Dienstag, 26. April 2016

ገንዘብ ከሰጠኝ ያረጋጋኝ ይበልጥብኛል








ሕይወት በጣም ይገርማል፡፡ ምክናያቱም፤ በህይወትህ ቢያንስ አንድ ግዜ ያልጠበከው ነገር ይገጥምሃል፡፡ እኔ ግን ወገኖች አንድ ነገር ልንገራችሁ፤ ዘረኛ በጭራሽ የማልሆንበት ምክናያት ከመላአክ የማላስተናንሳቸው ነጮች በጠንካራው የአርባ አመት ስደት ህይወቴ ገጥመውኛል፡፡ ደግሞም የሚገርመው፤ በህይወቴ ወሳኝ ሚና የተጫወቱ እና አሁንም የሚጫወቱ አምስት ኢትዮጲያዊ ሴቶች እና አንድ ኢትዮጲያዊ ወንድ ገጥመውኛል፡፡ሁሉም እርስ በእርሳቸው አይተዋወቁም፡፡ እኔ ግን እያንዳንዳቸውን አውቃቸዋለሁ፡፡ እነዚህ ስድስት ሰዎች እጅግ በሚገርም ሁኔታ እኔን ለማረጋጋት እና ለማጠንከር የተነሱ መሆናቸው ይገርመኛል፡፡ ደግሞም እንደማልፈበት ፈተና፤ እነዚህ ባይኖሩ፤ የእግዚአብሄር ተስፋ በማን እንደሚመጣ አላውቅም፡፡ መንአልባትም ተስፋዬ ከመከራዬ ባነሰ ነበር፡፡ እምነቴም ከንቱ በሆነ ነበር፡፡


እምነትህን ሚዛን ላይ የሚያስቀምጡት በእነሱ በኩል በረከት እንዲያልፍባቸው እግዚአብሄር የፈቀደላቸው ሰዎች አለሁ ብለው ድምጽ ሲያሰሙ ነው፡፡ አለሁ ሲሉህ፣ አይዞህ ሲሉህ፤ አትዘን ሲሉህ፣ በእቅፋቸው ሲያስገቡህ የእግዚአብሄርን ሙቀት ታገኘዋለህ፡፡ አዎ ካለሰው እግዚአብሄር አይሰራም፡፡ እናም በአለም ሁሉ የእሱ በረከት ይፈልቅልሃል፡፡ ከማንኛውም ዘር ብሄር ሀይማኖት አማኝ ሁሉ ታአምራትን ያዘለ ቃል ብርታት የሚሰጥህ ምስራች ትሰማለህ፡፡
ከወደክበት አዘቅት እንድትነሳ ቃል ማግኘት አለብህ፡፡ ገባህ አባባሌ ብርታት እና ሀይል ያለው ቃል፡፡ የሚደቁስህ እና አለቀልህ፤ ምን መሰለች ምን መሰለ፤ ደግ ሆንክ እያለ የሚያጋንን አይደለም፡፡ ብትሳሳት እንኩዋን ከስህተትህ እንድትወጣ የሚያደርግ እንጂ የሚኮንን እሱ ከእግዚአብሄር አይደለም፡፡ ከሳሾችሽ የሉም ቀና በይ ይላል የእግዚአብሄር ቃል እና፡፡
አዎ አይዞህ ብለው፤ ከገደል አፋፍ ይመልሱሃል፤ ከሰመጥክበት ባህር ዋኝተው ያወጡሃል፡፡ እየሱስ ሊያድን ሲመጣ እምነታቸው አላታየውም ከዛም ቀጥሎ ዘራቸው ብሄራቸው አልታየውም፡፡ ህመማቸው ስቃያቸው እና ፍላጎታቸው እንጂ፡፡ መዳን ከመጣልህ የእሱ እጅ እንዳለበት እምን ወዳጄ፡፡ ታዲያ ተስፋ የሰጡህ ሁሉ የለምለሙ የእግዚአብሄር መንፈስ የዳሰሳቸው ይሆናሉ፡፡ ሰይጣን ሊደቁሰ እንጂ ሊያበረታኝ አይችልም፡፡ ታዲያ ይህስ ቢሆን ቀድሞ ክፉ አድርጎ ሰዎችን ባላሰማራብኝ እና፤ ለህይወቴ ምስቅልቅል ባልዳረገኝ ፡፡


የእግዚአብሄር መንፈስ፤ በሁሉም ለሁሉም የተሰጠ ነው፡፡ ፍቅር ብቻ፤ ከብዙ ጥላቻ ጠብታ ፍቅር ይበልጣል፡፡ ሰውን በጥላቻ ለመግደል ለማጥፋት ብዙ ሀይል ይላል፡፤ ግን የፍቅር ጠብታ ሙትን ይቀሰቅሳል፡፡ የተሰበረ ልብን ይጠግናል፡፡ ህሊናን ያነቃል፡፡ አይምሮን ያሰፋል፡፡
በከንፈር መምጠጥ ያልተወሰኑ፤ እኔን ወደታች በችግሮች ለመጫን ያልተነሱ፤ በድክመቴ ያልተጠቀሙ፤ ግን ወደፊትን ያሳዩኝ ናቸው፡፡ የሚገርመው፤ ስድስቱም ብሄራቸው ብሄሬ እምነታቸው እምነቴ ያልሆኑ ናቸው፡፡ የሚገርመው ይህ የረዳኝ በማንኛውም ብሄር እና እምነት ላይ ጠባብ አስተሳሰብ እንዳይኖረኝ እና አይምሮዬን እንዳሰፋ እረድቶኛል፡፡ ረዳቴ ከሰማይ መጣ የሚለውም ቃል ያንጸባረቅልኝ መጽናናትን ከጠበክበት ቦታ እንደማያገኝ ነው፡፡ ታዲያ ዛሬ ለሊት የገረመኝ ከምኝታዬ ድንገት ነቃሁ፡፡ ስነቃም ይህንን እንድጽፍ የሆነ ሀይል ከውስጤ ይገፋኝ ነበር፡፡ እውነት ነው ምስክርነት ውስጥን ከማለምለም አልፎ ሁላችንም አይናችንን እንድንከፍት ያደርጋል፡፡ ምንግዜም እግዚአብሄር የሚያልፈው፤ መባረክን ካገኙ እና ለእግዚአብሄር ቅርብ በሆኑ ሰዎች ብቻ ነው፡፡
የአንተ ያልሆነ ዘር የአንተ ያልሆነ እምነት፤ ያንተ ያልሆነ ብሄር አያጽናናኝም ደግ አይሆንልኝም ብለህ አታስብ፡፡ እግዚአብሄር ይሆነኛል ወይ በል፡፡ እግዚአብሄር እንኩዋንስ በሰው በአህያዋ አፍ ይናገራል እና፡፡ በገደሉ ይናገራል፡፡ በሲና በረሃም ያች ነዳ ያልከሰለች ዛፍ ትዝ ይበልህ፡፡ አዎ እግዚአቤህር በማን እንደሚናገር እንደሚደርስ አታውቅም እና በማንም የሚመጣ ተስፋ አትናቅ፡፡ አንበሳንም አይጥ የታሰረበትን ገመድ ልትበጥስለት ትችላለች፡፡ ብቻ እግዚአብሄር አንተን እንዴት እንደሚያጽናናህ፡፡ እንደሚናገርህ ልብ በል፡፡ መናገሩን ልብ በል፡፡ መድረሱን እወቅ፡፡ አንተ ማየት ያለብህ ከአንተ ጋር ያለው ሀይል ያመጣውን በረከት ነው፡፡ እነሱንም ትባርካለህ፡፤ አዎ ትባርካለህ፡፡ ትመርቃለህ፡፡


አዎ እነዚህ ሰዎች እነማን እንደሆኑ ይህንን ስጽፍ እራሳቸውም እኔ ነኝ እንደማይሉ አውቃለሁ፡፡ ምክናያቱም ብዙዎች ደግነታቸው እና እግዚአብሄር በእነሱ ውስጥ እንዴት እንዳለፈ አያውቁትም፡፤ ለእነሱ ያደረጉት ነገር ሁሉ ታላቅ መሆኑ አይሰማቸውም፡፡ ታላቅነታቸውን የሚያውቀው ግን ፍቅርን ተቀባዩ ነው፡፡ ዘወትር ያለፍኩበትን ሳስታውሰው እና፤ እነዚህን ሰዎች ሳስብ ከልቤ ምርቃት ዘወትር እንደሚፈልቅ አውቃለሁ፡፡ አያችሁ በወሎ ትውልድ ሰፈሬ አፍ አይደለም የሚመርቀው ይላሉ ልብ እንጂ፡፡ የሆነ ነገር ልብህን ሲነካው ደስ ሲለው ምርቃን ያፈልቃል፡፡ ልብህ ሲያዝን እና ሲደማ እርግማን፡፡
ባዩሽ ነኝ