Donnerstag, 6. Oktober 2016

ለውጥ በሁሉም ከሁሉም




           ለነገሩ በፌስ ቡክ ላይ የሚገኙ ታላላቅ ፖለቲከኞች ብዙ አይደሉም፡፡ ሁሉ ስለወያኔ ኢሕአዴግ ወይም ስለተቃዋሚ ስላወራ ፖለቲከኛ ነው ማለት አይደለም፡፡ እኔ ለምሳሌ አይደለሁም፡፡ ስለዚሕ እኔ ብሳሳት ማንንም ስለማልወክል በእኔ ስም የሚወቀስ ፖለቲካ ፓርቲ አይኖርም፡፡ አንዳንድ ሰዎች ፌስቡካቸው ተቃዋሚ አስመስለው፤ ደግሞም አንዳንዶች ወያኔን አስመስለው እራሳቸውን ቅርብ የፓርቲ ሰው በማስመሰል የአድርባይነት ወይም እናናግረው የማለት በቦዘኔነት የሚካሄድ የስምማጥፋት ወንጀል ይሰራሉ ፡፡ በባህላችን የመናገር ነጻነት ባለመለመዱም፤ እነሱን ተከትሎ የሚያጫፍር አጥተው አያውቁም፡፡ እነዚህ ምንም አይነት የፖለቲካ ታርጌት ወይም ስብእና የለላቸውን ጥቂት ሰዎችን በመከተል በማጫፈር ጊዜአችሁን እንድታባክኑ ከማድረጋቸሁ በላይ አይምሮአችሁ እንዲደነጋገረው እና እግዚአብሄር በማይወደው ሀሰተኛ ፍርድ እንድትጠመዱ ትሆናላችሁ፡፡ እነዚህ የፓርቲ ሳይሆን የዳቢሎስ ስራ አስፈጻሚ፤ ከመሆናቸው አልፈው፤ እስኪ የሚሉትን እንስማ እያሉ የሚያሾፉ ናቸው፡፡እናንተ ወጣቶች የፖለቲካ ግንዛቤ ወይም የሰብአዊ መብት ግንዛቤ እና ደግሞ እርቅ እና ሰላም አንድነትም የሚመጣበትን ነገር በመለዋወጥ እራሳችሁን ለመልካም ለውጥ አዘጋጁ፡፡

                     እርግጥ ነው፤ ሁሉም በትግል አለም ለኢትዮጲያ ሲባል ሞተውበታል እየሞቱበትም ይገኛሉ፡፡ ይህ እኔስ እዛ ብሆን ብላችሁ ማሰብ ይገባችሁዋል፡፡ ኢትዮጲያ ከሁሉም ዘር ለለውጥ ሲባል ተገሎበታል ተገዳድለውበታል፡፡ ዛሬም ይህ ቀጥሎአል፡፡ ሁሉም የምናሾፍበት ነገር አይደለም፡፡ የአንድ አገር ህዝብ ተበታትኖ መነጋገር ሳይችል ቀርቶ እንደአውሬ እየተያዬ ያለበት ሁኔታ ነው፡፡ ይህ ሊያስለቅሰን ሊያሳዝነን የሚገባ እንጂ እርስበእርሳችሁ አንተ ተቃዋሚ ነሕ አንተ ደጋፊ ነሕ እየተባባልክ የምትሰዳደብበት የምታሾፍበት አይደለም፡፡ እኔ ምኞቴ በፖለቲከኞች ውስጥ እርቅ እንዲመጣ ነበር፡፡ ግን እኔ አንድ በጣም ትንሽ የሆንኩ ማንንም ያልሆንኩ ስም የለሽ ሴት ነኝ፡፡ ግን ዘወትር የምጸልይበት ነገር ነው፡፡

                 ሁሉንም ውድቀታቸውንም እንዲያዩ ለማድረግ የማልሞክርበት ግዜ የለም፡፡  እንደእድል ሆኖ ለኢትዮጲያ ህዝብ ፖለቲከኞቻችን ምሳሌ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ ተቃዋሚንም ሆነ ወያኔን በማፍቀር፤ በለለ ነገር የሰውን ስም በማጉደፍ ሞራል ለማድቀቅ ሀሰትን የሚያሰራጩ ከሆነ ይህ ፍጹም የተሳሳተ ፖለቲካ ነው፡፡ እኔ አንድ ነገር የማምነው አለ፡፡ በኢትዮጲያ ዲሞክራሲ ኖሮ አያውቅም ዛሬም የለም፡፡ ይህን ደግሞ አካሄያድ ፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆኑ የሰዎች ስግብግብነት እና እራስን ወዳድነት ያመጣው ነው፡፡ አዎ ዲሞክራሲን ስግብግቦች አይፈልጉትም፤ ካለመስገብገብ የሚኖሩ አይመስላቸውም እና፡፡ የኢትዮጲያ ሀብት ሁሉንም ማስተናገድ ማብላት የሚችል የፖለቲካ አቅም የሚገነባ ዲሞክራሲያዊ ሲስተም/ ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲ / እኩል የሚያስተናግድ እስካልተገነባ ድረስ፤ ስግብግብ ሰዎች ፖለቲካውን ምንግዜም አቅም ያሳጡታል፡፡ ይህን መሰል ሰዎችም አዎ ፌስቡክ ውስጥ ቁጭ ብለው ፖለቲከኛ መስለው የሚያደናግሩ አሉ፡፡

           ሌላው ጉዳይ እኔ ምክናያቱን በማልረዳው መልኩ ዛሬም፤ ስልጣን የያዙ በጭራሽ በፍቃደኝነት ስልጣን  የመልቀቅ ፍላጎት ሲያሳዩ አይታዩም፡፡ ሁሉም እኔ በእድሜዬ የማውቃቸው፤ ሀይለስላሴም ደግሞም ደርግ በፍቃደኝነት አለቀቁም፡፡ ንጉስ ለልጁ ስልጣንን ዙፋንን ማውረስ እንኩዋን ሲገባው ሀይለስላሴ ለልጆቻቸው እንኩዋን ለመስጠት አልፈለጉም ነበር፡፡ ለነገሩ አልጋወራሹን እግዚአብሄር ጠብቆአቸው እንጂ ስልጣኑን ቢያገኙም የእነሱን ስርአት የሚጥል ውሎ አድሮ መፈጠሩ አይቀርም ነበር፡፡ ሕዝብ አፍንጫው ብዙ ነገር እየሞላው እንደሚሄድ በአለም የሚታይ ሀቅ ነው፡፡ ዛሬም ሰው አፍንጫውን የሞላው ነገር አልጠፋም፡፡ ያም ሆነ ይህ የኢትዮጲያ ዙፋን ወይም ቤተመንግስት ምንአባዜ እንደተጠናወተው ባይታወቅም፤ ዛሬም እረጅም ግዜ ታገልን የሚሉት ኢሕአዴጎችም ስልጣን ሊለቁ አልፈለጉም፡፡ ተቃዋሚም አንድ መስመር ይዞ ሲጉዋዝ እስከዛሬ አላየንም፡፡ ምንአልባት ዛሬ ሆኖ እንደሁ አላውቅም፡፡

            ስለዚህ የሚመጣውም በሀይል ለማውረድ እየተራወጠ እየታገለ ይገኛል፡፡ ይህ ባህል ሆኖአል፤፤ አለቅም ያለውን በሓይል ማስለቀቅ፡፡ እንግዲሕ ይህ ባህላችን በሆነበት አገር ሁሉም መጠንቀቅ ያለበት፤ በፖለቲከኞች እርቅ አለመፍጠር የተነሳ አንዳንድ ሰዎች ምንም አይነት አለማ የለላቸው፤ አንደዬ ተቃዋሚ ደግሞም የገዢው ፓርቲ ሰው በመሆን ፌስ ቡኩን ሰው ቁም ነገር እንዳይጠቀምበት እንዳይነቃቃበት፤ አስተሳሰብን እንዳይለዋወጥበት አሉባልታ ይዘው፤ እከሌ ወያኔ ነው፤ እከሌ ተቃዋሚ ነው እያሉ የስም ማጥፋት ስራ ሰውን የመበከል ስራ በመስራት ይገኛሉ፡፡ በባህላችን ብዙውን ግዜ ደግሞ የተለመደው፤ ካለማረጋገጫ ሌላውም ተከትሎ አስተያየት መስጠቱ አብሮ ማጫፈሩ ነው፡፡ ለእኔ በአገሬም በፌስቡክም ወያኔ እንዳለ ወይም ተቃዋሚም እንዳለ አውቃለሁ፤ አገሬ ውስጥ ከሕዝቡ እና ደግሞ የአገሬ ሰው ፌስቡክን ከሚጠቀመው ማለቴ ነው፡፡ ስለዚህ አስተያየታችሁን እንጂ የማስተናግደው ማንነታችሁን አይደለም፡፡ ክርቲክ አደርጋለሁ እንጂ ማንኛቸውንም አልሸሽም እንዲሸሹም አላደርግም፤ አልሳደብም፡፡ ሁሉም በአገራችን እንዳለ እስከአወቅን ድረስ እዚህ የሉም ወይም ፌስቡኩን የእራሴ አስተሳሰብ ማስተናገጃ ብቻ አደርጋለሁ የሚል የዋህ ካለ ሞኝ ነው፡፡

             ሁሉንም ተቃዋሚ ሁሉንም ወያኔ አደርጋለሁ የሚል ሕልመኛ እለዋለሁ፡፡ ግን ምንድን ነው መሆን የሚገባው የወጣቱን አስተሳሰብ መረዳት እና አገራችን ይጠቅማታል ወደምትሉት የፖለቲካ አመለካከት ለምን እንደሚመጣ መገላለጽ ነው፡፡ እንዴትም እንደሚመጣ ማስተዋል ነው፡፡ የፖለቲካ ስራ ዕንዲሕ ነው፡፡ እንዳው እየተሳደቡ ማስበርገግ የፖለቲካ ስራ ሳይሆን አምባገነንነት ነው፡፡ ይህ የአምባገነን ባህሪ በሰው ደረጃ  እሁሉም ፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ እንክት አለ፡፡ የፖለቲካ ውይይት ለሚፈልግ ሰው ማለቴ ነው፡፡ ስለዚህ ወጣቶች መሰረት የለለው አሉባልታ ይዘው የሚመጡ ማንንም ያልሆኑ እንዳያደነጋግሩዋችሁ ተጠንቀቁ፡፡ ወያኔ ኢህአዴግ ዲሞክራቲክ አይደለም ካልን የእኛ የህብረተሰቡ በባህሪያችን ውስጥ የሰረጸ ነገር እራስን ወዳድነት እንዳለ ልብ እንበል፡፡ ይህ የባህሪያችን ችግር ያመጣው በመሆኑ እኛም ኢዲሞክራቲክነታችንን ለመተው ጥረት ማድረግ አለብን፡፡ ፌስቡክ ላይ አዎ ወያኔ አለ ተቃዋሚ አለ፡፡ ሚዲያው አፈጣጠሩ ዲሞክራቲክ ነውእና ፤ የሁሉም መሆኑን አትዘንጉ፡፡ ስለዚህ ሰውን ከሚወነጅሉ ተጠንቀቁ፡፡ የእራሳችሁ ግንዛቤ ምንይላል ምንስ ደረጃ ላይ ደርሶአል፡፡ እራሳችሁን መርምሩ፡፡

 
በቸር ባዩሽ

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen