Dienstag, 9. September 2014

እርዮተ አለም፤ ሀይልን እንጂ እግዚአብሄርን አያምንም



እርዮተ አለም፤ ሀይልን እንጂ እግዚአብሄርን አያምንም

ፖለቲካ ፓርቲዎች ሀይማኖት ኖሮአቸው አያውቅም፡፡ አላቸው የምትሉ እስኪ፤ ለምሳሌ የደርግን፣ የኢሕአዴግን፣ የግንቦት 7ን፣ የአንድነትን፣ የሰማያዊ ፓርቲን…….አንድ ሀይማኖት ንገሩኝ፡፡  በቃ ትክክለኛው  ነገር እምነት ባይኖራቸውም ግን እምነትህን መሳሪያ እንዳያደርጉብሕ ለምንም አይነት እርዮተ አለም እምነትህ ወገናዊነት እንዳያሳይ ጥረት ማድረግ የአማኝ ልብ ወሳኝ ነው፡፡ እርዮተ አለምን ማጥፋት አይቻለም፡፡ ግን እርዮተ አለም በአለም የተተበተበ ስለሆነ ከባድ የሆነ የእምነት ፈተና ያመጣብሃል፡፡ እርዮተ አለም ለህዝብ ይጠቅማል ብሎ ያመነበትን ነገር በጉልበትም በተግባር ለማሳየት የሚጥር በመሆኑ፤ እምነት ለአለም አይጠቅምም ካለ ለእምነት ነክ ነገር ክብርም አይኖረውም፡፡ ለምሳሌ ቤተክርስቲያንን አፍርሶ  መሬቱን ለእርሻ ቢጠቀም፤ እርዮተ አለም ጉዳይ የለውም፡፡ ምክናያቱም እግዚአብሄር ሰውን ይመግባል ብሎ አያምንም፡፡ ኢሕአዴግ ሀይማኖት የሚያራምድ ሳይሆን፤ ኮሚኒስት ወይም ካፒታሊዝምን እያራመደ እዚህ የደረሰ የፖለቲካ ፓርቲ ነው፡፡ እንደማንኛውም ፖለቲካ ፓርቲ ባህሪ፤ የሚያራምደው እርእዮተ አለም አለው፡፡ ስለዚህ የሚወስደው እርምጃ ሁሉ ማንኛውንም ሀይማኖት ሊያስደነግጥ ይችላል፡፡ እንደፖለቲካ ፓርቲ ግን ባህሪው ይሕ ነው ስራው፡፡ ለምሳሌ ደርግም እኮ ለእርዮተ አለሙ እንቅፋት ነው ያለውን እምነት ሁሉ እንዳጨናነቀው ማስታወስ ይገባናል፡፡ ብቻ ፖለቲከኛ ስትሆን እግዚአብሄር ህዝብን የመመገብ አቅም አለው ብለሕ  ለማመን  ትቸገራለሕ፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ ባህሪው፤ እንዲሕ እንዲያ ባደርግ ህዝብን ላስደስት አልያም ላረጋጋ ደግሞም ልመግብ እችላለሁ ባልክበት የሰው ፍልስፍና ውስጥ ገብተህ ለመተግበር ትጥራለሕ፡፡ የሁሉም ችግር ግን እርዮተ አለም ሁሉንም ህዝብ እኩል የማስተናገድ ባህሪ መፍጠር የተቸገረ ነው፡፡ በኢይሮፕ የሚገኘው እርዮተ አለም የተራበ እንዳይኖር ለማድረግ ጥረት አደረጉ እንጂ፤ የሰውን ልጅ ግን እኩል ለማስተናገድ እስከአሁን አልቻሉም፡፡ ለምሳሌ በሀብት እኩል አይደለም፡፡ አንዱ ሀብታም  አንዱ ደሃ ነው፡፡ ያማረውን ሁሉ አድርጎ የሚያልፍ ሲኖር እያማረው ደግሞ ምራቁን የሚውጥ ሞልቶአል፡፡ በህክምና እረግድ ብትሄድ የግል ኢንሹራንስ ያለው የተመኘውን ህክምና ሁሉ ሲያገኝ፤ በመንግስት ኢንሹርድ የሆነው ሁሉን ማግኘት አይችልም፡፡ ኮሚኒዝም እና ሶሻሊዝም የሚከናወንበት አገር እማ፤ የተራበም ሞልቶአል፡፡ ማንኛውም የአለም የፖለቲካ ሁኔታ ሁሉንም ህዝብ እኩል አስደስቶ አያውቅም፡፡ ምክናያቱም የሰው ልጅ ተፈጥሮአዊ ባህሪው ሳይሆን ከምንኖርበት አለም ላይ የሚኖረው ሰይጣን፤ ስግብግብነትን፣ ሙስናን ፣ ማንአለብኝነትን እና እራስንወዳድነትን ባህሪያችንን ስላለበሰው ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የእግዚአብሄርን ነገር ማራመድ ቢችሉ ብዙ ነገሮች ይቀሉ ነበር፤ የሀብትም ክፍፍሉ ይሰምር ነበር፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሉ እምነት የለሽ ስለሆኑ እኔ እርምጃቸው ሁሉ አያስደነግጠኝም፡፡ በቃ ባህሪው የፖለቲካን ፍልስፍና እውን ለማድረግ ጥረት ማድረግ ነው፡፡  በሌላ መልኩ እምነት እራሱ በተለያየ ሀይማኖት የተከፋፈለ ስለሆነ እርዮተ አለም የእንድ ሀይማኖት አራማጅ ባህሪን ቢይዝ በዛሬው አለማችን ላይ ሁከት እና ብጥብጥ ደግሞም አለመረጋጋትን ያሲዛል፡፡ ኢጅብት የነበረው ችግር ይህ ነው፡፡ ዘመኑ መቀየሩን እና የሰው ልጅ በተጨናነቀበት በዚህ አለም ጣጣ መባዘን፤ የተለያየ የእምነት መንገድ እንዲፈልግ መገደዱን ብዙዎች አልገባቸውም፡፡ በነበረበት እምነት እንዳይቀጥል ያደረጉት ችግሮች ወደሌላ እንዲሰደድ አድርጎታል፡፡ ሰው በስጋ ብቻ ሳይሆን በመንፈሱም እንደሚሰደድ ልብ ላለ መረዳት ይችላል፡፡ ነፍሴ ወደአምላኬ ተጠማች እንጂ የሚለው፤ ነፍሴ ወደሀይማኖት ተጠማች አይልም፡፡ በዚህ የተነሳ የሰው ልጅ መንፈሱ የሚረካበትን ነገር በመፈለጉ የተነሳ፤ አንድ አካባቢ ወደአለመደው እምነት ሊሄድ ይችላል፡፡ ሰው ወደሌላ እምነት ሲሄድ ከነበረበት እምነት  የወጣበትን ነገር ለማወቅ ከመጣር ይልቅ፤ ያ ሰው እሄደበት አዲስ እምነት ምን ያህል መረጋጋት እንደመጣለት መመልከት አይፈልግም፡፡ በዚህም የተነሳ አዲስ ሀይማኖት በማለት ወደጦርነት የገባል፡፡ ብቻ የአለም ህዝብ ከቦታ ቦታ፤ በፖለቲካ የተነሳ፤ በአየር መዛባት የተነሳ፤ በኢኮኖሚ የተነሳ በተፈጠረው ችግር ስፍራን በሚለቅበት በዚህ በአሁኑ ሁኔታ አለም የተጨናነቀበት ሰው አምላክን እንዲፈልግ የሚያደርገው ብዙ አይነት ነገር አስገድዶታል፡፡ በአለም ፖለቲከኞች የሰው ልጅ ተከፍቶአል፡፡ በሀይማኖት መሪዎች ተስፋ የለሽ ሆኖ እጁን አንስቶአል፤ በነበረበት እምነት አርአያ የሚሆንለት ሲያጣ የሰው መንፈሱ ይጨናነቃል፤ ይረበሻል፡፡ ስለዚህ የሰው ባህሪው እራሱ ህይወቱን ከሞት ለማትረፍ ጥረት ማድረግ ስለሆነ ሁሉንም እርምጃ ይወስዳል፡፡ በዚህም የተነሳ ዕርዮተ አለም የሚያራምዱም እምነት የሰውን ልጅ ህይወት ይለውጣል ለማለት አማኝ ነኝ ከሚሉትም ትክክለኛ የባህሪ ለውጥ አያዩም፡፡ ስለዚህ እርዮተ አለም፤ የሰውን ፍልስፍና የሚያራምድ እንጂ የእግዚአብሄርን ሊሆን ከቶም አይቻለም፡፡ የአለምን እርዮተ አለም ለማጥፋት የሚቻለው፤ በአለም ላይ አንድ ሀይማኖት ብቻ ሲኖር ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሊሆን ከቶም አይችልም፡፡ ምክናያቱም ሰይጣንም የሚኖርበት አለም ላይ ስለሆንን፤ እምነት አንድ ሊሆን ቀርቶ ጭራሽ እንደአሽዋ ይበዛል፡፡  ዋናው ነገር እራስን ለማስደሰት ትፈልጋለህ? ስግብግብ አትሁን፡፡ የእለት እንጀራህን ተመኝ፡፡ ወርቅን አትውደድ፡፡ ወርቅ አንተ  ሞተህ እምትቀበርበት ምድር አፈር ውስጥ ቀድሞም ሞቶ የተቀበረ ስለሆነ፤ እዛ ታገኘዋለሕ እና፤ በአለም ሳለህ ከንዋይ እራቅ፡፡  እንግዲህ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሉ ሀይማኖት የለሽ ለመሆን ግዴታ አለባቸው፡፡ በዚህም ከመደንገጥህ በፊት እራስህ እምነት እንዳለሕ ጠይቅ፡፡ በእምነት የሚኖር  አለምን የናቀ እንጂ አለምን የወደደ አይሆንም እና፡፡
ባዩሽ

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen