የሕይወት
ልምድ በጨለፍታ
እና ታላቅ የፈጣሪ ችሎታ ምስክርነት
የሚገርመው
አንድ ግዜ ሆስፒታል ገብቼ ነበር፡፡ እሱም ካንሰር አለብሽ ተብዬ ነው፡፡ ለእኔም ይህ ሁኔታ በጣም አስደንጋጭ እና አሳዛኝ ነበር፡፡
ጭራሽ የሚገርመው ከጎኔ ማንም የሚያጽናናኝም አልነበረም፡፡ አንድም ሰው፡፡ አዎ ከሰው ተፈጥሬአለሁ፤ ግን ምክናያቱን በማላቀው ነገር
ከኢትዮጲውያን ወገኖች ያልታደልኩ ሆኛለሁ፡፡ ውነት እግዚአብሄር ይህን አውቆ ይሆን ባልበሰለ እድሜዬ ጀምሮ ለፈረንጅ አገር ያበቃኝ፡፡
ፈረንጅ አገር ዘመድ የለለውንም የሚያስታምም፤ የሚያበላ የሚያጠጣ፡፡ በዚህ የተነሳ ነው አንድ አገር ላይ ጥሩ ሲስተም ያስፈልጋል
ብዬ የህግን የበላይነት እንዲሰፍን የምናገረው፤ የምተቸው፡፡ ካንሰር አለብሽ የሚለው ነገር በእጅጉ አስደንግጦኝ ስለነበር፤ ያልደወልኩበት
ዘመድ አዝማድ ጎረቤት የአገር ሰው የለም፡፡ ወይም የማውቀውን ሰው ሁሉ ደውያለሁ፤ ግን አንድ ሰው ብቅ ብሎ ያጽናናኝ የለም፡፡
የሚገርመው እነሱ ጉንፋንም ሲይዛቸው ዘመድ አዝማድ ያጅባቸዋል፡፡ አይቻለሁ በእህቶቼ በወንድሞቼ፡፡ እነሱ ግን አለሁበት ቦታም ቢገኙ
ብቅ ብለው ሊጠይቁኝ አልፈለጉም፡፡ ሌላ ቀርቶ በስልክ እንኩዋን የሚጽናናኝ አላገኘሁም፡፡ እኔ ግን ድንጉጥ ነኝ አልቃሻ ነኝ፡፡
እንዳውም ዛሬ ዛሬ ሳስበው፤ ሰውን እንዳፈቀርኩት የፍቅር ምላሽ ባገኝ ኖሮ፤ በእግዚአብሄር ሳይሆን ዘመድ ወገን ጉዋደኛ አምላኪ
ሆኘ እቀር ነበር፡፡ ባጠቃላይ ብቸኛ ነበርኩ፡፡ ወልጄ መታረስ የሚባል አላውቅም፡፡ ሰው ጭክን ያለብኝ ሴት ነኝ፡፡
ይገርማል
ከቶ ለዚህ ይሆን ወደዚሕ ወደተረጋጋ ሲስተም፤ ዘመድ አዝማድ አብላኝ አጠጣኝ የማትልበት አገር ከልጅነቴ ጀምሮ ከወሎ አውጥቶ አዲስ
አበባን አቁዋርጦ እዚህ ቁጭ ያደረገኝ፡፡ እውነት ነው፤ አስቀድሞ የሚጨነቅልህ ጌታ ብቻ ነው፡፡ የወደፊቱን የሚገጥምህን እሱ ያውቃል
እና ያዘጋጃል፡፡ ግና ከበሽታው ይልቅ ጠንከር ያለብኝ ዘመዶቼ ምንእንደሚያስቡ እና የዘመድ ሀቅ ባለመወጣታቸው አዘንኩ፡፡ በጣም የፈለኩዋቸው ወቅት ነበር፡፡ ነፍስ እንኩዋን የተጋደለ ይቅር ይባባላል፡፡
ያለፈው 23 አመታት ሙሉ የሰው ትም የጠማን ብቸኛ ነበርኩ፡፡ እነሱ ተሰባስበው የሚደርጉት ነገር ሁሉ ላይ ተጋብዠም አላውቅ፡፡ ሰርግ እንኩዋን
ደግሰው የሚነጥሉኝ ትዝ ሲለኝ እረበሻለሁ፡፡ ግን ጌታ እኔ እያለሁ ይላል፤ ሁሉነገሬን ማቃለል ዘዴ የሚዘይድልኝ አምላኬ፤ አይምሮዬን
ባይቆጣጠር ኖሮ የምሆነው ትዝ ሲለኝ ከክርስቶስ ጋር ያለኝ ፍቅር ጭራሽ ጥብቅ ክርር እንዲል ያደርገዋል፡፡ ክርስቶስ አዎ ፍቅር
ነው፡፡ ወድ ወዳጆቼ ይህን የምጽፍላችሁ የግድ ስለአምላኬ መመስከር ስላለብኝ ነው፡፡ ክርስቶስ ያልተወኝ ያልጣለኝ፡፡ ሳያንኩዋካ የሚገባው፡፡ የሚያጽናናው፡፡
የካንሰሩ
ጉዳይ ቀኑ ደርሶ ወደ ኦፕሬሽን ልገባ ስል፤ ደም ስለሌለሽ ቶሎ ወደ ክፍልሽ በቶሎ ላትመለሽ ትችያለሽ ብለው የሚረብሽም ነገር ጨመሩልኝ፡፡
አዎ ኮማ ውስጥ የሚያስገባ ሪስክ ላይ ነሽ በማለት በካንሰሩ ላ ጨመሩልኝ፡፡ የመጨረሻውን ልጄን ወልጄ ገና ሶስት ወሬ ነበር፡፡
በደስታ የወለድኩትን ልጅ በሁለታችን መካካል ልዩነት ሊያመጣ ሰይጣን በሰፊው ሊገዳደረኝ እንደተነሳ አወኩት፡፡ ሁለት ለየት ያሉ
ህልም መሰል እራእዮች ግን አይቼ ነበር፡፡ ስለእግዚአብሄር እምነት እንጂ አካሄዱን የማላውቀው ግን እስከዚህም እራእዮቹን ማጤን
አላሰብኩም፡፡ ተውኩት እረሳሁት፡፡ ብዙ ህልም የማላየው ግን መልሶ መላልሶ ወደህልሙ እሳባለሁ፡፡ ግን ነገሮች ሁሉ ልክ እንደህልሙ
መቀጠል ጀመረ፡፡ መጀመሪያ ምንም ደም ሳያስፈልገኝ፤ ሀኪሞቹም እንዳሰቡት ሳይሆን ኦፕሬሽኔን ጨርሼ ወዲያው ቆም አልኩ፡፡ ይገርማል
ኦፕራሹኑም አላመመኝም መድሀኒት ማደንዘዣም አላስፈልገኝም፡፡ እኔ ግን ስለህልሙም ስለእግዚአብሄርም አላስብም ነበር፡፡ የማስበው፤
የሚጎበኘኝ ሰው ይመጣል፤ አበባ ይዘው ቸኮላቱን ምናምኑን ይዘው፤ ብሶቴን ሊካፈሉ ቁስሌን ሊጠይቁኝ፡፡ ግን የጠበኩዋቸው የውሃ ሽታ
በመሆናቸው አዘንኩ፡፡ ከቁስሉ ይልቅ ህመም የሆነኝ ሰው አልባነቴ ነበር፡፡
የተኛሁበት
ሆስፒታል ጀርመን ውስጥ በጣም ትልቁ እና ምርጡ ነበር፡፡ ያለሁትም ካንሰር የታመሙ ጀርመኖች መካከል ነው፡፡ በአሰቃቂ ሁኔታ ያሉ
መካካል ተኛሁ፡፡ መጽሃፍ ቅዱስ ብቻ አጠገቤ አለ፡፡ በዛን ሰአት ስድስት አመቱ የነበረው ልጄ አጠገቤ መጥቶ ጋደም አለ፡፡ „ማማ
አይዞሽ ስትሞቼ አበባ ሁልግዜ መቃብርሽ ላይ ይዠልሽ እመጣለሁ አልልይሽም፡፡ ትናፍቂኛለሽ እና፡፡ ግን ማማ አንዳንደዬ ከመቃብሩ
መውጣት አትችይም፡፡ ለመቻል ግን ሞክሪ“ አለኝ፡፡ አዎ ትሞታለች
የሚል እንጂ አይዞአችሁ ድና ትመጣለች ብሎ ያጽናናቸው ወዳጅ እንዳላገኙ ተረዳሁ፡፡ ሰይጣን የሚያውጀው በእኔ እና በልጆቼ ላይ ፍርሀትን
መለየትን የመሳሰለ ነገር ነው፡፡ ደግሞም የተኛሁበት ሆስፒታል ልጆቼ ካሉበት እራቅ ያለ ስለነበር የማያቸው በሳምንት አንድ ቀን
ብቻ ነው፡፡ አልጋ ላይ ጋደም እንዳልኩ ዘወትር አንዲት መስቀል በመስኮቱ እራቅ ብላ ትታየኛለች፤ እኔም እሱዋን እያየሁ አነባዬን
አፈስ ነበር፡፡ ያቺ በእሩቅ ለች ቤተክርስቲያን ጫፍ ላይ ያለች መስቀል
እግዚአብሄርን ዘወትር እንዳስበው አደረገችኝ፡፡ አጠገቤ የተኛችው
ሁለቱን ጡቱዋን የተቆረጠችው አንዲት ምሁር ሴት አልፎ አልፎ ታጫውተኛለች፡፡ „ ታድለሻል ፕሮፌሰሩ ሁላ የወድሻል“ በማለት የታዘበችውን
ትነግረኛለች፡፡ አዎ በጣም ነው የሚንከባከቡኝ፡፡ እኔም ሳቅ ስለምወድ ፈገግታ ከፊቴ አይጠፋም፡፡ ካንሰር ግን ተስፋ አስቆርጦኛል፡፡
የልጆቼ ነገር አሳስቦኛል፡፡ ጥርሴ ይሳቅ እንጂ ውስጤ ግን ቀልጦአል፡፡ ሀኪሞች ምን ቢወዱኝ ካንሰርን ከሌላው የተለዬ ፈውስ ታአምር መፍጠር አይችሉም፡፡ ሶስት ሳምንት ከተኛሁ በሁዋላ ግን፤ አንዲቱዋ
ዶክተር ጠራችኝ፡፡ እኔ ስጠባበቅ የነበረው የትኛው ኦርጋኔ ይወጣ
ይሆን? መቸስ የኬሚካል ትርቲመንቱን እቀጥል ይሆን ብዬ ተጨናንቄአለሁ፡፡ የሚያረጋጋ ታብሌትም እንድወስድ ጠይቀውኛል፡፡ የተኛሁት
ስንት ማሽን አፋቸው፣ አፍንጫቸው እና አካላቸው ላይ የተተከሉባቸውም አሉ፡፡ አንድ ክፍል ሁለት ብቻ ብንሆንም በአጠገባችን ያለው
ሁሉ በአሰቃቂው ካንሰር የተለከፈ ነው፡፡ ህክምናውም አሰቃቂ እና ህመም ያለው ነው፡፡ እተጠራሁበት እዶክተሮቹም ቢሮ እንደገባሁ ፊት ለፊት ተቀመጥኩ፡፡ የምታነጋግረኝ ዶክተሩዋም እንዲሕ ስትል
መናገር ጀመረች፡፡ „ እኛ በአንንቺ ውስጥ ታይቶአል የነበረውን ካንሰር
አጥተነዋል፡፡ በጣም የሚገርም ነው ብላ ሳትጨርስ ተወርውሬ አንገቱዋን ተጠመጠምኩባት፡፡ በጀርመን አገር ሰው ደስ ሲለው ዘሎ ማቀፍ
ነው፡፡ እሱዋም እኛ ኦፕሬሽን በማድረጋችን አዝነናል በማለት በማዘን ተደናግጣለች፡፡ የእኔን መልስ የጠበቀችው እንደሚመስለኝ፤ ንዴት
አልያም ወይ እከሳለሁ ምናምን እንድል መሰለኝ፡፡ እኔ ግን በተለያዩ
ሀኪሞች ጋር ሄጀ ካንሰሩ አለብሽ እንዳውም በጣም አግሬሲቭ ስለሆነ በአስቸኩዋይ ኦፕሬሽን አድርጊ ተብያሉ፡፡ እኔም ሀኪሙዋን፤ አትጨነቂ
አልኩዋትእና ካንሰሩ ነበር ግን እግዚአብሄር አስቀድሞ ፈውሰኛለው በማለት >ያየሁትን ህልም ልነግራት ጀመርኩ፡፡
በህልሜ አንድ ሰው ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፡፡ እሱም የወረደበት ቦታ ላይ ብዙ ህዝብ ተሰልፎ ይጠባበቀው ነበር፡፡ እኔም ከተሰለፉት
ውስጥ ሶስተኛ ተራ ቁጥር ላይ ነበርኩ፡፡ እኛም ፈራጁእና ፈዋሹ ስለሚመጣ እሱ ጋር እንቀርባለን ብለን ነበር ወረፋ የያዝነው፡፡
ግን ይህን የምነግርሽን ህልም ያየሁት ሀኪሞች ካንሰር እንደተገኘብኝ
ሳይነግሩኝ ቀድሞ ነው፡፡ ተራም ደርሶኝ ፈራጁ እና ፈዋሹ ጋር ቀርቤ
ነበር፡፡ እኔ ገና ምንም ሳልናገር፤ „እዚህ ምን ታደርጊለሽ ፈውሸሻለሁ
ብየ ነግሬሽ የለምእን ?ለምን አታምኒም? ብሎኝ ነበር አልኩዋት፡፡ ግን የቀውስ ንግግር እንደሚመስል አውቃለሁ፡፡ እንኩዋን
ለፈረንጅ ያውም ሳይንስን በሚያምኑ ሀኪሞች እምነት አለን ለሚሉ ሰዎችም
ይከብዳል፡፡ እናም ለእራሴ አልተቀበልኩትም ነበር እና ቅዠት መስሎኝ ነበር፡፡ ይህን ህልም ያየሁት ኦርቶዶክስ ውስጥ እያለሁ ነው፡፡ ለነገሩ እሱዋን ተሰናብቼ ከሆስፒታሉም እንድወጣ ተነግሮኝ ወደክፍሌ ሄድኩ፡፡
ክፍሌም
ገብቼ ትንሽ ጸጥ በማለት አንድ ወቅት ያየሁትን ህልም መሰል እራእይ
ትዝ አለኝ፡፡ ያለምኩት ጀርመን ሆኘ ነው፡፡ ግን ህልሙ ተውኒቱ ኢትዮጲያ ነው፡፡ እንዲህ ልንገራችሁ፡፡ ብዙ የኢትዮጲያ ህዝብ የተሰበሰበበት
አንድ አካባቢውን የማውቀው አንባ ላይ እኔም እዛ ተገኝቼ አየሁ፡፡ ግን እኔን አንድ በፍጥረቱ እንደእስስት የሚመስል አውሬ በጥርሱ
የእጀን አንገት ነክሶ ይዞታል፡፡ እኔም እጅግ ተጨንቄ እጮሃለሁ፡፡ የሚያላቅቀኝ አጥቼ እራወጣለሁ፡፡ ድንገት ግን አንድ በፈረስ
ላይ የተቀመጠ ሰው እየጋለበ ይመጣል፡፡ ሌሎች ፈረስ ጋላቢዎችም አጅበውታል፡፡ እሱም ወደእኔ በመገስገስ መጣእና „እጅሽን ወዝውዠው
አይዞሽ ወዝውዥው“ በማለት እተለዬ ፈረስ ላይ የተቀመጠው ሰው በፈረሱ ዙሪያዬን ይዞረኝ ነበር፡፡ እኔም በሃይል ወዘወዝኩት፡፡ ያ አውሬም ተምዘግዝጎ በእርቀት ከእኔ ተለይቶ
ወደቀ፡፡ እጄን ግን በጥርሱ በስቶት ምልክት ትቶ ነበርእና፤ እንደገና
ሰውየውን እየተከተልኩ ነክሶኛል መርዞኛል መርዞኛል ስል ተመልሶ እየጋለበ መጣናእና ከመቅጽበት እጁን እራሴ ላይ ጫን አድርጎ „ፈውሸሻለሁ“
በማለት እንደውሃ በሚፈስ ድምጽ „አይዞሽ አይዞሽ ተፈውሰሻል“ እያለ እንደመጣ ከመቅጽበት ከህዝቡ መሃል ወጥቶ ይሄዳል፡፡ ብንን
ስል ግን የነከሰኝ አውሬ ከፊቴ ሊጠፋ አልቻለም፡፡ ወዳውም ለአንድ ቅርብ ሰው ህልሙን ነገርኩት፡፡ እሱም እና አትጨነቂ እባክሽ
እኔ አንድ ግዜ አለም ጨልሞ አይቼ ነበር፡፡ ግን እስከአሁን አልጨለመም በማለት ሊያስቀኝ ቢሞክርም እኔ ግን ያ አውሬ ሳቄን ወስዶታል፡፡
የሆነ ፈተና እንደሚመጣብኝም ብረዳ ግን ፈውሸሻለሁ የሚለውን ለማመን እኔ ማነኝ ፈውስን አያለሁ በማለት እምነቴን እራሴን መመርመር
ጀመርኩ፡፡ ህልሙ ህይወቴን ቀየረው፤ መጽሃፍ ቅዱስንም ማንበብ ጀመርኩ፡፡
ልጄን ወልጄ ኢትዮጲያ ይዠ ልሄድ ስነሳ አሞኝ ላደረኩት ምርመራ ካንሰር የሚል ምላሽ በስልክ ተደወለልኝ፡፡ በአስቸኩዋይ ወደኦፕሬሽን
እንደሄድ ተወሰነ፡፡ አስቀድሞም ኢትዮጲያ ለመሄድ ፕላን ነበረኝ እና ኦፕሬሽን ሳልገባ ለመሄድ ወስኜ ስለነበር ወደኢትዮጲያ ሄድኩ፡፡ ግን ደስታዬን ሁሉ ያ አውሬ ቀይሮታል፡፡ አውሬውም
ካንሰር ሆኖአል፡፡ ኢትዮጲያም ደሴ እንደሄድኩ የሚካኤልን ባእል ለማክበር ወደደሴ ሚካኤል አመራሁ፤ ግን እዛ ከነበረበት ቦታ ሚካኤል ተነስቶ ሌላ ቦታ እንደሆነእና እዛም ቤተክርስቲያኑን ለመስራት የመሰረት
ድንጊያ ስለሚጣል በሙሉ ህዝቡ እዛ ነው አሉኝ፡፡ እኔም ወደዛ አመራሁ፡፡ ብዙ ህዝብ ተሰብስቦአል፤ የአመቱ ሚካኤል ነበር እና፡፡
አንድ ነገር ግን አስደነገጠኝ፤ እነዚህ ሰዎች ልክ አውሬውን ነክሶኝ እንዳየሁት ተሰባስበዋል፡፡ ጀርመን ሳለሁ ያየሁት ህልም አንባውም
ቦታውም ይህ እራሱ ሆኖ አገኘሁት፡፡ በድንጋጤም ለየት ብዬ ቁጭ አልኩ፡፡ እግዚአብሄር አይሳሳትም፡፡ ሰው መቼም
ሰው ሲመሰክርለት ለማመን ይሳነዋል፡፡ እኔም ብሆን በዛን ወቅት ሰው ቢመሰክርልኝ ለማመን እቸገራለሁ እና፡፡ ሳይንስ ቀዶ ስለሚያረጋግጥ
እና መረጃ ስለሚያቀርብ እነሱ የሚሉትን ቶ እንቀበላለን፡፡ ግን እግዚአብሄር
የሚያደርገው ማዳን ሳይቀድ ሳያደማ በመሆኑ ለማመን ይቸግራል፡፡ ከሆስፒታሉ ስወጣ ያቺ ሁለቱንም ጡትዋን የተቆረጠችው ምሁር ሴት፤
የምታነቢው ግን ምን ነበር አለችኝ፡፡ እኔም ባይብል ነው አልኩዋት፤ እኔ ግን አንብቤው አላውቅም በማለት አርቃ ወደዛች እኔ ስተኛ
ወደማያት በሩቅ ያለች ቤተክርስቲያን ተንጠራርታ አያየች በሃሳብ ሰመጠች፡፡
እኔም መልካሙን ተመኘሁላትእና ከሆስፒታሉም ሀኪሞቹን አመስግኚ ወጥቼ ሄድኩ፡፡ ይህ የሆነው ከአስራ ስምንት አመት በፊት ነው፡፡
እንኩዋን በካንሰር በጉንፋንም ወደሀኪም ቤት ሄጀ አላውቅም፡፡ በእርግጥ በኢትዮጲያ ውስጥ ያየሁት አንዳንድ ግፍእና መከራ ለስነልቦናዬ
ፈታኝ ሆነውብኛል፡፡ መቼም ኢትዮጲያ አገሬ ናትእና ትናፍቀኛለች፡፡ የህግ የበላይነት የማያውቀው አኑዋኑዋራችን በጣም ያሳስበኛል
ይረብሸኛል፡፡ ለእራስችንም ምን ያህል እውነተኞች እንሆን ብዬ እራሴን እጠይቃለሁ ፡፡ ሁልግዜ በፖለቲከኞች ላይ የምናሳብበው ነገር
ይበዛል፡፡ ግን ፖለቲከኞች ደግሞ የእኛን አጋዥነት የሚጠይቁ ናቸው፡፡ እራስን ወዳድነት እና ማንአለብኝነት በህዝብ ማሃል የገባ
ነው፡፡ ብዙ ጉዳቶች በውስጤ አሉ፡፡ የእኔን መሰል ደግሞ በሚሊየን ይኖራሉ፡፡ ብዙውን ነገር ግን አናወራውም፡፡ አንነጋገርበትም፡፡
የአስተሳሰብ ባህላችን የግልጽነት ሁኔታችን ለውጥ ካላመጣ፤ ጥሩ ሲስተምም መመስረት ቢቻል እውን ለማድረግ ብቃቱ ያጥረናል፡፡ የባህሪ
ለውጥ የአይምሮ እድገትን ያመጣል፡፡ ባህሪችን ሲለወጥ የሌላው አዘን አዘናችን ይሆናል፡፡ ከዚህ የህይወት ልምድ ተነስቶ እንግዲህ
ሰው እራሱን ይመርምር፡፡ ጌታ ከሁላችሁ ጋር ይሁን፡፡
ባዩሽ