Donnerstag, 2. April 2015

እባካችሁ ተረዱኝ /3/



.
ምእራፍ 3
ሕግ የተጉዋደለበት ሰው፤ አልያም ሲጉዋደል ያዬ እና ያላስቻለው ሰው ቢጮህ፤ አይምሮው የተነካ ሊባል ይችላል፡፡ „እብድ“ የሚለው ቃል፤ የዘመኑ የተመቻቸው ሰዎች ላልተመቻቸው መግለጫ ሆኖአል፡፡ እንዚህ ሰባአዊነትን የማያውቁ ግለሰቦች እራሳቸው ህግን የሚዳፈሩ እና የሚያጠፉ ናቸው፡፡ ስለዚህ ባሉበት የኑሮ ደረጃ ላለመውረድ፤ ሌላውን „እብድ“ ቢሉት አይገድም፡፡ ሌላው ደግሞ እነሱን ሌባ ለማለት አይቸኩል፡፡ „ሌባ“ ብሎ እብድ የተባለ ቢሳደብ ጤነኛ እብድ አያስመስለውም፡፡ እሱ ዝም ብሎ ቢጮህ ይሻላል፡፡ የጤነኛ እብድ ጩሀት አንድ ቀን ሌባውን ያደነቁረዋል እና ስፍራ መልቀቅ ያመጣል፡፡ ስለዚህ አንተ የአገርህ ህግ መጉዋደል ያሳበደህ፤ „ እብድ“ ተብዬ ዝም ብለሕ ጩሕ፡፡ጤነኛው አንተ መሆንህን እግዚአብሄር ያውቃል እና፡፡ ቀጥል ጩህ፡፡
       ግን አንድ ነገር አለ፡፡ ለመሆኑ የአገር ጉዳይ፣ የመብት ሁኔታ፣ የሰላም ኑሮ ፣ የአድሎ ጉዳይ፣ ዘረኝነት፣ ምቀኝነት፣ ድህነት፣ ሕግመጉዋደል፣ የመናገር ነጻነት ማጣት፣ ካለሙስና አለመንቀሳቀስ፣ አድርባይነት እና በመካከላችን ውስጥ ያለውስ አምባገነንነት ግፍ እና መከራ የማያሳብደው በሽተኛ ያልሆነ ማን ይሆን? አገሩ ሆኖ ባእድ ሆኖ የሚኖረው፤ አገሩ ተገፍቶ መኖር ፈርቶ የሚሸሸው እንዳይጮህ እንዲታፈን ማነው አዛዡ፡፡ አያችሁ አሁን እኔ የማወራው ስለኢህአዴግ፤ ቤተመንግስቱን ብቻ የሙጥኝ ማለቱ አይደለም፡፡ ግን የእነሱን ሁኔታ ተጠቅሞ በየጎናችን የሚደነፋብንን፣ የሚሰድበን፣ የሚያዋርደን እና በገዛ አገራችን በገዛ ቤታችን በገዛ ቀያችን በገዛ ገንዘባችን አላስቀምጥ ያለውን እስኪ ላነሳሳው፡፡ የአምባገነኖች በሰላማዊ ዜጎች ውስጥ የሚያመጣው የስነልቦና ቀውስ ይህ ነው የሚባል አይደለም፡፡ አምባገነን ካለ የሰው ልጅ እርስ በእርሱ በህዝብ መካካል ስልጣኑን መለማማጃ ደካማው እና ጠባቂ የለለው እንደሚሆን አንድና ሁለት የለውም፡፡ ስለዚህ ነው በህዝብ መካካል የተሰወረ የጥፋት የማንአለብኝነት ቀውስ የሚፈጠረው፡፡
       እኔ ባዩሽ አበበ ነኝ፡፡ ገጠመኞቸን ሳጫውታችሁ ቆይቻለሁ፡፡ የታደለ ያነባል እና የሚጨብጠውን ይጨብጣል፤ የማያነብ ደግሞ ተጨባጭ ነገር በለለው ከላይ ከላይ ወይ የገዢ ፓርቲ ደጋፊ ይሆናል ወይም የተቃዋሚ፡፡ በሀሰት ፍርድም ይጠመዳል፡፡ እምነቱም የምታታበታል፡፡ ወዳጄ ለዚህ ነው ተጨባጩን ነገር ለመረዳት አንብብ የምልህ፡፡ አንብበህ እራስህን ትመረምራለሕ፡፡ ደግሞም ሌላውንም ትታዘባለህ፡፡ ከዛም መብት መደፈርን ተመልከትህ ሚናህን ትለያለህ፡፡ ማንበብ የሚረዳው የአንተን አስተሳሰብ ወይ ያጸድቅልሃል አልያም ይቀይርልሃል፡፡ ሰው እኮ የሚጮህበትን ምክናያት ምንአልባት ገዢው ፓርቲ አልተረዳም ይሆናል፡፡ ችግር መኖሩን ወያኔ ኢሕአዴግም ይናገራሉ ይላሉ፡፡ ችግሩን ግን መኖሩን የሚያምን ሳይሆን መፍታት የሚችል ነው ያሚያጉዋጉዋው፡፡ ታዲያ ሶስተኛው ክፍል መጻጽፌን „እባካችሁ ተረዱኝ“ የሚለውን በዚህ መልኩ አቀረብኩላቸሁ፡፡መቼም ለመረዳት እናንተን መለመኑ አሳፋሪ ቢሆንም ግን ለግንዛቤ ለመለዋወጥ አይን ያውጣሁ ለማኝ ሆኛለሁ፡፡ ለኪስ ከመለመን የሰውን ልጅ አስተሳሰብ የሚቀይረውን ለአይምሮ ሲባል ሰውን መለምን ይሻላል ብዬ አምናለሁ እና፡፡ አይምሮእና ህሊና አገርን ያድናል ይታደጋል፡፡ ሕሊናው የማይወቅሰው፤  አገርን ለአደጋ አሳልፎ ይሰጣል፡፡
              በደርግም መጨረሻ ወቅት ላይ ነበር ናፍቆት አስቸግሮኝ ከብዙ ዘመን ስደት በሁዋላ ወደአገሬ የተመለስኩት፡፡ የሚያነጋግረኝ ሀኪም፤ „ ባዩሽ የአገር ናፍቆት ችግርሽ መሆኑን ነው የማየው፤ ይህም ሌላ አካባቢ መኖር አንዳትቀበይ ከማድረጉም በላይ እድገትሽንም ገቶ ይይዛል“ በማለት ደመደመ፡፡  አገሬን እንደምወድ እና በባህሉም እንደተሳሰርኩ እንዲህ ሲል አስረዳኝ፡፡ „ሌላው አካልሽ  ሁሉ ፍጹም ጤነኛ እና ሊያደግ የሚችል ነው፡፡ አይምሮሽም ማመዛዘን የሚችል፡፡  ይህ ደግሞ የነበሩበትን የሚያውቁትን ባህል መውደድ እና መናፈቅ የመታመም አይደለም፡፡ ጤነኛ አይምሮ ማድረግ የሚችለውን እያደረገ ያለ አይምሮ ነው ያለሽ፡፡ አንቺ የተቸገርሽው ናፍቆትሽ ወደሕመም ሊያመጣ እንደሚችል አለመገመትሽ ነው፡፡ ስለዚህ ለዚህ መድሃኒቱ አገርሽ ተመልሰሽ መኖር፤ አልያም እዛ ያለውን ነገር ዘግተሸ መመለስ ነው፡፡ እኔ አገርሽ ያለውን ፖለቲካ መቀየር አልችልም፡፡ ስደት እኮ ጉዳት አለው፡፡ ከአገርሽ የወጣሽው እመለሳለሁ ብለሽ እንጂ፤ እዚህ ኢኮኖሚው ስለተሻለ እኖራለሁ ብለሽ አይደለም፡፡ ስለዚህ ያለመመለሱ ዘመኑ በጨመረ ቁጥር መጎዳት አለ“፡፡
           ዘወትር የጎደለኝን ነገር ለማወቅ የምጥር ሴት ነኝ፡፡ አንዱ ከድህነት ለመላቀቅ ያተኮርኩበት ሲሆን ሌላው ደግሞ መብት እና የመናገር ነጻነትን የምፈልግ ግልጽ ሰው ነኝ፡፡ በቃ ለግልጽነቴ ኢትዮጲያ እንደማይመቸኝ፤ ሀኪሙ ቢነግረኝም፡ ግን ደግሞ የተወለድኩበት አካባቢን ማጣት ስነልቦናዬን ፈተና ውስጥ እንደከተተው፤ አይኔን የከፈተልኝ የማነጋግረው ሀኪም ነበር፡፡ መድሃኒት አላዘዘልኝም እንጂ መድሃኒት ወስጀ ወይም አልኮሆል ጠጥቼ የኢትዮጲያን ናፍቆት ለመርሳት በደነዘዝኩ ነበር፡፡ ሀኪሙ ያለኝን ነገር ዘወትር አስበዋለሁ፡፡  ያለኝ ነገር „ይህንን ጤነኛ የሆነ አካልሽን አይምሮሽን በመድሃኒት ማደንዘዝ አላስፈላጊ ነው፤ በትችይ ቆርጠሸ አገር መግባት ነው፡፡ ያነዬ ለውጥን ታያለሽ“ ነበር መደምደሚያው፡፡
 በእርግጥም የጀርመኑን የተሰጠኝን ፓስፖርት መልሸ ነበር፤ በኢትዮጲያ ዜግነት የተመለስኩት፡፡ እንደእውነቱ ከሆነ ገና በጀርመን የኢትዮጲያን ዜግነቴን የያዘውን ፓስፖርቴን ስጨብጥ ነበር ማንነቴ ውስጥ ለውጥ ማምጣት እና መረጋጋትን በር ያሳየኝ፡፡ በእርግጥም ደርግን ፈርቻዋለሁ፡፡ የተረሸኑትን ወጣቶች ስም ስም ዝርዝር ከሰማሁ በሁዋላ እንደደነገጥኩ አውቃለሁ፡፡ እንደእና በልጅነት እና በአዋቂነት ሽግግር ላይ የነበሩ ስለነበሩ፡፡ ምንድነው አገር ማለት ፤ ወጣት ወጣትነቱን የማይለማመድበት ብዬም ተስፋ ለመቁረጥ የዳዳሁበትን ያንን እድሜ አስታውሳለሁ፡፡ ያስፈራል፡፡  ግን መጨረሻ ላይ ደርግ መራራት ይዞ ስለነበር፤ ሁሉም ይህንን የናፍቆት ሲቃዬን ያዩ ወዳጆቼ ብርታት ሰጡኝ፡፡ እንዳውም ከወዳጆቼ እና ከሚወዱኝ ፈረንጆች መካከል አንዱ አብሮኝ ወደአዲስ አበባ ለመጉዋዝ ወሰነ፡፡ ጀርመኖች ለሚወዱት እና ላመኑት ሰው መስዋእትነት ይወስዳሉ፡፡  የኢትዮጲያ ኢምባሲውም ምንም ችግር የለም፡፡ እንኩዋን እሱዋ ምንም የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ የለለችበት ይቅር እና፤ እነሚኤሶንም፤ ኢሕአፓም፤……. ዛሬ ፖለቲከኞችም እኮ እየገቡ ነው በማለት እኔን በማጣጣል ተናገረ፡፡
ውነትም እኮ ዶ፤ክተር አይደለሁ ፕሮፌሰር፡፡ ተራ ሰው፤ ተራ ስደተኛ ነኝ፡፡ የተራ ሰው ችግሩን ማን ያውቃል ማን ይገነዘባል? ሁልግዜ ታላላቆች ብቻ የሚደመጡበት ኢትዮጲያችን፡፡ ችግርም ምቾትም በእነሱ ብቻ ወስነዋት የሚንቀሳቀሱ ይመስላሉ፡፡ ህዝብ የትምም ምክክር ላይ ተጠርቶ አያውቅም፡፡ ፈርመው ግን ተቀበሉት ይሉናል፡፡ ዘወትር  ስደተኛውን ተራ የሚያደርገው እኮ የተቃዋሚ ተለጣፊ ነው ስለሚባል ነው፡፡ በዚህም ሁኔታ የህዝብ ችግር  ትኩረት ስቦ አያውቅም፡፡ መረጠ አልመረጠ፤ እራሱን ለመረጠ ፖለቲከኛ ምን ፋይዳ አለው፡፡ ንቄቱም ከዚህ የመጣ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ ለመሆኑ ምን ችግር ነበር ያሰደደሽ ብሎ የሚጠይቅ ማንም ይለም፡፡ ለምን ግን ተሰደድክ ቁጣ እና ጅራፍ ማግለል ግን ይቀድማል፡፡ ይቺ ናት ፖለቲካችን፡፡ በተራነትም የተሰደደው ስደተኛ ምንያህል እንደሚያውቅ፤ ገዢ ፓርቲዎችም ፖለቲከኞችም ግንዛቤ የላቸውም፡፡ ህዝብ ግን እነሱን ተገንዝቦ አላምጦ ተፍቶአችዋል፡፡ ለዚህ ነው ዝምታው ፡፡ በአገራችን ሁሉም ለመግደል ወደሁዋላ የማይሉ ናቸውእና ይፈራቸዋል እንጂ አያከብራቸውም፡፡    
        ድሮም እራሴን ከፍ አድርጌ ስለማላውቅ፤ በኢምባሲው ንግግር አልተደናገጥኩም፡፡ ከእኔ ይልቅ የእነሱ አገዛዝ የፈጠሩብን  ችግር በእኔ ላይ ይበልጣል እና፡፡  ለእንባሲው አነጋጋሪዬ ግን አንድ ነገር ሳላስበው ከአፌ ወጣብኝ፡፡ በወቅቱ ወጣትነቴም  ለድንገተኛ ድፍረቴ አስተዋጽኦ ነበረውእና፡፡ „ እንዳፍዎት ያድርግልኝ“ ነበር ያለኩት፡፡
ውነትም ምን ችግር አለ ብገባ እንድል እና እንድደፋፈር በጀርባየ ያለው የኢትዮጴያ ብሎም የደሴ የልጅነት ትዝታ እያደፋፈረኝ መጣ፡፡ በጀርባዬ ያዘልኩት ትዝታ ሁሉ የወደፊቱን ኑሮዬን ዘግቶ ጠፍሮ ይዞት ስለነበረ፤ ለማንኛውም እድገቴ እንቅፋት ሆኖአል፡፡ እኔ በ1969 እንደኢትዮጲያ አቆጣጠር ስወጣ ከልጅነት ወደ ወጣትነት እየተሸጋገረ ያለ አስተሳሰብ የያዝኩ ነበርኩእና፤ለማስተዋል ልጅ ለመርሳት አዋቂ ፡፡ በደሴ ከተማ፤ ፒያሳ ላይ እና ሆጤ ሜዳ ላይ፤ የተጫወትኩት አሆይ ወለሎ የጥምቀት የልጃገረድ ጨዋታ ከአይምሮዬ አልወጣም፡፡ የማስታውሰው በሕብረት የሰራሁዋቸውን ነበርእና፡፡ምን ታየኛለህ አንገት አንገቴን፤ ወደሐኝ እንደሁ ለምን አባቴን፡፡ እናምን ይላል ይህ ጉታናው ዋሾ፤ ሲሸሽ አየነው ጌሾ ለጌሾእያለን የምንቀባበለው ስርአትን እና ጀግንነትን ለጉብሉ እየነገርን ያዜምነው ምክር አዘል ግጥም እስከአሁን አልረሳውም፡፡ ቤተሰብ ያለውን ለእኛ አስተላልፎልናል፡፡ እኔ ግን የስደት ህይወቱ እና የተናጋው የኢትዮጲያ ፖለቲካ ለሌላ ለማስተላለፍ ማነቆ ሆነኝ፡፡ በዚህም የተነሳ፤ የድሮው እንደመጥፎ እየታዬ፤ ጠቃሚውም እና ምንም አይነት ጉዳት የማያደርሰው ነገር ሁሉ እንዲጠፋ እየተደረገ ሄደ፡፡ ዛሬ አሆይወለሉ ማን ደፍሮ ይጫወተዋል፡፡ ሁሉም በሜካአፕ እና በማናውቀው ሬጌ ፣ አልያም ሁዋትስ አፕ እና   ኩል እና ራፕ በሚባሉ ነገሮች ተተካ፡፡ ሁሉ አይኔ ላይ እንደእራእይ እየመጣ ስላስቸገረኝ፤ ወደ ኢትዮጲያ ደርግ ሊወርድ አካባቢ በድፍረት ገባሁ፡፡ ቀጣዩን እውነተኛ ገጠመኞሸቼን በክፍል 3 ይከታተሉ፡፡

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen