Montag, 18. August 2014

ከፖለቲካ ባሻገር፤ ያልታየው የባህሪ ለውጥ




አሁን ከፌስ ቡክ የምለይበት ወቅት በመሆኑ፤ አጠቃላይ ሀሳቤን በዚህ ጹሁፍ ላቀርብላችሁ ወደድኩ፡፡ የመሰነባበቻም ይሆነን ዘንድ በማሰብ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት ሊሰፍን ባለመቻሉ ኢሕአዴግን እንወቅሳለን፡፡ ግን የህግ የበላይነት እንዲከበር የእያንዳንዱንም ህብረተሰብ ክፍል አጋርነት ይጠይቃል፡፡ ይህም አጋርነት በሰፊው ሊታይ ያልቻለበትን አጋጣሚዎች ለማየት አገሬ የቆየሁበት ጊዜ እረድቶኛል ፡፡ ይህም ሁኔታ ተቃዋሚም ወደ ስልጣን ቢመጣ ይለዋጣል ብዬ ለመገመት እቸገራለሁ፡፡ እህት በወንድሙዋ ከቤቱዋ ብትፈናቀል፣ ባል ሚስቱን ቢደበድብ፣ የሰውን ንብረት ሰው ቀምቶ   ቢክድ የመሳሰሉ ነገሮች ሁሉ፤ ለመፋረድ ጉልበት እና አቅም የለለው ክፍል ኢሕአዴግ ነው እንዲህ ያደረገን ብለን እንኮንናለን፡፡ ይህ ሁሉ ስከታተለው ለአንድ ሰው አንድ ፖሊስ ያስፈልግ ይሆን? ብዬ የወታደር አገዛዝ ምንአልባት በአካባቢያችን የተሻለ ተቀባይነት እና የተሻለ የእርስ በእርስ መከባበር ወይም የደካማውን የሕይወት ሁኔታ ለማስከበር  የተሻለ አመርቂ ውጤት አምጥቶ ሊሆን ይችላል ብዬ ገመትኩ፡፡ ጭካኔዎች አሁን ባለው ኢሕአዴግ ጊዜ እየታየ ነው፡፡ ጭቃኔዎች ስል በህብረተሰቡ መካከል የሚደረገውን የእርስ በእርስ ግፍ በማስተዋሌ ነው፤ ከፖለቲካ ባሻገር፡፡ ብዙ እህቶች ከውርስ የገዛ ቤተሰቦቻቸው ሲያስወጡዋቸው እና ለወንድም፤ ወንድ በመሆኑ ውርሱ ሲሰጥ እና እርሱዋም ሜዳ ላይ ስትወድቅ ያየሁት አጋጣሚ ይህ ነው አይባልም፡፡ በሴት ላይ ብቻ ሳይሆን ይህ በገዛ ዘመድ ወይም በሀሰት ሰነድ ሰዎች በተመሳሳይ ችግር ሲጨናነቁ ማየት የዘወትር ልምዳችን ሆኖአል፡፡ ይህ ሁሉ ግን የህግ የበላይነት ኖሮ ወንጀል የሰራው ቢከሰስም፤ ነገሩን ለመቁረጥ አስቸጋሪ እና አሰልቼ በመሆኑ አሸናፊው ክፍል በዳዩ ይሆናል፡፡  ይህ ብቻ ሳይሆን ለጠበቃ ገንዘብም ማግኘት አትችልም፡፡ በሙስና ያልገባም ጠበቃ ለማግኘት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ በግል ቂምም በመነሳት በሀሰት ወደእስር ቤት የመወርወር ሁኔታ የተለማመድን አንጠፋም፡፡ ይህ ሁሉ በደል የሚፈጸመው በአሰራር ጉድለት እና በአፈጻጸም ጉድለት እንጂ፤ ያለው አስተዳደር በህግ ስለደነገገው አይደለም፡፡ ህግ ካለአስፈጻሚው ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል እና፡፡ይህ የግለሰቦች የባህሪ ጉዳይ የሚመታው ነው፡፡
ብዙ ግፎች በህብረተሰቡ ውስጥ እንዲፈጸም የሚያደርገው ኢሕአዴግ ብቻ ስለፈለገም ሳይሆን የወቅቱ የማተሪያል ፍላጎት ማደግ እና ብሎም የመሬት ጥቅም ማወቅ ያመጣው የእድገት ውጤት ነው፡፡ በቃ ከሰው መሬት የበለጠበት ጊዜ በመሆኑ ሽጦ ለመጠቀም ወይም ብቻዬን ልስራበት የሚለው ሁኔታ፤ በአገሪቱ ውስጥ ልክ ባህል የለለው እና መንግስት አልባ እንዲሆን የማስመሰል ሀይል አምጥቶልናል፡፡ መንግስትም ቢሆን ተቃዋሚዎች ልብ በሉልኝ እዚህ ላይ፤ መንግስትም ቢሆን ለአንድ ሰው አንድ ዳኛ አንድ ፖሊስ ሊያቆም አይችልም፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፤ ውልና ማስረጃ እንኩዋን ወደን ያፈራረመንን ሰነድ አንዱ ሲፈልግ አፍራሽ ሆኖ አካኪዘራፍ ብሎ ሽጉጥ ይዞ የሚነሳበት የግንዛቤ አልባ ስድነትን የተቀናጀንበት አካባቢ ላይ መኖራችንን መዘንጋት የለብንም፡፡ ይህ ሁሉ ህጋዊ ለማድረግ ወይም ወደህግ ለማምጣት አቅም የለለን ሰዎች የምናማርረው ኢሕአዴግ እንዲህ አደረገን ብለን ነው፡፡ እኔ ብቻ የሚለው እራስን ወዳድነት የተጠናወተው በአንዱ እሬሳ ላይ ተሸጋግሮ እራሱን ማሳደግ በመሆኑ ይህን መሰል ነገር ለማረጋጋት የኢሕአዴግ መንግስት የቻለው እስከማይመስል ድርስ እያየነው ነው፡፡ በውነትም ህዝብ አብሮ አስፈጻሚ ካልሆነ አንድ ፓርቲ አንድ አገር ላይ ህግን የበላይ ሊያደርግ  ከቶም አይችልም፡፡ ካደረገ ሀይል ጠተቃሚ ይሆናል እንጂ ህግ አስፈጻሚ ሊሆን አይችልም፡፡ ህግ የህዝብን ፍቃደኝነት የሚጠይቅ ሃይል ነው፡፡ ወንጀል ፈጻሚውም ከመካከሉ ይኖራል እና፡፡
ከላይ የጠቀስኩዋቸው ነገሮች ስር እየሰደዱ የሄዱት እና ዛሬ መግታት ያልተቻለበት ምክናያት ፤ኢህአዴግ ምንም አይነት የፖለቲካ ስራ ከመስራቱ በፊት ዘሎ የገባው ልማት የሚለው ነገር ላይ በመሆኑ ነው፡፡ መጀመሪያ የኢንቬስትሜንት ጥቅሙም ሆነ የሚመጣው ሳካ ሳይገናዘብ እና በደርግ ተጽእኖ ስር ወድቆ በፍርሀት የኖረውን ህብረተሰብ ነጻነትም ምን እንደሚመስል ሳያሳይ፤ ልማት ብሎ እንቅስቃሴ መጀመሩ መረበሽን አምጥቶአል፡፡ ይህም ቢሆን  ቀውስእና ቀላል የማይባል መወናበድን ያመጣ ሁኔታ ነው፡፡ የአሰሪን ጥቅም ያላወቀ እንደጠላት ያየዋል እና፡፡ እኛ ግን አንዳንድ የባህሪ ለውጦች አስፈላጊነት ከመነጋገራችን በፊት እና ግንዛቤ  ከመጨበጣችን በፊት የተጋፈጥነው ነገር በማተርያል እድገት እንጂ በአይምሮ ወይም በአስተሳሰብ አልነበረም፡፡ ይህ የሁዋላ ሁዋላ ኢሕአዴግን የሚያስደነግጠው ነገር ቢሆንም፤ መሰረት የለለው ጅማሮው ጉዳዩ ግን ህዝቡን  ወደመደነጋገር ሊከተውም ችሎአል፡፡ አይምሮ ሳያድግ እድገትበማተርያል ሲታሰብ የሚያመጣው ቀውስ ሙስናን እና ህገመንግስትን ያለማክበር ጉዳይ ይሆናል፡፡ ሕገመንግስትን ጥቅሙን እና የሚችለውን ችሎታ ማሳየት የገዢው ፓርቲ ስራ ሆኖ ሳለ፤ ይህንን ግን በተግባር ማሳየት ማስመስከር አልቻለም፡፡ መንግስትን አለማክበር ማለት በሕግ የበላይነት አለመተማመን መሆኑን ያልገባው ስራ አስፈጻሚ በእራሱ አንገት ላይ ገመድ እንደማስገባት ሆኖአል፡፡ ያየሁት ሁኔታ ህግ አክባሪው ተርበትብቶ ሲኖር፤ ህግ አፍራሹ ግን ደረቱን ነፍቶ የሚሄድበት ሁኔታ ለኢሕአዴግ ተቃዋሚ የተመቻቸ መንገድ እንደከፈተለት መሆኑን አይተናል፡፡ ተቃዋሚ ምንግዜም በውድቀት ላይ የሚያተኩር  በመሆኑ በቂ የሆነ እንቅፋት ለገዢው ፓርቲ ማዘጋጀት የሚከብድ አልሆነም፡፡ ይህ ስልት በማንኛውም አለም ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚሰሩበት በመሆኑ፤ ኢሕአዴግ መስራት የነበረበትን ጥሎ፤ ግን ሲናገር የነበረው ሁሉ የተቀዳጀውን ድል ልማት የሚለውን ብቻ ነበር፡፡ ውድቀቱን እና የገጠመውን እንቅፋት እራሱ በይፋ ቢናገር ኖሮ ተቃዋሚን ሽባ አድርጎ በጣለው ነበር፡፡ ምክናያቱም ያሉትን ጥፋቶች መመልከቱ እና ማመኑ ስራ እንዲሰራእና እንዲሻሻል ያደርጉት ነበር እና፡፡ ሕዝብ የጠፋውን እያየ፤ ገዢው ፓርቲ እንዳልጠፋ ዝም ቢል ወይም ሀሰት ነው ቢል፤ ያንን ጥፋት ተቃዋሚ ደመቅ አድርጎ አውጥቶ ስለሚጠቀምበት ህዝብ ንን ሲሰማ፤ እውነተኛ የሚያደርገው ተቃዋሚውን እንጂ ገዢው ፓርቲን አይሆንም፡፡ ይህ አሰራር በሁሉም ያለ እንጂ ኢትዮፒ ላይ ብቻ ተነጥሎ የሚታይ አይደለም፡፡ ተቃዋሚ የሚያዳምጠው የህዝብን የልብን ትርታ ሲሆን፤ ገዢው ፓርቲ ግን የተቃዋሚን ሆነ፡፡ ያም ሆነ ይህ ተቃዋሚ ሊመለከት ያልቻለው ነገር ደግሞ ሁላችንም ከእራስ ወዳድነት እና ከኢኮኖሚ ድህነታችን የተነሳ የምናደርገው ውስጣዊ መካካድ፣ መበዳደል እና ክፋት በእሱ ጊዜ ደህና ሊሆንም አለመቻሉን ነው፡፡ ኮለኔር መንግስቱም  ቢሆኑ በብዙ ምሳሌ የህዝቡን ከእሳቸው ጎን አለማበር ይናገሩ ነበር፡፡ እንዳውም ዛሬ ኢሕአዴግ ተሸሎ ሕዝቡ እንደሚያብረው ይናገራል፡፡ ግን እኔ እራስን ለማጽናት ካልሆነ በቀር፤ የህዝቡን አጋርነት ሳይሆን የማየው መሰላቸትን ነው፡፡ ምክናያቱም ብዙ መንግስት የለለ የሚያስመስል በስራ አስፈጻሚው እና በህብረተሰቡ መካከል የተዝረከረከ ነገር ይታያል እና፡፡ በዚህም የተነሳ ማንኛቸውም የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቃዋሚም ሆነ ገዢው ፓርቲ ትልቅ የሆነ የስራ እንቅፋት እንደገጠማቸው እናውቃለን፡፡  ለትክክለኛ ዲሞክራሲ ለውጥ እንቅፋት ሊሆን በሚችለው ነገር ላይ የባህሪ ለውጥ ለማምጣት የሚያደርጉት የማነቃቂያ እና የግንዛቤ መስጠት ስራ ሲሰጡ አይታዩም፡፡ እንዳውም ሁሉም የሚነጋገሩበት ነገር የተፋጠጡበት ነገር ወደመበቃቀል የጥላቻ ዘመቻ እየሆነ እያየነው ነው፡፡ ሁሉም ጀብደኛነትን ለማሳየት እንጂ ትክክለኛ ለውጥ በአገራችን ላይ እንዴት ሊመጣ ይችላል የሚለውን ሊሆን አልቻለም፡፡ ሁለቱም የሚያደርጉት የጥላቻ ዘመቻ ደግሞ የህዝብን አጋርነት ሊያስገኝላቸው አልቻለም፡፡ ኢሕአዴግም ስልጣን መያዙ ብቻ በቂ ነው ብሎ ከገመተ የሕዝብ ድጋፍ ምንያህል ጥቅም እንዳለው ለመመልከት አቅም አጥቶአል ማለት ነው፡፡ ህዝቡ ችግር አለ ብሎ ቢገምትም ተቃዋሚዎች እራሳቸውን ሳያስተካክሉ የሚያደርጉት የፕሮፖጋንዳ ስራም ለህዝቡ ድጋፍ ማገኛ መሆኑ ቀርቶ እንዳውም መደነጋገሪያ ሊሆን ይችላል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ሁለቱም ገዢውም ሆነ ተቃዋሚ ፓርቲ ሃያሶስት አመት ያህል አይጥ እና ድመት ሆነው ኖረዋል እንጂ ለሕዝቡ ያመጡለት የፖለቲካ ንቃተ ህሊናም ሆነ ለውጥ ስለለለ፤ ገዢው ፓርቲም ተረጋግቶ እንዲገዛ፤ ወይም ተቃዋሚ አስቸኩዋይ ለውጥ እንዲያመጣ የሚያደርግ ግንዛቤ  ለህዝቡ ሊፈጠሩለት አልተቻላቸውም፡፡ ደግሞም እኛ የሚለውን ነገር እንኩዋን መፍጠር ያልቻሉ ሁለቱም ተጻራሪዎች እንዳውም እኔ ወደሚለው ስግብግብነት እና እራስን ወዳድነት እየነዱን እንዳይሆን እፈራለሁ፡፡ ሁለቱም የሚጠቀሙት ስልት፤ ተቃዋሚን እንዳታነጋገር ደግሞም ገዢው ፓርቲንም እንዳታነጋግር በማለት ሆኖአል፡፡ እንግዲህ ይህ ወደየት እንደሚወስደን ዝም ብሎ ማየት ነው፡፡ እኔም ሁለቱም ቢያኮርፉኝም ባያኮርፉኝም ቀድሞም ለማያውቀኝ ብዙም አልጨነቅ ብዬ ይህንን ለመጣፍ አሰብኩ፡፡   በዚህም የተነሳ በአሁኑ ሰአት ተቃዋሚም ሆነ ገዢው ፓርቲ የኢትዮጲያ ህዝብ ጋር የሚያስተዋውቃቸው ሳይሆን የሚያስተዛዝባቸው ነገር እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ በማለት ነገሬን እዚህ ላይ በመቁዋጨት፤ ፊስ ቡኬን ለመዝጋት የመጨረሻ ደብዳቤዬን  ይዠ በሚቀጥሉት ቀናቶች ብቅ እላለሁ የምላችሁ ባዩሽ ነኝ፡፡

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen