዳት ያለበት ሀቅ ነው፡፡ ሌላው ይህን ጉዳይ ዝም ብሎ ከገዢው ፓርቲ ጋር ብቻ በማያያዝ ማለፍ በኢትዮጲያ ላይ ያለው የባሕሪ ለውጥን ወደ  ስግብግብነት እና ማንአለብኝነትን ይሁንታ እንደመስጠት መሆኑን አውቆ፤ ተቃዋሚም ቢሆን በዚህ አይነት መጥፎ የባህሪ ለውጥ፤ነገ ለእሱም ቢሆን እንደማይመች እና የፖለቲካ  ሥራ እንቅፋት መሆኑን አውቆ በማንኛውም ሀይማኖት የመረጋጋት እና ሌላውን የመረዳት የመርዳት ትብብር ህብረተሰቡ እንዲላበስ የሚያደርግ ትምህርት ቢሰጥ መከላከል የለባቸውም፡፡ ለጊዜው የፖለቲካ ለውጥ በማታይበት አገር እምነት እጅግ በጣም የሞራል አስተማሪ መሆኑን መረዳት አለባቸው፡፡  በኢኮኖሚ እራሳቸውን ለመቻል ጥረት የሚያደርጉ ሴቶች እና ብሎም ደካማ ሰዎች ህብረተሰቡ ጉልበት፤ መከታ እና አለኝታ እንዲሆናቸው እንዲጠብቃቸው ትምህርት መስጠት ግድ ሊለው ይገባል፡፡ የተለቀቀ ወፍን መልሶ ማጥመድ አስቸጋሪ ይሆናል እና፡፡
ካልሆነ ሀይማኖት አያስፈልግም የሚቀድመው ሌላ ነው የሚል፤ ላም አለኝ በሰማይ ወተቱዋንም አላይ ይሆናል፡፡ የህግ የበላይነት በማይታወቅበት እና ብልሹ አመራራ ባለበት አገር መሪር እንባ እየወረደ ባለበት ሁኔታ የሴቶችን ጉዳይ እንዳለ መዝጋት ማለት እጅግ ሁዋላ ቀርነትን የሚያሳይ ነው፡፡  ሌላው የኢትዮጲያ አኑዋኑዋር ትንንሽ ማህበረሰብ መስርቶ ከመኖር እንዲወጣ ማንም የረዳው የለም፡፡ ይህም የሚያሳየው ሕግ አለመኖሩን እና አለመታወቁን ሲሆን በትንንሽ ግሩፕ መወሰኑ የሚያመለክተው፤ አንድ በግሩፕ ዘረፋ ሌላው ደግሞ በግሩፕ ሆኖ እራሳን ማዳን መከላከል ነው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጲያ ፖለቲካ እንደትናንትናው ዛሬም ነገም ገደል የገባ እድገት የማያሳይ ሲሆን ጉራና ትእቢታችንም ከአፍ ያላለፈ  መሆኑን ለመረዳት ችያለሁ፡፡ አዎ ጉራ ብቻ፡፡ ቢሆንም በቸር ኑ፤ ለክሪቲኩ መለቴ ነው፡፡
ባዩሽ

Mittwoch, 23. April 2014

ታሪክ ባህል ሲሆን





ታሪክ ባህል ሲሆን

ኢትዮጲያ ከ17ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ከውጭ ጥላት በመከላከል ብቻ ኖራለች፡፡ ይህም ብዙውን የኢትዮጲያን እድገት እንደልማት አይነቱን በእጅጉ ሰባብሮት አልፎል፡፡ ኢትዮጲያ እንደአነሳሱዋ እንዳትጉዋዝ ያደረጋት ጊዜዋም መከላከል ስለወሰደባት ነው፡፡  ያው መከላከል ልምድ ሆኖብን ደግሞ በገሀድ የምናየው የውጭ ጥላትም ባይኖር፤ አሁንም ግን የፊውዳሉ ስርአት የሀይለስላሴ መንግስት እረጅም ግዜ የእራሱን ህዝብ ፖለቲካሌ የሚቃወመውን ቀንዱን እየሰበረ እረጅም ግዜ መቆየቱን አንክደውም፡፤ ጭራሽ ዙፋኑን እንኩዋን ንጉሱ ላልጋወራሹ ለማስተላለፍ በጭራሽ እምነት አልነበራቸውም፡፡ ይህ መረጃው ለማንም ቢሆን ግልጽ ነው፡፡ ሀይለስላሴ እድሜአቸውም ገፍቶ እነኩዋን ለወለዱት ልጅ ዙፋኑን ለማስተላለፍ አልደፈሩም፡፡ አላመኑም፡፡ መከላከል ዘይቤ ሆኖ ፤   እነመንግስቱ ነዋይ ለእኛ ግልጽ ባልሆነ መልኩ ወይም ታሪኩን እስከዛሬ ግልጽ ባልሆነ መልኩ በስቅላት ተቀተዋል፡፡ የእያሱም ጉዳይ አከራካሪ ሆኖ ብዙውን ያስኮረፈ እና ያስቆዘመ ነው፡፡ እኔ ሰሞኑን የንጉሱን ታሪክ የያዘውን ፎቶ እንኩዋን በግለጽ ባወጣ፤ ከየቦታው የሚወረወረው ተቃውሞ፣ ቀላል አልነበረም፡፡ ግን ንጉሱ ወደድንም ጠላንም ታሪካችን ሆነው አልፈዋል፡፡ ሌላው ደግሞ ትልቁ ቀውስ ደርግ ፊውዳሉን ገለሰሰኩ ብሎ እጅግ ብዙ ምሁሮች የሞት ሰለባ ማደርጉ ነው፡፡ ሁሉም በይፋ እና በአደባባይ ነው የገደሉት፡፡ ጭራሽ እንደአምልኮ ግንቦት ወር በኢትዮጲያ እጅግ የተፈራ እንደሆነ ልቦናችን ያውቀዋል፡፡ ልክ ደም እንደሚጠማ ወር ታይቶ በደም የሚዘክሩት ብዙዎች ናቸው፡፡ በግንቦት ደምን ለማድማት የሚሮጡ ብዙዎች ናቸው፡፡  ሲያደሙም እናያለን፡፡ በግንቦትም ወር ብዙ የመንግስት ለውጥ ይሆናል ብሎ የሚያምንም አይጠፋም፡፡ ይህ ግንቦት መጣ ብሎ የመንግስትን ለውጥ የሚመኝ አለ ደግሞ የሚፈራም አለ፡፡ እንግዲሕ ሚስጥሩን እግዚአብሄር ይግለጸው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ደርግም የውጭ ጠላት ሳይመጣበት ልማት የለ ምን የለ ሲከላከል የነበረውን ተቃዋሚውን ነበር፡፡ ይህ የቅርብ ግዜ ምስክር ነው፡፡ እጅግ ብዙ ተቃዋሚ የከበበው ደርግ የቅርብ ግዜ ትዝታ ነው፡፡ ከዚያም ወያኔ ኢሕአዴግ ገብቶአል፡፡ እሱም ዛሬ የምናየው የውጭ ጠላት የለውም ግን የሚኖረው  ተቃዋሚውን በመከላከል ነው፡፡ ሰላማዊ ሰልፍ ይፈራል ግን ዲሞክራሲ አለ ይላል፡፡ ፐሮፖጋንዳውም ሆነ ሁሉም እርምጃው እራሱን ትክክለኛ ተቃዋሚውን ደግሞ እንደጠላት አድርጎ አለምን በማሳመን ብዙ ድካም የሚያደርግ እና ብዙ ወጪ የሚያደርግ ፤ እንደሌሎቹ የእራሱን ዘሩን ከፋፍሎ ተቃዋሚ ብሎ በመከላከል የተቀመጠ መንግስት ነው፡፡ ለእኔ አዲስ ነገር የለም፡፡ አስራሰባተኛው ክፍለዘመን ያመጣብን ድኝገተኛ ጦስ ለምዶብን መሰለኝ በመከላከል እንኖራለን እንጂ የፖለቲካ ስራ የሚሰራ ገዢ አላገኘንም፡፡ ስለዚህ ቀኑን ባናውቀውም አንድ ቀን በድንገት ይህ መንግስት ይለወጣል፡፡ የተከላከሉ ሁሉ ከመውደቅ ድነው አያውቁም፡፡ ካየነው ልምድ፡፡ ስለዚህ ዘወትር አንዳንድ ሰዎች ተቃዋሚ ወይም ደጋፊ እንድንሆን ይመኛሉ፡፤ ደግሞም ፔንጤው ፔንጤ፤ ኦርቶዶክሱ ኦርቶዶክስ፡፡ ግን እባካችሁ መጀመሪያ እራሱን ያላወቀውን፤ ሌላውን እንዲሆን አትመኙ፡፡ እናንተን መሆን ሳስብ የሚከተለው መደነጋገር ነው፡፡ የእናንተን አላውቅም በመቃወም ወይም በመደገፍ አይደለም ነጥቡ ፤ ነጥቡ የምንቃወመውን ነገር ለይተን ማወቅ ነው፡፡ መቃወም መቃወም መንግስታቶቻችን ሁሉ በመቃወም አሳልፈዋል፡፡ ኮሎኒን ተቃውመዋል ደግሞም ዘራቸውንም አሁንም እየተቃወሙ በመከላከል እንደቆቅ ሆነው ጆሮአቸውን አይናቸውን አቁመው ይኖራሉ፡፡ ልምድ ያመጣው ካልሆነ ምን ሊሆን ይችላል፡፡ እንደምትወድቅ እያየህ ዘላለም በወጣደር እየተጠበክ መኖር፡፡ ለዚህ ጥሁፍ መነሻ ያደረገኝ ቃል በግል የመጣልኝ ስድብ መሰል ክርቲክ ነው፡፡
Looks like you are knowingly or unknowingly confused. ..cheating your self. ..and increasingly becoming a laughing stock. If you run out of ideas please take your time and come up with something relevant. ...otherwise you better keep your crap for your self.”
እየሳቁብሽ ነው አይነት ነገር፡፡ እርግጥ ነው፡፡ ለሚስቁ ማልቀስ ነው፡፡ እንጂ እንግዲህ አልናደድም፡፡ ምክናያቱም አረማመዴ መሬት የተረገጠ ካልሆነ እሰበራለሁ፡፡ አያችሁ ፔንጤው ፔንጤ፣ ኦርቶዶክሱ ኦርቶዶክ፣ ደግሞ ተቃዋሚው ተቃዋሚ፣ ገዢው ፓርቲም እሱን እንድትሆንለት ስለሚፈልግ ይናደዳል፡፡ ግን ሁሉም የእራሱን ባህሪ አይመረምርም፡፡ ማንንም እንዳንሆን ፊት ለፊቴ ቆሞ የሚናገረው ንግግር ያግደኛል እና፡፡
ለማኝኛውም በመከላከል  ለዘመናት የኖረ ህዝብ የማጥቃት ልምምድ አለማድረጉ ችግር ላይ ጥሎታል፡፡ በዚህም የተነሳ ኢሕአዴግ ሰላማዊ ሰልፍን ይፈቅዳል ብዬ አልገምትም፡፡  ምክናያቱም ይህ ባህሪ የፖለቲካችን ባሕል ሆኖአል እና፡፡ ብዙ ወዳጅ የለለው፤ ያደፍጣል፡፡ ብዙ ወዳጅ ያለው ደግሞ ውጣ ውጣ ይለዋል እና፡፡ እባካችሁ ተቃዋሚ ነሽ ደጋፊ አትበሉኝ፡፡  መደነጋገርም ካላችሁት ባህሬየን ያልተደናገረው አንድ ሰው ስሙን ጥሩልኝ፡፡ ያልኩት አድርባዩን አይደለም፡፡ ይህ በሁሉም አለእና፡፡ ስሙን ደብቆ እንደለቡ የሆነውን፤ እኔ ስሜን እና ፎቶዬን ያወጣሁትን እሱ ተደብቆ የሚለውን እንድልልት ሲፈልግ ከት ብዬ እስቃለሁ፡፡ ይህ ለዘመናት ያለፍንበት ነው፡፡ ኢትዮጲያ ከመከላከል አስተሳሰብ ካልወጣች በመሸነፍ እና በማሸነፍ፤ በጀግና እና በፈሪ ባህል ለሚመጣውም ዘምን እንኖራለን፡፡ ታሪክ ባህል ሲሆን  እንዲህ ይመስላል፡፡ በቸር ልበላችሁ፡፡
 
ባዩሽ

Samstag, 12. April 2014

ለኢትዮጲያውያኖች ፤ የአንድ ለአምስት መሰረቱ



         ለኢትዮጲያውያኖች ፤ የአንድ ለአምስት መሰረቱ

ሰው ያሰበውን እና የተለማመደውን በመጻፍ ወይም በመናገር ማካፈል እጅግ በጣም የሚከብድበት አገር ኢትዮጲያ ተወልጄ አድጌአለሁ፡፡ አገሬ ኢትዮጲያ ላይ በተለያየው አጋጣሚዎቼእና በደረሱብኝ ኢሰብአዊ ነገሮችም ሆነ በእራሴው ደግሞ እጅ ያለመስጠት ሁኔታ 1969 . ጀምሮ በምእራቡ አለም ላይ በስደት እገኛለሁ፡፡ ይሁንና ግን በተለያየ ግዜ ኢትዮጲያ ለመኖር ወደኢትዮጲያ እየሄድኩ ሞክሬአለሁ፡፡ በማንኛውም ምእራብ አለም አሜሪካ፣ ጀርመን፣ አውስትራሊያ እና ካናዳ በተጉዋዝኩባቸው ሁሉ መልካም የሆኑ ፈረንጆች አጋጥመውኛል፡፡ ግን የአገሬ ናፍቆት አይሎ ስለነበርእና በአገሬም ደርሰውብኝ የነበሩ እጅግ አሳዛኝ ተግባሮች በሕይወቴ ላይ ሚዛኔን ጠብቄ እንዳልሄድ እጅግ አስቸጋሪ የሆነ ሁኔታ ጥለውብኝ ስለነበር ፈረንጆች ያቀረቡልኝን እድል ሳልጠቀምበት አልፎአል፡፡ ይሁንና ግን ዛሬም በተለያየው ውጣ ውረድ ሕይወቴ የጀርመን ጉዋደኞቼ ጣልቃ እየገቡ የሚያደርጉልኝ የስነልቦና ድጋፍ ልረሳው የማልችለው ፍጹም የሆነ ሰብአዊነትን በእነሱ ውስጥ እንድማረውም እረድቶኛል፡፡ ይገርማል አገሬ ወገኔ ያልኩት ሰባብሮ ጥሎኝ፤ ሌላው እንደጠላት ሳየው የነበረው ፈረንጅ ሲገነባኝ፡፡ የሕይወቴ ገጠመኞሽ አዳጋች ተራራ ያስተማረኝ ዘረኝነት ዝምብሎ በጭፍን የምናስበው አስተሳሰብ እንጂ፤ ማንኛውም ዘር ለሰው አስፈላጊ እንደሆነ ነው፡፡ ወደ ቁም ነገሩ ልመለስ እና፤
የተወደዳችሁ ኢትዮጲያውያኖች፤ እኔ ችግር ደርሶብኝ የነበረው በአገሬ በወንዜ እና በዘሬ ሰዎች ነው፡፡ እኔ የማውቀው በእኔ ዙሪያ የተሸከረከሩትን ጉዋደኛ ብዬ ዘመድ ብዬ እና በስራዬም አካባቢ ያሉትን ስለሆነ  የኢትዮጲያን ሕዝብ እንዲሕ ነው ባዬ ለመወንጀል
ይከብደኛል፡፡ ምንም እንኩዋን በጣም ከባድ እና ሊረሱ የማይችሉ ግን ተለማምጄ መኖር እንዳለብኝ የተረዳሁት ችግር ቢኖርም በጣም ክፉ፣ በጣም በዳይ፣ አስለቃሽ እና አሳዛኝ ነገር የሚፈጸመው ሰው በቀረበው ወዳጁ በሚለው እንደሆነ እንድትረዱት እፈልጋለሁ፡፡ ይህ ሁኔታ ስመለከተው ግን „ጠላት ከእሩቅ አይመጣም“ የሚባለውን እውነት መሆኑን አረጋግጫለሑ፡፡ ይረዳኝል ትረዳኛለች ብለህ የተጠጋህው ሰው ጭራሽ የአንተን ችግር የእሱ ሞራል ማጠናከሪያ አድርጎት አንተን በማሳነስ ሲኮፈስ ታየዋለሕ፡፡ ተላላኪ ሊያደርግህም ይፈልጋል፡፡ የአንዳንዶችን ከንቱነትም የተረዳሁት ቤተክርስቲያን ይሂዱ እንጂ፤ ዘመድ አስቀየመኝ ብለሕ ለአንዱዋ ብትነግራት፤ የእሱዋን ዘመድ ወርቃማነት ነግራ ልታስቀና ትፈልጋለች፡፡ ያጋጠሙኝን ነው የምነግራችሁ፡፡ ቀሚስ የለኝም ብትል የእሱዋን ቀሚስ አውጥታ ውድነቱን ልትናገር ትፈልጋለች፡፡ አንድ ባለስልጣን እኮ በደለኝ ብትል እሱዋ አፈጉባኤውን ወይም የውጭ ጉዳይ ሚኒስተሩን እንደምታውቀው ትነግርሀለች፡፡ እጅግ ያሳዝናል፡፡ የደሃ ዘር ነኝ ብትል እሱዋ የሞተውን የደጃዝማች ዘርነቱዋን ትነግርሃለች፡፡ እከሌ እኮ እንዲህ በደለኝ ብለህ ለመንፈሳዊ አባት ብታማክር ፤ እንዴ እሱ እኮ ለቤተክርስቲያን ይህን እያደረገ ነው ወይም ይህን እያደረገች ነው እና የማይታመን ነገር ነው ብለው ከእነገብሬል አብልጠዋቸው በቄሱ እንኩዋን እንደወሬኛ እና እንደማረባ ሆነህ ትገለላለህ፡፡ ደግሞም ማሀበራዊ ህይወቱ ወርቅ ነው እየተባለ ዲያቆናቱም ሲመሰክርለት እየሰማህ፤ ተበዳይ ወሬኛ ሀሰተኛ ሆኖ ምንም አይነት መረዳት ባለማግኘት እንዲቆዘም ይደረጋል፡፡ እንዳውም ይረዳኛል ብለሕ ያጫወትከው ሰው በትልቁ ደግሞ የአንተው ስም አጥፊ ሆኖ ይቀራል፡፡ ወዳጆቼ „ የወደቀ ግንድ ምሳር ይበዛበታል“ ለኢትዮጲያ ባህል ትልቅ አባባል ነው፡፡ እንግዲህ እንደኔ ከሆነ አይምሮ ባልተለወጠበት አካባቢ በውነት ችግርን መናገር ማለት ወረቀትን ፎቶ ኮፒ ማሽን ላይ ማድረግ ነው፡፡ ይበዛል ይበዛል ይበዛል፡፡ ፎቶ ኮፒ ቀለሙ ሲያበቃ ወይ መብራት ሲጠፋ ነው የሚቆመው፡፡ ሰውም እስካልሞተ ድረስ በስቃይ አለንጋ አንዱ ገራፊ ሌላው ተገራፊ ሆኖ ይኖራል፡፡
ይህ ሊመራችሁ ይገባል፡፡ ከጥንት ጀምሮ የነበረ ግን እየባሰበት የሚሄድ እንጂ እየተሸለ የሚሄድ አይደለም፡፡ አገራችንም ይህን ተረድታ አይምሮን የሚቀይር ነገር መስራት አልቻለችም፡፡ እንዳውም የተበላሸውን ባህሪ የፖለቲካ ፍጆታ ቀለብ እየሆነ የሚደሰትበትም አይጠፋም፡፡    በፖለቲካም የተጠላው ሰው እንዲሁ አንድ ፖለቲከኛን እስከሚሰባበር እስከሚወድቅ እስከሚሸማቀቅ ጤናውም እስከሚታወክ ነግ በእኔ ሳይሉ የስነልቦኛ ጦርነት ያካሂዱበታል፡፡  ወድእነሱ ወደአሰቡት አላማ ለማምጣት በጭራሽ  የለም፡፡ ይሙት በቃ ፍራጃ፡፡ የተሳሳተ የሚማር አይመስላቸውም፡፡ ፖለቲካ እንደእምነት መጽሀፍ የሚታይበት አገር ኢትዮጲያ፡፡ ኢትዮጲያን የምንወዳት አንዳንዶቻችን ጥሩ ልምድ ወይም የተሻለች አገር ሆና ሳይሆን ግን እኛም አገራችን ስለሆነች እና የተሰጠችን ምድር ስለሆነች ነው፡፡ ሰው ግን ደግሞ በአይምሮው የተቀረጸው እና የተገነባበት ሆኖ እንጂ ምድር ሁሉ ለሰው የተሰጠች ነበር፡፡ ግን ሰው በተሞላው ይኖራል እና አገሬ የሚል አባዜ ተተናውጦናል፡፡ አገሬ እላለሁ ዘሬ ለማለት ግን እኔም ሰው ነኝ እና ዘሬም ያልሆኑ ችግሬን ተጋርተዋል እና በሁሉም የሰው ዘር አምናለሁ፡፡ መልካምነት የሚፈልቀው ከዘር ሳይሆን ሰብአዊነትን ከመረዳት ነው፡፡ እንዲህም ስላችሁ ከጀርመን አገር ክፉ ነጭ የለም ማለቴ አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ ደግሞ አንዲት ከኤርትራዊ እና ከትግራይ ጋብቻ የተወለደች ሴት በሕይወቴ ላይ ትልቅ የሆነ ስራ ሰርታለች፡፡ ማንም ባልደረሰብኝ አጋጣሚ በውድቅት ለሊት ተገኝታ ነፍሴን ታድጋኛላች፡፡ ወደ 17 የሚሆኑ ወንዶች ከበውኝ ነበር፡፡ ግን ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ በመገኘት እነዛን ወንዶች አንድ ቃል ተናገረች፡፡ „ ለአንዴት ሴት 17 ወንድ ለማስደንገጥም ለመግደልም ከተገኜ በውነት ይህቺ ሴት ጀግና ናት ማለት ነው፡፡ ባትሆንስ ምነው አንድ ወንድ ብቻ በበቃት“ ፡፡ የሚገርመው በእኔ ዘር ግንድ ያልሆኑ፣ የዘር ጥላቻ ፖለቲካ የነዳቸው የዋሆች፣ አርቀው ማስተዋል የተሳናቸው፣ የረዳሁዋቸው ሁለት ሰዎች አስራ አምስት አጋር ጨምረው ነበር ሊያጠቁኝ የመጡት፡፡ አዲስአበባ ላይ ይህ ብልሹ ነገር የተፈጠረው የዘር ፖለቲካን የሚያራምዱ የሚነዙት ዝሪት ነው፡፡ እርግጥ ነው ፌድራል ፖሊስ በፍጥነት ባይደርሱልኝ ኖሮ ዛሬ በህይወት ባልተገኘሁም ነበር፡፡ የከተማው ፖሊስ እማ ፌደራል እጅ ከፍንጅ ይዞ የሰጠውን ወደፍርድቤት ሳያቀርባቸው ቀርቶአል፡፡ እግዚአባሄር ግን አፋጣኝ ፍረድ የሰጠበትን ሁኔታ ለመመልከት ችያለሁ፡፡ ይሁንና ኢትዮጲያ እንዲሕ እንደፓራዲስ የምታየው ገነት አይደለም ወዳጀ፡፡ ግን ሊለወጥ የሚገባው ነገር እንዳለ መረዳቱ እና ማተኮሩ የሚገባ ነው፡፡ ወገኖቼ ካለትዳር ላለች ሴት ኢትዮጲያ ሲኦልም ይሆናል፡፡ ተቀበሉት፡፡ እንዲህ ሰው የሚናገረው ካየው እና ከተለማመደው ነው፡፡ በዚህ ባልተለወጠ ነገር ላይ የህግ የበላይነት ጠቃሚ ቢሆንም ግን ምንያህሉ ወደዛ መስመር ሄድዋል የሚለው አስቸጋሪ ነው፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ግን የግሩፕ ወገንተኝነት ከጥንት ጀምሮ ባንሰራራበት አገር የተወሰነ ሰው ላይ እያተኮሩ መሰባበር ያለ እና የተለመደ ነው፡፡ አንድ ግዜ ኢሕአዴግ አንድ ለአምስት እያደራጀ ነው የሚል ነገር ፌስቡክ ላይ አይቼ ነበር፡፡ እና ተንሽ አሳቀኝ፡፡ ሰው በግሩፕ ከኢህአዴግም በፊት የሚኖር መሆኑን እናውቃለን፡፡ ስለዚህ አንድ ለ20 ቢያደርገው ከባሃሉ ውጭ ሊሆንበት ይችላል፡፡ ብዬ አሳቀኝ፡፡ ቁም ነገሩ ሰው ግሩፕ መስራቱ ሳይሆን ግሩፕን ብዙው የሚጠቀምበት ሌላውን ለመሰባበር መሆኑ ነው፡፡ እንግዲሕ ኢትዮጲያ ለእኔ ፓራዲስ ባትሆንም ግን አገሬ ናት፡፡ እንጂ የለለውን ነገር አለ ብል የማበራክተው ውሸትን ነው፡፡ ዛሬ እኔ የምታገለው አገሬ ኢትዮጲያ ህዝቦችዋ የአስተሳሰብ ለውጥ አምጥተን ሰብአዊነትን እንድንገነባ ነው፡፡  ይህ ከሆነ የሚያለቅሰውን ቁጥር ልንቀንሰው እንችላላን፡፡ ጉራ እና ትእቢትህን ለተቸገረው ብታሳየው አይረዳውም፤ መረዳት ያለብህ ግን ባትሰጠውም እቅፍ አድርገህ ልክ ሌላው አለም እንደሚያደርገው ጀርባውን መታ መታ አድርገህ አይዞሕ ወዳጀ ያልፋል ብለሕ አጽናኝ ቃል ስትነግረው ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ውስጥ መግባት ማለት ክርስቲያን ሆነ ማለት አመኑዋል ማለት አይደለም፡፡ መንፈስ ቅዱስ አጽናኝ እንጂ መረበሽን የሚፈጥር አይደለም፡፡ ወገን ማለት ደግሞ የደሙ መቀራረብ ሳይሆን የምትረዳዳው ነው፡፡ እዚህ ግን የሰው ባህሪው በቤተክርስቲያ ስጦታ በመስጠቱ የሚወሰንለት ከሆነ እና ደግሞም ባፈራው አጃቢ ከሆነ እንግዲህ ያልሰጠው ካለመስካሪ የሚኖርበት አለም ማለት ነው ኢትዮጲያ፡፡ ስለዚህ የማግኘት ወሳኝነት የሰውን ባሕሪ የሚወስነው ከሆነ ሰው ከፍቅር ይልቅ  ለገንዘብ ላይ ቢሮጥ ስህተት አይደለም ማለት ነው፡፡ ሕመምተኛ የማይፈለግ ከሆነ ደግሞ ሰው ጠንቁዋይ ፍለጋ ቢሮጥ ስህተት አይደለም ማለት ነው፡፡ ሰው ዘመድ እና ወገን ከለለው የማይፈለግ ከሆነ እግዚአብሄርን ትቶ ለሹማምንቱ ቢያጎበድድ ምንም ሐጢያት የለውም ማለት ነው፡፡ ሴት አጠገቡዋ ወንድ ከለለ የምትደፈርእና የምትዘረፍ ከሆነ ብዙ ባል ቢኖራት ሀጢያትነት የለውም ማለት ነው፡፡ ሴት ፖሊስ የማይደርስላት ከሆነ ጡንቻው የፈረጠመ ሀይለኛ ወንድ እንድትፈልግ ትገደዳለች ማለት ነው፡፡ ይህ እንደባህል ስር የጠመጠመ ነገር የባህሪ ለውጥ ካላመጣ አበበ መጣ አሰፋ መርገም መብላት ነው፡፡ በቸር ልበላችሁ መሰል፡፡,
ባዩሽ