Dienstag, 8. April 2014

አይድረስ ነው፡፡



አይድረስ ነው፡፡ 

አንድ ቀን ለሊት ደሴ ላይ ድንገት የመጡ ጅቦች ከበቡኝ፡፡ ልቤ በጣም ተጨነቀ፡፡ ዙሪያየን ከበቡኝ፡፡ አንድ በርም ስላልተውሉኝ፤ ወደዚህም ወደዚያም ልሽሽ አላልኩም፡፡ መሬቲቱ ተሰንጥቃ ካልዋጠችኝ ወይ ከሰማይ መጥቶ የሆነ ነገር ካልነጠቀኝ ማምለጫ የለኝም፡፡ ሂድ ሂድ እያልኩ በድምጼ ብቻ ነበር የምከላከለው፡፡ የሴት ድምጽ እንኩዋን ለጅብ ሊያስደነግጥ ለውሻም አይሆን፡፡ ውሻ ታውቁ የለ ሰፈር ለሰፈር የሚውለው ውሻ፤ ምንም የማይሰራ፣ ባለቤት እንደለለው የሚሆነው፡፡ ለእሱ እንኩዋን አይሆንም ድምጼ፡፡ ገረመኝ ወይ ሴት አልኩ ወይ ጉልበት የላት የምትመካበት አልያም ድምጽ፡፡ ጉዴ ፈላ በዚህ በከበበኝ ጅብ፡፡ እግዚአብሄር ግን ጥሎ አልጣለኝም እና አንድ በግምት ከ7 እስከ 10 አመት የሚሆነው ልጅ፤ ሹልክ ብሉ ገባ፡፡ ጅራፍ አያያዙ  የበግ እረኛ ይመስላል፡፡ በጎኑ ያነገበውን ኮሮጆ ሳይ ደግሞ የቆሎ ተማሪ፡፡ ግን ጅብ ከቁመቱ ያጠረውን ሰው ይበላል ሲሉ ሰምቼ ነበር፤ እናም ቶሎ ብዬ የልጁን ቁመትእና የበጉን ቁመት ማመዛዘን ጀመርኩ፡፡ በቁመትም በውፍረትም ማን እንደጅብ፡፡ ልቤ በተስፋ መቁረጥ ተሞላ፡፡ ግን ከሁሉ ደግሞ የሰቀቀኝ ልጁ ከእኔ ቀድሞ ሲበላ ሲቆረጨም ማየት ነበር፡፡ ለእኔ ተውኩእና ለልጁ መጸለይ ጀመርኩ፡፡ ደግነት ይሆን ወይስ ተስፋ መቁረጤ፤ ይህ ከብት እረኛ ለእኔ ብሎ የሚወስደው መስዋእትነት እጅግ እኔነቴን ጠላሁት፡፡ ምነው ፈጣሪዬ የጅብ መንጋ ከመላክ አልፈህ ደግሞ ይህንን ጨቅላ ልጅ  እፊቴ ልታስበላው ነው ብዬ አለቀስኩ፡፡ እኔ የማላደርገውን እሱ ለእኔ ሊሞት? አምላኬን ወቀስኩት፡፡ወቀሳየም ከመጠኔእና ከልኬ አልፎ ይሆናል፡፡ ግን ልጁን ሲበላ የሚያይ አንጀት የለኝም፡፡ አንጀቴ የተሰራው ለስጋዬ የማስገባውን እንጂ የሰው ፍቅርን፣ ለሰው ማዘንን እንዴት አድርጎ መሸከም ይችላል፡፡ ሆዴ ቡጭቡጭ አለለችሁ እና አረፈ፡፡ ወዳው ከወደውስጤ አንድ ድምጽ ሰማሁ፡፡ የሚወቅሰኝ ደግሞም ሊያስተምረኝ የሚፈልግ፡፡ „አንቺ ደግሞ ብለሽ ብለሽ አምላክሽን ጅብ አስበሌ አደረግሽው እንዴ? አንቺ በለሊት ማን ከቤት ውጪ አለሽ? ጅቦቹስ በለሊት እንዲንቀሳቀሱ የጨለማው ኑዋሪ መሆናቸውን ዘነጋሽን?? እያለ ይወርድብኝ ነበር፡፡ ወዳውም ሁለተኛው ድምጽ ተነሳ“ አንቺ አሁን ይህ ሕጻን ሊያስጥልሽ ነው? ደግሞ በአንድ ጉርሻ ቅርጭም የሚያደርገው ይህ ከዶሮ የማይሻል እያለ ጭራሽ ልቤን አስለቀሰው፡፡ „ምን አልሽ“ አለኝ ጅራፉን ወደጅቦቹ እያጮሀ፡፡ በመጮሕ እና በሲቃ እባክህ የእኔ ልጅ ሊበሉህ እኮ፤ ሊበሉህ እኮ ነው፡፡ እሱም „አዎ ሊበሉኝ ነው ግን ገና አልበሉኝም“፡፡ እያለ በአንድ ወገን ሰበሰባቸው፡፡ አሁን በአንድ መስመር ሲሆኑ „ሂጂ ሂጂ አምልጪ“ በማለት እንዳመልጥ መንገድ ከፈተልኝ፡፡  እኔ ግን አንተን ጥዬ፤ ከቁግ የተሰራ ጅራፍ ነው እኮ በእጅህ ያለው፤ ሽጉጥ ወይ ጠበንጃ አይደል በማለት ጥየው ላለመሸሽ ተሙዋገትኩት፡፡ ተስፋ ቆርጦ እንዲሸሽ አስፈራራሁት፡፡  ልጁም ቆም አለእና ወደእኔ ፊቱን በማዞር፤ „ „ዳዊት ጎልያድን በጠጠር ነው እኮ የገደለው፤ ታዲያስ ጅራፍ ከጠጠር አይጠነክርም እን?“ በማለት  የጅራፉን ሀይላኛ ድምጽ ወደጅቦቹ ለቀቀው፡፡  በዛ ልጅ ትከሻ ይህ ከባድ ድምጽ ከጅራፉ ማውጣት በከበደ ነበር፡፡ የጦሳ ተራራ እና አዛዋገደል ማዶ ለማዶ እየተቀባበሉ ድምጹን አስተጋቡት፡፡ የአገሬ የገደል ማሚቱ አጋዡ አዳናቂው አወካ፡፡ ልክ ድምጹ ደሴን ሲያናውጣት ግዜ ነው መሰል ከሰመጠ እንቅልፌ ብንን ብዬ ነቃሁ፡፡ ሻወር እንደወሰደ ሰው ላብ ስምጥ አድርጎኛል፡፡ ልቤ ይመታል፡፡ አይኔን አሻሸሁእና ገለጥኩት፤ ጅብም የለ እረኛውም የለም፡፡ ግን ህልሙ ከአይኔ ሊሰወር ባይችልም የጅራፉ ድምጽ ከተማውን የበጠበጠውን፤ በጦሳ ተራራ በአዛዋ ገደል የገደል ማሚቶው ያስተጋባውን በጆሮዬ የቀረውን እንደትዝታ ይዠ ከጅብ ሳልበላ ተረፍኩላችሁ፡፡ ወይ ጉድ አልኩ ጅብን በእረኛ ጅራፍ ገረመኝ፡፡ ሕልም እረኛ ባለጌ ነው፡፡ የማይገባበት የለው የማይዳክርበት፡፡ ይህ እንደልቡ፡፡ ወዳጆቼ መልካሙን እንቅልፍ ይስጣችሁ፡፡ ከብት እረኛም ለካ አይናቅም፡፡ ዋናው ፍቅሩ ነው፡፡ እኔ ደግሞ ማመን፡፡
ባዩሽ

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen