Sonntag, 17. April 2016

መጻፍ መድሃኒት ይሆናል


           ስደት እንደአባጨጉዋሬ የሚኮሳኮስ እንጂ ድሎት የለውም፡፡ እኔ ዘወትር አገሬ ለመግባት የማደርገው ሙከራ ሁሉ፤ አሳፍሮኝ ለምንስ አደረኩት ብዬ አላውቅም፡፡ ብዙ ኪሳራ ቢደርስብኝም፤ ብዙ ነገር ባጣም ብዙም የስነልቦና ተጽእኖ ቢኖረውም አገሬ ኢትዮጲያን ግን እንድኖርባት ዘወትር እጥራለሁ፡፡ ምክናያቱም ጀርመን ለስጋ እሱም ብትንሹ ቢመቸኝም ለመንፈሴ ግን በጭራሽ ተመችቶኝ አያውቅም፡፡ አሁንም አገሬ ለምግባት ነው የምጥረው፡፡ ኢትዮጲያ ሆኘ አንድ ልጅ ሲሞትብኝ፤ በዛ መረበሽ የተነሳ ከዛ ቀን በሁዋላ የምይዘውን የምጨብጠውን አጥቼ ቆይቻለሁ፡፡ አንዱ ትራዋማ ይህ ነው፡፡ አንዱ ትራዋማ የአስገድዶ መደፈር ቢሆንም፡፡ ያም ሀዘን ሰበብ ሆኖ፤ ሌሎቹን ልጆቼን አተርፋለሁ ብዬ የገባሁበት ጋብቻ ከገሃነም ያልተለዬ ነበር፡፡ ሌሎቹ ልጆቼ በህይወት ቢኖሩም እንዳጣቸው መልሸም እንዳላገኛቸው ሆኛለሁ፡፡

            
ኢትዮጲያ ከተመለስኩ በሁዋላ የሚገርመው፤ ደሴ ልጆቼን በመተው ወደአዲስ አበባ ለአንድ ቀን መጣሁ፤ እሱም ጀርመን ኢንባሲ ዳግም ለመመለስ ቪዛ ለመጠየቅ ነበር፡፡ እዛም ለመኖር የልጆቼ ነገር አሳሰበኝ፡፡ ችግር ገጠሞኝ ነበር እና፡፡ አገሬን እወዳለሁ እንጂ፣ በውነቱ በአገሬ ያለውን የባህሪ ለውጥ አላጤንኩትም ነበር፡፡ በልጅነት አይን ነበር እና አገሬን የማውቀው ፡፡ ለካስ ስደት ባይተዋር አድርጎኛል፡፡ ናፍቆት እድገትን ይጎትታል፤ በአየር ላይ ያንሳፍፋል፡፡ ፈረንጅ አገር ከመኖር ይልቅ፤ ፈረንጅ አገር ሆኘ የምኖረው ኢትዮጲያን ስለነበር ብዙ ያጠፋሁት እና የዘነጋሁት ነገር ነበር፡፡ እንደአዋቂ እንዴት እንደሚኖር የሳትኩት ይመስለኛል ዛሬ ሳስበው፡፡ ወረቀቴን አበላሽቼ ነበር እና ወደኢትዮጲያ የገባሁት ፡፡ ችግር ወደጀርመን ሲመልሰኝ እንደገና ቪዛ መጠየቅ ነበረብኝ፡፡ እንዳልኩት ዘወትር ከኢትዮጲያ ተለይቼ አላውቅም፡፡ በቃ ያለው ትስስር ከእኔ እና ከኢትዮጲያ ጋር እርሃብም ችግርም መጥፎ ልምድም ቢኖር እርም ብዬ ሊበጠሰ ያልቻለ ፍቅር በውስጤ ነበር፡፡ ናፍቆት አለኝ፡፡


            እንደእውነቱ ቢሆን፤ አንዳንድ ግዜ ኤርትራ እና ኢትዮጲያ ችግር ባይኖራቸው፤ ከጀርመን ኤርትራንም እንደምመርጥ አውቃለሁ፡፡ እዛ ሄጄ አገሬን ባሸት እወዳለሁ፡፡ ጠረናችን ሁላችንም አንድ ነው፡፡ ግና የፖለቲካ እና የፖለቲከኞች መናጋት እንጂ ፡፡ ምንድን ነው ከኢትዮጲያ የናፈቅሽ ብትሉኝ ፍቅር አይጨበጥም ከማለት የምሰጠው ምላሽ የለኝም፡፡ ብቻ ጀርመን ኢንባሲ ተቀምጬ ቪዛ ጠይቄ ፈቅደውልኝ ፓስፖርቱንም በነጋታው እንደምወስድ ነግረውኝ ደስ ብሎኝ፤ አዲስ አበባ በእንግድነት ወደአረፍኩበት ቤት ተመለስኩ፡፡ እዛ ግን የጠበቀኝ ዋይታ ነበር፡፡ የለቅሶ ጋጋታ፤ ለካስ የታመመው ልጄ እኔ ጀርመን ኢንባሲ ቁጭ ብዬ እሱ ሞቶ ደሴ እየተቀበረ ነበር፡፡

 
               ህይወት ምስቅልቅል ናት፡፡ ምን ብትጠር ለምን እንደሁ ሳታውቅ፤ የእዮብን እንባ ታለቅሳለህ ፡፡ ምሬቱንም ታማርራለህ፡፡ እግዚአብሄርን ሳታስበው ፍርደገምድል ነው ለካ ትላላህ፡፡ ዛሬም አገሬ ለመኖር፤ እና ሳልሳቀቅ ትንሽ ተንፈሸ የቀረችኝን ህይወት ብኖር እፈልጋለሁ፡፡ በነገራችን ላይ ብዙ ሰዎች ከተለያዬ ቦታ መጽናናትን አድርጋችሁልኛል፡፡ ከኢንባሲም ምን እንርዳሽ ብለው የፌስ ቡክ እሮሮረዬን የተመለከቱ ጠይቀውኛል፡፡ የኢንባሲው ያልጠበኩት በመሆኑ ደስታ እና ሀዘን የተፈራረቀ እንባ አስለቅሶኛል፡፡ አዎ መንግስት ለእሮሮ መለስ ሲሰጥ የመጀመሪያ ልምድ ነበር እና፤ ከቶም አልረሳውም፡፡ የእርካታ ነገር በውስጤ አሳድሮብኛል፡፡ እስራኤል አገር ወስዳ ያዝናናችኝንም እህት አልረሳትም፡፡ ያው አካፍያችሁዋለሁ፡፡ ደከመኝ እና እንጂ ዛሬም አሜሪካም ወጭሽን ከፍለን ነይ ትንሽ እረፊ ለአንቺ የሚሆን ማሪፊያ አለን ያሉኝም መልካም እህቶች አአጋጥመውኛል፡፡ የፌስ ቡክ አክቲቪቲ ማድረጌ እራሴን እንዳይ እና ግልጽ መሆኔ የታመቀውን እንዳወጣ እረድቶኛል፡፡ እናንተ ጋር ተካፍየዋለሁ፡፡

 
           በቃ ከፈረንጆች የተማርኩት ይህንን ነው፡፡ ልቤን የሰበረውን ባዋይ የቻለ እና የተረዳ ያጽናናል፡፡ ያልቻለ ዝም ይላል እንጂ ሌላ ትርፍ ንግግር አይናገር፡፡ እሱ አያስተነፍስም እና፡፡ ብዙ ሲቃ እና ህመም አለውእና፡፡ ልጄ ቀድሞ መሞቱ ግርም ይለኛል፡፡ ዛሬ ቢኖር 25 አመቱ ነበር፡፡ መሞት እኮ ያለ ነው፡፡ ግና ሕመሙግን ሁኔታው ነው፡፡ ገጠመኘሹ ነው፡፡ ምነው አንድ ወር ጨምሮለት በነበር፤ እያልኩ ዘወትር የነበርንበትን ሁኔታ እያስታወስኩ ማዘን አይቀርም፡፡ እንደእውነቱ ምንአልባትም ስህተት አድርጌ የማየው መውለዴን ነው፡፡ ይሁን እና ግን ዘወትር ሀላፊነቴን ለመወጣት ባለሁበት ድካም አልተገታሁም፡፡ የቻልኩትን አድርጌአለሁ፡፡ ያላደረኩት ያልቻልኩትን ነው፡፡ ዛሬም ኢትዮጲያ ለመሄድ እኔ ቀሪ ህየወቴን ከመሰል ልምድ ካላቸው ሰዎች ጋር እየተካፈልኩ መኖር እፈልጋለሁ፡፡ ካልሆነም አገሬን አይቼ መመለስ፡፡ የልጄን መቃበር እንኩዋን ከአንድ ቀን በላይ ለማየት አልደፈርኩም፡፡ዛሬ ግን ላየው እፈልጋለሁ፡


መቃብሩ ሀውልት ስለለለው፣ ምንአልባትም ላላገኘው እችላለሁ፡፡ አላውቅም፡፡  ቢሆኑም አንዱን ልጄን እዛው ጥያለው ቀሪው ልጅም ከእኔ ጋር የለም፡፡ እኔ ግን ያው አለሁ፡፡ በእግዚአብሄርም እጸናለሁ፡፡ ምን ቢመር ቢከፋ፤ እግዚአብሄርን ብጠላውም የምመልሰው ነገር የለኝም እና፡፡  እንዲሁ ፈጣሪን እንደወደድኩት መጨረሻውን ማየት ነው፡፡


የሌሎቹን ልጆቼን ሁኔታ አላውቅም፡፡ በህይወት ይኑሩ አይኑሩ፤ ይድላቸው አይድላቸው አላውቅም፡፡ አያችሁ እኔ የማፍርበት ነገር የለኝም፡፤ ማፈር የሚገባው ለችግር የዳረገን መንገዱ እና ሰው እንጂ፡፡ በየቤቱ ብዙ መከራ የተቁዋደሰ አለ፡፡ ግን በአገራችን ኩራት እራት ስለሆነ መካፈል የለም፡፤ ብታካፍለውም ይንቅሃል፡፡ ይሁን እና ግን ብዙ ባህሎች የአስተሳሰብ ባህሎች ቢቀየሩ፤ የመጎዳት ሀዘን ሊያገግም ይችላል፤ የልብ ስብራትም፤ እንደድሮው ባይሆንም ይጠገናል፡፡ እዮብ እኮ የመጀመሪያ ልጆቹን አላገኘም፡፡ መጽሃፍ ከፊልም የሚበልጠው፤ የፊልሙ መነሻ ስለሆነ ነው፡፡

ባዩሽ አበበ

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen