
ባዩሽ አበበ
ስለትግሌ ሳስበው እና ሳስታውሰው ልቤ በሲቃ ይሞላና እንባዬን መቆጣጠር
ያቅተኛል። ሴት ሆኜ እንድፈጠር አምላኬ ስለፈለገ ሴትነቴን በጸጋ ተቀብየዋለሁ። ሴት በመሆኔ ደግሞ በምንም መልኩ ከወንዶች ያነሰ
ኑሮ እንድኖር አላደረገኝም። ድሌ ያመጣሁት ውጤት ሳይሆን ትግሌን አለማቋረጤ ብቻ ነው። ምንም እነኩዋን የሚደረጉብኝ ተጽኖዎች መድረስ የምፈልግበት እድገት ላይ እንዳልደርስ
ቢገዳደረኝም ፤ ተስፋ ቆርጬ ግን ከትግሉ ጎራ አልወጣሁም። እያንዳንዱዋን
የኖርኩባቸውን ቀናቶቼን ደግሞ ሴት በመሆኔ ሊያንገላቱኝና ሊጨቁኑኝ ከተነሱ ሰዎች ጋር በሰጥ አገባ አሳልፊአለሁ። የገጠሙኝ ስራ
አስፈጻሚዎች አድካሚና አታካች ቢሆኑብኝም፤ቀላል እንዳልነበርኩና መብቴን በቀላሉ የማልለቅ ሴት መሆኔንም ተገንዝበዋል። ብቻ „ሞኝ
እንቢ ብሎ ይረታል“ ነውና ፤ በኢኮኖሚ እራሴን ሊያስችለኝ የሚችለውን መንገድ ጠፍሮ በማያዝ እረትተውኛል። የሚገርመው ግን እኔን ወደድህነት ማስገባት
ማለት ፤አገሪቱንና የአለምን እቅድ እንደሚጎዱት አለመረዳታቸው ነው። ባለፈውም ሆነ አሁን ባሉ የመንግስት ስራ አስፈጻሚዎች መገለል
ደርሶብኛል። መገለል ማለት ድምጼ ወይም አቤቱታዬ እንዳይሰማ ማድረግ ነው፤ በዚሕ መልኩ ለህገወጥ ሰዎች ታልፎ የመሰጠት ቅጣት ደርሶብኛል። አንዲትን ሴት የሕግ ከለላ እንዳታገኝ ማድረግ መራራ፣ አሳዛኝእና፣ ሃላፊነት
የጎደለው ነው። ይህ ሁኔታ በስደቴ ዘመን እንደህልም የምትታይኝ አገሬ
ኢትዮጲያን በምሬት፣ በፍርሀትና በተስፋ መቁረጥ አይን እንዳያት አድርጎኛል።
በአገሬ ኢትዮጲያ ውስጥ በውስጣቸው ምንም አይነት ፈሪሀ
እግዚአብሄር የሌላቸው እራስን ወዳድ ጨካኞች በበቂ እንዳሉ እንድረዳ
ሆኛለሁ። በዚህ አስቸጋሪው ጉዞዬ ኦርቶዶክስ፣ ሙስሊምና ጴንጤ ነን ከሚሉ ሰዎችም መጥፎ ልምድ ወስጃለሁ። ይህ ደግሞ ያስተማረኝ
በሁሉም ሀይማኖት ውስጥ ኢሰብአዊ የሆኑ ሰዎች እንደሚገኙ ነው።
መኖር
ስላለብኝ ለመኖር መጠንከር ነበረብኝ። ይህ ትግሌ ደግሞ ተቀዋሚና
ሀይለኛ የመሳሰሉ ስሞች አሰጥቶኛል። ትግሌ እግዚአብሄር በሰጠኝ ማንነት ለመኖር እንድችል እንጂ የቀበሌ ሊቀመንበርነትን
ወይም ስራ አስፈጻሚነትን እንዳገኝ አይደለም። ዘመኑን እምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ የማያውቁ አንዳንድ ሰዎች አሁንም ሁዋላ ቀር
የሆነ በራስ ወዳድነት የተመሰረተ አጀንዳቸውን አንግበው፤ ሴት የህጉ ተጠቃሚ እንዳትሆን ያደርጋሉ። በአቅሜም ስራ ፈጥሬ መስራት ጀምሬ ነበር። ግን በወቅቱ የድህነት ቅነሳ
ማለት እራስን በስራ ዘርፍ አሰማርቶ ህብረተሰብንና መንግስትን መጥቀም መሆኑ ያልገባቸው ስራ አስፈጻሚዎች ከመሰረትኩት የስራ ዘርፍ አስወግደውኛል። እነሱ ሲበሉ እኔ እንድራብ ነበር ያደረጉት።
ሰላማዊ
ትግሌ ይቅርታ አያውቅም፤ ያነገበው አቤቱታ ሰላማዊ ነውና። እንቅፋት ሆነው ትግሌን ሲያፍኑ የነበሩ ሁሉ አረመኔዎች፣ እራስን ወዳዶች
፣ ሆዳሞችና በፈጣሪ የማያምኑ ናቸው። እንዳውም እግዚአብሄር የመረጠልኝን ጾታ እንዳልኖር እንቅፋት እንዲሆኑ ሰይጣን ጋግሮ በየጥጉ
ያስቀመጠልኝ የዲንጋ ዳቦዎች መሆናቸውን አውቄአለሁ። አንዳንድ አመራሮች ምንም አይነት የፖለቲካ ሚና በአስተዳደሩ ውስጥ የሌላቸውን
ሴትም ሆኑ ወንዶችን፤ በሰፈር ውስጥ እንደልባቸው እንዲያንገላቱኝ ፈቅደውላቸዋል። በዚሕም እከክልኝ ልከክልህ ስውር ፍላጎት፤የሙስና ቅብብሎሽም ይፈጽማሉ። ለተመልካች ደግሞ ይህ ሁኔታ በአስተዳደሩ እንዳይተማመን አድርጎታል። ጊዜዬን እንክት አድርገው የበሉት ለኢትዮጲያ መልካም አስተዳደር የሚሰሩ አይደሉም።
እንዳውም መልካም አስተዳደር እንዳይኖር የሚጥሩ እንጂ። ምንም እንኩዋን ውስጤ ቢሰባበርም፤ ሴት መሆኔ እራሴን እንዳያሳዝነኝ መጠንከር
ነበረብኝ። ለሰብአዊ መብት ሲባል ደማቸውን በየበረሃው ያፈሰሱበትን ትግል፤ ከተማ ሆነው የተቀበሉአቸው እንደኔ አይነቱዋን እንዳትኖር
ማድረግ ሊያሳፍራቸው ይገባል።
ያስቡልናል ይቆሙልናል የምንላቸው የፖለቲካ ሰዎች ህይወታችንንእና
እድላችንን ሲሰባብሩትና ጊዜያችንንም እንክት አድርገው ሲበሉት እንለማመዳለን። አንዳንዶች አስቦ መስራትን የማይችሉና በነቀፊታ ውስጥ
መሻሻል መኖሩን የማያውቁ፤ የሚወስኑበት ወንበር አግኝተው ሳይጠቀሙበት ጊዜው ያልፋል። ኢትዮጲያ የሰው ያለህ ለማለት የዳዳት ትመስላለች።
ህግ ያላት ግን አስፈጻሚ የሌላት ሆናለች። በአንድ ቦታ ላይ የህግ
ጠለላ አግኝቼ እንዳልኖር ባደረጉ ሀላፊነት በጎደላቸው ሰዎች የተነሳ ብዙ ቦታ እንድቀይርና ተረጋግቼ እንዳልኖር ሆኛለሁ። ይህም
የደረሰብኝ በደል ማንም ለውጥ ፈላጊ ላይ የሚደርስ ነው። ለኔ የትግሌ ውጤት አበባ ብቻ ሆኖ ቢቀርም፤ ለሴት ልጆቻችን ግን ፍሬው
የሚበላ ይሆናል። ልጅ ነኝ፣ ጊዜ አለኝ ደግሞም ኩራት አለኝ ሳልል በማንኛውም ዘመኔ ሰለሰብአዊ መብት ብሎም ስለሴት ሰው መሆን
ለመናገር አልታከትኩም። አንድ የፖለቲካ ፓርቲ እንደብርድ ልብስ ሆኖ
ሴት ልጅ ከምትጋፈጠው ፈተና ይሸፍናታል የሚል እምነቴ፤ ዛሬም በአፈጻጸም ችግር የተነሳ በእጅጉ የተዳከመ መሆኑን እያየሁ ነው።
ቢሆንም ግን ህገመንግስት ተግባራዊ ሆኖ በሰው ልጅ ሁሉ ዘንድ እንዲከበር ዛሬም ያለሰለሰ ጥረቴን ከማድረግ ወደሁዋላ አልልም። ለሰብአዊ
መብት መከበር ካለህገመንግስት ሌላ አማራጭ የለም። በዚህም የተነሳ፤ አሁንም ይህንን ትግሌን ለማፈን የሚጥሩት አስመሳይ ፖለቲከኞች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡልኝ እመኛለሁ። እኔ የምታገለው እንደሰው ለመኖር እንጂ፤
እንደሰው ገዠ ለመሆን አይደለም። የኢሕአዴግ አስተሳሰብ መግለጫው
እርግጠኛውን የትግል መንገድ ሲከፍት ነው። ስለዚሕ የሴቲቱ ትግል ሊደገፍ እንጂ ሊታቀብ ሊስፈራራና ሞራሉም ሊነካ የሚገባው አይደለም።
እንኩዋን ኢትዮጲያ በመብት ዳዴ የሚባልበት አገር ቀርቶ እነአሜሪካም፤ እነጀርመንም ደግሞም እነራሽያና ቻይና የመሳሰሉት ሃያላኖች፤
ሴት የምትታገለውን ትግል ይበቃል ብለው ዛሬም እንኩዋን አልገቱትም። የመብት መከበር ጥያቄ ፓርቲ የሚሰጠኝ ስጦታ ሳይሆን ግዴታ
ነው። ለእኔ አዲስ ነገር ያገኘሁት የለም። ለመብቴ የማደርገው ትግል
ትናንትም፣ ዛሬም እና ነገን የኖረና የሚቀጥል ነው። ትግሌ ሊደገፍና ሊበረታታ የሚገባው እንጂ የሚነቀፍ አልነበረም።
በኢትዮጲያ ብዙ የተለያዩ ታጋዮች ህይወት ተቀስፎበታል፤ ቤተሰብ ተበትኖበታል። የተካሄዱትም ለውጦች ግዴታ መፈጸም የነበረባቸው
ነበሩ። የሀይለስላሴም ሆነ የደርግ መለወጥ ትክክለኛ ነበር። የኢሕአዴግም
መለወጥ ትክክለኛ የሚሆንበት ምክናያት ይኖራልም። ሁልግዜ ለውጥ እንኩዋን በኛ አገር በሃያላኖቹም አስፈላጊ ነው። እነ በላይ ዘለቀ፤
መንግስቱ ነዋይ ደግሞም በየበርሀው ለለውጥ የፈሰሰው ደም ሁሉ፤ ስለሰው
ልጅ እንጂ ሰለየግላቸው ጉዳይ አልነበረም። እነአቶ መለስም ከሚማሩበት ይኑቨርሲቲ አቁዋርጠው ከቤተሰብ ተለይተው በለጋ እድሜ ወደትግል
የገቡበት ምክናያት ለተልካሻ ነገር እንዳልሆነ እረዳለሁ። ትግላቸው
ፍርድ ለተጓደለበት ለእኩልነት ሲባል እንጂ። ታዲያ የሰው ልጅ የራሱን ፍላጎት ትቶ ስለሌላው መስዋእትነት የወሰደበትን ትግል፤ ለራሳቸው
ብቻ በሚያስቡ ሰዎች የፈሰሰውን ደም ከንቱ ማድረግ አያሳዝንምእን? እነሱ ከፈለጉ ስልጣኑን ይያዙ፤ ለእኔ ግን የሰው ልጅ መብቴን
ይስጡኝ። በውነቱ ለዘመናት የታገልኩበትን የማንነት ጥያቄ፤ ዛሬ በዚሕ ዘመን ብተወው እውን ኢሕአዴግን ወይስ መሪን ያረካልን? እኔ
የምናገረው ስለፖለቲካ ፓርቲ አይደለም። የሴቶች ትግል ተጀመረ እንጂ አላበቃም። አንድ የማምንበት ነገር አለ፤ ምንም እንኩዋን ሕዝብ
በተሰራው ስራ ባይረካምእና አንዳንድ ተግባራቸውም በመጨረሻ ተጠያቂእና ተወቃሽ ሊያደርጋቸው ቢችልም፤ ማንኛቸውም መሪዎች ያደረጉት
ድርጊት ለኢትዮጲያ ይጠቅማል ብለው ያሰቡትን እንጂ ይጎዳል ብለው አይደለም። በዚሕ የተነሳ አሁንም ክቡር አቶ መለስ ሴቶች በኢኮኖሚ
እራሳችንን እንዳንችል ፈታኝ የሆነ የስነልቦና ተጽእኖ የሚያሳድሩብንን ስራ አስፈጻሚዎችን ግንዛቤ እንዲያስጨብጡልን ጥሪዬን አስተላልፋለሁ።
የምንወዳቸው ሰዎች በሞት ይለዩናል። ያመናቸው ሰዎች ይከዱናል። ያፈቀርነው
ይጎዳናል። የጠበቅናቸው ፖለቲከኞች መስመር ይስታሉ። አዎ ብቸኝነት እንደራስህም እንደህዝብም የሚሰማህ ጊዜ ይኖራል። ፖሊሱ፣ ወረዳው
ወይም ዳኛው ህገመንግስቱን መተግበር ሲያቅተው በልብህ ፍርሀት ይሞላል። ሚስጥር ሸክሙዋ ቢከብድህም እንኩዋን፤ የምታስቀምጥባት ቦታ
ግን ስለምታጣ ተሸክማሀት ለዘመናት ትኖራለህ። ይህቺ አለም አድካሚ ብትሆንም ግን ልትለያት አትፈልግም። ጉቦን ብትበላ ትጠየቅበታለህ።
አለመብላትንም ወንጀል አድርገው የሚያሳድዱህ ሰዎች እንደማይጠፉ እወቅ። ይህ ግራ የገባውን አለም መሪዎች ቢረዱትስ ሁሉንም በነጻነት
እንዲናገር በፈቀዱለት ነበር። በውስጥህ ብዙ የታፈነ ነገር አለ። ምንአልባት ሳንባ ሌላው እንዲሆነን ስለምንፈልግ፤ አንድ ጋዜጠኛ
ወይም አንድ ፖለቲከኛ እንመርጣለን። በውስጣችን የሚብላላውን ብሶትና ፍላጎት ሲናገርልን ጀግና የሚል ስም እንሰጠዋለን። ጀግና ያልናቸው
ሁሉ ግን ለጥያቄአችን መልስ ስላስገኙልን ሳይሆን ደፍረው ስለተናገሩልን ብቻ ነው። በዚሕም የተነሳ መናገር ለሰው ልጅ ምን ያህል
እፎይታ እንደሚሰጥ ተገነዘብኩ።
ሴትን ለማጥቃት የተነሳሱ ሰዎች፤ አንድ ሰው የግድ ማሸነፍ እንዳለባቸው
ድክመታቸው ስላስገደዳቸው እንጂ ሌላ ምክናያት የላቸውም። የውስጣቸው ወኔ አንድ ማረፊያ ይፈልጋል፤ በዚህም የሚያሸንፉትን ይፈልጋሉ።
ሴቱዋም ደካማ ናት ብለው ስለሚገምቱ ስልጣናቸውን ይጠቀሙባታል። ስለዚህ
ሴትን የሚያጠቁ ሰዎች የስልጣን ልምምድ እያደርጉብን እንደሆነ ተረድቻለሁ። እኔ ግን የስልጣን መለማመጃ ለመሆን አሻንጉሊት አይደለሁም።
ሴቱዋ ልጄ ሆይ፤ ልብሽ ቁምሳጥን ውስጥ በሰቀልሽው ልብስ አይደሰት። እሱስ ብል ይበለዋልና። የማይበላውን የትውልድ እናት እንድትሆኜ
በርቺ። የሚመጣው ዘመን ፈታኝ ነውና።
ቸር ይግጠመን።
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen