አገር የጋራ ሀብት ነው
ስለምልጃ ብዙ ክፍፍሎች አያለሁ፡፡ እኔ ግን እስከአሁን ሁሉም ትክክል ነው ብዬ ክፍፍሉን ትቸዋለሁ፡፡ በእርግጥ የመጀመሪያው የክርስትና ሀይማኖት ኦርቶዶክስም ቢሆንም፤የመጨረሻው ግን እንዳልሆነ እያየነው ነው፡፡ ሁሉም እምነቱ ክርስታናን በመሆኑ ስህተቱ የሁሉም አልታይ ብሎኛል፡፡ ግን ስህተተኛ አድርጌ የማየው ክርስትናን ሰማያዊውን አለም በመዘንጋት በምድር ክብረት ብልጽግና ተወስነው የሚሰብኩ እና ትክክለኛውን የክርስቶስ የተሰቀለበትን አላማ እንድንዘነጋ የሚያደርጉን ሲሆኑ፤ ሌላው በባለሀብት ላይ ብቻ የተወሰነ አግልግሎት ማለትም ቤተክርስቲያኑዋን ብቻ ለማክበር የሚደረግ እሩጫ እና የተሻለ አባል አለን ለማለት እንዳይሆን እፈራለሁ፡፡ የሰው ልጅ በየበረንዳ በወደቀበት ሰአት፤ እኩልነት በተዛባበት አለማችን፤ የሚሰሩ ውድ የሆኑእና ውብ የሆኑ ቤተክርስቲያኖች ሀጢያት አይሆኑብንም ወይ ብዬ ብዙ ግዜ አስባለሁ፡፡ ሰው ተርቦአል ተፈናቅሎአል፡፡ እናቶች ህጻን ይዘው ማደሪያ እያጡ በየቦታው ወድቀው እናያላን፡፡አይምሮ በሽተኛዎች እና በሌላም ህመም መስፈሪያ ያጡ፤ ጎዳናችንን አጨናንቀውታል፡፡ እንዳውም ብዙዎች ይህንን ውብ የሆነ ቤተክርስቲያን ከበው በየአጥሩ ስር በብርድእና በውርጭ ተደግፈው ማደሪያ አድርገውታል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ሌሎች ቤተክርስቲያን የሚያመልኩ አልያም የሚሳለሙ በነዛ በረንዳ በወደቁ ሰዎች ጥግ መኪናቸውን እየነዱ ስፍራ ያስለቅቃሉ፡፡ የእነሱም መኪና ማቆሚያ ቦታ ይፈልጋል፡፡ እነዛም ማረፊያ ይፈልጋሉ፡፡ ትግሉ እዚህ ላይ ነው፡፡ አስፈላጊም ከሆነ ደሃው እዚህ አካባቢ መለምንም አይቻልም ብሎ ፖሊስም ሊከለክል ይችላል፡፡ እኔ በበኩሌ ይህ ምልጃ የሚለው ሙግት፤ ስለክርስቶስ ትክክለኛ መልእክት እና መፈጸም የሚገባንን ነገር እንዳንፈጽም አልያም እንድንዘነጋ ብሎም እንድንስት የሚያደርግ እና ወርቃማ ጊዜአችንን የሚያባክን አየድምሮአችንን እንዳናሰባስብ የሚያደርግ እንዳይሆን እፈራለሁ፡፡ ያው ያማልደኛልም የሚለው ወደእግዚአብሄር ነው፡፡ አያማልደኝም ቀጥታ ወደእሱ ነው የምለምነው የሚለውም ለእኔ ችግር የለውም፡፡ ዙሮ ዞሮ ስናየው ለሁሉም ቁም ነገሩ የያዘው ልብ እንጂ ከሌላ ነገር ላይ አይመስለኝም፡፡ ለምሳሌ ማንኛውም ቤተክርስቲያን፤ በኢንቬስትሜንት ፖለቲካ፣ በተፈጥሮ አየር መዛባት እና በድህነት የተነሳ ሜዳ የወደቀውን ሰው ቦታ እና ስፍራ የማመቻቸት ተግባር ብትወጣ ደስ ይላል፡፡ ዛሬ ከበርቴ ቀሳውስቶች መፈጠር፤ እየበዛ እና አለቅጥ ውድድር ውስጥ የተገባበትን ሁኔታ በጨለፍታ በጋዜጠኞች ድፍረት ሚስጥር እየወጣ በአለም ላይ እንሰማለን፡፡ ቤተክርስቲያን ሳትሆን የአለምን ሚስጥር የምታወጣው አለም የቤተክርስቲያንን ሆኖአል፡፡ ይህም በእጅጉ የአማኙን ቁጥር ወደታች እያሽቆለቆለው የሚሄድ አሳፋሪ ነገር ሆኖአል፡፡ መቸም ክርስቲያንነትን ለመግለጽ ብቻ የሀይማኖትን ስም መናገር በቂ ከሆነልን መልካም ነበር፡፡ ይህ ቢሆን ኖሮ በአለም ላይ የሚያጠፋው ባልበዛ፤ እኛም ሰውም ለሀጢያት ታልፎ ባልተሰጠ፡፡ ዛሬ በኢትዮጲያ ከሰው መሬት በልጦ ወንድም እህትን ከቤት እያባረረ ነው፡፡ እናት ብልጁዋ እየተቀጣች ነው፡፡ ብዙ አንገብጋቢ ነገር አለ፡፡“ እርቦኝ አብለተሀኛል እን…?…“ የሚለው ዋናው የየሱስ ነጥብ ይመስለኛል፡፡ አለም በብዙ ነገር በተጨናነቀችበት በዚህ ዘምን እርስ በእርስ መካሰስ እና ዋናው የሆነውን የእግዚአብሄር ነገር መዘንጋት ይገርማል፡፡ እንዲህ ብለን ካየን ሁሉም ሀይማኖት፤ ፔንጤም ሆነ ወይም ኦርቶዶክስ አልያም ካቶሊክ ሁሉንም ምእመናን ጻድቅ የሚያደርግ ስራ አናይም፡፡ ከሁሉም ደግሞ መልካም ሌት እና ቀን ስለሰው ልጅ የሚቃትቱም አልጠፉም እና፡፡ ዛሬ ዛሬ የተያዘው ጥቂቶቹን ማጎልበት ሳይሆን ጥቂቶችን አጥፍቶም ወደአለም መደብለቅ ነው፡፡ሎጥ እግዚአብሄር የጠየቀውን ጥቂት አማኝ ቢያጣ ነው ብቻውን ተነጥሎ ከጥፋቱ እንዲሸሽ የተደረገው፡፡ ብዙውን ግዜ ግን እኛ እምነት ያለን ሰዎች ማንን እያገለገልን እንደሆነ እራሳችንን መመርመር ግድ ይለናል፡፡ ውነትም እውነተኛስ ብንሆን ኖሮ የሀጢያትን ውጤት ባላየን ነበር፡፡ ዛሬ የሀጢያት ውጤት ፊት ለፊታችን ላይ ተጋርጦ እያየነው ጆሮ ዳባ ልበስ ብለን ልባችንን አሳውረን እንገኛለን፡፡ በአፍሪካ ኢቦላ፤ በአረብ አገር የሚታየው መተራረድ የአየር መዛባቱ እና ቅጥ ያጣው ልቅነት በአለም ላይ መስፋፈቱ፤ በጋራ የሚጸለይበት ሁኔታ ተጋፍጦብን እያለ፤ ወጣቱን በሚደረገው እሰጥ አገባ ተሰላችቶ ከቤተክርስቲያን እንዲሸሽ ማድረግ በአጽኖኦት የምቃወመው ነው፡፡ ቤተክርስቲያን የእግዚአብሄር አገልጋይ እንጂ የሰው ስርአት መሆን አይገባውም፡፡ በዚህም የተነሳ ለፍቅር ለሰላም ቅድሚያ ሁሉም ስፍራ መስጠት አለበት፡፡ አንድ በፈረንጆች የምጽሀፍ ቅዱስ ትምህርት ተለይቶ ያየሁት ነገር፤ አንዱ አንዱን አየተችም፡፡ ቄሱ መጽሀፍ ቅዱሱን ይከፍታል፤ ቃል ያወጣ እና ስለዛ ብቻ ሰብኮ ይሄዳል፡፡ ሁሉም ይህን ያደርጋሉ፡፡ አንዱ ሌላውን የሚያነሳበት አጋጣሚም ሁኔታም የለም፡፡ በቃ ከዛ ጨርሶ ሁሉም ሲገናኝ፡፡ ካቶሊኩም ከኢቫንጀሊካኑ ጋር ሌላውም ጋር በመስሪያቤት ወይም በተለያየ ቦታ ሲገናኙ ስለሀይማኖት አያወሩም፡፡ እንዳውም ስለማህበራዊ ችግሮቻቸው ይወያያሉ፡፡ ምክናያቱም የአገሩ ሰላም የሚከበረው እና ሁሉም እንዲሕ በተለያየው ቤተክርስቲያን ተገናኝተው አምልከው የሚለያዩት አንድ አይነት ቴማ አላቸው፤ እሱም ስለፖለቲከኞቻቸው ስራ እድገት የመሳሰሉ፤ በነጻ እኩል መወያየት ነው፡፡ ስለዚህ ወዳጆቼ፤ መድሀኒአለም የምህረት እና የሰላሙ ንጉስ እንደመሆኑ ሁሉ፤ ሁሉም የእኔ ይበልጥ የእኔ ብቻ ትክክል እያለ የሚወዳደርበት አገር ላይ ፖለቲከኞቻችንንም እርቅ እና ሰላም ጸልየን ልናስተራረቅ ምህረት ልንደራረግ አንችልም፡፡ ጠንካራ ልብ ጠንካራ ነገር ይገጥመዋል እና፡፡ ሁሉም ልበ ደንዳና ሆኖአል፡፡ እግዚአብሄርን ማንም ሊወስድብኝ አይችልም፡፡ አማላጅም አልኩ አላልኩ አገሬ ሰላምዋ የሚዘልቀው በሀይማኖትም ምጉት እና መናናቅ ሲቀር ብቻ ነው፡፡ በነገራችን ላይ የሁሉም ሀይማኖት ለእራሱ ትክክል ነው፡፡ አገሪቱ ግን የሁሉም ናት እና፤ ሰላም መሰጣጠት ከቤተ እምነት ይጀምር፡፡ ለእግዚአብሄር ማንም ወኪል ሆኖሎት ሌላውን በቃላትም ሆነ በመሳሪያ የምንዋጋለት ደካማ አምላክ አይደለም፡፡ እሱ ግን ስለእኛ ይዋጋል፡፡ ግን ወደሀይማኖቱ በፍቃደኝነት የሚመጡትን ማስተማር እንጂ፡፡ እኛ ሁሉንም የፓርላማ ሰው ፔንጤ፣ ኦርቶዶክስ፣ ሙስሊም አልያም ሌላ ለማድረግ አንችልም፡፡ ሁሉም በዚች በኢትዮጲያ ምድር ተፈጥሮአል፡፡ ሁሉም ደግሞ ስለእራስ ማውራቱን ትቶ ስለእኛ ማለት አለበት፡፡ አንዱ ሰላሙ ከተደፈረ፤ ሌላው ሰላም ሊኖር አይችልም እና፡፡ በቸር ኑልኝ የምላችሁ ባዩሽ ነኝ፡፡
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen