Dienstag, 24. Februar 2015

ወጣቱን ማን አቅጣጫ ያሳየው?????



ወጣቱን ማን አቅጣጫ ያሳየው?????


እናንተ ኢትዮጲያውያኖች፤ በአሁን ሰአት ከበድ ያለ ጥላቻ ከየአቅጣጫው እየጎረፈ እንደሆነ በማህበራዊ ሚዲያ የሚደረገውን የእርስ በእርስ ስድድብ እና ዝልፊያ እየተመለከትኩ ነው፡፡ እውነትም ጥላቻን ማቆም የምንችልበት ሁኔታ እንደለለ እያየሁት ነው፡፡ ይህ እንዳይሆን፤ የእምነት ቤትም እንዲሁ ውስጡ ለሁለት የተሰነጠቀ አይነት ነገር ሆኖአል፡፡ የሀይማኖት መሪዎች የፍቅር አስተማሮነትን አዲዎ ብለው የተሰናበቱ አልያም ተስፋ የቆረጡ ይመስላል፡፡ ይሁን እና አለማችን ክፉና ደጉን በመለየት፤ ሚዲያዎችን ሁሉም እንደሚፈልገው ሄዶ እንዲስተናገድ የለየች ትመስላለች፡፡ ይህን ግን እኛ ኢትዮጲያውያኖች  መለየት ያቃተን ይመስላል፡፡ ይህ እንዳይሆን የፖለቲካ አቅጣጫ የሚያሳየን አላገኘንም፡፡ እንደዘወትሩ ፖለቲከኞች እርስ በእርሳቸው አይጥና ድመት ሆነው ተፋጠዋል፡፡ ጠበንጃም እየተማዘዙ ነው፡፡


ለማለት የፈለኩት፤ ምንም እንኩዋን በሕዝብ መካከል መደነጋገር እና አቅጣጫ ማጣት ቢኖርም፤ ግን ሁሉም አፉን ዘግቶ የሚቀመጥበት ዘመንን ያለፍን ይመስላል፡፡ ሰው ስሙን እና መልኩንም ቀይሮ የሚፈልገውን የተከለከለውን አልያም በተለምዶ መናገር የፈራውን፤ እየተናገረው ይገኛል፡፡  ፌስ ቡክ ከእንግዲህ ማንም ሊያግደው የማይችል ማህበራዊ ሚዲያ ሆኖአል፡፡ ሰውም የገነባውን ፍርሃት ከልቡ ሲያወጣ ብዙዎች እንደማያደርጉት እራሱን ይገልጣል፡፡ እያንዳንዱ ለእራሱ ጋዜጠኛ የሚያደርገውእና ውስጡንም አውጥቶ የሚዘከዝክበት ሆኖአል፡፡ ይህንም አለም በሙሉ ተቀብላ ይለፍ የሰጠችው ነገር ሆኖአል፡፡ የፈለከውን እንደፈለገህ የምታስተላልፍበት ዶሞክራሲን እነሆኝ ያለ ይመስላል ፌስ ቡክ፡፡ በውነትም ይህንም ሚዲያ የማይፈልጉት አምባገነኖች በአለም ዙሪያ በአገራቸው እንዳይኖር ጥረት ቢያደርጉም፤ ማቆም የማይቻል እራሱን ነጻ ያወጣ ግዙፍ ማንነት ይዞአል፡፡ ጭራሽ ወደፊት የኢንተርኔት አክሰስ በአለም ላይ ነጻ መተላለፉ ስለማይቀር፤ ፌስ ቡክ በግሎባል የምንጠቀምበት እና በየሜዳው፤ በየጫካው በየከተማው በቤት ውስጥም የሰው ልጅ ግንኙነት የደራ ይሆናል፡፡ በሀሳብ በፖለቲካ አመለካከት  የሚገናኙ የአለም ሰዎች በዚህ መልኩ አብሮነት ይፈጥራሉ፡፡ ግሎባል ማለት ይህ ካልሆነ ምን ይሆናል?


ጉዳያችንን የምንካፈልበት፤ ነውሮችም ይፋ የሚገለጥበት እና፤ አንዱ ህዝብ ለሌላው ህዝብ የሚታገልበት መሆኑ የማይቀር ሀቅ ነው፡፡ ባዩሽ ይህንን ዘመን ታያለች ወይ የሚለውን ስናይ ደግሞ፤ ምንአልባት ነው፡፡ አለም በአፋጣኝ በቴክኖሎጂ እያደገች በመሆኑ፤ እነዚህ ነገሮች አመትም ባልሞላ ግዜ ውስጥ ሊፈጸሙ ይችሉ ይሆናል፡፡ አለም ባላወቅነው እርምጃ ወደግሎባል እየገባች ነው፡፡ ስደቱ፤ ሀብት ማካበቱ ኢንተርናሽናል እየሆነ እያየነው ነው፡፡ የአለም ህዝብ ወይ ሀብት በማካበት አልያም በስደት እየተዛመደ መጥቶአል፡፡  


የኢትዮጲያ የፖለቲካ ንቃተ ህሊና እና አለም የደረሰችበትን  ሁኔታ ለማወቅ ባጣነው ግንዛቤ ግን ባህሪያችንን እየጎዳነው አይምሮአችንን ፈታኝ በሆነ ጠባብነት እየገደልነው እንገኛለን፡፡ በዚህም የተነሳ ሰው መነጋገር ሳይሆን መሰዳደብ መዘላለፍ ይዞአል፡፡ እንደእውነቱ የተቃዋሚውም ሆነ የገዢው ፓርቲ ደጋፊ የሚያደርጉትን የሚያወቁ አይመስልም፡፡ አልያም ጊዜያቸውን በቡዋልት እና በፌዝ በማሳለፍ የለመዱ ናቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ አንድ ነገር ግን የምናቀውቀው፤ ይህ በከፍተኛ ጥላቻ የተደገፈው መዘላለፍ ግን ሞራል የለሽ ነገርም ሲተላለፍ የማህበራዊ ሚዲያውን አጠቃቀም ያላወቁ ሲበክሉት እያየን ነው፡፡  እኔም ዘግቼ የማላልፈው ጉዳይ ሆኖብኛል፡፡ እያንዳንዳችን ሕብረተሰባችንን መጠበቅ የግድ ተከፋይ ወይም ወገንተኛ መሆን የለብንም፡፡ ሰው ሰው ሆኖ ማለፍ አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ሰው ጅራት የለውም፡፡ ሰው የማያደርገው ሌላ ተቀጥያ ነገር የተፈጠረው በተፈጥሮአዊ ይዘቱ ሳይሆን ባህሪው በፈጠረለት ብቻ ነው፡፡  


በእርግጥ ኢትዮጲያ ከባድ ፈተና ላይ እንደምትገኝ ተቃዋሚም ሆነ ገዢው ፓርቲ የሚክድ አይመስለኝም፡፡ እኛም እያየነው ነው፡፡ ሁሉም ፖለቲከኞቻችንን በዚህ ነገር ሀላፊነቱ ጠምዶአቸው ይገኛል፡፡ ምንአልባት ልባቸው ሀላፊነትን የፈራ እና የተጨናነቀ ሊሆን ይችላል፡፡ በማንኛውም ወቅቱ የትላቻው መናር ሰብሮ ሊወጣ የሚችለው ነገር ሊኖር ይችላል እና፡፡ እኛ ጥቂቶቻችንን ግን ሀላፊነት በጎደለው መልኩ፤ ለማንኛቸውም አጋዥነት የሚሆን ባህሪ መፍጠር አልቻልንም፡፡ የተቃዋሚ ደጋፊ ገዢ ፓርቲውን፤ የገዢው ፓርቲ ደጋፊ ተቃዋሚውን ስለሰደበለት አይደለም የምትረዱዋቸው፡፡ ይህ ሁኔታችሁ የሚያሳየው የእራስን ጋጥ ወጥነት ብቻ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉም ግን ኢትዮጲያዊ ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ ጣት ገማ ተብሎ ተቆርጦ አይጣልም የሚል አባባል አስታወስኩ፡፡ ታዲያ እነዶ/ር ብርሃኑም ሆነ እነ አቶ መለስ ዜናዊ፤ ተመቸንም አልተመቸንም የፖለቲካ አላማ ይዘው የተነሱ እንጂ ይህ በፌስ ቡክ እንደሚተላለፈው በሴት እራቁትነት፤ አልያም  ልቅነትን በሚያሳይ ምስል ላይ ሊቀመጡ የሚገባቸው አይደሉም፡፡  ይህ አንዳንዶች የምትልኩት ልቅነትን የሚያበረታታ እንጂ በምንም መልኩ የእነዚህን ኢትዮጲያውያን ወገኖቻችንን ባህሪ የሚያሳይ አይደለም፡፡ ጥቂት ሰዎች በድግግሞሽ ወጣቱን አቅጣጫ እንዲስት የሚያደርግ የቆሸሸ ምስል ማስቀመጥ እና በማህበራዊ ሚዲያ ማቅረብ ሁላችንም ልንቃወመው የሚገባ ሀቅ ነው፡፡  ይህ እርኩስ ባህሪ የሚያሳየው የእናንተን ጋጥ ወጥ ባህሪ እንጂ ተቃዋሚንም ገዢ ፓርቲውንም ባህሪ አያሳይም፡፡ ሁሉም ተሳሳቱም ጥሩ ሰሩም፤ ያንጸባረቁት በእኛ ውስጥ የሚጉላላውን የኖረውን ወደፊትም የሚኖረውን የፖለቲካ ፍላጎታቸውን ነው፡፡ እነዚህን ሰዎች ልቅነትን በያዘ ምስል ላይ እነሱን ለጥፎ ማቅረብ ግን መላው የኢትዮጲያን ህዝብ እንደመሳደብ እንደመኛቅ ይቆጠራል፡፡ ስለዚህ ይህንን የምታደርጉ ሰዎች፤ ከዘመናዊነትም ጋር፣ ከዜግነትም ጋር፣ ከፖለቲካም ጋር፣ ከማህበራዊ ሚዲያ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፡፡ ባለድረገጾች ሊያስተውሉ የሚገባቸው፤ ድረገጹን ለምን ብለው እንደከፈቱት ማሰብ መልካም ይሆናል፡፡  ስለዚህ ወደጤነኛ የሆነ የፖለቲካ ንግግር ቀርባቸሁ፤ በዳዴ የሚሄደውን የወያኔን ዲሞክራሲ ወይ ለማሳደግ መጣር፤ አልያም 60% እንኩዋን ዲሞክራሲ እንዲኖር መታገል ነው፡፡ ሀግ ባይ የለለበት አገር ወጣቱን አቅጣጫ የሚያሳየው ጠፍቶአል እና፡፡
ባዩሸ

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen