በወሎ ሰማይ ክፍት መሆኑን አረጋገጥኩ
ክፍል 1
ውስጤን የሚያቃጥለው እና አይምሮዬን የሚያጨናንቀው ነገር አለ፡፡ እሱም ተወልጄ ያደኩበት አገር ላይ በሰዎች ክፋት በሰላም
መኖር አለመቻል ነው፡፡ ማንም ሰው እንኩዋን ከኢትዮጲያ ወንዝ ተሻግሮ ወደውጭ አገር መሄድእና ሳይወድ በግድ ሁኔታዎች በሰዎች የተነሳ
ተበላሽተውበት ከወሎ ተነስቶ ወደአዲስ አበባም ሸሽቶ ቢሄድ ይህ ለሸሸበት አገር በጣም መርገም እንደሚሆን ነው፡፡ ማንኛውም ስድት
መራራ እንባ የልብ አዘን አለውእና፡፡ አንድ ሰው የነበረበትን የለመደውን ባሕል ቁዋንቁዋ እና ዘመድ አዝማድ ባይተዋር እንዲደረግ
አድርጎ እንዲባረር ማድረግ ወደእግዚብሄር የሚሰቀል እርግማን ማንም ሊፈታው የማይችል ሚስጥር ምድሪቱ ላይ ማስቀመጥ ነው፡፡ ለዚህ
ደግሞ ኢትዮጲያ የታደለች ነች፡፡
ይህ የመፈላሰፍ ጉዳይ ሳይሆን ሰው ሲከፋ እና እጅግ በጣም ሲያዝን ስጋው እና መንፈሳዊ ሕይወቱ የሚዛባበትን ነገር የሚፈጥር
ነገር እንዳለ ለመረዳት ለማንም ከባድ ሊሆን አይገባውም፡፡ ማንም ሰው ማንንም ለማሰቃየት የተሰጠው ምንም አይነት ስልጣን የለም፡፡
ግን ሰይጣን ሰው ላይ ሲሰፍር የሚያደርገው ማንነትን ማስረሳት ስለሆነ ሰዎች ልክ በስልጣንም ሆነ ወይም ባለስልጣንን በማወቃቸው
በመቅረባቸው የተነሳ የሚያደርጉት ነገር አንድን ግለሰብን ልቡን ሊሰብሩበት ይችላሉ፡፡ ይህም የአንድ ሰው ልብ መሰበር ወደእግዚብሄር
ያለውን ደውል ሊያስነሳው እና ሊያጮሕ እንደሚችል ምንም አይነት ጥርጥር የለውም፡፡መኖር ከልብ ያለ ሀዘን ከእግዚአብሄር ጋር በቶሎ የመገናኘት ጉልበት እና ሀይል
አለው እና፡፡ አገሩን ሳይወድ በግድ የተለዬ ሰው፤ ዘወትር ለመመለስ የሚያደርገው ጥረት የእሱ ፍላጎት ሳይሆን፤ ተገዶ በሚሸሽበት
ጊዜ ጥሎ የሄደው አንድ እኛ የማናውቀው ለእግዚአብሄር ግን ግልጽ የሆነ አገልግሎት እንደነበረ የሚያስረዳ ነው፡፡ እየሱስ ታላቅ
መሆኑን እንረዳለን፡፡ የትም ቢሄድ ለመኖር የሚያስችለው ሃይልን በላይቱ ላይ ተሸክሞ እያለ ግን ከኢጅብት ስደቱ ወደተወለደበት ምድር እንደገና እንዲመለስ
ሆኖአል፡፡ አገልግሎቱም ለአለም ይትረፍ እንጂ የጀመረውም እዛው ማርያም የምታውቀው አካባቢ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ትክክለኛ ይሆናል
ብዬ የምገምተው ነገር ቢኖር መንግስታቶችም ሁሉ ማወቅ ያለባቸው ሳይወድ በግዱ የተሰደደው ሁሉ ወደመነሻው ካልተመለሰ ምንም አይነት
በረከት እና ሰላም አያገኙም፡፡ ምክናያቱም ሁልግዜ በውስጣቸው የናፍቆትም
ስቃይ አለእና፡፡ ይህን የሚያደርገው እግዚአብሄር በሰዎች ውስጥ የፈጠረው መንፈሳዊ ነገር እንጂ፤ በስጋ ካየነው ግን
በስደትም እጅግ በጣም ሞልቶአቸው ወደአገሬ ወደሚለው አካባቢ ለመመለስ የሚደርጉ ጥረቶች እጅግ ከፍ ያለ ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡
በእራሱ ሳይንቲስቶች የሰዎችን መቃብር እየቆፈሩ እያወጡ ከነበሩበት አካባቢ እየለዩ የሚወስዱት አጽም፤ ምንአልባት የእግዚአብሄርም ፍላጎት ሊሆን
የማይችልእና በዛ በአጽም ላይ የነበረች ነፍስ ከምታውቀው አካባቢ የተሰጣት ያ የስጋ አጽም ወደማታውቀው አካባቢ መወሰዱ ሊያሳዝናት
ይችል እንደሆነ አይችልም እንደሆነ የምናውቀው መረጃ የለም፡፡ ቢሆንም በመጨረሻው ዘመን አጽም ሁሉ ይነሳሉ ከተባለ፤ እዚሕ ላይ
ያለው የሚያስረዳን ነፍስ እና ስጋ እንደገና መፈላለጉን ነው፡፡ ስለዚህ እንደእኔ እንኩዋን በሕይወት ያለ ሰው ይቅር እና በስባሹን
ስጋ ተሸክሞ የነበረው አጽምም ቢሆን ከሚያውቀው አካባቢ አንስቶ ወደማያውቀው አለም መውሰድ ለምድራችን መርገምት ይሆናል ብዬ እገምታለሁ፡፡
ድፍረቱ የለኝም ወይም ስልጣኑ አልተሰጠኝም እንጂ ይህ ሁሉ ነገር እስከአልተስተካካለ ድረስ የአንድ አጽም ከመቃብር ቆፍሮ መውሰድ
በማናውቀው ቦታ ያለችም ሕያው ነፍሱ ምን ያህል እንደምታዝን እና ደግሞም በአንድ ሳይወድ በግድ የተሰደደ ስደተኛ ሁኔታ አንድ አገር
ሰላሙ በረከቱ እና የንዋሪው አይምሮ አለመረጋጋትን ሊፈጥርበት ይችላል ብዬ እገምታለሁ፡፡ እንዴትም እንደሚኖር መሪዎችም እንዴት
እንደሚገዙ እና እንደሚያስተዳድሩ ጥበብም እውቀትም ይጠፋቸዋል፡፡ የእግዚአብሄር ጥበብ በምትማርበት ዩኝቨርሲቲ ወይም በምትቀበለው
ዲግሪ የተወሰነ ሳይሆን፤ በሚሰጥህ መረዳት ብቻ ነው፡፡
ለምሳሌ እራሴን ስወስደው በደርግ እና በኢሕአዴግ ግዜ ዘወትር አገሬ ላይ ለመኖር የማደርገው ጥረት ነው፡፡ በስደት እያለሁ
የምኖረው ኑሮ አገሬ ውስጥ ከምኖረው ኖሮ በእጅጉ የተሻለ ቢሆንም ሁልግዜ ጉጉቴ ናፍቆቴ በአገሬ በምለው ኢትዮጲያ ውስጥ መኖር ነው፡፡
አንድ ግዜ የሆነውን ልንገራችሁ፡፡ ኢትዮጲያ ተመልሼ በኢኮኖሚ እራሴንም ችዬ እንድኖር እንደአቅሜ እፍጨረጨር ነበር፡፡ ልብ በሉ
ሀብታም ለመሆን ሳይሆን፤ የተሰጠኝን ሕይወት ለመኖር ብቻ የሚበቃ ያሕል መፍጨርጨር ነበር፡፡ ከዛ በላይም ላድርግ ብል፤ አካባቢውም
የሚፈቅድበት ደረጃ ላይ አልደረሰም እኔም ያንን የሚሸንፍ አቅም ለመገንባትም አልችልም፡፡ አንድ ስራ ታዲያ መስራት ስለነበረብኝ፤
አንድ አምስት ሰዎች የላባቸውን የምከፍላቸው ቀጥሬ አብረን እየሰራን ነበር፡፡ ግን እኔ ከፈረንጅ አገር ስኖር ብዙ ግዜ በስራ የተጠመደ
አገር በመሆኑ፤ ስራ ሲኖር ሰኞን ከእሁድ መለየት የሚቻልበት ሁኔታ ስላልነበረ፤ እኔም እሁድንም እሰራ ነበር፡፡ እነዚህ ከእኔ ጋር
ስራ የሚያግዙኝ ሰዎች በጣም ክርስትናን በኦርቶዶክስ ሀይማኖት የሚያጠብቁ በመሆናቸው ግን አንድ እሁድን እንደሌላው እሁድ ስራችን
ሊሆን እንደማይችል ሊያስረዱኝ ሞከሩ፡፡ እኔ የሀይማኖት ሆነም የእምነት ሕይወቴ የሚታይ ነገር አልነበረውም፡፡ የምለው ኦርቶዶክስ
ነኝ ነው፡፡ ክርስትናዬም ቢሆን ለሰዎች ታማኝን መሆን አለመግደል የመሳሰሉትን ልቤን የማረኩኝን አስርቱ ቃላት ላይ ብቻ ያተኮረ
እንጂ የሀይማኖቱ ወግ እና ስርአት ምንነቱን በውል አላውቀውም ነበር፡፡ ግን እንዲሁ እንደልምድ ሆኖብኝ ሚካኤል የሚባለውን የእግዚአብሄር
መልአክ በጣም ስለምወድ፤ በወር አንድ ቀን ሚካኤልን ስራ ሳልሰራ፤
ሻማ እለኩስ እና ጸጥ ብየ አሳልፋለሁ፡፡ በአምት አንድግዜ ደግሞ የጣላእና የዳቦ ድግስ አደርጋለሁ፡፡ ጠላየን አስደንቃለሁ፡፡ ሰዎችን
እንዲሰክሩ እፈቅዳለሁ፡፡ ማርያም ወይም እየሱስ በእኔ መንፈሳዊ ሕይወት አድምቄያቸው ስማቸውንም ጠርቸው አላውቅም ነበር፡፡ በቃ
መንፈሳዊ ሕይወቴ ባይመቻችሁም ይህን ይመስል ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ነበር ሰንበትን ስሰራ የነበረው፡፡ በስራ አምን ነበር እና፡፡
ካልሰራሁም የሚያበላኝም የሚያጠጣኝም የለም እና፡፡ እግዚአብሄርም ሳይሰሩ የሚበላ አምላክ ነው ቢባልም፤ ቁጭ ብሎ ግን እሱን መጠበቅ
ድፍረቱም እምነቱም የለኝም፡፡ በዚህ የተነሳ በስራ አምናለሁ፡፡ ስራንም አልንቅም፡፡ አንድ እሁድ ግን ከእኔ ጋር የሚሰሩት አምስት
ወንዶች አካፋእና ዶማቸውን እንደያዙ መጥተው“ ዛሬ የተደራረበ በዓል
ስለሆነ እባክሽ ስራ አንስራ፡፡ ሰንበትም ነው፤ ደግሞም የአመቱ ገብርኤል ነው“ ፡፡ በማለት ለመኑኝ፡፡ እኔም በጭራሽ መስራት አለብን
በማለት የመስራት ፍላጎቴን በአለቅነቴ ደመደምኩ፡፡ እነሱም እኔም የቅዳሜውን ስራ ጨርሰን የበነገታውን ሰንበት እና የአመቱ ገብርኤል
የዋለበትን ለመስራት ወስነን ወደየማረፊያችን ሄድን………..ወደ ክፍል ሁለት
ባዩሽ
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen