ስደት ይህችን አለም አሳይቶኛል፡፡ እኔም አይምሮዬ ግሎባል ሆኖአል፡፡
ግን አንድ በፈረንጆች ላይ ያየሁት ኩዋሊቲ ድንቅ የሚለው፤ ሰው ሲወድቅ የማይሸሹ፤ ሲያጣ የማይጥሉ፤ በህመሙ የሚገኙ እንባ የሚጠርጉ
ናቸው፡፡ ይህም ለምድራቸው እንደበረከት ሆኖላቸዋል፡፡ የፈለገ ቢሆን ለደስታህ ላይገኙ ይችላሉ፤ ጋባዡም ቢቀር አይቀየምም፡፡ ግዜ
ከለለው ግዜ የለውም ይላሉ፡፡ ግን በተከፋ፣ በአዘነ፣ በተሰቃየ እና ባጣበት ግዜ፤ ማንም ግዜውን መሰዋእት መውሰድ እንደግዴታ ነው፡፡
አስገዳጁ ግን ሕሊና ነው፡፡ እኔ ብዙ ያዘንኩበት ነገር ነበር፡፡ ስቃይም ነበረኝ፡፡ በዛን ሰአት ግን የተገኙልኝ ፍጹም የማላውቃቸው
ያልተዋለድኩዋቸው ፈረንጆች ነበሩ፡፡ መጽናናትን አግኛቻለሁ ፍቅራቸውንም አይቻለሁ፡፡ ይሁን እና ግን እኔ ከወደድኩዋቸው፤ ካመንኩዋቸው
እና ከጠበኩዋቸው የአገሬ ሰዎች፤ ከተወለዱኝም በወደኩበት ሰአት የቀረበኝ የለም፡፡ በታመምኩበት ሰአት የጠየቀኝ የለም፡፡ ይህን
ስል ግን ስለ የኢትዮጲያን ዘጠና ሚሊዮን ህዝብ አይደለም የምናገረው፤ እኔ የምናገረው እራሴ ከጠበኩዋቸው ሰዎች ነው፡፡ እነዚህም
ኢትዮጲያን ይወክሉ አይወክሉ አላውቅም፡፡ በባህሪ ደረጃ ነው የምለው፡፡ ብዙ ግዜ የወደቀን ግንድ ምሳር ይበዛበታል እስከምሳሌው
ይባላል፡፡ እንዳውም በሕመሙም እና በድካሜ ወቅት ይስቁብኝ ነበር፡፡ ብቻየንም በመጣሌ ይዝናኑበት ነበር፡፡ እግዚአብሄርንም ለምን
እያልኩ እጠይቀው ነበር፡፡ እሱም ብቻሽን ተውኩሽእን ያለኝ እስኪመስለኝ ፍቅሩን እሰማው ነበር፡፡ ለካስ እግዚአብሄር እነዛ የደረሱልኝን
ፈረንጆች እያስነሳ ወደእኔ የሚልካቸው እሱ ነው ብዬ አመንኩ፡፡ ለካስ የእግዚአብሄር እጅ የሚታየው በረከት እንዲቀበሉ በፈቀደላቸው
ሰዎች በኩል ነው፡፡ ሁሉ ለበረከት የታደለ አይደለም እና፡፡ እዚህ ሲስተሙም ሰውም የፖለቲካውም ስርአት በመከራህ ግዜ ብቻህን አይተውህም፡፡
እኔም እግዚአብሄርን አየሁት፡፡ በውነት አየሁት፡፡ ወገን ማለት በወደክ ግዜ ሊያነሳህ የሚታገል ነው፡፡ ወገን ማለት በታመምክ ግዜ
አይዞህ አላበቃም ትድናለህ የሚልህ ነው፡፡ ወገን ማለት ስታለቅስ እቅፍ አድርጎ እያጽናናህ እንባህን የሚያብስልህ ነው፡፡ ባዘንክ
ግዜ ብሶትህን የሚያዳምጥህ ነው፡፡ አዎ አይቸዋለሁ፡፡ በራፋቸው ሲዘጋ አይቻለሁ፡፡ አዎ ፊታቸው ሲጠቁሩብኝ አይቻለሁ፤ አዎ አብቃልሽ
ከእንግዲህ ሰው አትሆኚም የሚለኝ አይቻለሁ፡፡ አዎ ብዙ አይቻለሁ፡፡ እኔ እንደከፉብኝ ሰዎች እንዳልሆን አምላኬ ትልቅ ትምህርት
ሰቶኛል እና እኔ እንደእዛስ አልሆንም፡፡ ብችል አጽናናሃለሁ፡፡ ባልችል ግን በመከራህ ሰአት ፊትህን እያየሁ አልስቅብህም አልንቅህም፡፡
ቀን ተገላባጭ ነውእና፡፡ ሙስሊም የሆኑ ደጎችም አይቻለሁ፡፡ ይሁን እና ግን እኔ ክርስቲያን ነኝ፡፡ ደስታን አይደለም፤ መከራን፣
መጣልን እና መገለልን ያሳየኝን ክርስቶስ ግን አይቸዋለሁ፡፡ ስራው እረቂቅ ነው፡፡ አምላክ በጤነኞች ቤት፣ አምላክ በሀብታሞች ቤት፣
አምላክ ክርስቲያን ነን በሚሉ ቤት፣ አምላክ በደላቸው ቤት ብቻ ዘግቶ የሚቀመጥ አይደለም፡፡
አንድ ግዜ የገጠመኝ አስመራሪ ነገር ነበር፡፡
ብቻዬን ነበርኩ፡፡ ቤቴ በዲንጋ ይደበደብ ነበር፡፡ ብዙ መገለል ደረሰብኝ፡፡ እኔ ያጠፋሁትን አላውቅም፤ ባውቀው በደለኞችን ለመቻል
መጽናኛ በሆነኝ፡፡ ተወልጄ ባደኩበት ኢትዮጲያ ደሴ መራራ ነገር እየኖርኩ
እንዳለ ብዙው ህዝብ የሚያውቅ አልመሰለኝም፡፡ አልኮሆል አልጠጣም፤ የሰከርኩም አይደለሁም፡፡ ከህብረተሰቡ ባህልም የወጣ ልብስም
አለበስኩም፤ ያደረኩትም ወንጀል አልነበረኝም፡፡ የሰውን ክፋት ያቺን ያየሁባት ወቅት ትገርመኛላች፡፡ አይኔ ሰው ይፈልግ ነበር፡፡ አፍንጫየም ሰው በማሽተት ተርቦ ነበር፡፡ ግን ሰው ጠፋ ሰው አልተገኘም፡፡ ጭራሽ የዲንጋው ውርወራ እና፤ ነይ
በላይታችን ላይ ንጅብን እያሉ በጫት የደነዙ ወጣቶችም በመንገድ አላስኬደኝ አሉ፡፡ ስቃዬን ግን ስንቱ ያቀው ነበር፡፡ ለመሆኑ ያንን
ለማየት እግዚአብሄር ካላሳዬ ማን ያየዋል፡፡
አንድ ቀን ታዲያ ወደመድሃኒአለም ቤተክርስቲያን ድንገት
ሳላስበው አመራሁ፡፡ ቀኑ ሁሉ ጠፍቶኛል፡፡ ለምንም ወደእዛ እንደወሰደኝ አላውቅም፡፡ ሰው ባገኝ ብዬ ፔንጤ ጋር እሄድ ነበር እና፡፡
መኪናዬንም ውስጥ ብዙ ከተቀመጥኩ በሁዋላ፤ እዛው እበራፉ ላይ አቁሜ ገባሁ፡፡ እንደምንም ህይወቴን ማትረፍ እፈልጋለሁ፡፡ ሕይወቴን
ግን ለምን እንደፈለኩት አላውቅም ነበር፡፡ ምንአልባት የናፈኩዋቸውን የተለየሁዋቸውን ልጆች ላለማስቀየም ይሆናል፡፡ እራሴን ብገል
የሚያዝኑ እነሱ ብቻ እንደሚሆኑ አውቃለሁ፡፡ እንጂ ሕይወቴ መሮኝ ነበር አንገፍግፎኝ ነበር፡፡ አዎ ለልጆቼ ስል፤ እድሜ ልካቸውን
ይህንን ያንን አድርገን በነበር እናታችን እራሱዋን አትገልም ነበር እንዳይሉ፡፡ እራሳቸውን ጥፋተኛ እንዳያደርጉ እና የማንንም ግፍ
፤የገፋኝን እና ያሰቃዩኝን ሀጢይት ተሸካሚ እንዳይሆኑ፡፡ ልክ ወደቤተክርስቲያኑ ስገባ፤ በራፍ ላይ የሚለምነው ሁሉ ተኮልኩሎአል፡፡
ኦርቶዶክሱም፤ ግማሹ ፍራንክ ግማሹ ዳቦ በመደዳው የተኮለኮሉትን ያድላል፡፡ አዎ የ አመቱ መድሃኒአለም ነበር ለካ ፡፡ ሰውም ነጫጭ
ለብሶአል፡፡ ኮለል እያለ ወደደብሩ ይጠጋል፡፡ እኔም ግን ወደዛ አልሄድኩም፤ እግቢው ውስጥ ገባ ብዬ አንዲት ዳገት ላይ ዲንጋ ተደግፊ
ቁጭ አልኩ፡፡ ጸሎትም የለኝም አደራም የለኝ፡፡ ግን አንድ ልቤን የሰበረው ነገር፤ ነበር፡፡ ሰው ናፍቆኝ አገር ናፍቆኝ መጥቼ ሰው
ሳላገኝ ሰው ሳልተዋወቅ፤ ሰው ፈልጌ በሰው ተሰቃይቼ፤ ደሴን ለቅቄ መኮብለሌ ህዝቡ ሳያውቅ መለየቴ ነበር፡፡ እንባዬ እንደጎርፍ
ይጎርፍ ነበር፡፡ የናፍኩዋት ኢትዮጲያ ለካስ እሱዋ አልናፈቀችኝም ፡፡ አንድ የሚያሳድደኝንም ፖሊስ በሩቅ አየሁት ልቤ በሲቃ ተሞላ
በእልክ መታ፡፡ አይኔን ብዥ አለብኝ፡፡ አዲስ የሸመትኩት የፍርሃት እና የእልክ በሽታ፡፡
ወዲያውም ከእኔ ጀርባ ኮረብታው ላይ አንድ ወጣት አስራ አምስት አመት
በታች የሆነ፡፡ ከወገቡ በላይ እራቁቱን ነው፡፡ ሀፍረተስጋው ብቻ ቆዳ መሰል የተቀዳደደች ልብስ ተሸፍኖአል፡፡ ብዙ ነገሮች በአንገቱ
ላይ አንጠልጥሎአል፡፡ ወዮልሽ ኢትዮጲያ፡፡ ወዮልሽ ደሴ የሚለው ድምጽ ነው በጀርባዬ ሰው መቆሙን ያየሁት፡፡ እኔም ከተቀመጥኩበት
አልተነሳሁም፡፡ መድሃኒአለም ተመለሱ ይላል ሲል፡፡ የመድሃኒአለምን ቃል ስሰማ ልቤ ወከክ ይላል፡፡ የአይኔም ብዥታ ግፍፍ አለ፡፡
አንድ አንድ እያለ ሰውም ግጥም ማለት ጀመረ፡፡ እኔም ከዛ ውስጥ ወጣሁእና ወደመኪናዬ ላመራ ስል ድምጹን ከፍ እያደረገ መስበክ
ጀመረ፡፡ ፌቴንም ዘወር አደረኩ፡፡ ወዩላችሁ እናንተ መልካሙን የምትቀጥፉ፤
መልካሙን የምታባርሩ የሚለው ድምጽ በጆሮዬ አስተጋባ፡፡ ወዮላችሁ እነሱስ ምንም አይሆኑም እናንተ ግን ወዮላችሁ እያለ ቀጠለ፡፡
ከዛም መኪናዬ ውስጥ ገባሁ፡፡ ካለምንም ልብስ እና ጉዋዝ፤ የምሰናበተውም አልነበረኝም እና፤ ወደቤቴ አልተመለስኩም፡፡ፊቴንም ወደሁዋላ
ዙሬ ለማየት አልደፈርኩም፡፡ እንባዬ በአይኔ እየተሞላ በምሃረቤ እየተረኩ 400 ኪሎሜትር ሀ ብዬ ከመድሃኒአለም ጀምሬ ወደ አዲስ አበባ ሸመጠጥኩ፡፡
ወደሁዋልም እንዳልዞር አንገቴ የደረቀ መሰለኝ፡፡ የመኪናውን ቴፔን ከፍ በማድረግ፤ የኦርቶዶክሱን ዘለሰኛ እና ደግሞም የፔንጤውን
ሃያል ነው እግዚአብሄር የሚለውን እና ክብር ይገባሃል የሚለውን እየዘመርኩ አዲስ አበባ ገባሁ፡፡ የምሄድበትንም አላወኩት፡፡ የማርፍበትንም
አላውቅም ነበር፡፡ያለፕላኑ የምሬት የፍርጠጣ ጉዞ፡፡
መኪና ልንዳ እንጃ ሁሉም ግራ የገባ ነበር፡፡ ኪሴም ባዶ
ሆኖአል፡፡ አላሰራኝ ብለው ነበር እና፤ አትራፊም አልሆንኩም፡፡ የሰራሁት ነገር ሁሉ ገደል ገብቶአል፡፡ ያለምኩት ሁሉ ቅዠት ሆኖአል፡፡
በፈረንጅ ጉዋደኞቼ በኩል ወደተዋወኩባት አንዲት ወዳጄ ቤት አመራሁ፡፡ ባለምርጡ ሬስቶራንት ባለቤት፡፡ ደፋ ቀና ብላ በስራ የተወጠረች፡፡ ወደዛም
አመራሁ፡፡ ትዝ ያለኝ የደሴው የባህታዊው ምልእክት ነበር፤“ መልካምን የምታሰድዱ ፣ እናንተ ወዮላችሁ፣ እነሱ ግን ምንም አይሆኑ“
የሚለው ቃል ነበር፡፡ መልካም ነኝ ማለቴ ሳይሆን፤ እኔ ግን ማንንም አላሳደድኩም፤ አላሰቃየሁም እና፤ ቃላቱ ተስፋ ሆነኝ፡፡ እሱዋም
በታላቅ ፈገግታ ተቀበለችኝ፡፡ ምግቡንም በጠረንጴዛው ሞላችው፡፡ እኔ ግን ሳላስበው እንባዬንም አፈሰስኩት፡፡ መንገዱ ያደከመኝ መስሎዋት
ነበር እና፤ እንባው ግን እረበሻት፡፡ እሱዋም ምን ሆንሽ ምን ተበደልሽ ብላ አላጨናነቀችኝም፡፡ እንባዋ ግን አብሮ ፈሰሰ፡፡ ባይተዋር
እንደተደረኩ ሳይገባት አልቀረም፡፡ እንዲህም አለችኝ፡፡ „አይዞሽ፡፡ ሁሉም ያለ ነው፡፡ መከራም ያለ ነው፡፡ ያልፋል፡፡ አሁን አዲስ
ሀ ብለሽ ጀምሪ ፡፡ መኖር ስላለብሽ ለመኖር የሚረዳሽን አይምሮ አታበላሺ፡፡ ሻወር ውሰጂ፤ ከተማም ሄደን ልብስ እንግዛ፡፡ ልብስሽንም
ቀይሪው፡፡ ጸጉርሽንም ነይ ተሰሪ፡፡ እዚህ እነዛ ያሰቃዩሽ ሰዎች የሉም፡፡ 400 ኪሎ ሜትር እርቀሻል፡፡“ እኔም ያለችኝን ምክር አደረኩ፡፡
መኪናዬን መሸጥ ነበረብኝ፡፡ እና ጉዋደኛዬ እባክሽ አንቺ አስቀሪው አልኩዋት፡፡ እሱዋም ረጋ ባለ አነጋገር እንዲህ ስትል መለሰችልኝ፡፡ „ጉዋደኛዬ አንቺ እኮ ከስረሽ ነው የምትሸጭው እንጂ ሌላ መኪና ቀይረሽ አይደለም፡፡
ስለዚህ እኔ በጉዋደኛዬ ክስረት አላተርፍም፡፡ ቀን ያልፋል፡፡ ቢኖረኝ በሰጠሁሽ ካልሆነም ባበደርኩሽ ነበር „፡፡እሱዋ ስራዋ አድጎ
ሰራተኛውም በዝቶ ለስራም ሁለተኛ መኪና ያስፈልጋት ነበርእና፡፡ በኪሳራ እንደምሸጠው ስላወቀች፤ እሱዋ ግን በጭራሽ አልገዛውም አለች፡፡
እባክሽ አስቀሪው አንቺ ጋር ይግባ፤ ብየም ለመንኩዋት፡፡ ባዩሽዬ ፤ብትጥይውም ጣይው እንጂ፤ እኔ ግን አልገዛውም፡፡ እኛ እኮ የምንቀጥል ጉዋደኛሞች ነን፡፡ በተገናኘን ቁጥር ይህንን መኪና እያየሽ ክፉ
ግዜሽን በእኔ ቤት እንድታስታውሽው አልፈልግም ብላ ዘጋች፡፡ የሚገርመው ይህቺ መልካም እና አስተዋይ ህይወቴንም የታደገች እና ያጽናናች
ሴት ከትግራይ ቤተሰቦች የተወለደች ትገሬ ነበረች፡፡ ፍቅር ከእግዚአብሄር ሲሆን ምላሹም ማዳን፤ መረዳት እና እንባን መጥረግ ይሆናል፡፡
ግን ፍቅር ከሰይጣን ሲሆን ከጥቅም ጋር ይያያዛል፡፡ አመሰግናለሁ፡፡ ቀን ቢገጥመኝ በአንድ ሚዲያ አግንቻት አመሰግናለሁ ብላት ለብዙ
ሚሊዮን ህዝብ ትምህርት በሆነ ነበር፡፡ ግና ምንአልባት አጋጣሚው ላይመቻችልኝ ይችላል፡፡ አላውቅም ነገ ምን እንደሚያመጣ፡፡ ደግመንም
ካልተገኛኘን፡ እግዚአብሄር ዘመኑዋን ሁሉ ይባርክ፡፡ እሱዋ በዛን ሰአት ባትገኝ ምን እንደሚገጥመኝ ለእናንተ ልተወው፡፡ ሰላማችሁ
ይብዛ፡፡
ባዩሽ