ቡሄን ማሰቡ
ድንቅ ቢሆንም፤ ግን አንድ ነገር ትዝ ሲለኝ ይህችን መልእክቴን ላስተላልፍ ወደድኩ፡፤ ዘንድሮ በአለም ላይ ብዙ አዲስ ነገር እያዬን
ነው፡፡ እና በእኛ አገርም የደነገጥንበት ነገር በሽ ነው፡፡ ይሁን እና ግን ዲሞክራሲን እና እምነትን እንዴት ጎን በጎን ማስኬድ
ይቻላል የሚለውን ነገር ማየት መልካም ይመስለኛል፡፡ ብዙ ግዜ ከሰዎች ጋር መነጋገር ብፈልግም ግን ብዙውን ግዜ ወግ አጥባቂነታችን
ለመነጋገር እንደሚያዳግተን ልብ ብዬ አስተውያለሁ፡፡ መነጋገር ክብሪት ይዞ እሳት እንደመለኮስ የሆነበት ኢትዮጲያችን፤ የህብረተሰቡም
ባህሪ ፖለቲከኞቻችን የተመቻቸው ይመስላል፡፡ ለሽ ብለውበት፤ አብረው ዳንኪራ ይመቱበታል፡፡ ለምሳሌ ስለለውጥ ወይም ስለዲሞክራሲ
አካሄያድ ስንነጋገር፤ ብዙዎቻችንን ዲሞክራሲን እንመኘዋለን ግን እንደፈልግነው ደግሞ ፍላጎታችንን ማሳየት አለብን፡፡ ሁሉም ጻድቅ በመሰልንበት አገር፤ ሀጢያተኛው
ታዲያ ማን ሆኖ ነው፤ የምናማርረው?
የእኔ ፍርሃት
አንድ ነገር ነው፤ እሱም ቅርስ ስንል ያልተለወጠ የፖለቲካ አስተሳሰብ ባህላችን አድርገን ቅርስ አድርገነው እንዳንቀር ነው፡፡ በብዙ
ቦታ ስመለከት ሁሉም እንደጻድቅ ማውራት እና፤ የሚጥረው ጥረት ምድሪቱን ገነት ለማድረግ ይመስላል፡፡ ይህ ግን በምንም ሊሆን የሚችል
አይደለም፡፡ እንዳውም የዲሞክራሲ አገሮች ያረጋጋቸውን የ ሕገ መንግስት የበላይነት እንደመጠየቅ እና እንደመስራት፤ እንደፋሽን እና
እንደባህል ሀይማኖቴ እምነቴ እያለን የምንተዳደርበትን ሕግ የረሳን
እና እንደልባችን አልቃሽ እና አስለቃሽነታችንን ተቀብለን እንድንኖር ሆነናል፡፡ ደግሞ እውን እምነት እንዲህ ከሆነ ጭንቅር ብሎ
ይቅር እያለ ሰው እንደሚሸሽ ይሆናል፡፡ ምክናያቱም እምነትም አንድ ነገር ካላሳዬ ተስፋ አስቆራጭ
መሆኑ የማይቀር ሀቅ ነው፡፡ የአለምን ታሪክ ስናስበው፤ ሁሉም በእምነት የተጉዋዘ እንደነበር ታሪካቸው ያስታውሰናል፡፡ ዛሬ ፋሽን
ሆኖ እኔ ኦርቶዶክስ ነኝ ፔንጤ ነኝ አልያም ሙስሊም ነኝ እየተባለ በሚኮራበት እና በሚመጻደቅበት ሰአት፤ የኢትዮጲያ ሁኔታ ምን
ያህል እንደተለወጠ እራሳችን አይተን መታዘብ ነው፡፡ ወዴትስ ተለወጣ ማለትም ያሻል፡፡ ዋናው ነገር ሰው እራሱን አለመዋሸቱ ነው፡፡
ኢትዮጲያ ሲታሰብ፤ ጥሩ ነው ይላል የደላው፤ ያልደላው ደግሞ መራራ ይለዋል፡፡ ይሁን እና ግን እምነት መራራ እና ጣፋጭን የሚበላ
አማኝ በአንድ የእምነት ዘርፍ ውስጥ ይዞ ለዘመናት መራመድ ያቅተዋል፡፡
እንዳየናቸው የሩቅ አገሮች፡፡ ተግባር የለለው እምነት ምድርን ከበጎ
ወደክፉ እየለወጠ የሚሄድ እስኪመስል ድረስ ፤ በማስመሰል እግዚአብሄርስ ይገኝበት ይሆን ወይ ብሎ የሚጠይቅ መብዛቱን እኔ አላውቅም
ብዬ ባልፈው እወዳለሁ፡፡ ሕሊና ሁሉም አለው እና፡፡
ሕግን ለዲሞክራሲው የሚመች እንደማድረግ፤ እያደረግን ያለነው፤ ሰማያዊ አለም ሌላ ስፍራ መሆኑን
ዘንግተን ምድርን ገነት ለማስመሰል ጥላሸት ተኮናንበን ስናስመሰል እንውላለን፡፡ ባህሪውን እንኩዋን ሳንይዝ ጻድቅ ሆነን የሚያለቅስን
እያዬን በትእቢት እየተወጠርን፤ አንገትን በማቅለስለስ፤ ወይም አስር ግዜ የምናምነውን እምነት ስም እየጠራን እንመጻደቃለን፡፡ እኔም
ውድቀቴን ዛሬ አየሁት፡፡ ሽንፈት የሚያሲዝ የሚያስለቅስ፤ ሲበሉ እና ሲጠጡ እያየሁ፤ በሰላም የበደሉኝ ሰዎች በጎኔ አብረው እግዚአብሄርን
እየጠሩ፤ ስለት እያስገቡ ደግሞም እየዘመሩም እኩል እነሱ ጋር ጎን በጎን እነሱ እንደባለእድል ሲጨፍሩ እኔ እንደሀጢያተኛ ሳለቅስ
አሳልፌአለሁ፡፡ ይህ ሞኝነት ይበቃል እላለሁ ዛሬ፡፡ እግዚአብሄር ይህንን ለእኔ ይመኛል ማለት ካነበብኩት እና ከተማርኩት ላገኘው
አልቻልኩም፡፡ ይህ እድሌ እና ሀጢያቴ ነው የሰጠኝ ብዬ አፌን የሚያዘጋ በእንባ ጎርፍ ፊቴን የሚያጥብ እግዚአብሄር ነው የሚለኝ
ካለ ሞኝነት እለዋለሁ፡፡ የደላቸውን እንደጻድቅ እያየሁ የእነሱ የመንፈስ ባሪያ መሆን እንጂ ያመጣልኝ፤ የፈጣሪ አድርጎኛል ማለት
የዋህነት ነው፡፡ ፈረንጆችም በዚህ በዋህነት አሳልፈውት ነበር፡፡ የለም ለምድር የፖለቲካ ስርአትም ወሳኝነት አለው ወዳጄ፡፡ የእኔ
እንባ ብቻ ምስክር ሆኖ በፌስ ቡክ የረጨሁትን አልረሳውም፡፡ አዎ አንዳንዱ እንባም እይታን ያጥባል እና፤ ሳየው ምን ያህል አዘቅት
ላይ ወድቄ እንደነበር እና የስንት ክፉ ሰዎች መሸጋገሪያ ድልድይ መሆኔን ሳስበው ካለመገረም ውጭ ምንም ልመልሰው አልችልም፡፡ አዎ
ሕግ ባለመተግበሩ፤ ህግ ላልሆነ ታልፎ የተሰጠ በመሆኑ፤ ሰይጣን ነበር ለካስ ዳንኪራ ሲመታብኝ የነበረው እንጂ፤ እግዚአብሄር ለእኔ
በጭራሽ ያንን አይሰጠኝም ነበር፡፡ አያችሁ ዛሬ የምቆጥረው ሰይጣንን አሜን ብዬ በመቀበል ማልቀሴን እንጂ እግዚአብሄር የፈረደብኝ
አልነበረም፡፡ በእምነት ስም እንድታለል ያደረገኝ አስተምህሮ እውን ከእግዚአብሄር ነበርን ብዬ ዛሬ ለመጠየቅ ተገድጃለሁ፡፡
አሁንም እምነትን እና ሀይማኖትን እንዳውጅ አታድርጉኝ፡፡ ምክናያቱም ዛሬ የተገነዘብኩት፤እምነቴ
የግሌ እንጂ የእናንተም አይደለ፡፡ የእናንተም የግላችሁ ነው፡፡ ግን አገሪቱ የጋራችን እንጂ እኔ ስለተገለልኩ እንዳለቅስ፤ ያልተገለለው
እንደተመረጠ እንደተባረከ ሆኖ እንዲኖርበት አይደለም፡፡ ይህንን ሰበካ ከአሁን በሁዋላ ከማንም ልሰማው አልፈልግም፡፡ እስከዛሬ ግዜዬን
እንክት አድርጎ የበላው ይገርመኛል፡፡ የሚገርመኝ ዛሬ ለምን ሁሉም እምነት እንደፋሽን ሌትም ቀንም መወራት ያዘ፤ እውን ሰውን የህግን
የበላይነት ሳያይ ተሸፍኖበት እድሌ ነው እያለ እንዲያማርር ነውእን?
እምነት ይቅርም
ብንል የሚቀር አይደለም፡፡ እግዚአብሄር አለእና፡፡ ግን እሱ ለሰማያዊ አለም እንጂ እዚህ አለም ለምንቁይባት ምድር ጥቅሙ እራስን
ላላማበሳጨት እና እራስን ለምግዛት ሌላውን ላለመበደል ብቻ ነው፡፡ በዚህ አለም ላይ የሚጠቅመው፤ ሁሉንም እኩል የሚያስተናግድ የህግ
የበላይነት በየምንኖርበት አገር ማስከበር ብቻ ነው፡፡ ይህ ሕገመንግስት በጉቦም በአድሎም ሆነ በተለያየው ነገር የተሸመደመደበት
እና የአፈጻጸም ችግር የተዛባበት፤ እውን ክርስቲያን ወይስ ሙስሊም በአገራችን ጠፍቶ ነውእን? አይደለም፡፡ ስለዚህ ለዲሞክራሲ የምናደርገው
ግንባት እንዳውም አግቶ የያዘው የሁላችንም እምነት ጨዋታው ምድርን ገነት ለማድረግ በምናስመስለው የለበስነው ማስክ ይመስለኛል፡፡
ማስክ ስል አስመሳይነት ነው፡፡ ይህ ካልሆነ የሁሉም እምነት በተለይ ኢትዮጲያ ውስጥ የሚሰበከው ሰበካ፤ አዎ የለለውን ምድሪቱን
ገነት ባደረጋት ነበር፡፡ ግና እንኩዋን ምድሪቱን ገነት ሊያደርግልን ቀርቶ፤ የሰማዩም እንዳይታዬን በማስመሰል አይናችንን ሸፍነን
ልባችን አሳውረን፤ እንገኛለን፡፡ ወዳጄ ሀይማኖት እና እምነት በውነት ሁሉም የእራሱ የግሉ ነው፡፡ እኔ አይመለከተኝም፡፡ የፈለገው
እምነት ተከተል፤ አፍንጫዬን እስከአልነካህ ድረስ፤ መብትህ ነው፡፡ ግን አሁን የሚያስፈልገን በእምነት እና በሀይማኖት ሽንፈታችንን፣
ስንፍናችንን እና ሕግ ጣሽነታችንን ደብቀን ከመኖር፤ ሁላችንም ለፖለቲከኞች የሚመች የህግ የበላይነት ምን እንደሚመስል እና እንዴትስ
እንደሚፈጸም አይናችንን ፈጠጥ አድርገን ብንጠብቅ መልካም ይመስለኛል፡፡ እኔ እግዚአብሄርን በጣም እወደዋለሁ፡፡ ሰውን እንዳልበደል
አጋዥ ነበር እና፡፡ ሰይጣን ግን ሲያስለቅሰኝ፤ እግዚአብሄርን ለምን አላገዘኝም ልል አልችልም፡፡ እኔ የተቀበልኩትን እና ተሸንፌነት ያስለቀሰኝን ሰይጣን ተዛምጄ ኖሬ ፤ ድሮም እሱ ለማላቀቅ የእኔን
ፍቃድ ይጠይቃል እና፡፡ ግን የሰጠንን አይምሮ በትክክሉ ተጠቅመን ለሕግየበላይነት እስከአልቆምን ድረስ፤ የምታለቅስ ሴት፤ ደሃ ደካማ፤
ፍርድ የተጉዋደለበት እና በማንአለብኞች እና በእራስ ወዳዶች የተንገላታው፤ ሰማይ ያስከፍትልኛል ማለት ዘበት ነው፡፡
ሊሆን የሚችለው
ሰው ለተበደለውም አለሁ ሲል፤ ጎረቤቱን አካባቢውን ሲመለከት እና እራሱን በእምነት መሸንገል ሲያቆም ያነዬ እምነትህም እርባና ይኖረዋል፡፡
ካልሆነ እምነትህ እምነት ሳይሆን ምሽግ ይሆናል፡፡ እኔ አልተመቸኝም፡፡ የሚመቸኝ፤ እራሳችንን ማታለል ትተን፤ ለህገመንግስት የበላይነት
ሁላችንም ቆመን ሕግን የበላይ አድርገን ስንቆም ነው፡፡ ካልሆነ የማንም እምነት ከስደት ህዝብን ሲያስመልጥ አይተን አናውቅም፡፡
እሱ ስራው ከሰማያዊ አለም እና ደግሞም በልብህ እውነተኛ እምነት ስለሆነ፡፡ ወዳጄ በጾም ብትበላ ባትበላ፤ ብትጸልይ ባትጸልይ ይህ
የእራስህ የእራሴ የግሌ ጉዳይ ነው፡፡ ለምድሪቱዋ ስርአት ግን የሚጠቅማት የፖለቲካ ስርአት ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ካልሆነ፤ ዘወትር
አንተ ስትዝናና እኔ በእግዚአብሄር እና በሰይጣን እያመካኘሁ ሳለቅስ መኖር ነው፡፡ ይህ ደግሞ ጦርነት ጋባዥ መሆኑን እያየነው ነው፡፡
አዎ ሰላም የሚደፈርሰው፤ እምነትም እራስ ማታላያ ሲሆን በመሆኑ፤ ወደሕግ የበላይነት እያንዳንዱ እስካልተመለከተ እና እንዲተገበር
ካልጣረ፤ የእምነቱ ቀላጅ ፍቃደኛ ባሪያ፤ ወሬኛ እና አድርባይ ይሆናል፡፡ ይህ ያስመርራል ይበቃል፡፡ ስለዚህ የፈለከውን እምን፤
ግን የህግ የበላይነትን በምድራችን ላይ ዛሬ መኖር አለበት በል፡፡ የህግ የበላይነት በኢትዮጲያ ይስፈን እላለሁ፡፡
ባዩሽ አበበ
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen