Freitag, 28. August 2015

የበረሃው ድምጽ/


ወገናዊነት ወገኔ ላላልከው ሕመም ነው


ዛሬ ለተበደለ በመቆርቆር ከእምነት አገልጋዮች በላይ ፖለቲከኞች በልጠዋል፡፡ እርስ በእርሳቸው ሀጢያታቸውን ይገላለጣሉ እና፡፡ አህዛብ የተባሉት በመገሳሰጽ እከሌ እና እነእከሌ ሐጢያት ሰርተዋል ከስልጣን ይውረዱ እያለ ይደክማል፡፡ እከሌ እርቦታል ጠምቶታል ይላል፡፡ ስለተሳሳቱ ስላዳሉ የምድርን ስልጣን አይገባቸውም እያለ ይጮሃል፡፡ ዛሬ ግን ቤተክርስቲያን ተስማምተው ወንጀልን በሚደባበቁ ቀሳውስቶች የእግዚአቤሄር ቤት የሀጢያት ደባቂ እየሆነች መጣች፡፡ እርስ በእርሳቸው የወንጌላዊው፤ የፓስተሩ የዘማሪው ደጋፊ እና ቲፎዞ አበጁ፤ ለሰው የማይታይ ለእግዚአብሄር የማይታይ መሰላቸው፤ ሰማዩን የሚያዘጋ መንፈስ ቅዱስን የሚያርቅ ስራ ፈጸሙ፡፡ ሐጢያት ዝም ሲባል ሁሉ ያደርገዋልእና ጤነኛ መሰለ፡፡ እንዳውም ሀጢያት ያለ ነው ይሉን ጀመር፡፡ የሚሰርቀውንም እግዚአብሄር የመረጠው ነው ይሉን ያዙ፡፡ ለእነሱ ለሰሩት ሀጢያት መቀጫ ይሆናል ብለው ግን ሊነግሩን ፈሩ አልያም አይደፍሩትም፡፡


የቤት ቁዝምዝም እቃ ይፈጃል እንዲሉ፡፡ የክርስቶስ ሳይሆን የፓስተሮች የቄሶች ስም የነገሰባት ቤተክርስቲያን እየሆነች መጣች፡፡ ሰው እንደፈለጋችሁ ልበሱ ጠጡ ብሎ ሁኑ የሚል፡፡ ሴቱ ቆዳውን መለጠጥ ጸጉርን መቀጠል እና ቂጡን መቀጠል፤ ለሰው የቀናው እግዚአብሄር የለወጠው መስሎ እንዲታይ ተደረገ፡፡ ከቶም በተሰጣቸው ስጋዊ ማንነት፤ በአፍንጫቸው አፈሩ፤ በሰውነታቸው በጸጉራቸው ተሸማቀቁ፡፡ በእግዚአብሄር ትእዛዝ ሳይሆን በሰው ትእዛዝ የምትመራ ቤተክርስቲያን፡፡ ያለባበስ ችግር እና የመልክ ችግር ሆነ እና የሰው ልጅ ችግሩ፡፡ በእሱስ ነጻ አወጡን፡፡ እኛም አማርን አሸበረቅን፡፤ ባታችንን ዳሌያችንን ይህ ነው እኔ እበልጣለሁ የሚሉ ውድድር ውስጥ ገባን፡፡ በቢሮም በትዳርም ተፈላጊ እሱዋ እንድትሆን፤ ተመከረ፡፡ በአፍሪካ ሁሉን በማያዳርስበት ሚካፕ ጸጉር ቅጠላ፤ ያሸበረቀ ለብስ፤ ሰውን ሰውን የሚያበላልጥ አዋጅ ታወጀ፡፡ ማድረግ ያልቻሉ እውቀታቸው ሳይሆን ሰውነታቸው መመዘኑ አይቀርም እና፡፡ በአይን የሚበላበት አገር እያፈራን መጣን፡፡ ይህ ሁሉ ሙስና ጋባዠ መሆኑ ግን የገባው እና የተረዳው የለም፡፡ ያለበሰችው ተናቀች ተሰደበች፤ ባላገር የማትሰለጥን መበል መጣ፡፡ ሁሉም ለንዋይ እሩጫ ሆነ፡፡ መንፈሳዊው ግን እንደታሰረ ሳይፈታ አለም ልታልፍ መሆኑን ለማየት አሳወሩን፡፡ እሱ ከባድ ነው እና እሱ ገሳጭ ነውእና ፡፡ እንዳውም ለአገር ለወገን የሚጠቅመው፤ የሰው የስጋ ልብሱ ሳይሆን፤ የመንፈሳዊ ልብሱ ነበር፡፡ እሱ ግን ክልክል ነው፡፡ሌባን ሌባን ማለት አይቻልም፤ አይገሰጽም፡፡ የሚገርም የሚደንቅ መንገድ ተያዘ፡፡ለንዋይ ውድድር፤ ሰው እራሱን ሸጨ፡፡ 

እንደእውነቱ ሽሕ ምእመናን ከሚደናገረው እና መደነጋገር ላይ ከሚወድቅ፤ በአንድ ሰውም የተነሳ ዝማሪያችሁ እና ጸሎታችሁ ሰማይ የሚያዘጋ እንዳይሆን፤ ከማሃልህ ያለውን የፓስተር፣ የቄስ የዘማሪውን ሰው ነውር አጋልጠው፤ ለየው በአደባባይም እንዲጸጸት እና ንስሃ እንዲገባ አድርገው፡፡ መልሰህም ያንን ቦታ አትስጠው፡፡ አርአያነቱን አጉሎአል እና፡፡ ተወካይነቱን ንዶአል እና፡፡ ይህንን በቤቱ ካደረክ አርአያ ቤተክርስቲያንህ ትሆናለች፡፡ እንዳው ምእመናኑ ቁጥሩ እንዳይቀንስብኝ፤ እያለክ፣ አየሁ አላየሁም ብለህ የምታልፍ ከሆነ፣ ምእመናን ውስጥ ጉዳዩን ቀብረሃል፤ ወገናዊነት ወገኔ ላላልከው ቁስል ነው፡፡ እንኩዋን አዲስ ሰው ልትስብ፤ የያዝከውም ስጋው እንጂ መንፈሱ ተለይቶሃል፡፡ ሰማይን የሚያዘጋ ስራ ሰርተሃል፡፡ አድራጊው ብቻ አይቀጣም፤ እያየውም ያልገሰጸው፤ እየሰማም ልቡ ያመረቀዘው ሁሉም ሀጢያት ሰርቶአል፡፡ ከሀሰት ጋር የምትተባበር ቤተክርስቲያን የጌታ ጣት ያለባት አትሆንም፡፡ እሱ የመሰረታት የተለየች ነች፡፡ ወዳጄ ሆይ በጌታ የተመረጠው የመጽሃፍ ቅዱስ ዳዊት እንኩዋን ነውሩ በመጽሃፍ ቅዱሱ ተጽፎ ቀርቦአል፡፡ አንተም እየተማርክበት እና እያስተማርክበት ነው፡፡ ሌላው ግን በአንተ ጽድቅህ እንጂ ሀጢያትህ እንድንማርበት የማትፈልገው አንተ ማነሕ? ምነው ወንጌል በብዛት ተሰበከበት በተባለችበት ኢትዮጲያ፤ የሰው ልጅ በትእቢት የተወጠሩ፤ ጉቦ የሚበሉ፣ የሚያዳሉ፣ በዘር የሚለዩ በሀሰት የሚፈርዱ ዳኞች፣ ሰውን የሚደበድቡ ፖሊሶች፣ ሰራተኞች በምድሩ ላይ በዛ? ንዋይ ያሳበደው ዜጋ ተተካ ፡፡ ህንጻው ያማረ ውስጥ ኑዋሪ፣ የሚያብረቀርቅ ልብስ ለባሽ የቆሸሸ ህሊና ተሸካሚ ለምን ሆነ? እራስህን ከሌላው ሀይማኖት ጋር ለማወዳደር ለምን ትሮጣለሕ፤ ወዳጄ ሆይ አንድ ነገር ልበልህ፤ ቤትህን የምታጸዳው ሌላው ሲያጸዳ አይተህ ነው እን? እኔስ የምጠብቀው እንግዳ ካለቀጠሮ ይመጣል እና ልዘጋጅ አትልም?

ቤተክርስቲያን ደግሞ ለምእመናኑዋ ትግለጠው፡፡ ሀጢያት መማሪያ መሆኑን፤ ከዳዊት ነፍስ ገሎ ተደብቆም መደበቅ አለመቻሉን አንተ ተምረሃል በእሱም አስተምርሃል፡፡ አንተ ሀጢያትን ካላወጣህ፤ ነገ የእግዚአብሄር እብድ የተባለው እሱ እራሱ በመረጠው አስነስቶ በሚልከው ይገልጠዋል፡፡ አንተ በጉዋዳህ የደበከው ለለአደባባይ ነገ ይታወጃል፡፡ ነውርን የደበቀች ወይም የምትፈጽም፤ የምትተባበር የሌባ ደባቂ እንጂ፤ እሱም የአባቱ ን ቤት ሊያጸዳ ይነሳል፡፡ አፍርሶም ይገነባታል፡፡ ስለእዛ አንተ በቤትህ ስሙን አጥፍተህ እንዲሸማቀቅ ያደረከው ትክክለኛ አማኝ፤ እግዚአብሄር ተነስቶ አንተን ደግሞ በአደባባይ እንድትዋረድ ያደርጋሃል፡፡ እግዚአብሄር ትናንት ይህን ሰርቶአል፡፤ ዛሬም ይሰራል ነገም ይቀጥላል፡፡ አለም እስከምታልፍ፤ እሱም የእሱ ይሆኑትን እስከሚሰበስብ ድረስ ህዝቡን አይጥልም፡፡ የማያምን ሰው እንኩዋን ቢሆን እግዚአብሄር ሀሰትን ስሩበት አላለም እና፤ ለማያምንም ሊፈርድ ይነሳል፡፡ እሱ የእውነት አምላክ ነውእና፡፡ ሰላም ይብዛላችሁ፡፡
 ባዩሽ 

Mittwoch, 19. August 2015

እምነት መደበቂያ ሲሆን ፤ አድርባይ ያደርጋል



ቡሄን ማሰቡ ድንቅ ቢሆንም፤ ግን አንድ ነገር ትዝ ሲለኝ ይህችን መልእክቴን ላስተላልፍ ወደድኩ፡፤ ዘንድሮ በአለም ላይ ብዙ አዲስ ነገር እያዬን ነው፡፡ እና በእኛ አገርም የደነገጥንበት ነገር በሽ ነው፡፡ ይሁን እና ግን ዲሞክራሲን እና እምነትን እንዴት ጎን በጎን ማስኬድ ይቻላል የሚለውን ነገር ማየት መልካም ይመስለኛል፡፡ ብዙ ግዜ ከሰዎች ጋር መነጋገር ብፈልግም ግን ብዙውን ግዜ ወግ አጥባቂነታችን ለመነጋገር እንደሚያዳግተን ልብ ብዬ አስተውያለሁ፡፡ መነጋገር ክብሪት ይዞ እሳት እንደመለኮስ የሆነበት ኢትዮጲያችን፤ የህብረተሰቡም ባህሪ ፖለቲከኞቻችን የተመቻቸው ይመስላል፡፡ ለሽ ብለውበት፤ አብረው ዳንኪራ ይመቱበታል፡፡ ለምሳሌ ስለለውጥ ወይም ስለዲሞክራሲ አካሄያድ ስንነጋገር፤ ብዙዎቻችንን ዲሞክራሲን እንመኘዋለን ግን እንደፈልግነው  ደግሞ ፍላጎታችንን ማሳየት አለብን፡፡ ሁሉም ጻድቅ በመሰልንበት አገር፤ ሀጢያተኛው ታዲያ ማን ሆኖ ነው፤ የምናማርረው?

 የእኔ ፍርሃት አንድ ነገር ነው፤ እሱም ቅርስ ስንል ያልተለወጠ የፖለቲካ አስተሳሰብ ባህላችን አድርገን ቅርስ አድርገነው እንዳንቀር ነው፡፡ በብዙ ቦታ ስመለከት ሁሉም እንደጻድቅ ማውራት እና፤ የሚጥረው ጥረት ምድሪቱን ገነት ለማድረግ ይመስላል፡፡ ይህ ግን በምንም ሊሆን የሚችል አይደለም፡፡ እንዳውም የዲሞክራሲ አገሮች ያረጋጋቸውን የ ሕገ መንግስት የበላይነት እንደመጠየቅ እና እንደመስራት፤ እንደፋሽን እና እንደባህል ሀይማኖቴ እምነቴ እያለን የምንተዳደርበትን  ሕግ የረሳን እና እንደልባችን አልቃሽ እና አስለቃሽነታችንን ተቀብለን እንድንኖር ሆነናል፡፡ ደግሞ እውን እምነት እንዲህ ከሆነ ጭንቅር ብሎ ይቅር እያለ ሰው እንደሚሸሽ ይሆናል፡፡ ምክናያቱም እምነትም አንድ ነገር ካላሳዬ ተስፋ አስቆራጭ መሆኑ የማይቀር ሀቅ ነው፡፡ የአለምን ታሪክ ስናስበው፤ ሁሉም በእምነት የተጉዋዘ እንደነበር ታሪካቸው ያስታውሰናል፡፡ ዛሬ ፋሽን ሆኖ እኔ ኦርቶዶክስ ነኝ ፔንጤ ነኝ አልያም ሙስሊም ነኝ እየተባለ በሚኮራበት እና በሚመጻደቅበት ሰአት፤ የኢትዮጲያ ሁኔታ ምን ያህል እንደተለወጠ እራሳችን አይተን መታዘብ ነው፡፡ ወዴትስ ተለወጣ ማለትም ያሻል፡፡ ዋናው ነገር ሰው እራሱን አለመዋሸቱ ነው፡፡ ኢትዮጲያ ሲታሰብ፤ ጥሩ ነው ይላል የደላው፤ ያልደላው ደግሞ መራራ ይለዋል፡፡ ይሁን እና ግን እምነት መራራ እና ጣፋጭን የሚበላ አማኝ በአንድ የእምነት ዘርፍ ውስጥ  ይዞ ለዘመናት መራመድ ያቅተዋል፡፡ እንዳየናቸው የሩቅ አገሮች፡፡ ተግባር የለለው  እምነት ምድርን ከበጎ ወደክፉ እየለወጠ የሚሄድ እስኪመስል ድረስ ፤ በማስመሰል እግዚአብሄርስ ይገኝበት ይሆን ወይ ብሎ የሚጠይቅ መብዛቱን እኔ አላውቅም ብዬ ባልፈው እወዳለሁ፡፡ ሕሊና ሁሉም አለው እና፡፡

 ሕግን ለዲሞክራሲው የሚመች እንደማድረግ፤ እያደረግን ያለነው፤ ሰማያዊ አለም ሌላ ስፍራ መሆኑን ዘንግተን ምድርን ገነት ለማስመሰል ጥላሸት ተኮናንበን ስናስመሰል እንውላለን፡፡ ባህሪውን እንኩዋን ሳንይዝ ጻድቅ ሆነን የሚያለቅስን እያዬን በትእቢት እየተወጠርን፤ አንገትን በማቅለስለስ፤ ወይም አስር ግዜ የምናምነውን እምነት ስም እየጠራን እንመጻደቃለን፡፡ እኔም ውድቀቴን ዛሬ አየሁት፡፡ ሽንፈት የሚያሲዝ የሚያስለቅስ፤ ሲበሉ እና ሲጠጡ እያየሁ፤ በሰላም የበደሉኝ ሰዎች በጎኔ አብረው እግዚአብሄርን እየጠሩ፤ ስለት እያስገቡ ደግሞም እየዘመሩም እኩል እነሱ ጋር ጎን በጎን እነሱ እንደባለእድል ሲጨፍሩ እኔ እንደሀጢያተኛ ሳለቅስ አሳልፌአለሁ፡፡ ይህ ሞኝነት ይበቃል እላለሁ ዛሬ፡፡ እግዚአብሄር ይህንን ለእኔ ይመኛል ማለት ካነበብኩት እና ከተማርኩት ላገኘው አልቻልኩም፡፡ ይህ እድሌ እና ሀጢያቴ ነው የሰጠኝ ብዬ አፌን የሚያዘጋ በእንባ ጎርፍ ፊቴን የሚያጥብ እግዚአብሄር ነው የሚለኝ ካለ ሞኝነት እለዋለሁ፡፡ የደላቸውን እንደጻድቅ እያየሁ የእነሱ የመንፈስ ባሪያ መሆን እንጂ ያመጣልኝ፤ የፈጣሪ አድርጎኛል ማለት የዋህነት ነው፡፡ ፈረንጆችም በዚህ በዋህነት አሳልፈውት ነበር፡፡ የለም ለምድር የፖለቲካ ስርአትም ወሳኝነት አለው ወዳጄ፡፡ የእኔ እንባ ብቻ ምስክር ሆኖ በፌስ ቡክ የረጨሁትን አልረሳውም፡፡ አዎ አንዳንዱ እንባም እይታን ያጥባል እና፤ ሳየው ምን ያህል አዘቅት ላይ ወድቄ እንደነበር እና የስንት ክፉ ሰዎች መሸጋገሪያ ድልድይ መሆኔን ሳስበው ካለመገረም ውጭ ምንም ልመልሰው አልችልም፡፡ አዎ ሕግ ባለመተግበሩ፤ ህግ ላልሆነ ታልፎ የተሰጠ በመሆኑ፤ ሰይጣን ነበር ለካስ ዳንኪራ ሲመታብኝ የነበረው እንጂ፤ እግዚአብሄር ለእኔ በጭራሽ ያንን አይሰጠኝም ነበር፡፡ አያችሁ ዛሬ የምቆጥረው ሰይጣንን አሜን ብዬ በመቀበል ማልቀሴን እንጂ እግዚአብሄር የፈረደብኝ አልነበረም፡፡ በእምነት ስም እንድታለል ያደረገኝ አስተምህሮ እውን ከእግዚአብሄር ነበርን ብዬ ዛሬ ለመጠየቅ ተገድጃለሁ፡፡

 አሁንም እምነትን እና ሀይማኖትን እንዳውጅ አታድርጉኝ፡፡ ምክናያቱም ዛሬ የተገነዘብኩት፤እምነቴ የግሌ እንጂ የእናንተም አይደለ፡፡ የእናንተም የግላችሁ ነው፡፡ ግን አገሪቱ የጋራችን እንጂ እኔ ስለተገለልኩ እንዳለቅስ፤ ያልተገለለው እንደተመረጠ እንደተባረከ ሆኖ እንዲኖርበት አይደለም፡፡ ይህንን ሰበካ ከአሁን በሁዋላ ከማንም ልሰማው አልፈልግም፡፡ እስከዛሬ ግዜዬን እንክት አድርጎ የበላው ይገርመኛል፡፡ የሚገርመኝ ዛሬ ለምን ሁሉም እምነት እንደፋሽን ሌትም ቀንም መወራት ያዘ፤ እውን ሰውን የህግን የበላይነት ሳያይ ተሸፍኖበት እድሌ ነው እያለ እንዲያማርር ነውእን?
እምነት ይቅርም ብንል የሚቀር አይደለም፡፡ እግዚአብሄር አለእና፡፡ ግን እሱ ለሰማያዊ አለም እንጂ እዚህ አለም ለምንቁይባት ምድር ጥቅሙ እራስን ላላማበሳጨት እና እራስን ለምግዛት ሌላውን ላለመበደል ብቻ ነው፡፡ በዚህ አለም ላይ የሚጠቅመው፤ ሁሉንም እኩል የሚያስተናግድ የህግ የበላይነት በየምንኖርበት አገር ማስከበር ብቻ ነው፡፡ ይህ ሕገመንግስት በጉቦም በአድሎም ሆነ በተለያየው ነገር የተሸመደመደበት እና የአፈጻጸም ችግር የተዛባበት፤ እውን ክርስቲያን ወይስ ሙስሊም በአገራችን ጠፍቶ ነውእን? አይደለም፡፡ ስለዚህ ለዲሞክራሲ የምናደርገው ግንባት እንዳውም አግቶ የያዘው የሁላችንም እምነት ጨዋታው ምድርን ገነት ለማድረግ በምናስመስለው የለበስነው ማስክ ይመስለኛል፡፡ ማስክ ስል አስመሳይነት ነው፡፡ ይህ ካልሆነ የሁሉም እምነት በተለይ ኢትዮጲያ ውስጥ የሚሰበከው ሰበካ፤ አዎ የለለውን ምድሪቱን ገነት ባደረጋት ነበር፡፡ ግና እንኩዋን ምድሪቱን ገነት ሊያደርግልን ቀርቶ፤ የሰማዩም እንዳይታዬን በማስመሰል አይናችንን ሸፍነን ልባችን አሳውረን፤ እንገኛለን፡፡ ወዳጄ ሀይማኖት እና እምነት በውነት ሁሉም የእራሱ የግሉ ነው፡፡ እኔ አይመለከተኝም፡፡ የፈለገው እምነት ተከተል፤ አፍንጫዬን እስከአልነካህ ድረስ፤ መብትህ ነው፡፡ ግን አሁን የሚያስፈልገን በእምነት እና በሀይማኖት ሽንፈታችንን፣ ስንፍናችንን እና ሕግ ጣሽነታችንን ደብቀን ከመኖር፤ ሁላችንም ለፖለቲከኞች የሚመች የህግ የበላይነት ምን እንደሚመስል እና እንዴትስ እንደሚፈጸም አይናችንን ፈጠጥ አድርገን ብንጠብቅ መልካም ይመስለኛል፡፡ እኔ እግዚአብሄርን በጣም እወደዋለሁ፡፡ ሰውን እንዳልበደል አጋዥ ነበር እና፡፡ ሰይጣን ግን ሲያስለቅሰኝ፤ እግዚአብሄርን ለምን አላገዘኝም ልል አልችልም፡፡ እኔ የተቀበልኩትን  እና ተሸንፌነት ያስለቀሰኝን ሰይጣን ተዛምጄ ኖሬ ፤ ድሮም እሱ ለማላቀቅ የእኔን ፍቃድ ይጠይቃል እና፡፡ ግን የሰጠንን አይምሮ በትክክሉ ተጠቅመን ለሕግየበላይነት እስከአልቆምን ድረስ፤ የምታለቅስ ሴት፤ ደሃ ደካማ፤ ፍርድ የተጉዋደለበት እና በማንአለብኞች እና በእራስ ወዳዶች የተንገላታው፤ ሰማይ ያስከፍትልኛል ማለት ዘበት ነው፡፡ 

 ሊሆን የሚችለው ሰው ለተበደለውም አለሁ ሲል፤ ጎረቤቱን አካባቢውን ሲመለከት እና እራሱን በእምነት መሸንገል ሲያቆም ያነዬ እምነትህም እርባና ይኖረዋል፡፡ ካልሆነ እምነትህ እምነት ሳይሆን ምሽግ ይሆናል፡፡ እኔ አልተመቸኝም፡፡ የሚመቸኝ፤ እራሳችንን ማታለል ትተን፤ ለህገመንግስት የበላይነት ሁላችንም ቆመን ሕግን የበላይ አድርገን ስንቆም ነው፡፡ ካልሆነ የማንም እምነት ከስደት ህዝብን ሲያስመልጥ አይተን አናውቅም፡፡ እሱ ስራው ከሰማያዊ አለም እና ደግሞም በልብህ እውነተኛ እምነት ስለሆነ፡፡ ወዳጄ በጾም ብትበላ ባትበላ፤ ብትጸልይ ባትጸልይ ይህ የእራስህ የእራሴ የግሌ ጉዳይ ነው፡፡ ለምድሪቱዋ ስርአት ግን የሚጠቅማት የፖለቲካ ስርአት ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ካልሆነ፤ ዘወትር አንተ ስትዝናና እኔ በእግዚአብሄር እና በሰይጣን እያመካኘሁ ሳለቅስ መኖር ነው፡፡ ይህ ደግሞ ጦርነት ጋባዥ መሆኑን እያየነው ነው፡፡ አዎ ሰላም የሚደፈርሰው፤ እምነትም እራስ ማታላያ ሲሆን በመሆኑ፤ ወደሕግ የበላይነት እያንዳንዱ እስካልተመለከተ እና እንዲተገበር ካልጣረ፤ የእምነቱ ቀላጅ ፍቃደኛ ባሪያ፤ ወሬኛ እና አድርባይ ይሆናል፡፡ ይህ ያስመርራል ይበቃል፡፡ ስለዚህ የፈለከውን እምን፤ ግን የህግ የበላይነትን በምድራችን ላይ ዛሬ መኖር አለበት በል፡፡  የህግ የበላይነት በኢትዮጲያ ይስፈን እላለሁ፡፡
ባዩሽ አበበ




Samstag, 1. August 2015

አንድ ለአምስት፤ በሰው አይምሮ ውስጥ


ስትወድቅ የጣለኝ ምንድን ነው በል፡፡ እሱንም እወቀው፡፡ የጣለህን ነገር ሳታውቅ፤ የጣለህን መላቀቅ አትችልም፡፡ እራስህን ለመርዳት ጥረት አድርግ፡፡ ከሌላው ከጠበክ እሱ የበለጠ ጉልበት ያስወጣሃል፡፡ ጠላትህን አትጉዳው፤ ግን ደጋግሞ እንዳይጎዳህ፤ ሽሸው፡፡ ለመሸሽ ግን መጀመሪያ የጎዳህን ሜተዱን/የመጉጃ መሳሪያውን እወቅ፡፡ ሰው እራሱን ለማትረፍ ጥበብ ተሰጥቶታል እና፤ መንገድህን ይዘህ ሂድ ቀጥል፡፡ ሰው ምንግዜም የሚለው አያጣም እና፤ ወደሁዋላ አትመልከት፡፡ 

 ሞት ሞት እንዲሸትህ የሚያደርጉ ሰዎች በአገራችን ጥቂት አይባሉም፡፡ እንግዲህ ባህሪያቸውን ልንገርህ እና ከእነሱ እራስህን አሽሽ፡፡ ቢቻለህ በሮኬት፣ አልያም በመኪና፡፡ ባይቻልህ በፈረስ ሽሽ፡፡ ይህ ሁሉ ካልተቻለህ፤ መንፈስህን አሽሸው፡፡ ባህሪያቸው፤ ጉሮኞች፣ ውሸታሞች፣ ሸንጋዮች፣ ድግስ አብዝተው ሰው የሚጋብዙ፣ ማህበራዊ ህይወት ላይ ተፍ ተፍ የሚያበዙ፤ ስውር የክፋት አጀንዳ የሚያራምዱ፣  ሰውን  አግለው የሚያስገልሉ፣ የባለስልጣን እና  የተዋቂ ሰው ስም እየጠሩ እከሌን አውቀዋለሁ እከሌ ዘመዴ ነው  የሚሉ፡፡ ስጦታ መስጠት የሚያበዙ፣  ደግሞም ስትመለከታቸው፤ በእራስ መተማመን የገነቡት፤ ከእነሱ በቀለም ትምህርት አንሶ ያዩትን በግሩፓቸው ውስጥ በመሰብሰብ ነው፡፡ ከእነሱ በእውቀትም ሆነ በኑሮው ያነሰውን ሰው በመሰብሰብ፤ እራሳቸውን ትልቅ በማድረግ እንዲወራላቸው እና ዝነኛ ሆነው እንዲቀርቡ የማድረግ ጥበብ አላቸው፡፡  የእነሱ የሸር ጥበብ  ወጥመድ ውስጥ የወደቁ አጫፋሪዎች፤ ሰውየው የፈለገውን ክፉ ቢሆን እና ስውር የሆነ አጀንዳውን ሊያቁበት አይችሉም፡፡ ይገርማል፡፡ እነዚህ ሰብስቦች፤ ይህ በማሀበራቸው ደምቆ ተፍ ተፍ ተብሎ በእነሱ አንቱ የተባለ ሰው፤ እንኩዋን እነሱ የሰውየውን ስውር አጀንዳ ሊያቁበት ቀርቶ፤ እንዳውም ጥሩ ሰው መልካም እየተባለ እንዲመሰገን እና ስሙ እንዲገን ያደርጉታል፡፡ ይህ የንቃተ ህሊና ድክመት እና የግንዛቤ እጠረት የሚከሰተው ብዙውን ግዜ በሴቶች ውስጥ ሆኖ አይቸዋለሁ፡፡ ለምሳሌ ያቺ ሴት በአስተሳሰብም ሆነ፣ በመልክ አልያም በትምህርት ሆነ በተለያዬ እሱዋ እራሱዋ ትበልጠኛለች ባለቸው ነገር የተናደደች ሴት፤ የአንድ ሴትንም ስም ለማጉደፍ ለማግለል የግድ ተወታትረው በቤተክርስቲያን ወይም በበጎ አድራጎት አልያም በሌላ ነገር ተሳቦ ማህበር ሊያቁዋቁሙ ሲውተረተሩ አያለሁ፡፡ ተመልክቻለሁም፡፡  ይህ አላማው የጠላችውን ወይም በተለያየው እይትዋ ትበልጠኛለች ያለችውን ሰው ወይም ሴት ለመጉዳት የታቀደ አላማ ብቻ ነው፡፡ ብዙ ግዜ ፖለቲከኞች ብቻ አይደሉም አንድ ለአምስትን የሚመሰርቱት፡፡ ይህንን ለመመስረት የአንዳንድ ሰዎችም መርዛማ ባህሪ አስረጂ መሆኑን አረጋግጫለሁ፡፡ 

 
              እዚህ ማህበር ውስጥ በምንም ታአምር፤ የማሃበሩ አለቃ የሆነቸው ባለስውር አጀንደዋ፤ መጀመሪያ የምትነዛው ፕሮፖጋንዳ፤ የጠላቸውን ሰው ስም በማጥፋት እንድትገለል እንዳትታመን  የሚያሰደርጋትን ወሬ በየተራ ለሰዎች በየግላቸው ከነዛች በሁዋላ ነው፡፡ ልብ በሉ ማህበር ውስጥ የአንድ ሰው የጥላቻ ነገር በጅምላ በአዋጅ አይታወጅም፡፡ ልብ ብላችሁ ስትመለከቱ፤ የአንድ ሰው እርኩስ ምግባሩ፤ ለማህበር ያጨውን ወይም ሊያሰባስባቸው ያቀዳቸውን ሰዎች፤ በየተራ እቤቱ በዶሮ ወጥ በጥሬ ስጋ እና በታላቅ ክብር ግብዣ እየጠራ እያበላ ነው  ስውር አጀንዳውን የሚያስተላልፈው፡፡ መርዙን የሚረጨው፡፡ ብዙ የሚገርሙ ነገሮች አይቼ ለመታዘብ የረዳኝን አምላክ ስሙ የተባረከ ይሁን፡፡ ሰውነታቸውን ስብእናቸውን ግን በምግብ ብቻ በሆዳቸው ብቻ እንደሸጡት ያልገባቸሰው ሰዎች፤ ፍጹም የማያውቁት ሰው ስም ሲጠፋላቸው፤ አምነው ተቀብለው የበሉትን የቅቤ እና የበርበሬ ጠረን እያገሱ፤ አይ ዶሮ ወጥ እያሉ ይወጣሉ፡፡ ከዛም የተነገራቸውን የሀሰት ቫይረስ እነሱም አስተጋቢ ይሆናሉ፡፡  ይህም ነው በአገራችን ፍርደገምድልነት እያደገ፤ በቀበሌውም በፖለቲካውም ገብቶ የሚያምሰው፡፡ 

              ብዙ የተለያዬ የህይወት ልምድ ብወስድም፤ በአንድ በኩል ግን ለምንድን ነው እከሌ እከሌ ከእኔ የራቁት በማለት ነገሩን ኮስተር ብዬ መመልከት ጀመርኩ፡፡ ሰውን ማኩርፍ አልፈልግም፡፡ ለማኩረፍ በቂ ምክናያት ቢኖረኝም፡፡ እኔ ግን ሁኔታዎችን መሰረቱን ማወቅ እፈልጋለሁ፡፡ የሚገርመኝ የጎዱኝ ሰዎች በጣም ህይወቴንም ገንዘቤንም ሆነ ጉልበቴን እና ፍቅሬን የሰጠሁዋቸው እና ይሆኑኛል ብዬ የመረጥኩዋቸው ያገለገልኩዋቸው ሰዎች መሆናቸው ነው የደነቀኝ፡፡ ስለዚህ ጌታ የረዳኝ በደንብ መሰረቱን እንዳውቀው እንድመራመርበት ይመስላል እማይቀየም ፣እማትከፋ  እና ቻይ አድርጎኛል፡፡  ስለዚህ የሚጎዱኝን ሰዎች ደጋግሜ መገናኘት ግድ ይለኝ ነበር፡፡ ሞኝም ያስመሰለኝ ይህ ባህሪዬ ነው፡፡ በእርግጥም እነዚህ ሰዎች የበለጠ እየናቁኝ፤ በእኔ ውድቀት ግን እራሳቸውን እየገነቡ፤ ልባቸው እና ሰውነታቸው እያበጠ ሲሄድ አየው ነበር፡፡ መቸም ሰውን ሰው የሚጎዳው የአስተሳሰብ አይምሮው ሚዛኑን ያልጠበቀ ነው ብዬ ከልጅነቴም አምናለሁ፡፡ እዚህ ላይ የምትረዱልኝ ነገር፤ እኔ ከሁሉም ተሸዬ እና አልያም የተሻለ እውቀት ኖሮኝ ሳይሆን፤ ብቸኝነቱ እና የተደረገብኝ የስም ማጥፋት ዘመቻ፤ ስለመረረኝ እና አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ስላደረሰኝ እና ጉዳት ስላመጣብኝ ነው፡፡ እግዚአብሄርንም እንድወደው ያደረገኝ የማይተወኝ እና የሚቆምልኝ  በከተማው ውስጥ የማደርገውን የበረሃውን  ጉዞ እንዳቁዋርጥ የሚረዳኝ እሱ ብቻ ሆኖ ስላየሁት ብቻ ነው፡፡ ምን አልባት አማራጭ ቢኖረኝ ኖሮ በእግዚአብሄር እምነት ባልተጉዋዝኩ ነበር፡፡ የእግዚአብሄርን አካሄዱን እና ሀይሉ፤ ባልተረዳሁ ነበር


ከባዱ ምንም ሳትበድለው የጎዳህን ሰው ከመሸሽ፤ ባህሪውን ለመረዳት መጣር ፈታኝ የሆነ የስነልቦና ተጽእኖም እንዳለው መረዳት ነበረብኝ፡፡  ቢሆንም ግን በዚህ መልኩ  ለማወቅ ቀጠልኩ፡፡አንድ ግዜ  የጠቀምኩዋት ሴት ግን የእኔን በጎ ነገር እንደማትወድ በተደጋጋሜ ያረጋገጥኩት ሴት፤ ለምን እንዲህ እንደምትከታተለኝ   ያደረኩትን  የእራሴን የህይወት የማትረፍ ምርምሬን ተመልከቱ፡፡ ድንገት አንድ ቀን እንደሚስጥር አድርጌ ኢህአዴግ መሆኔን አጫወትኩዋት፡፡ 
 እኔ ግን እንኩዋን ኢህአዴግ ልሆን ቀርቶ ምንም ፖለቲካ ውስጥ የለለሁ ሴት ነኝ፡፡ ግን እራሴን የሚረዳኝን የማወቅ ዘንባሌ በውስጤ አይሎብኛል፡፡ እሱዋም አንድ ሰሞን የኢህአዴግን ጥሩ ገጽታ በማውራት ከእኔ የበለጠች የኢህአዴግ ደጋፊ በመሆን  ድምጹዋን ከፍ አድርጋ፤ ኢህአዴግ ምንም ያላደረገን ድርጅት ነው፤ ጥሩ ነው፡፡ ልማት ነው  ምናምን እያለች  ወዲያው አንድ የተገናኘንበት ቦታ ላይ ማውራት ጀመረች፡፡  ነገሩ ገና ከኢህአዴግ ታገኛለች ብላ የፈራችውን ስልጣን ቀምታ ለመውሰድ መሆኑን ገብቶኛል፡፡ አንድ ሁለት ሴቶችንም በመጥራት  ኢህአዴግ ጥሩ ነው እያለች ቀጠለች፡፡ ያልገባት፤ ኢህአዴግ እሱ ያደራገውን እንጂ፤ ተደራጅተው የመጡትን፤ዝም ብሎ የሚቀበል አለመሆኑን የተረዳች አልመሰለኝም፡፤ አልያም መመርመሩ የማይቀር መሆኑን፡፡ በቃ እኔ ስለኢሕአዴግ ላወራ ስል አፌን በማለት ዋና አውራ ለመሆን እንዴት እንደጠራች ሳስበው፤ ሆዴ እጅግ ይስቃል፡፡ 

እንደቤተክርስቲያን ሳይሳለሙዋት የሚውሉም አጃቢዎቹዋ ለአንድ ሰሞን በዛው በእሱዋ አባባል ቀጠሉ፡፡ ከአንድ ወር በሁዋላ ያቺን የስልጣን ጥመኛ እና እኔን የምትከታተል ሴት፤    በናትሽ ይህ ግንቦት 7 የሚባል ድርጅት እንዴት አይነት ጥሩ ድርጅት መሰለሽ፤ በቅርቡ እኔን ሊያነጋግሩኝ ሳያስቡ የሚቀሩ አልመሰለኝም፡፡ ኢሳትም ኢንተርቪው ሊያደርገኝ እየሮጠ ነው አሉ አልኩዋት፡፡  ፊቱዋ በርበሬ ሲመስል አየው ነበር፡፡ እሱዋም ወዲያው፤ ስልክ ደዋውላ ታገኛለች ብላ የፈራቸውን  ሹመት ወደእሱዋ ለማዞር ይመስላል
እነዛን የከበቡዋትን ሚስኪኖች ሌክቸር ስታደርግ መዋሉዋን ሰማሁ፡፡ ወዲያውም ደግሞ ተቃዋሚ ሆና የሰበሰበቻቸውን ልጆች፤ አማራው እንዲህ ሆኖ እንዲያ ሆኖ፤ትግሬው ይህን አድርጎ ያን አድርጎ ስትል መዋሉዋ ገረመኝ፡፡  እውን ድጋፍም ጥፋትም የሚመጣው ከግለሰቦች መቀናናትም መሆኑን ያውቃሉ፡፡ ዘላቂነት ያለው ነገር መመስረት የማይቻልበት ብዙ ምክናያቶች ተመለከትኩ፡፡

 መደነጋገር የሚመጣው ከቅናት መሆኑን አየሁ እና ግርም ብሎኝ፤ ሌላ ቀን ፔንጤ እንዴት አይነት ጉደኛ እምነት መሰለሽ፤ እዛ ገብቼ የእርዳታ ነገር ለማቁዋቁዋም እጥራለሁ አልኩዋት፡፤ ወዲያው እከሌ እከሌ ፓስተር ቅርብ ወዳጁዋ መሆኑን አጫወተችኝ፡፡  እዛም የተሻለ ነገር እንድትሰራ እንደአማከሩዋት እና በቅርቡም እንደምተሰራ ተናገረች፡፡ በስሩዋ ያሉትንም ለአንድ ሰሞን እናንተ ጴንቴ ምን አደረጋችሁ፤ እና ፔንጤ ጋር መሰዳደብ የለብንም፡፡ እኔ ለምሳሌ ቤተክርስቲያናቸው ሄጃለሁ፤ የሚያስተምሩትም መሬት ጠብ አይለም በማለት ቀጠለች፡፡
መቼም እኒህ ሰዎች ከማርያም ንቅንቅ የማይሉ ሆኖባቸው እንጂ፤ በአንዲት ለሊት ፔንጤ አድርጋቸው ታድር ነበር፡፡ ማሪያም ግን ጴንጤ ጋር የለችም ብለው ስለሚያምኑ፤ ፔንጤን እንዳይቃወሙ ልታደርግ ትችላለች እንጂ ሌላውን መቀጥል እንደሚቸግራት አምናለሁ፡፡ ያም አልሆን እንደሚላት ስትረዳ
ፔንጤዎችንም እየተገናኘች፤ እኔን የሚያጣጥል፤ ከቶም ጠጪ ናት፤ ተደብቃ ትጠጣለች ማለቱዋን ሰማሁ፡፡ እንዳውም አንድ ወንድ፤ ባዩሽን የፈለግሽውን በያት፤ ግን እንኩዋን ልትጠጣ ቀርቶ ጠጪም
ትቃወማለች ሲል መመለሱን ሰማሁ፡፡ ፓስተሩ ሁሉ በእጄ ናቸው ስትል፤ ባዩሽ ቀድማኝ ፓስተር እንዳትሆን ያለች ይመስላል፡፡  ገረመኝ፡፡ ቅናት ማስተዋልን ይዘጋል እና፤ እኔን ለመጣል የምታደርገው ሁኔታ ሰውሮአታል እና፤ ሌላ ቀን  ግን  ማህበር አቁዋቁሜ የሚካኤልን ጸበል እንድንጠጣ ፤ አንዱዋን አንቺን አደርጋለሁ እና ምን ታስቢያለሽ አልኩዋት፡፡አስብበታለሁ ብላኝ ተለየን፡፡ በጣም የሚደንቀው አይንያወጣው ሁኔታ ግን   በሳምንቱ የሚካኤልን ማህበር kkkkkkk አቁዋቁዋመች፤ የሚገርመው እውነቱ የመሰከረልኝ እኔን ግን ነይ እስኪ ብላ አልጋበዘችኝም፡፡ እስኪ አሁን ምን ትሉታላችሁ ? ደሞ አንድ ቀን ሳገኛት አንድ ነገር አስቤአለሁ፡፡ እሱም ፕሬዝዳንት ኦባማ ሁዋይት ሃውስ ሊጋብዙኝ እንዳሰቡ፡፡  ኑሮ እንዲህ እያሉ የሚገፉ በሽ ናቸው፡፡ ግን ግርም የሚለኝ እንደልባቸው የሚያገለባብጡት  ተከታይ ግሩፕ መሰሪዎች ማፍራት መቻላቸው ነው፡፡
ወዳጄ ሆይ ፈራጅ ከሚያደርገው ዶሮ ወጥ  ለእውነት የቆመ ጠበቃ የሚያደርግህ ደረቅ እንጀራን ምረጥ፡፡
በቸር ባዩሽ