የስም ድግስ
በኢትዮጲያ
የኢትዮጲያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተመካክረው በአንድ እስከአልመጡ ድረስ፤ ግልጽ የሆነ የሕዝብ ድጋፍ የሚያገኙ አይመስለኝም፡፡ ሁሉም ፓርቲዎች ተቀራርበው ወደአንድ ውህደት ለመምጣት ያልቻሉበት ምክናያት የፖለቲካ ጉዳይ ሳይሆን በጥላቻ የመተያየታቸው ጉዳይ ዛሬ ዛሬ እየመሰለኝ ሄደዋል፡፡ የፖለቲካ ጉዳይ ቢሆን መፍተሄ መቼም ባላጡ ነበር፡፡ እንደተማረ የፖለቲከ ሰው ከሆኑ ማለቴ ነው፡፡ እንግዲሕ እራሴን ግልጽ ላድርገውእና፤ ኢሕአዴግን ባለው ቀውስ ብቻውን ተጠያቄ ማድረግ ለእኔ እየከበደኝ መጥቶአል፡፡ ምክናያቱም ሕዝብ ተቃዋሚ ፓርቲ አለ የሚለውን ተስፋ እስከአላነሳ ድረስ መንከራተቱ እና መሰደዱ፤ መታሰሩእና መሞቱ አይቀሬ ነው፡፡ ህዝብ ተቃዋሚ የለም ካለ ግን አንገቱን ደፍቶ ለአንድ ኢህአዴግ ያድራል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አላችሁ ወይም የላችሁም ተቃዋሚዎች? እናንተ ችግራችሁን ፈትታችሁ ካልቀረባችሁ፤ እንዴትስ የኢትዮጲያን ህዝብ አንድ አድርጋችሁ ልታስተዳድሩት ትችላላችሁ? ስለዚህ እኔ በእናንተ በኩል ያለኝ ተስፋ እየመነመነብኝ ሄድዋል፡፡ ወይስ የእናንተ አንድ አለመሆን ምልክት የኢትዮጲያ መበታተን ይሆን? እኔ የፖለቲካ ሰው አይደለሁም ግን ይሁንና እያንዳንዱ የኢትዮጲያ ህዝብ በኢትዮጲያ ሰላም የሚያገባው ይመስለኛል፡፡ ኑሮው ከመክበዱ በላይ ብዙ ነገሮች በውስጣችን ብዙዎቻችንን እንዲደነጋገረን የማድረግ ተጽእኖ እየፈጠረ ያለው ሁሉም ነው፡፡ አንድነት እያሉ የሚለፈልፉ ፓርቲዎች አንድ ሆነው አናያቸውም፡፡ ለነገሩእማ የኢትዮጲያ ህዝብ በትእግስት አብሮ እየኖረ ይገኛል፡፡ ያልተስማማ ፓርቲ የሚያፈራው ያማይስማማ አባል ነው? ሁሉም የአባል ባለቤት ለመሆን ነውእን አባል የምትፈልጉት ወይስ አገሪቱን በትክክለኛው መንገድ ለመምራት? ስለዚህ ለውጥ ከእናንተ ካልመጣ እንወክለዋለን የምትሉት ህዝብ አምኖ ሊያዳምጣችሁ አይችልም፡፡ የእናንተ ጉዳይ እስረኛውን ካለማብዛት በስተቀር የተሸለ ነገር ያመጣል ብዬ መገመት አልችልም፡፡ ስለዚህ ባህላችሁን ቀይሩ፡፡
እግረ መንገዴን አንድ ልበላችሁ፡፡ ባለፈው የሆላንዱዋ ንግስት ለልጅዋ ንግስናዋን አወረሰች፡፡ ነገ ደግሞ የስፓንያው ንጉስ ካርሎስ ንግስናውን ለልጁ ያወርሳል፡፡ እኛ ለዚህ ያልታደልነው፤ ልቤ በቅናት ይቃጠላል፡፤ በቀሚስ ወይም በባል አልቀናም፡፡ የምቀናው በአገር መሪዎች ነው፡፡ ባልም ቀሚስም በአገር ሰላም ያምራል እና፡፡ ትናንት ሀይለስላሴ ያደረጉት ስህተት ዘላለም ሊይዙት የማይችሉትን እይዛለሁ ብለው፤ ለውጥን በሰላም ሳያሳዩን አለፉ፡፡ እኛም ተረግመን ነው መሰል ይህ እጣ ፋንታ ዛሬም ተከትሎን፤ ስልጣንን በሰላም መልቀቅ ልንላመደው አልቻልንም፡፡ እንደአሜሪካ አውሎ ንፋስ ስም ብቻ እያወጣን እና እየቀያየርን እዛው የፖለቲካ ባህሉን እያገላበጥነው እንገኛለን፡፡ እስኪ አንድ ተከፍሎ ስም የወጣለትን ስለ ዲያስፖራ ትንሽ ላነሳሳው፡፡
ዲያስፖራ
ዲያስፖራ፤ ኢሕአዴግ አገራችሁ ግቡ ካለ በሁዋላ ግን ዲያስፖራ ብሎ በከፈለ ስሜት ስም ሰጥቶ ተወልዶ ካደገበት አገር ከዘሩእና ከወገኑ ተለይቶ እንዲታይ ሆን ብሎ ያወጣለት ስም ባያተዋር እንዲሆን ሆን ብሎ ያደረገው ይመስላል፡፡ ስደት ሁሉም ተሰዶአል፡፡ ሁሉም ከአገር ወጥቶአል፡፡ ወያኔ ኢሕአዴግ እራሱ ኢትዮጲያ ወጣ ገባ እያለ የነበረ እና በጫካ የኖረ ነው፡፡ ተሰዳጁን ዲያስፖራ እንዳለው ሁሉ እራሱን ደግሞ የጫካው ብሎ ወይም ሌላ ስም መስጠጥ ነበረበት፡፡ እራሱን ባላባት አድርጎ እግሩን አስራርቶ፤ ዲያስፖራ የተባለውን ክፍል አየር ላይ አንሳፎ የቀረው ወያኔ ኢሕአዴግ፤ ግራ የሚያጋባ ፓርቲ እንደሆነ አንድእና ሁለት አይባልም፡፡ ይሁንና ግን ተቃዋሚም ቢሆን ለዲያስፖራ ለሚባለው ክፍል ቀሎ አልታዬም፡፡ ምክናያቱም ዲያስፖራው አገሩ ጉዋጉቶ ቢገባ እንደወያኔ ቀኝ እጅ ተደርጎ በብዙ መልኩ ኢታማኒ እንዲሆን መደረጉ ነው፡፡ ገረፍ አድርጌው ልለፍ እና፡፡ „ሀዘንሽ ቅጥ አጣ ከቤትሽ አልወጣ ሆኖ“፤ ዲያስፖራ ለተቃዋሚ ወያኔ ነው፤ ለኢሕአዲግ ደግሞ ተቃዋሚ ነው፡፡ የህ አለመታደል የሆነ ውንጀላ፤ ሁሉም አንድ የሆኑብኝ ምክናያት አለእና፡፡ ያልተለወጠ ነገር፡፡ ኢሕአዴግ አገሩን እንደልቡ በእጁ ይዞ ችግር እንኩዋን ቢደርስብህ ለመርዳት አቅም የለለው ስራ አስፈጻሚ ይዞ በህግ ይጫወታል፡፡ የሚጠብቀው ቤተመንግስቱን እንጂ ሕዝቡን ለመጠበቅ አቅምም የለውም፡፡ ለመሆኑ በፈለገውም ሁኔታ ቢሆን አገሩ የሚገባ በሁሉም መወንጀል አለበትእን?
አሳፋሪ ምግባሮች የሚታዩበት አገራችን፤ ሁሉም መተማመን የለለበት መንታ መንገድ ላይ ገብቶ ቆሞአል፡፡ ለመሆኑ ዛሬስ ከአገር የሚወጣው ሁሉም እውነት የፖለቲካ ችግር ኖሮበት ነውእን? እውነት ተርቦ ነውእን? አይደለም በነገው የማይተማመነውም ሀብታምም ልጁን ያሸሻል፡፡ ሁሉም ግን አንድ ቀን ዲያስፖራ ተብሎ ወያኔ በሰየመለት ስም ይገባል፤ ከዛም በባይተዋርነቱን ይኖራል፡፡ በተቃዋሚም ሆነ በገዢው ፓርቲ ዲያስፖራ እየተባለ የሚነገርለት ይህ ህዝብ ግን፤ ችግር የገጠመው የዲሞክራሲን አካሄዱን ስለሚያውቅ ብቻ ነው፡፡ ከዛም ወያኔ ኢሕአዴግ አያዳምጠውም ኢዲሞክራሲ የሆነ ምግባር አለውእና፤ ተቃዋሚም ያኮረፈው የማያምነው ሆኖአል፡፡ ሁሉንም ወያኔ፤ ሁሉንም ተቃዋሚ ብሎ በጥርጣሬ ማየት አገር መግባት ያመጣው ቀውስ ነው፡፡ አዎ ሁሉም አገሩን ይፈልጋል፡፡ ነውረነትም አይታየኝም፡፡ ይህን ክፍፍል ለምዶባችሁ እንዳይቀር እና የእቃ እቃ ጨዋታ እንዳይሆናባችሁ ወደመልካም ስራ ሁሉም ቢያስብ መልካም ነው፡፡ ካልሆነ ግን ህዝቡን እንዳው ድንግርግሩን ሁሉም ባያወጣው ምልካም ነው፡፡ ችግር አለ ግን ችግሩን የሚፈታውን መንገድ ሳትጨብጡ ሁሉም ህዝብን መወከል አይችልም፡፡ የኢትዮጲያ ህዝብ አማራ ነው፣ ትግሬ ነው፣ ኦሮሞ ነው፣ ጉራጌ ነው፣ ዲያስፖራ ነው………. ይህ ክፍፍል ለማስተዳደር ይቀል ይሆንን? ወይስ ዘላለም የማይቆየውን ስልጣን ለማራዘም? „ፈስ ያለበት ዝላይ አይችልም“ ሆነእና፤ እራሱን ያላመነ ሌላውን ማመን ይሳነዋል፡፡ የኢትዮጲያ ህዝብ ድምጹን የሚያሰማብት ገዢም ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚም የለውም፡፡ ምክናያቱም የፖለቲካ አካሄዳችሁ በጥላቻ የተሞላ እና በድብቅ ሚስጥር የተሞላ በመሆኑ፡፡ እስከዛው የኢትዮጲያን ህዝብ እግዚአብሄር ይሁነው፡፡
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen