Montag, 6. April 2015

የፋሲካው የንስሃ ጥሪ




            ምን አልባት ወያኔ ኢሕአዴግ ያመጣው የብሄር መደራጀት የሚለው ነገር ጥሩ አስበው ሊሆን ይችላል፡፡ እኔ ግን ጥሩነትን ያየሁበት  ነገር የለም፡፡  አሁን ፓርቲውን ለመውቀስ ሳይሆን፤ ፓርቲው ግን የጠነሰሰውን ጥንስስ፤ ተጣርቶ እንዳይጠጣ የተከፈተው የስነልቦና ጦርነት አስቸግሮናል፡፡ አልያም በተቃራኒው  የጥንንስሱን ወጤት እያጠጡን ከሆነም፤ መራራ ሆኖብናል፡፡  የጥቂት የደነቆሩ እና ሞኝነት ያጠቃቸው ሰዎች አሉእና፡፡ እንግዲሕ እነዜህ በገዛ ቀያችን አካባቢ እንኩዋን በአፋቸው በሚወጣው በጸያፍ ቃሎቻቸው አንገታችንን እንድንደፋ ተደርገናል፡፡ እነሱን እንጂ አምላካችንን እንዳናስብ ጎዳናው ላይ ቆመውብናል፡፡ መሳሪያነታቸውን ለማን እንደሆነ እነሱ ያውቃሉእና፡፡ የእግዚአብሄርም  ህግ ተጥሳለች የምድርም ህግ አድሎ አላትእና፡፡ በዚህ የተነሳ ሰው የገዛ ብሄሩን አፉን ቢጠብቅ መልካም ነው በማለት ጠሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡ ሰው እግዚአብሄርን በማመን ይናገራል እና፡፡ ካልሆነ ተመልካችነት እና አዳማጭነታችሁ፤ በዛም ላይ ልኩን ነገረው፤ ልኩን ነገረቻት በማለት ማፌዝ እና ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት  ከግብረ አበርነት የዘለለ አይሆንም፡፡  የማይለወጥ እየመሰለው ሰው አንድን ብሄሩ አሸናፊ ሆኖአል በሚባልበት አዋጅ ተከትሎ ሌላውን ብሄር ሊደመስስ የሚችል ነገር፤ ሊያፍን የሚችል ነገር መስራት እውን የኢትዮጲያ ህዝብ እምነት የለውም እን? ሰገዳችን በባዶ መስጊድ፣ ቅዳሲያችን እና ዝማሬያችን በባዶ ቤተክርስቲያን እንዳይሆን ልብ እንበል፡፡ የበላዩ እግዚአብሄር ብቻ ነው፡፡ ወዳጀ ሆይ አሸናፊነትስ ሌላውን ለመጫን ከሆነስ ባታሸነፍ በተሻለሕ ነበር፡፡ አምላክስ ሰው ሌላውን እንዲጫን ማሸነፍን አይሰጥም እና፤ ምንአልባት ጥሩ መሪ አድርጎ መርጦህ ሳይሆን፤ ለሚወደው ህዝብ  ጥሩ ቀጪ አድርጎህ ሊሆን ይችላል እና መጽሀፍን መርምር፡፡

            ብሄር የሚባል ሁሉ  ዘር ከብሄር መደነጋገር እና መሳሳት የገዛ ብሄሩን ህዝብ ያውጣ፡፡ በዘለፋ እና በብቀላ እድገት ከቶም አትታሰብም እና፡፡ ሰው የገዛ መሞቻውን የፍርድ ትእዛዝ በእጁ ይዞ ይጉዋዛል ፖስታውን ከፍቶ እምነቱ እንዳያነብ አድርጎታል እና፡፡ ሰው የዋህም ነው ሞኝም ነው፡፡  ምንአልባት በስነልቦና ላይ አንዱ ከአንዱ ዘር የመብለጥ ግንባታ በሰው ልጅ ትእዛዝ ተደርጎለት  ሊሆን ይችላል፡፡ ሌላውም የመኖር መብት አለው እና፤ በዚህ ሁኔታ ላይ ተፋጣችሁ ከመኮራረፍ ከመነጋገር ከመጣላት ከመደበቅ ከማፈር አፋችሁን ከፍታችሁ፤ በብሄራችሁ  ስም የሚያጠፋውን ሰው ተው ብሎ መገሰጽ የሰውነት ግዴታችሁን እንድትወጡ አሳስባለሁ፡፡ በዚህ ውስጥ ብዙ የተጎዳ ልብ አለእና፡፡ ልቡ ያለቀሰበት ሞልቶአል እና፡፡ ልብ የእግዚአብሄር ማረፊያ መሆኑን እወቁ፡፡ አፍ ግን የሰይጣን፡፡ ከእግዚአብሄርስ መጥፎ ትፈልቃለችን? ሁሉ ነገር እንደነበረ አይሆንም፡፡ ዛሬ ያዋረደ ነገ በእራሱ ላይ መርገምት ስቦአል እና፡፡  የሚገርመው አፋቸውን ከፍተው ዘርን የሚዘልፉ ሰዎች፤ ብዙ ግዜ ያለውን መንግስት ከለላ በማድረግ፤ በተለያዬ አነስተኛ የሆነ ድጋፍ የተሰማሩ በብዛትም ሴቶች ናቸው፡፡ እባቡዋም በሴቲቱ በኩል ማለፉ እና አዳምን እንዳሳተው ይነገራል እና፤ ይሕን የተገበሩ ዛሬ በባአላቱ ማስተዋሻ ፋሲካ ያስታውሱ፡፡ በፋሴካ የእስራኤል ህዝብ ቡሃቃውን ያጥባል፡፡ ያለፈውንም እርሾ ለሚመጣው አያስተላልፍም፡፡ የተባረከ ህዝብ ይህንን ለመረዳት እንዴትስ ያጣዋል፡፡ በረከትን የሚበላስ ህዝብ አርባ ቀን ጾሞ እንዴትስ ክፋትን ይሰራል፡፡ እንዴትስ እግዚአብሄር አይታየውም፡፡ እንዴትስ ስብእናን አይጠብቅም፡፡ እንዴትስ ሰውን ይገፋል፤ ጎረቤቱን ያሳድዳል፡፡ እንዴትስ ጥጋብ የሚበርድበት ግዜ መምጣቱን አያውቅም፡፡ እግዚአብሄር የሚያጠግብህ የራበህን ዘመን የሚያስረሳ እና ከላይ ከላይ እንድትሄድስ እንዳልሆነ አታውቅምእን? 

           ልብ በሉ፡፡ የገዢውን ፓርቲ ስም የሚጠቀሙ እና የእግዚአብሄር ማደሪያ የሆነውን የሰው ልብን የሚሰብሩ፤ ለትናናሽ ከርሳቸው የቆሙ ናቸው፡፡ ይህን ማለፍ የማንገባው ነገር በመሆኑ የዛሬው የፋሲካው ጥሪዬ ይህ ይሆናል፡፡ ፔንጤም በፔንጤ ስም፤ ኦርቶዶክሱም በኦርቶዶክስ ስም፤ ሙስሊሙም በሙስሊም ስም መከታ በማድረግ የሰውን ስብእና እየመረጡ የሚንዱትን ጌታ ይገስጻቸው፡፡ የሰው ልጅም እነዚህን ሰዎች አይተባበር፤ የእግዚአብሄር መንፈስ በዚህ ዘመን ለአንተ ለእራስህ የሰውንመንፈሱን እንድትመረምር አድርጎአል እና፤ ከቶም ክፉ መንፈስ የሰፈረበትን ሰው ለማየት ለአንተም አይሳንም፡፡ ትችላለህ እግዚአብሄር ይህ ማድረግ አይቻለውምን? በስሙ ይሁን ያላችሁት ይሆናል፡፡  በእግዚአብሄር መንገድ ተጉዋዝ፡፡ አይንህንም የእሱን ያድርግልህ፡፡  በላይታቸው ላይ ብዙ የመርገምት እንባ ፈሶአል እና፡፡ ለሰው ድብቅ ከእንግዲህ አይሆኑም፡፡

        ምንአልባት የበላዩ የቤተ መንግስት ሰዎች፤ ሰውን የተማረረበትን ያውቁ እንደሁ እኔ አላውቅም፡፡ ነብይ አይደለሁም እና፡፡ ነብይም ከሰው መካከል የተመረጠ ነውእና፡፡  ካላወቁ አሁን ይወቁ ብዬ ከማስተላለፍ በቀር የምለው የለኝም፡፡  ትንሽ ወረድ እንዲሉ እና እግዚአብሄር የፈጠረውን በዘሩ ብቻ እያሳደዱ የሚዘልፉትን ማሳሰቢያ ይስጡ፡፡ ይህ በእነሱ ዘመን ተፈጽሞአል እና፡፡  መሪዎችም ቢሆኑ፤ ሰው ተብለው ተፈጥረዋል፡፡ እንደሰውም እንዲያስቡ ግድ ሊላቸው ይገባል፡፡ ሰውን የሚያስተዳደር ባህሪም  ከተላበሱ እንደአውሬ ሳይሆን እንደሰው ስብእናን አስበው ያስተዳድሩ፡፡ ካልሆነ ግን ማንም ከእግዚአብሄር በላይ አይሆንም፡፡ እሱንም አስሮ ቤተመንግስትም ሆነ በየቤቱ በየአድባራቱ  ያስቀመጠው  ንጉስም ፓስተርም ሆነ ማንም አካል የለምእና ሀሰተኛ ነብዮች የሚነግሮአቸው ካሉ ይቆጠቡ፡፡ እንዳውም በባዶ ቤት ጩሀት እንዳይሆን፡፡  እግዚአብሄርን እንኩዋን ጥላቻ አንግቦ ፤ በፍቅርም ማርኮ ለእራሱ ብቻ የሚያደርገው አንድም አካል አይኖርም፡፡  አንድም ብቻውን ስለተጣለ ስለተገለለ እግዚአብሄር የለውም የሚል ማንም ሰው በእጁ መረጃ የለውም፡፡ ካመንን ኤልያስን እናስታውስ፡፡ ናዮሚን እናስታውስ፡፡  የተጠሉም እና የተገለሉም የመንፈስ ዘራቸው የለመለመ ሆኖአል እና፡፡ ይሁን ያልከው ይሆናል፡፡  

          ፍርድም እሩቅ አትሆንም እና፡፡  እግዚአብሄር የትም ሁን የትም በክፉዎች መካከል ነውር በሚታይበት ቦታ ሁሉ አይገኝም፡፡ ተኩዋርፎ ሰገዳ የለም እና፡፡ አመጸኛ ልብ ይዞ መዘመር የለም እና ይህንንስ ጌታ ቆሞ አይቀበለውም፡፡ ሎሌው ጌታው የለለበት ቦታ ይንበረከካልእን? እንኩዋንም ንጉሱ መላአኩም በነውር ቦታ አይገኙም፡፡ በአጠገብህም የለለው እንዴትስ ሊያማልድህ ይነሳል፡፡ ወዳጄ ሆይ እርቅ የማያደርግ ልብ ብቀላ የሚያስተላልፍ ነውእና፤ ዘመንን ቆጥሮ ሊበቀል የሚመጣ የእግዚአብሄር ከቶም ሊሆን አይችልም፡፡ ቅድም አያትህ ይህን ሰርቶአል ያን ሰርቶአል የምትለኝ አንተ በዛን ወቅት ነበርክን? ሰውነታችን ስድብ ጠግቦአል እና ቤታችንን ለቀናል፤ መጽሃፍ ቅዱስን ሰቅለናል፡  ቤተክርስቲያንን በሰዎች የተነሳ ሸሽተናል፡፡  የገዛ ዘመዶቻችንን፤ የገዛ ጎረቤቶቻችንን የገዛ ፖሊሶቻችንን የገዛ ገንዘባችንን ለእኛው መሰደጃ ያደረጋችሁ እግዚአብሄር የሚፈርድባችሁ ዘመን ይመጣል እና በየትም ያላችሁ ንስሃ ግቡ፡፡ ፋሲካውም ገናውም እኛስ በልባችን አለእና፡፡ ተሳልሜ የምሄደው ሳይሆን ይዠው የተሰደድኩት መድሃኒአል በልቤ አለእና፡፡ አካባቢን መልቀቅ የሰቆቃ ጉዞ አድርጋችሁብናል፤ አንገታችንን እንድንደፋ ሆኖአል  እና ፤ ልብ ግዙ እርስበእርሳችሁ ብሄራችሁን ከሚያደርጉት ድርጊት እንዲቆጠቡ ልብ በሉ፡፡ በተለየም እምነት አለኝ የሚል እግዚአብሄርን እየሸነገለ እንዳይሆን ልብ ይበል፡፡ ሁላችንም በተሰጠን ቃዬ ስቀን እግዚአብሄረን አመስግነን መኖር እሱ የሰጠን መብት ነውእና፡፡ ይህንስ የሚያነሳው የሚጠፋ እንጂ የሚለመልም ተክል አይሆንም፡፡  እስራኤልም ወደቤትዋ የተመለሰችበት ዘመን እሩቅ አልሆነም፡፡ የንስሃ ፋሲካ ያድርግልን፡፡ በቸር ባዩሽ

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen