Samstag, 10. Mai 2014

በለስ የቀናው ፓርቲ?



በለስ የቀናው ፓርቲ?

ሁላችንም ለመልካም አስተዳደር መታገል እንችላለን፡፡ ግን ፖለቲከኞቻችን የሚሆኑት በጣት የሚቆጠሩ ጥቂቶች ናቸው፡፡ እነሱም የፖለቲካ ጥበብ የተሰጣቸው የተካኑ የተማሩ መሆን አለባቸው፡፡ ከእንግዲህ በሁዋለ ሁሉንም ማግበስበስ የለብንም፡፡ ባለሙያ ፖለቲከኛ በአገራችን አያስፈልጋትም ያለው ማንነው? የሚጠቅመንንም ፓርቲ አስቦእና አስተውሎ መደገፍ እና ለዛ ፓርቲም መቆም ጠቃሚ ዋንኛ መንገድ ነው፡፡ ካልሆነ በበረት ውስጥ እያለች የፈረጠጠች ጥጃ ወይም የማይጨበጥ ህልም አላሚ ቅዠታም እንሆናለን፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ፣ አንድነት፣ ግንቦት 7 እና እራሱ ወያኔ ኢሕአዴግም በተደጋጋሚ ሲጠሩ  እሰማለሁ፤ እነዚህ ፓርቲዎች እንግዲህ በጭራሽ በአንድ ላይ ሆነው የተቀራረበ ስራ ሊሰሩ አልቻሉም፡፡ ግን እንደማየው ሁሉም እንደየመጠናቸው የሚፈልጋቸው ሕዝብ ያላቸው ፓርቲዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ አሁን ያዋጣል ብዬ የማስበው ነገር አለ፡፡ እሱም እነዚህን ፓርቲዎችን እንደምንም  ማወዳደር ነው፡፡ ለመወዳደር ግን የሚመቸው የህዝብ ለውጥ መፈለግ ብቻ ሳይሆን መደራጀትም ነው፡፡ በእርግጥ ወያኔ ኢሕአዴግ የሚመርጠውን ለማደራጀት ወይም ለመስበክ በለስ የቀናው ድርጅት ነው፡፡ ሚዲያውም አገሩም በእጁ ሆኖአል፡፡ ህዝብን በእጁ ማድረግ ደግሞ ካቃተው ችግሩ የእሱ ነው እንጂ የተቃዋሚ ሊሆን አይችልም፡፡ ተቃዋሚ ህዝብን ለማደራጀት የሚከብደው ነው፡፡ ግን ደግሞ የማይቀናው ነው ለማለት የሚዳግት ሁኔታ ላይ ገብተናል፡፡ ይህም በምኑም በምኑም ሕዝብ እየተሰላቸ እና ያለውን አስተዳደር እየኮነነ እየሄደ ነው፡፡

 በአገር ውስጥ ያሉ ፓርቲዎች በይፋ እየኖሩ ይገኛሉ፡፡ ግን ደግሞ አባሎቻችን እየታሰሩብን ነው ይላሉ፡፡ ሁለቱም የሚጋጭ ነገር ነው፡፡ ለምሳሌ በይፋ ከተንቀሳቀሱ እና አባል ከታሰረባቸው፤ የተሰጣቸው ሊሚት አለእና ያንንም እንዳታልፉ የተባሉ ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ ከዚህ መታዘዝ ወጥተዋል ማለት ነው፡፡  ያንን ቃል የተሰጣቸውን ነገር ማፍረስ የለባቸውም፡፡ ካፈረሱ ችግራቸው የራሳቸው ነው፡፡ ልብ በሉ ገደብ ካለህ ወይ ትቀበላለህ ወይም አትቀበልም እንጂ ዘወትር አባሎቻቸው እየታሰሩ ዲሞክራሲ የለም እያሉ መጮሑ አባል እያደር ያሳጣቸዋል፡፡ ምክናያቱም ሰው ሲታሰር ሲደበደብ እያየ የሚገባ ኢትዮጲያዊ ስንቱ ነው ብሎ ማሰብም ተገቢ ነው፡፡ እንኩዋን ሲደበደብ አይቶ ተቃዋሚን ማነጋገር የሚፈራ እኮ ብዙ ነው፡፡ ለምሳሌ ባለፈው የተደረገው የአንድነት ሰላማዊ ሰልፍ ሀይለኛ ብዙ ሰው ያካተተ ነበር፡፡ የበቀደሙ ግን ከዛኛው በእጅጉ አንሶአል፡፡ ስለዚህ ሰው ተስፋ ቆርጦአል ወይም በፓርቲው እምነት አጥቶአል አልያም ፈርቶአል ማለት ነው፡፡

እንግዲህ ይህን እንዳለ ልተወው እና ግንቦት 7 የሚባለውስ፡፡ እሱ ደግሞ በአገር ውስጠ ገብቶ ሊወዳደር የማይችል ፓርቲ ነው፡፡ እሱም ከመጀመሪያውም እንደምሰማው ዲሞክራሲ የለም እና ለምርጫውም ግባም ቢባል እንደማይገባ አይነት ነገር ነው፡፡ ኢህአዴግን በጭራሽ አያምነውም፡፡ ኢህአዴግም ግንቦት 7ን አያምነውም፡፡ ሁለቱ ቀንደኛ ተጻራሪዎች ሆነዋል፡፡ አሁን አሁን ደግሞ ፤በአገር ውስጥ ሌላውስ ተነቀሳቅሶ ያመጣው ምንድን ነው ብለውም የሚጠይቁ ብዙዎች ሆነዋል፡፡ ሕዝብስ ይደግፈው ይሆን የሚለውን ደግሞ ስዳስሰው፤ 70% ቱ ህዝብ  ግንቦት 7 የሚባለው ድምጽን ይወስዳል ብዬ እገምታለሁ፡፡  ዲሞክራሲ  የለም፣ ህዝቡም የመናገር መብት የለውም፡፡ ስለዚህ የሚናገርለትን የጠላቴ ጠላት ወዳጀ ነው ማለቱ አይቀርም፡፡ ማን ይጠላልእና ጠበቃ፡፡ በኢህአዴግ ችላባይነት የተሰላቸው ሰው፤ አማራ፣ ትግሬ ኦሮሞ…. ከሚለው አልፎ በዛው ውስጥ በጎጥ ተከፋፍሎ ቅጥ አምላኩ ጠፍቶት ሲያዩ ተስፋ ይቆርጣሉ፡፡ ግንቦት 7 ማደራጀትም የሚያስፈልገው ድርጅት አይደለም፡፡ ሰማያዊ ፓርቲም ሆነ አንድነት ፓርቲ የመሳሰሉት በሚደርስባቸው መንገላታት ግንቦት 7 የሚናገረውን የኢህአዴግን ኢታማኒነት እውነት አድርጎለታል፡፡ እሱም „ ዲሞክራሲ የለም ነው“ ፡፡ እና ህዝብ ምን ጥፋት አለው? በጆሮው የሚሰማው በአይኑ እያየው ነው፡፡   አንድነት ፓርቲእና ሰማያዊ ፓርቲ ሁልግዜ ከማሳሰር ውጪ አመርቂ ነገር ሊያስገኙ አልቻሉም፡፡ ሰላማዊ ትግላቸውንም ኢሕአዴግ በመልስ እንኩዋን  አውንታዊ መልስ አልሰጣቸውም፡፡ እሰየው እስኪ ዛሪ ይህን ላድርግልህ አላላቸውም፡፡ ጭራሽ ዳርዳሩን እንዲሄዱ እያደረጋቸው ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ህዝብ ቀስ እያለ አይኑን ሊያነሳ ይችላል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ሌላው በዘር የተደራጀው ሁኔታም አመርቂ ነገር ሳይሆን የሚያስጠላ መሆኑ ከቀን ወደቀን የተማረው ክፍል፣ዘመናዊው አስተሳሰብ ያለው ወጣቱ፣ ግሎባል ማይንድ የያዘው ሰው  እና በእምነት የሚጉዋዘው ክፍል እንዳለ እየጠላው ሄዶአል፡፡ ይህንንም ነገር ኢሕአዴግ ሊያገናዝበው እና እርመት አድርጎ ሊያስተካክለው አልቻለም፡፡ በዚህ የተነሳ ግንቦት 7 በለስ የሚቀናው ድርጅት እየሆነ መጥቶአል፡፡ የታዘብኩትን ጻፍኩ እንጂ እኔ እንደሁ ማንንም አላውቅም፡፡ ምክናያቱም ቤቴንም አንኩዋኩቶ ደግፊኝ ብሎ የመጣብኝ የለም፡፡ ስብሰባም ሲጠራ በአካባቢዬ አይቼ አላውቅም፡፡ ወይ ስብሰባ አለ መባሉን እኑካውን ብንሰማ አድራሻው አይታወቅም፡፡ ያው የተለመደ ባህል አለ አይደል ያልተለወጠ፤ ሁሉም የሚያምነውን እንደኢሕአዴግ መጥራት፡፡ እኔ ግን እንደፈለጋቸሁ ተቹኝ እንጂ፤ ማንም ቢጠራኝ እሄድ ነበር፡፡ እረ ያሉበትንም ባውቅ፡፡ ግንዛቤ የሚመጣው እኮ በዚህ ነው፡፡ አይዞአችሁ፤ እኔ እንኩዋን ለመንግስትነት ለቀበሌም የሚሆን እውቀት የለኝም፡፡ ግን የሚገርማቸሁ እና የማትንቁት፤ ከተሹዋሚው ይልቅ የመራጭ ድምጽ ወርቅ ናት፡፡
በቸር የምትላችሁ፤ እራሱዋን ነጻ ያወጣችው  ባዩሽ ነኝ፡፡ አዎ ነጻነትን መጠበቁ ሰልችቶች እራሴን ነጻ አወጣሁት፡፡ ይህም መብት ነው፡፡ መቼም እስከቀኑ፡፡

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen