Samstag, 1. Oktober 2016

ኢትዮጲያውያኖች፤ በማግለል ህመም ከተያዝን ቆይቶአል



          ሁላችንም አንድ የምናገለው ቡድን አለን፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው አንድ ሀሳቡን ሲሰጥ፤ ኦርቶዶክስ፣ ሙስሊም፣ ጴንጤ፣አልያም 666 አማራ፣ ትግሬ፣ ኦሮሞ፣ ደቡብ ነው እንላለን፡፡ አስተያየት፣ ትችት ካልጻፉ እና ካልተናገሩ፤ ደግሞ የዲሞክራሲ ቁልፍ የሆነው የመናገር ነጻነት በሁሉም ዘንድ ውድቅ ነው፡፡ እና ሰው አስተያዬትን የመስጠት ነጻነትን እኔን አትንካ ግን ሌላውን እንዳሻህ የሚል ከሆነ፣ ሌላውም እራሱን እንደማያስነካ ልብ ማለት ግድ ይለዋል፡፡ እንግዲህ፤ በአንድ ህዝብ ድምጽ የሚናገር  ከለለ ፖለቲካውን ሁሉ አምባገነን የሚያደርገው፤ የእራሳችን አስተሳሰብ መመቸት መሆኑን ልብ ሊለው ይገባል፡፡

          አንድ አገር አንድ ህዝብ ሊመሰረት የሚችለው፤ ሰውን በአስተሳሰቡ መክሰስ መወንጀል ማግለል ሲቀር ብቻ ነው፡፡ እኔ እራሴ እከሌን 666 ነው አልለውም፤ አስተሳሰቡን ከሰጠ ማለቴ ነው፡፡ ምክናያቱም ጠንካራ እምነት ስላለኝ፤ ለእኔ የማይሆነውን አስተሳሰብ መምታት ወይ እንዲታረም መናገር ስለምችል ብቻ ነው፡፡በማንኛውም የሰው አስተሳሰብ አልደነግጥም፡፡ ቀድሞውንም አስተሳሰብ የሚሰጠው እንደንቀበለው ሳይሆን የሚጠቅመውን እና የሚጎዳውን እንድናስተካክል ነው፡፡ እንድናይ ነው፡፡ ለዚህ ነው የማዳመጥ ጥበብ ከለለህ ፤ ምን ሰምተህ ምን ተረድተህ ለመፍረድ ትቸኩላለህ?  ኦርቶዶክስም ሆነ ፔንጤ አልያም ሙስሊምም የሆነውን ባህሪውን መርምሬ አውቀዋለሁ፡፡ ነኝ በሚለኝ አላምነውም፡፡ ተግባር የመመርመር ጥበብን  የሚገልጽለኝ እየሱስ ክርስቶስ ከእኔ ጋር አለ እና፡፡ የምመጻደቀው አለም በሰጠችኝ ወይ በምታጉዋጉዋኝ ሳይሆን፤ እግዚአብሄር በሰጠኝ እና በሚገልጽልኝ ነው፡፡  ለዚህ ነው፤ በአምላኬ ጥበብ መስጠት ስመካ የጉራ እንዳይመስላችሁ፤ ክፉውን ከበጎው እንድትለዬ እና እንድትመረምሩ የሚመካ ካለ በእግዚአብሄር ይመካ፡፡ እኔ በምትናገረው፤ አንተን ወንጅዬ፤ አንተ ላይ ፈርጄ፤ ህዝብን አስቼ ፤ ማጆሪቲውን በጀርባዬ በማሰለፍ፤ ማሸነፍን ድልን አላምንበትም፡፡

              እንዳውም ካላችሁ፤ በአለም  የምናያቸው በሰዎች ላይ የሰፈሩ ነውሮች እንኩዋን ለህሊና ሚዛን፤ ለስጋ አይንም በግልጽ የሚታዩ  ናቸው፡፡ የእግዚአብሄር የሆነውን እና ያልሆነውን የማይለይ ዛሬ እሱ ማነው? በውስጡ ያለ አይደለምን? እሱ በአለም ነውር ውስጥ ይኖራል እና፤ እየወነጀለ በማግለል ቃልን ያፍናል፡፡ ሰይጣን ሰው እና ሰውን ሲያባላ፤ ምክናያት ሳይሰጥ አይደለም፡፡ ሰይጣን መሳሪያው ጥይት ሳይሆን ውጊያን የሚከፍት ምክናያት በአይምሮህ ውስጥ በመጠንሰስ ነው፡፡ ለዚህ ነው፤ በምክናያት ተጠምደን፤  አንድ ሰው አንድ ሀሳቡን ሲሰጥ፤ ኦርቶዶክስ፣ ሙስሊም፣ ጴንጤ፣አልያም 666 አማራ፣ ትግሬ፣ ኦሮሞ፣ ደቡብ  እንዲህ እንዲያ ነው እያልን በማግለል ህመም ተጠርንፈን መዳኒትም እንዳንፈልግለትም፤ በሽታነቱ  ሳይታወቀን ቫይረሱን ተሸክመን በመታመስ ዘላለም አለም የምንኖረው፡፡ ለዚህ ነው ለወሬም የምንመቸው፡፡  ህሊናችንን  ዘግተን ለምን እና እንዴት የሚለውን ሚዛናዊ ጥያቄ   አብሮን ሊኖረን የሚገባውን ዘንግተን በክስ እና በማግለል የምንኖረው፡፡ ነው በተባልነው፤ ሌላው በፈረደው ተጠምደን አብረን ፈራጅ ሆነን፤ ጠቃሚዎችን እንኩትኩታቸውን በማውጣት የምንረካው፡፡

                    አትንካብኝ የምንለው የበዛ ነው በአገራችን፡፡ ሀይማኖቴን፣ ብሄሬን  እና ባህሌን፤ ይህንን ያንን፡፡ ያልተነካን ውድቀት በውስጡ ተሸክመን ይዘን፤ ባህል አድርገነው፤ ድርቅናን እና አለማወቃችንን ፍራሽ አድርገን ለሽ ያልነው፡፡  ስለዚህ እኮ ነው አስተሳሰብ መገደብ የመጣው እና አብሮን የሚኖረው፡፡  እናንተ የተመቻችሁን ነው ፖለቲከኞችም የሚያደርጉት፡፡ ፋክቱን፣ስህተቱ ሲነገር ፤ለመስማት  አቅቶት እሪ ኡኡ ብሎ የሚወነጅለው፤ እሱ እራሱን እና ተልእኮውን ይመርምር፡፡ ለማግለል ለማስገለል የሚሮጠው፡፡ እራሱን ጻድቃን ፣ ባህለኛ እና ብሄርተኛ ያደረገ፤ እሱ ማነው ምንድን ነው የሚሰራው ብሎ የሚጠይቅ የለም፡፡ ባህላችን ለማግለል መሮጥ ነውእና፡፡ ሚዛን የት ገባ፡፡ ብዙ ቀና ልብ እና  የአይምሮ ተሰጥትኦ ሚዛን መዝነው ግልጽነት የዲሞክራሲ ዋንኛ መሳሪያ መሆናቸውን አውቀው የሚናገሩ አሉ እና፡፡

              ክርስቶስ፤ ተሰቀለ፡፡ ያሰቀሉትም አግላዮቹ ነበሩ፡፡ የሚለው እውነት ሀጢያታቸውን የገለጸባቸው፡፡ አልቻሉም እውነትን መስማት፡፡ ሀቁ አንቀጠቀታቸው፡፡ እውነትን ማጥፋት በስጋ የተወሰነ መስሎአቸው፡፡ እውነት ከመንፈስ ጋር የምትኖር የማትጨበጥ የማትገደል ሀቅ ናት፡፡ ዛሬ አንዱ ሲናገራት ቢገደል፤ ነገ ሌላው ይዙዋት እንዲነሳ አድርጎ አምላክ በመካከላችን ህያውነትን ተላብሳ እንድትኖር አድርጎአል እና፡፡ አዎ ሀቁ ይህ ነው፡፡ እውነት ህያው ናት፡፡ ስጋን ሰው ይገላል እንጂ፤ የማይሞት ማንነት እንዳለን ግን ሁሉ ይክዳል፡፡ ለዚህ ነው ሰውን በማግለል፤ አይምሮን ሊቀውጡ የሚነሱት፡፡ በዚህ በመጥፎ ህመም ታመን ፤ ማጆሪቲ የእኔ ነው፤ መለወጥ መቀወጥ እንችላለን ብለን፤ እኛም በመፍረድ ማግለል ተጠምደናል፡፡ ማጆሪቲን አሳምነን፣ ኮርነር ላይ እንዲጣል መቻል፤ መፍረድ፡፡ አዎ ይህ እንደድል እንፎክራለን፡፡ ሰራንለት ሰራንላት እየተባለ፡፡ አዎ ማጆሪቲ፡፡

                 እየሱስንም  ይህ ከእግዚአብሄር አይደለም ብለው ወነጀሉት፡፡ ማን ያውቃል፤ ያንዬስ ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ነው ተብሎ እንደሁ፡፡ አንዳንዱ ስም የማግለያ ስም ሆኖአል እና፡፡ የማስወንጀሊያ፤ በዲንጋ የማስወገሪያ፡፡ ዛሬ ግን የለም እሱ ከእግዚአብሄርም  እግዚአብሄርም ነው ብለን እንመሰክርለታለን፡፡ በሙስሊምም ብንሄድ  ሙሃመድ ነብዩን ያስገለሉ አሳዳዱ፡፡ ለዚህ ነው ተከታዮቻቸው ወደማያውቁት ባህላቸው ባህላቸው ወደአልሆነ ቁዋንቁዋቸው ቁዋንቁዋቸው ወደአልሆነ አገር ነጻነት ፍለጋ ወደኢትዮጲያ ሸሽተው የነበረው፡፡ እኛም ዛሬ ከፍርድ፤ እና የሰውን ስም በከንቱ ከማቆሸሽ አልወጣንም፡፡ ለመውጣትም አንታገልም፡፡ ለምን  እና እንዴት ይህን አለ  ይህን ተናገረ የሚለው የሚዛናችን ሞተር በእራስ ወዳድነት ፣በክፋት፣ በማንአለብኝነት  እና በምቀኝነት ተጠፍሮአል እና፡፡ ነጻ አስተሳሰብን ሳይቀበሉ ነጻነት አይገኝም በማለት ልሰናበታችሁ ፡፡

በቸር
ባዩሽ አበበ ነኝ

      

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen