Freitag, 14. Oktober 2016

የፖለቲካ ቁማር፤ ኢህአዴግ ሊያር ሲል ተገላበጠ





             ላለፉት 25 አመታት፤ ስለኢትዮጲያ አንድነት አፍጥጦ መናገር አማራውን ወደላይ ማውጣት ሆኖ ሲታይ ቆይቶአል፡፡ ስለአንድነት ማውራት ወንጀል ነበር፡፡ „አንድነት የሚሉ ጠባቦች ነፍጠኞች
ትምክህተኞች፣ አድሃሪዎች እና ደርጎች ተብሎአል ፡፡ አማራውም በብዛት  የኦርቶዶክስ  እምነት ተከታይ ስለሚበዛው፤ ኦርቶዶክስ ላይ ብዙ የሚከፋፍሉ እና በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ጠንካራ ናቸው የተባሉ ሰዎች ብዙ ስም የማጥፋት ዘመቻ ደርሶባቸዋል፡፡ ደግሞም የማግለል ሁኔታ ተፈጥሮባቸው  ለኦርቶዶክስ ምእመናን እምብርት የሆነ አገልግሎት እና አስተያዬት ከመስጠት ላይ እንዲወጡ ተደርጎአል ብለው የሚገምቱ ቀላል ቁጥር አይደሉም፡፡ በውስጡም የነበርን ሰዎች ችግሮችን አስተውለን ከነገሩ ጦም ይደሩ ያልን ቀላል አልሆንም፡፡ ኦርቶዶክስ እና አማራ፤ ለአገዛዙ ስርአት ብቻ ሳይሆን ለሙስሊሙም፤ ለሌላው ብሄር ሁሉ እንደጠላት እንዲታይ ብዙ ዘመቻዎች ተካሂደውበታል፡፡ የሚገርመው ታላቁ አይን ያወጣው የማግለል አኪያሄድ ግን፤ ሌላው ብሄር ውስጥ ኦርቶዶክስ እምነት መኖሩ እና፤ ደግሞም፤ አማራ ውስጥ ሙስሊምም ፔንጤም መኖሩ ነበር፡፡ በአማራው ላይ እና በኦርቶዶክስ ላይ የነበረው የስም ማጥፋት ወንጀል፤ ግን ሌላውን Brainwash ያደረጋ እና፤ ያደነጋገረ መሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ የታዘብኩት ነገር፤ ብዙ በኢትዮጲያ ቤት እና ንብረት መስርተው ሲኖሩ የነበሩት ኤርትርያኖች፤ ኦርቶዶክስ ስለነበሩ፤ እነሱን ከኢትዮጲያ ማባረር፤ ኦርቶዶክሱንም ለመምታት የታሰበ ሳይሆን አይቀርም ብለው የገመቱ ነባር የኦረትቶዶክስ እምነት አባቶች፤ በሹክሹክታ ሳያሳስባቸው እንዳልቀረ መናገራቸው ነበር፡፡  እንዳንድ ክልል ላይ ለኦርቶዶክስ እምነት ወሳኝነትም  ተካፋይ ምእመናን መሆናቸው ስለሚታወቅ ነበር፤ ሰዎች በዚህ አዝነው ወደትችት እና ወደማሳሰብ ገብተው የነበሩት፡፡

         ለምን ኦርቶዶክስ እና አማራ በኢትዮጲያ ውስጥ ሃያ አምስት አመት ሙሉ ፈተና ውስጥ ገባ ብለን ስንጠይቅ፤ እያንዳንዱ የእራሱን ግመት መስጠቱ ባይቀርም፤ ዋናው ግን ላለፉት ዘመናት የአገዛዙ ቁንጮ ተደርጎ ስለሚታይ ብቻ መሆኑ የማይካድ ሀቅ ነው፡፡  ለዘመናት ሆኖአል ብለው፤ ወላጆቻቸው ካስተላለፉላቸው፤ ተጨባጭነት የለለው ታሪክ፤ ጥላቻ የሰነቁት፤ አማራውን ለመበቀል ያነጣጠረ ክፋት እለዋለሁ፡፡


የዛሬው አማራ ትውልድ፤ ባልኖረበት ታሪክ መወንጀሉ፤ ፖለቲካ ሳይሆን፤ ሁኔታውን ለስልጣን መጠቀም እለዋለሁ፡፡
ጥላቻ ብቀላን ይወልዳል እና፡፡ ለምሳሌ ኦሮምያ አካባቢ የተተከለው የጡት ሀውልት ሲታይ ብዙዎች ሲያያይዙት የነበረው፤ ከአማራው ብሄር ጋር መሆኑ እጅግ አሳዛኝ ነበር፡፡ ይህ የጥላቻ ሀውልት እንዲተከል የተደረገው ፤ በዚህ ሀያ አምስት ዓመት ሙሉ በአገዛዙ ላይ ባለው የኢህአዴግ ስርአት ነው፡፡ በዚህ የተነሳ የጥላቻ ሰባኪው መንግስት ሰዎች ቢሉት ሊደንቅ የሚገባ አይሆንም፡፡

               አማራው ያለፈውም አገዛዝ ቁንጮ ነው ተብሎም ቢገመት፤ አማራው ከሌላው አካባቢ ህዝብ የተለዬ የፋይናንሽያልም ሆነ የትምህርት እድገት ማለትም የተለዬ ጥቅም ያላገኘ ህዝብ ያቀፈ ክልል ለመሆኑ ግን ይህንን የአማራውን ክፍል ብለው የመደቡትን ዞሮ ለማስታዋል የሞከረ ማንም አካል አልነበረም፡፡ የኢህአዲግ ፖለቲካ በጭፍን እና በፍርደገምድልነት የተመሰረተ እንጂ ፖለቲካዊ ይዘት የለውም፡፡ ፖለቲካ ፖለቲካ ነው፡፡ ሊያድግ እና ሊለወጥ የሚችል ነው፡፡ ታሪክ የሆነ እንጂ የሆነውን ሊለውጥ ማንም አይችልም፡፡ የሆነም አለ ከተባለ፤ ፖለቲካ አሻሽሎ መጉዋዝ እንጂ፤ ያለፈውን ቁርሾ ለዛሬ ብቀላ ያዘጋጀ መሆን የለበትም፡፡ ኢህአዴግ አማራውን ለመበቀል የመጣ እንጂ፤ ኢትዮጲያ ላይ ፖለቲካ ለመስራት ሆኖ አላየነውም፡፡ አስፈሪ እና አሳዛኝ ነገሮች ተጋፍጠናል፡፡ እራሱ ወዶ ባመጣው ነገር፤ እራሱ ነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ቢልም፤ ህዝቡን ያማረረ እና ደም አፋሳሽ ከሆነ ነገር ሊያስጥለው አልቻለም፡፡ ህዝብ እና ህዝብም በትክክለኛው የፖለቲካ ችግር እንዲተዋወቅ አልተደረገም፡፡ በደፈናው አንድነት ማለት አማራውን ብቻ ከፍ የሚያደርግ ፖለቲካ ሆኖ እንዲታይ እና፤ ይህንንም ብሄር ህዝቡን እጅግ እንዲጠላ ያደረገ አስፈሪ የማግለል ፖለቲካ ነበር ነውም፡፡ በዚህ ተጎጂው ህዝብ ቀላል አይደለም፡፡ አማራው፤ ከፖለቲካውም ከባህሉም፤ ከእምነቱም አንዲደበቅ እንዲሸማቀቅ በእጅጉ ተደርጎአል፡፡ ያላው አማራጭ ዝም ማለት ብቻ ነበር፡፡ አማራውም እስከአሁን በዝምታ በማሳለፍ ላይ ይገኛል፡፡

            ኦርቶዶክስ  በኢትዮጲያ  ለሃያ አምስት አመት ፈተና ውስጥ ገብቶ የነበረው፤  የኦርቶዶክስ አባቶች፤ ምንግዜም ለዘመናት በኢትዮጲያ አንድነት ላይ የመጣውን ፈተና ሊቁዋቁዋሙ ይችላሉ ተብሎ ስለሚገመት፤ ሀያአምስት አመት ሙሉ የኢትዮጲያን መንግስት የያዘው ከፋፋይ የሆነው የብሄር ፖለቲካን ወጣቱ ክፍል እያደር መጥላቱ ስለማይቀር፤ ወጣቱን ከኦርቶዶክስ እምነት እንዲለይ የተደረገ ማዳከሚያ ስልት ነበር፡፡ ምክናያቱም ኦርቶዶክስ፤ እንደ ካቶሊክ ሁሉ፤ በተቃውሞ የተነሳ መገለል የተደረገበትን አካል  ግልጽ አቁዋም ሊቁዋቁዋሙት ስለማይችሉ ብቻ ነው፡፡


             ይህ አማራውን እና ኦርቶዶክስን ለማዳከም የተሄደበት መንገድ ግን፤ ፍጹም የሆነ አይን ያፈጠጠ ታላቅ የታሪክ ስህተት መሆኑን እና፤ እራሳቸውም ገዢ ፓርቲ ሊወድቅበት የሚችል መንገድ መሆኑን አለማገናዘባቸው ነው፡፡ አማራ ካልን፤ ጴንጤም ሆነ ሙስሊም አማራ መኖሩንም ብዙዎች በወቅቱ ሊረዱት አልቻሉም ነበር፡፡ አማራው ላይ ጣቱን የቀሰረ ቀላል አልነበረም፡፡ እናም ዛሬ የኦርቶዶክስ  ምእመናን በሁለት ክፍል የመሰንጠቅ አዝማሚያ  ፈተና ውስጥ ገብቶ አንዱ  የዚህ አንዱ ደግሞ የዚያ ባንዲራ አውለብላቢ በመሆን፤ ፈታኝ የሆነ የስነልቦና ትግል ተጠምዶ እንዲገኝ አድርጎታል፡፡ የሚገርመው ግን  25 አመት ሙሉ አማራው እና ኦርቶዶክስ እንደአላስፈላጊ ሲታይ ቆይቶ፤ አሁን ግን በመጣው የብሄር የመከፋፈል አደገኛነት ሁኔታ እንደገና  ስለኦርቶዶክስ እና አማራ ናቸው ተብለው ተወንጅለው ሲጠሉ የነበሩት ታላቁ ሚኒሊክ  ዛሬ በገዥዎች አፍ ሲጠሩ መስማት ማታለል እና መሸንገል ይመስላል፡፡ ለእኔ ማለቴ ነው፡፡  እንደገና አንድነትን እንደአጥፊ እና እንደአማራው የበላይነት ጥያቄ አድርገው ሲያዋድቁት የነበረው፤  ለመጣባቸው ፈታኝ የአገዛዝ ወቅት ይጠቅም ዘንድ፤ ከሃያ አምስት ዓመት በሁዋላ፤ የአንድነት እና የኦርቶዶክስ ታላቅነት፤  ቀዳሚ ሰባኪ የሆነው አማራውን ሲያንቁዋሽሽ ሲጥለው የነበረው ያው ገዢው ፓርቲ መሆኑ ነው፡፡ ለዚህም  ፖለቲካ ለካ  ካላገላበጡት ገዥዎች ያራሉ  የምለው፡፡ አሁን ኢህአዴግ፤ አንድነት  ይሻላል አያለ ብዙ አመት ሲደርቅ የነበረውን ክፍል ኢትዮጲያ እንዳይፈርስ አድርጎ ሲታገል የነበረውን ክፍል ሊያመክነው የተነሳ ይመሳላል፡፡ ምክናያቱም ግብጽ መጣብህ የሚለው አነጋገር፤  ገዢው ፓርቲ፤ አርባአራቱን ታቦት አውጡ  እና አግዙኝ ከጎኔ ተሰለፉ መሆኑ አይቀሬ ነውእና፡፡  እንዲህ ካልተባለ ፤ ማን ይሰለፋል ታዲያ  ፤  አደጋ ነው፡፡
 አደጋ ነው፡፡


በከይር የምላችሁ
ባዩሽ አበበ ነኝ